የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የዘንድሮ ምርጫ የሚከናወንበትን ጊዜያዊ የጊዜ ሰሌዳ አውጥቷል። በጊዜያዊ ሰሌዳው መሠረት የመራጮች ምዝገባ ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዝያ 28 ቀን 2012 ዓ.ም.፣ የእጩዎች ምዝገባ ጊዜ ከሚያዝያ 13 ቀን እስከ ሚያዝያ 26 ቀን 2012 ዓ.ም፣ የምረጡኝ ዘመቻ ጊዜ ከሚያዝያ 27 እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም፣ የምርጫ ድምጽ መስጫ ዕለት ነሐሴ 10 ቀን ሲሆን ቦርዱ የተረጋገጠ ውጤት የሚያሳውቅበት ቀን ከነሐሴ 11 እስከ 20 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚሆን ተጠቅሷል።
አዲሱ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሥራውን ሲጀምር ካከናወናቸው ግዙፍ ተግባራት አንዱ የሲዳማን ሕዝበ ውሳኔ ማስፈጸም ነበር። ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም ከተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ አፈጻጸም ሒደት የተስተዋሉ ክፍተቶች፣ የአሰራር ችግሮች ለመጪው አገር አቀፍ ምርጫ ጠቃሚ ግብዐት ሊሆን እንደሚችል በብዙዎች ዘንድ ይታመናል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም የሕዝበ ውሳኔውን አፈጻጸም በዝርዝር ገምግሞ እና የምርጫ ታዛቢዎችን ሪፖርት መርምሮ ለቀጣይ ምርጫ ሂደት ላይ ግብዐት ሊሆኑ የሚችሉ ጠቃሚ ጉዳዮችን ይለያል ተብሎም ይጠበቃል።
ሁለት የአገር ውስጥ ተቋማት የሲዳማ ሕዝብ ውሳኔ ሒደት በመታዘብ በእኔ ዕይታ ነጻና ግልጽ የምርጫ ትዝብት ሪፖርታቸው ያቀረቡ ቢሆንም ተገቢውን ትኩረትና የሚዲያ ሽፋን አግኝተዋል ብዬ አላምንም። ሌላው ቀርቶ በራሳቸው በታዛቢዎቹም ሆነ በሌሎች ድርጅቶች ተነሳሽነት በትዝብት ሪፖርቱ ላይ ሰፋፊ የውይይት መድረኮችን በመክፈት ጠቃሚ ግብዐቶችን ለይቶ አውጥቶ ለቀጣይ ምርጫ ለመጠቀም ሀሳብ በማቅረብ ረገድ የታየ ጥረቶች ስለመኖራቸው የዚህ ጹሑፍ አቅራቢ መረጃ የለውም። የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ አገር ምርጫ ታዛቢዎች ሪፖርት ነጻና ገለልተኛ እንዲሁም ሙያዊ ሥነ ምግባሩን የጠበቀ መሆን ወይንም አለመሆን በምርጫ ውጤት ተአማኒነት ላይ የራሱ የሆነ ተጽእኖ እንደሚኖረው እሙን ነው።
በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት እንደታየው ሥርዓቱን ያልተከተሉ አድሎአዊ የምርጫ ትዝብት ሪፖርቶች ለሁከትና ብጥብጥ መነሻ እንደሚሆኑም የሚታወቅ ነው። ሩቅ ሳንሄድ በአገራችን ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም የተካሄደው 5ኛ ዙር ብሔራዊ ምርጫ የተረጋጋና ተአማኒነት የተላበሰ እንደነበር የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ሪፖርት ማመልከቱን ማስታወስ ይበቃል። ይኸም ሆኖ ገዥው ፓርቲ እና አጋሮቹ መቶ በመቶ ወንበር የተቆናጠጡበት አዲሱ ፓርላማ በቅጡ እንኳን ሥራ የመጀመር ወግ ሳይደርሰው፤ መቶ በመቶ መርጧል የተባለው ሕዝብ ለተቃውሞ መሰለፍ መጀመሩን እና ለውጥ እንዲመጣ ማስገደዱን የታዘብነው ነው።
