በሜዳሊያ ፉክክር የደመቀው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች

በጅማ እየተካሄደ በሚገኘው 6ኛው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች በተሳታፊ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች መካከል የሚደረገው ፉክክር ቀጥሏል። ትናንት በስድስተኛ ቀን የውድድሩ መርኃግብር በተለያዩ የስፖርት አይነቶች በተከናወኑ የፍፃሜ ፉክክሮች ቀደም ባሉት ቀናት የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባት ያልቻሉ ክልሎች ጭምር በውጤት የተንበሸበሹበት ሆኗል።

ትናንት ፍፃሜ ባገኘው የስፔሻል ኦሊምፒክ ውድድር አዲስ አበባ ከተማ አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን አጠናቋል። አዲስ አበባ በበላይነት ባጠናቀቀበት በዚህ ስፖርት 8 ወርቅ፣ 10 ብር እና 7 የነሐስ ሜዳልያ በመሰብሰብ ቻምፒዮን ሲሆን፣ ኦሮሚያ ክልል 2ኛ፣ ሲዳማ ክልል 3ኛ፣ ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 4ኛ በመሆን አጠናቀዋል።

በውሹ ስፖርት በሴቶች መካከል በተካሄደው “ቻንኳን” ፉክክር ሱማሌ፣ ኦሮሚያና ድሬዳዋ የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ አስመዝግበዋል። በተመሳሳይ በወንዶች ውሹ ስፖርት “ታይቺ” ፉክክር አዲስ አበባ ወርቅ፣ ድሬዳዋ ብር፣ ኦሮሚያ ነሐስ ሜዳሊያ ሲያስመዘግቡ “በናንዳኦ” ፉክክር አዲስ አበባ፣ ኦሮሚያና ሱማሌ ከ1-3 ያለውን ደረጃ ይዘዋል። “በቻንኳን” ወንዶች ኦሮሚያ፣ አዲስ አበባ ፣ ድሬዳዋ የሜዳሊያውን ደረጃ ይዘው ሲፈፅሙ፤ “በናንገን” አዲስ አበባ፣ ኦሮሚያና ሱማሌ በተመሳሳይ በበላይነት ውድድራቸውን አጠናቀዋል። በሴቶች “ናንኳን” ሱማሌ፣ አዲስ አበባና ኦሮሚያ ውጤት ሲያስመዘግቡ “በታይቺዲያን” አዲስ አበባ፣ ሱማሌና ኦሮሚያ የሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል። “በብሮድስ ዋርድ” ሴቶች ኦሮሚያ፣ አዲስ አበባ ደቡብ ኢትዮጵያ እንዲሁም “በሎንግስ ዋርድ” አዲስ አበባ፣ ኦሮሚያና ሱማሌ ሜዳሊያ አግኝተዋል።

በውሀ ዋና ሴቶች 400 ሜትር ነፃ ቀዘፋ አዲስ አበባ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ እና በወንዶች 100 ሜትር ነፃ ቅብብል ኦሮሚያ፣ አማራና ድሬዳዋ ወርቅ፣ ብርና ነሀስ በቅደም ተከተል ተሸላሚ ሆነዋል። በወንዶች 200 ሜትር ደረት ቀዘፋ አማራ የወርቅና ነሀስ ሜዳሊያ ሲያስመዘግብ ኦሮሚያ ብር ሜዳሊያ አግኝቷል። በሴቶች 200 ሜትር ነፃ ቀዘፋ ኦሮሚያ ወርቅ፣ አዲስ አበባ ብርና ነሀስ እንዲሁም በ200 ሜትር ነፃ ቀዘፋ አማራ ከ1-3 ያለውን ደረጃ በመያዝ ተሸላሚ ሆኗል። በሴቶች 200 ሜትር የግል ድብልቅ አዲስ አበባ ከ1-3 ያለውን ደረጃ ሲያስመዘግብ በወንዶች 200 ሜትር የግል ድብልቅ አማራ ወርቅና ነሀስ፣ ኦሮሚያ የብር ሜዳሊያ አስመዝግበዋል። በሴቶች 800 ሜትር ነፃ ቀዘፋ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ አዲስ አበባ የወርቅ፣ ብርና ነሀስ ሜዲያሊያ፤ በወንዶች 800 ሜትር ነፃ ቀዘፋ አማራ ወርቅና ነሀስ እንዲሁም ኦሮሚያ የብር ሜዳሊያ አስመዝግበዋል።

ሌላው ትናንት ፍፃሜ ያገኘው የኢትዮጵያ ኢትዮ ዩናይትድ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ አሶሴሽን ውድድር ሲሆን፣ በዚህም መሠረት፦ በወንዶች የቡድን ጥቁር ቀበቶ ፉክክር ኦሮሚያ ክልል የወርቅ፤ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የብር እና ድሬዳዋ የነሀስ ሜዳሊያ አግኝተዋል። በሴቶች የነጠላ ጥቁር ቀበቶ ፍልሚያ ደግሞ አዲስ አበባ የወርቅ፤ ኦሮሚያ የብር እና አማራ የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚዎች ናቸው።

በወንዶች የነጠላ ቀይ ቀበቶ አዲስ አበባ የወርቅ፣ ኦሮሚያ ክልል የብር እና ድሬዳዋ የነሀስ ሜዳልያ አግኝተዋል። በሴቶች የነጠላ ቀይ ቀበቶ አማራ የወርቅ፣ ኦሮሚያ የብር እና አዲስ አበባ የነሀስ ሜዳልያ ተሻላሚ ናቸው። በሴቶች የነጠላ ሰማያዊ ቀበቶ ፍልሚያ ኦሮሚያ የወርቅ፣ ድሬዳዋ የብር እና አማራ የነሀስ ሜዳሊያ ያገኙ ክልሎች ሆነዋል።

በወንዶች ጥቁር ቀበቶ ከ60-65 ኪሎ ግራም ፍልሚያ ድሬዳዋ የወርቅ፣ ኦሮሚያ የብር እና አዲስ አበባ የነሀስ ሜዳልያ ያገኙ ሲሆን፣ በሴቶች ጥቁር ቀበቶ ከ50-55 ኪሎ ግራም አማራ ክልል የወርቅ፣ አዲስ አበባ የብር እና ኦሮሚያ የነሀስ ሜዳልያ አግኝተዋል። በተመሳሳይ ስፖርት በተለያዩ ካታጎሪዎች በርካታ የፍፃሜ ፍልሚያዎች የተከናወኑ ሲሆን፣ በአጠቃላይ የሜዳሊያ ብዛትና ደረጃ ሲታይ ኦሮሚያ ክልል በ14 ሜዳልያ (በ5 ወርቅ፣ በ6 ብር እና በ3 ነሀስ) ቀዳሚ ሆኗል። አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ11 ሜዳሊያ (በ4 ወርቅ፣ በ5 ብር እና በ32 ነሀስ) ሁለተኛ ነው። አማራ ክልል በ9 ሜዳልያ (በ4 ወርቅ፣ በ2 ብር እና በ3 ነሀስ) ቀጣዩን ደረጃ ሲይዝ ድሬዳዋ አስተዳደደር በ8 ሜዳልያ (በ1 ወርቅ፣ በ1 ብር እና በ6 ነሀስ) በመሰብሰብ አራተኛ ሆኗል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You