
ጊዜው ክረምት ነውና አንዳንድ ነገሮችን ካለፉ ክረምቶች እናስታውሳችሁ። የዛሬ ሰባና ስድሳ ዓመታት ገደማ በአዲስ ዘመን ከወጡ የክረምት ወሬዎች መካከል፤ የመሬት ጉዞ፣ በዝናም ምክንያት የተናደው ተራራ፣ ምን ወሬ ከጎጃም፣ በእንቀሎ ተራራ ላይ የፈነዳው እሳተ ጎሞራን በተመለከተ የተዘገቡና ከተሳታፊዎችም የተነገሩ ጉዳዮች ነበሩ። በሌላ በኩል ደግሞ ከወደ ወሎ “አምሯል” ይላል፤ ያማረውስ ጉዳይ ምን ይሆን…እነዚህኑ የክረምት ወሬዎችን መልስ ብለን እንቃኛቸው።
የመሬት ጉዞ
በ1946 ዓ.ም በጥቅምት ወር በመጀመሪያ ላይ ከወረይሉ ምክትል ወረዳ ክሬ ወደሚባለው መሬቱ ከነአዝመራው ከነሰብሉ ጋር በአንድነት ተንሸራተው ወርዶ በቶ በሚባለው ወንዝ ላይ ተዘረጋ።
ያዝመራው ባለቤቶች መሬት ከሔደበት ሔደው አዝመራውን ለመሰብሰብ በላዩ ላይ የተሰበሰቡትን ገበሬዎቻቸውን፤ በብዛት አሰማርተዋል። ከዚሁ መሬት በላይ የሚታየው አዝመራ፤ ገብስ፣ ጤፍና ኑግ ነው። ከዚህም በቀር በብዙ የሚቆጠር የእህል ክምር በላዩ ላይ ይታያል። አውድማውን ከዚያው በማዘጋጀት ላይ ናቸው። በእነዚህ ሁለቱ ምክትል ወረዳዎች መካከል በቶ የሚባል ትልቅ ወንዝ አለ። ተነስቶ ሔዶ ወዲያ ማዶ ካለው ገደል ጋር ገጥሞ በጅረት የሚጓዘውን ውሃ ስለዘጋው፤ የተከተረው የባሕር ግምት ቁመቱ ከ1 ኪሎ ሜትር በላይ ይሆናል። በጎን ስፋት እስከ ሦስት መቶ ሜትር ሳይጠጋ አይቀርም።
የሔደው መሬት ቁመቱ በግምት አምስት መቶ ሜትር ይጠጋል። በጎን ስፋት አራት መቶ ሜትር ይደርሳል። የሔደውም መሬት ከደቡብ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ነው። ውሃው ግን አሥራ ሁለት ቀን ከተከተረ በኋላ በላዩ ላይ ሳይፈስ እንደተደረበ በደቡብ በኩል በገደሉና በድንጋዩ መካከል እየሸረሸረ እንደሚፈላ ምንጭ እየሆነ በየጫካውና በየዳገቱ ላይ ሲወርድ ይታያል።
ባካባቢው የሚገኘው ሕዝብ ጠበል ፈለቀ በማለት አስፋፍቶ ያወራል። የኔን አስተያየት የባሕሩ ስሜት ነው በማለት አሳርፌዋለሁ። ለሕዝቡ እንግዳ ታሪክ ሆኖበት ጉድ እናያለን በማለት ከየአውራጃው የሚመጣ እግረኛና ፈረሰኛ የሚደረገው እሽቅድድምና የሕዝብ ብዛት ግምቱ ከመጠን በላይ ነው።
በየነ አቻሜ
(አዲስ ዘመን ታኅሳስ 17 ቀን 1946 ዓ.ም)
በዝናም ምክንያት ተራራ ተንዶ ሰዎችና ከብቶች ሞቱ
በከንባታ አውራጃ በዴንሣ ጠንባሮ ም.ወረዳ ግዛት በአቶ ጽድቀ ጋረዴ ባላባትነት ውስጥ በነሐሴ 24/1946 ዓ.ም ለ25 አጥቢያ ሌሊቱን በዘነመው ኃይለኛ ዝናም ጦና ሸለቆ የተባለው ተራራ ተንዶ፤ ከዚሁ ጋር ሥር የሚኖሩ የቤቱ ጌታ አንቃሞ፣ 2ኛ ሚስቱ ቦቦሬ በዶሬን፣ 3ኛ ልጁን ሸክሜ አንቃሞ የሚባሉትን ሰዎችና ከበረት የነበሩ 11 የቀንድ ከብቶች፣ ሁለት ባዝራ ፈረሶች፣ 5 በጎች በናዳው የጋራ አደጋ ሲሞቱ፣ አንድ ዶሮና አንድ ባዝራ ፈረስ ከዚሁ አደጋ ድነው ታይተዋል። ከተናደውም ጋራ ሥር አንድ ምንጭ ፈንድቶ መታየቱን ያውቁት ዘንድ እገልጽልዎታለሁ።
ማኅተም የአርሲ ጠ.ግዛት ፖሊስ ዋና ጽ/ቤት
ፊርማ የሻለቃ አበበ ወልደሥላሴ የአርሲ ጠ.ግዛት ፖሊስ ም.ዋና አዛዥ
(አዲስ ዘመን ጥቅምት 13 ቀን 1947 ዓ.ም)
ምን ወሬ ነበር?
