የጤና ባለሙያዎች ጥያቄዎች ተገቢ፣ ነገር ግን ሕጋዊ መንገድን በመከተል ብቻ የሚመለሱ ናቸው

መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራባቸው ካሉ ዘርፎች መካከል የጤናው ዘርፍ አንዱና ቀዳሚው ነው። ምክንያቱም፣ የአንድ ሀገር መንግሥት እንደ ሀገር የሚጠበቀውን ለውጥና እድገት ማምጣትም ሆነ፣ የሀገርን ሉዓላዊነት አስጠብቆ መዝለ ቅ የሚችለው፤ ጤናማ፣ ብቁና አም ራች የሰው ኃይል ሲኖር ነው።

በዚህ ረገድ እንደ መንግሥት የጤናውን ዘርፍ በመሠረተ ልማት፣ በግብዓት፣ በቴክኖሎጂ እና በባለሙያ የተሟላ ሆኖ ተገቢውን ሕዝባዊ አገልግሎት የመስጠት ቁመና ላይ እንዲገኝ ለማስቻል እየሠራ ይገኛል። ይሄን ለማድረግም ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት አስፈላጊውን በጀት በመመደብ ነው እየሠራ ያለው።

ለምሳሌ፣ የጤናው ዘርፍ ከለውጡ ዓመት በፊት ከ70 ቢሊዮን ብር የዘለለ ዓመታዊ በጀት አልነበረውም። አሁን ላይ ግን መንግሥት በሰጠው ልዩ ትኩረት ከ130 ቢሊዮን ብር የተሻገረ በጀት ሊመደብለት በቅቷል።

የጤናውን ዘርፍ የመሠረተ ልማት ከማስፋፋት አኳያም ቢሆን፤ በጥቅሉ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በድምሩ ከ6 ሺህ በላይ አዳዲስ ጤና ኬላዎች፣ ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች ተገንብተዋል። ከእነዚህ መካከልም፤ ከ350 በላይ ጤና ኬላዎች፣ ከ100 በላይ ጤና ጣቢያዎች፣ 190 ሆስፒታሎች እና 11 ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች ተገንብተዋል። አንድ ሺህ 800 የሚሆኑ የጤና ተቋማት ላይም የማስፋፊያና የእድሳት ሥራ ተሠርቷል። በዚህም አሁን ላይ የመንግሥት የጤና ተቋማት ቁጥር እንደ ሀገር ከ22 ሺህ በላይ ደርሷል።

የጤናውን ዘርፍ በጀት ከማሳደግ እና የጤና ተቋማትን ከመገንባት ባሻገር፤ ተቋማቱ በተገቢው ግብዓት መታገዝ ስላለባቸው፤ የየአካባቢውን የበሽታ ስርጭት ታሳቢ ባደረገ መልኩ 15 የጤና ላቦራቶሪዎች ተገንብተዋል። የውሃ እና የሶላር አገልግሎት የሌላቸው ከአንድ ሺህ በላይ የጤና ተቋማት አገልግሎቱን እንዲያገኙ ተደርጓል። ቀደም ሲል ሦስት ብቻ የነበሩ የኦክስጅን አምራች ተቋማትም፣ አሁን ላይ 58 ደርሰዋል። ሌሎችች ግብዓቶችን በራስ አቅም የመሸፈን ተግባራትም በትኩረት እየተሠራባቸው ይገኛል።

ከመሠረተ ልማት ግንባታ እና የግብዓት አቅርቦት ባሻገር፤ የሰው ኃይል የማሟላትና የባለሙያዎች አቅም ግንባታ ሥራዎችም በዛው ልክ በትኩረት እየተሠራበት ይገኛል። ለምሳሌ፣ ከለውጡ በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ ከ219 ሺህ ያልበለጡ የጤና ባለሙያዎች ነበሩ። ባለፉት ስድስት ዓመታት በትኩረት በተሠራው ሥራ ግን የጤና ባለሙያዎችን ቁጥር ከ520 ሺህ በላይ ማድረስ ተችሏል።