በጥቅሉ ግን የአገር ውስጥ ታዛቢዎች ሪፖርት ለመጪው አገር አቀፍ ምርጫ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ትዝብት ውጤት አንዳንድ ነጥቦችን መልሶ ማንሳት ተገቢ ይሆናል።(ጊዜያዊ የምርጫ ትዝብቱ ሪፖርቱን ሙሉ ይዘት በቦታ ጥበት ምክንያት ማካተት ባለመቻሌ በዚህ አጋጣሚ ይቅርታ እጠይቃለሁ።)
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለምርጫ
…ቅድመ ሕዝበ ውሳኔ ትዝብት በተመለከተ፡- ጥምረቱ ከኅዳር 4 እስከ 9 ቀን 2012 ዓ.ም በተመረጡ ስድስት ወረዳዎች (ወንዶ ገነት፣ ሸበዲኖ፣ ሐዋሳ፣ ዳሌ (ይርጋ ዓለም)፣ አለታ ወንዶ (ጩኮ) ዳሌ ሚንሽ) የረዥም ጊዜ ታዛቢዎች ቡድን 15 አባላት ያሉት 6 ቡድኖችን በማሠማራት አጠቃላይ የፖሊቲካ ዐውድ፣ የምርጫ ቅስቀሳ፣ የሲቪክና የመራጮች ትምህርት፣ የምርጫ ቦርድ የሕዝበ ውሳኔውን ለማካሄድ ካደረገው ዝግጅት እንዲሁም ከዞኑ አስተዳደር አስተዳደራዊ ድጋፍ ዝግጅት እና የጸጥታ ዝግጅት አንጻር ትዝብት አካሂዷል።
የፖሊቲካው ዐውድ በተመለከተ ታዛቢ ቡድኑ ትዝብቱን ማካሄድ ከጀመረበት ከኅዳር 04 ቀን 2012 ጀምሮ እስከ ድምፅ ቆጠራና ውጤት ማሳወቅ ድረስ ፖሊቲካዊ ዐውዱ የተረጋጋና ሰላማዊ እንደነበር ታዝቧል።
ሀ. ከምርጫ ቦርድ ዝግጅት አንጻር
ቡድኑ በ6 ወረዳዎች የሚገኙ 147 የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች የነበረውን ዝግጅት ታዝቧል። በዚህም መሰረት የሚከተለውን መረጃ አግኝቷል፡-
– በሕግ የተቀመጠው በአንድ የምርጫ ጣቢያ ሊኖር የሚገባው የመራጮች ብዛት 1500 ሲሆን በአንዳንድ ምርጫ ጣቢያዎች ከእጥፍ በላይ የሚሆኑ መራጮች ተመዝግበው ተገኝተዋል። ይህንንም አስመልክቶ ጥምረቱ ከድምፅ መስጫው ቀን አስቀድሞ ጉዳዩን ለምርጫ ቦርድ በማሳወቅ መፍትሔ እንዲፈለግ ሐሳብ አቅርቧል።
– ለመራጮች በማያመቹ ሥፍራዎች፤ መንገድ የሌለባቸው፣ በዛፍ ጥላ ሥር፣ የተከፈቱ የድምፅ መስጫ ጣቢያዎችን ታዝቧል።
– የሕዝብ ውሳኔ አስፈጻሚዎችን በተመለከተ ሥልጠናና ግንዛቤ የተሰጣቸው ቢሆንም ከአበል ክፍያ ጋር በተያያዘ ቅሬታ ያላቸው መሆኑንና በተሠማሩባቸው አካባቢዎች በሚገኝ ኅብረተሰብ ላይ በምግብና በመጠለያ እንዲደገፉ መገደዳቸውን ለመታዘብ ተችሏል።
– ከሎጂስቲክ አንጻር በአንዳንድ የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች የኮሮጆና የመራጮች የምርጫ ካርድ እጥረት ይታይ የነበረ ሲሆን በምዝገባ ሂደትም ሆነ በሕዝበ ውሳኔው ዕለት የድምፅ መስጫ ወረቀት እጥረት እንዳይፈጠር ምርጫ ቦርድ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ ጥምረቱ ምክረ ሐሳብ ቀርቧል።