-የዝናም ወሬ
ምንም እንኳን በጣም ባይዘንም ሰሞኑን ሰማዩ በደመና ስለተሸፈነና ደመናውም ዝናሙን ለመስጠት ስለጀመረ በጣም ደስ አሰኝቷል። ትኩሳት ፀንቶበት የነበረውም የመሬቱ ገላ ቀዝቀዝ ብሏል። የፀሐዩም ግለት በርዷል። በእነዚህ ባለፉት ወሮች ሰማይ ዝናቡን ይሰጥ ዘንድ ስለዘገየ፤ ቦናው በጣም ፀንቶ ነበር። በየባላገሩ ከብቱ ድርቅ ስለያዘው መጎዳቱንና የየወንዙ ውሃዎች ሁሉ መድረቃቸውን ሰምተናል። ከቦናውም ፅናት የተነሳ የነፋሱ አነፋፈስ በጣም በመበርታቱ ብዙ ከብቶችና ብዙ ዛፎች ወድቀዋል።
ተጎጃም የተገኘ ወሬ
(አዲስ ዘመን ግንቦት 4 ቀን 1937 ዓ.ም)
በእንቀሎ ተራራ ላይ እሳተ ጎሞራ ፈነዳ
አሩሲ ኢዜአ፤- በአርሲ ጠቅላይ ግዛት በሊሙ በለሐቢሎ ወረዳ ከሚገኘው የእንቅሎ ተራራ ውስጥ በስተደቡብ በኩል እሳተ ጎሞራ ስለፈነዳ አያሌ የሆነ ፍል ውሀ ከተራራው ወጥቶ የስምጥ ሸለቆን በጎርፍ አጥለቀለቀው።
ከሥፍራው ዘግይቶ የደረሰን ወሬ እንደሚያስረዳው ከተራራው ውስጥ የፈነዳው እሳተ ጎሞራ ሚያዚያ 2 ቀን 1960 ዓ.ም ሲሆን፤ በዚሁ እሳተ ጎሞራ ምክንያት ተራራው ሲሰነጠቅ ኃይለኛ የሆነ ድምጽ በመሰማቱና መሬት በመንቀጥቀጡ በየአካባቢው በሚኖረው ሕዝብ ዘንድ ታላቅ ፍርሃት አሳድሮ ነበር። በዚሁ በፈነዳው እሳተ ጎሞራ ከተሰነጠቀው ተራራ መካከል የወጣው ፍል ዉሀ ጎርፍ ሸለቆውን በመከተል አካባቢው የሚገኘውን የጦናን ሸለቆ አጥልቆት ነበረ። ይኸው ፍል ውሀ ጎርፍ ደን ሆኖ የኖረውን እንጨት እየነቃቀለና ትልቅ የአለት ድንጋዮችን እያንከባለለ ወደ ዋቢ ወንዝ ወስዶ ተቀላቅሏል። እንዲሁ በዚሁ ዕለት ወደ ዕለት ተግባሩ ይሰማራ የነበረው የአካባቢው ሕዝብ በጎርፍ ምክንያት ለመሸጋገር ሳይችል መቅረቱ ይነገራል።
ይሁንና ይኸው ተራራ በፈነዳ ጊዜ በሰውና በእንስሳት ያደረሰው ጉዳት አለመኖሩን ባላንባራስ ወልደ አማኑኤል አብን ገልጠዋል።
(አዲስ ዘመን ሚያዚያ 24 ቀን 1960 ዓ.ም)
አምሯል
ዘንድሮ ወሎ ብላጊ በጣም በመያዙ ሕዝቡ በጣም ተደስቷል። አሁን ደግሞ በዚህ ግንቦት ወር ቆላ ደጋውን እያስማማ በፀሐይ ጣልቃ በመግባት ስለሚዘንብ በደጋው ግንቦቴ በቆላው ማሽላ በየዓይነቱ በመዝራት ላይ ይገኛል።
የወሎ ጠቅላይ ግዛት አዣንስ
(አዲስ ዘመን ግንቦት 15 ቀን 1951 ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2017 ዓ.ም