እነዚህ በለውጡ ዓመታት ለጤናው ዘርፍ ትኩረት በመስጠት በሰው ኃይል፣ በፋይናንስ፣ በመሠረተ ልማት እና የግሉን ዘርፍ ለማገዝ በመንግሥት በኩል የተደረገው ጥረት በልኩ እውቅና ሊቸረው የሚገባው ነው። ይህ ማለት ግን ሁሉም ነገር ተሠርቶ አልቋል፤ መንግሥት ሊጠየቅ የሚገባው፣ ሊወቀስበት የሚችለው ምንም ነገር የለም ማለት አይደለም። ምክንያቱም ካለው ፍላጎት አንጻር የተሠሩት ሥራዎች በቂ አይደሉም፤ የላቀ ተባብሮ መሥራትን የሚጠይቁ ናቸው።

ለምሳሌ፣ የጤና ባለሙያዎች እንደማንኛውም የሕብረተሰብ ክፍል እና የመንግሥት ሠራተኛ ሰፊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፍላጎቶችም፣ ጥያቄዎችም አሏቸው። እነዚህን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋላጎቶችና ጥያቄዎች ከማሟላት አኳያ ለመንግሥት እያቀረቡ ያለው ጥያቄ ተገቢ መሆኑ የታመነ ነው።

በዚህ በኩል እንደ መንግሥት ጥያቄውን አጢኖ አቅም በፈቀደ መልኩ ለመፍታት የተጀማመሩ ሥራዎች መኖራቸውም እሙን ነው። ይሄ ባለበት ሁኔታ ታዲያ፣ ተገቢ የሆነውን የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ በአንድ በኩል ሐኪም መሳይ ጋወን ለባሾች ለግል ፍላጎታቸው ማሳኪያ፤ በሌላ በኩል የከሰሩ ፖለቲከኞች የፖለቲካ ኪሳራቸው ማወራረጃ አድርገው ለመጠቀም ተገቢውን ጥያቄ ሕግን ባላከበረ መልኩ ለማስጓዝ አበክረው ሲሠሩ ቆይተዋል፤ እየሠሩም ይገኛል።

ይሄ ደግሞ ተገቢ ያልሆነ ብቻ ሳይሆን፣ ሕግን ያልተከተለ፤ ይልቁንም የጤና ባለሙያዎች የገቡለትን ቃለመሃላ፣ የሚኖሩለትንና የተሰጡለትን ሙያዊ ልዕልና ዋጋ የሚያሳንስ፤ የሐኪሞችን የማኅበረሰብ መሪነት ሚናም የሚነጥቅ አካሄድ ነው። በመሆኑም የጤና ባለሙያዎች ተገቢ የሆነውን ጥያቄያቸውን ከእነዚህ ያልተገባቸው ጋወን ለባሽና የከሰሩ ፖለቲከኞች የተሳሳተ አካሄድ መነጠል ይኖርባቸዋል።

ከሰሞኑም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከመላው ኢትዮጵያ ከተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች ጋር በመከሩበት ወቅት ይሄንኑ ጉዳይ አጽንዖት ሰጥተውበታል። በተለይም መንግሥት ከለውጡ ማግስት ከሠራቸው ሥራዎች አንጻር እነዚህን የጤናው ባለሙያ ጥያቄዎች ለመመለስ ፍላጎቱም፣ ቁርጠኝነቱም አለ። ሆኖም የሐኪሞች ጥያቄ የፖለቲካ ኪሳራ በገጠማቸው ሰዎች መጠለፉ ትክክል አይደለም፤ ሲሉ አስገንዝበዋል።

በመሆኑም በሕክምና ባለሙያዎች የሚቀርቡ ጥያቄዎች ትክክል ሆነው፤ ነገር ግን ጥያቄዎች የሚቀርቡበት መንገድ ስህተት ከሆነ የተፈለገው ውጤት ስለማይገኝ፤ የጤና ባለሙያው ይሄን ተገንዝቦ ከእነዚህ አካላት ራሱን ሊነጠል፤ ጥያቄዎቹን የነጠቁት አካላትንም ሊያወግዝ እና በሙያዊ ልዕልናው ሊገለጥ ይገባል። ይሄ ሲሆን ተገቢ የሆነው የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ አቅም በሚፈቅደው እና በሕጋዊ መስመር ተጉዞ መልስ የሚያገኝ ይሆናል።

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You