ለ. ከዞኑ አስተዳደር አንጻር
የዞኑ አስተዳደር ከምርጫ ቦርድ ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን አስተዳደራዊ ድጋፍ በመስጠት የድምፅ መስጫ ጣቢያዎችን በማቋቋም ተገቢውን የጸጥታ ኃይል በማሰማራት የህዝበ ውሳኔው አፈጻጸም የተሳካ እንዲሆን ጥረት ማድረጉን ታዝበናል። ሆኖም በታዘብናቸው የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች የአስተዳደርና የፖሊስ አካላት በምዝገባ ወቅት ከተፈቀደላቸው የስራ ድርሻ ውጪ የምርጫ ቦርድ አስፈጻሚዎች ሊሠሩ የሚገባቸውን ተግባራት ሲፈጽሙ ተስተውሏል።
ሐ. የጸጥታ አካላት
የጸጥታ አካላት ሕዝበ ውሳኔው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ታዝበናል።
መ. የመራጮችና የሲቪክ ትምህርት ዝግጅት
የመራጮችና የሲቪክ ትምህርት ዝግጅትን በተመለከተ በቂ ዝግጅት አለመደረጉንና ትምህርቱም ለኅብረተሰቡ በበቂ ሁኔታ አለመሰጠቱን ታዝበናል። በደቡብ ቴሌቪዥን የሚሰጠው የመራጮች ትምህርት የአንድ ወገንን የምርጫ ምልክትን መሠረት አድርጎ ሲሰጥ እንደነበር ታዝበናል። የኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሚሰጠው የመራጮች ትምህርት በሲዳምኛ ቋንቋ ባለመሰጠቱ ትምህርቱ ለመራጩ ሕዝብ በበቂ ሁኔታ አለመድረሱን መታዘብ ተችሏል።
ሠ. የሕዝበ ውሳኔ ቅስቀሳ
የታዛቢ ቡድኑ የመታዘብ ሥራውን ባከናወነባቸው ቀናት የአንድ ወገን ያመዘነበት የምርጫ አጀንዳ የሚያንጸባርቁ ማስታወቂያዎች ተለጥፎ ከማየት በስተቀር በተፎካካሪ ወገኖች መካከል የተጋጋለ የምርጫ ቅስቀሳ፣ የአዳራሽ ክርክርም ሆነ በሰላማዊ ሰልፍ አሊያም በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት የሐሳብ ልውውጥ አለመደረጉን ታዝቧል።
የተስተዋሉ ክፍተቶች
– በዚህ የህዝበ ውሳኔ ሂደት ድምፅ አሰጣጥ ምሥጢራዊነት ያልተጠበቀባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ታይተዋል፤ ይህም መራጮች ከአንድ በላይ እየሆኑ የምሥጢር የድምፅ መስጫ ድንኳኖች ውስጥ በመግባት ምልክት ሲያደርጉ ተስተውለዋል፤
– ጣት ላይ የሚቀባ ቀለም እጥረት የታየባቸው የምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸው፣
– ድምፅ ሰጥተው የጣት ቀለም ሳይቀቡ የወጡ መራጮች እንደነበሩ ታዝበናል፣
– በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች የሕዝበ ውሳኔው ውጤት ከቆጠራው መጠናቅቀ በኋላ በፍጥነት አለመለጠፋቸው፣
– በብዙዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች የተገኙት የአንድ ወገን ተወካዮች ብቻ መሆናቸው፣
– ለምርጫ ዕድሜአቸው ያልደረሱ የሚመስሉ ታዳጊዎች ድምፅ መስጠታቸውን ታዝበናል።
ማጠቃለያ
ከዚህ በላይ የቀረበ ሪፖርት የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት- ለምርጫ የሲዳማ ህዝብ ውሳኔ አካሔድን በሚመለከት ያዘጋጀው የመጀመሪያ ደርጃ ሪፖርት( preliminary report) ሲሆን በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ዝርዝር መረጃዎችን ያካተተ፤ ከዚህ ከተካሄደው የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ የተቀሰሙና ለመጭው የ2012 ዓ.ም አገራዊ ምርጫ ጠቃሚ ትምህርቶች ሊቀሰምባቸው የሚችሉ፤ የምርጫ አስተዳደሩን ለማሻሻል የሚረዱ ተሞክሮዎችን እና ምክረ ሃሳቦችን ያካተተ ሪፖርት በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ያወጣል።
ጥምረቱ ከሲዳማ ህዝብ ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ እለተ እና ማግስት የታየው ሠላማዊ ሁኔታ የሚያስደስት እና የሚያበረታታ መሆኑን እየገለጸ፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ይህ ሠላማዊ ሁኔታ በዘላቂነት እንዲቀጥል የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲውጡ ጥሪውን ያቀርባል። በዚህም አጋጣሚ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ እና በድምፅ መስጠት ሒደቱ ላይ የተሳተፉ አካላት ሁሉ እስካሁን ለነበረው አበረታች የምርጫ ሂደት ላሳዩት የአፈፃፀም ሰኬት አድናቆቱን ያቀርባል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ትዝብት ቁልፍ ግኝቶች
የመራጮች ምዝገባ በቅድመ-ምርጫው ወቅት
የመራጮች ምዝገባ በተሳካ ሁኔታ የተከናወነ መሆኑና 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ያህል መራጮች መመዝገባቸው ታውቋል። በሌላ በኩል የኢሰመኮ ክትትል ቡድን ለመራጭነት ዕድሚያቸው ያልደረሰ የሚመስሉ ነገር ግን ለአካለ መጠን የደረሱ መሆኑን የሚያመለክት መታወቂያ ካርድ ያላቸው የተወሰኑ ወጣቶች የተመለከተ ሲሆን፤ ይህም ለምርጫ ቦርድ ሥራ ልዩ ተግዳሮት መሆኑን ተገንዝቧል ።
ደህንነት በሁሉም ደረጃ ያሉ የክልልና የፌዴራል ባለስልጣናት እና የብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ለምርጫው አስፈላጊ የሆነው የጸጥታና ደህንነት ሁኔታ እንዲፈጠር በጥሩ ሁኔታ መስራታቸው ለመረዳት ተችሏል። የምርጫውን ሒደት የሚያውኩ የተወሰኑ የሕግ መጣስ ክስተቶች የነበሩና ይኸውም በሕግ አስከባሪ አካሎች ቁጥጥር ስር ከመሆኑ በስተቀር፤ የጸጥታና ደህንነት ችግር አልነበረም።
የምርጫ ቅስቀሳ ሁኔታ
የምርጫ ቅስቀሳው አዲስ የሲዳማ ክልላዊ መንግስት እንዲቋቋም በሚጠይቀው የሻፌታ ቡድን ከፍተኛ የበላይነት የተሞላ ነበር። ሲዳማ የደቡብ ክልላዊ መንግሥት አካል ሆኖ እንዲቀጥል የቀረበው የአማራጩ የጎጆ ቡድን የምርጫ መረጃ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት በቴሌቪዥንና ሬዲዮ በተመደበለት ሰዓቶች ከመደመጡ በስተቀር፤ የምርጫ ቅስቀሳ አልነበረውም ማለት ይቻላል።
በአንጻሩ የሻፌታ ቡድን (ወደ ክልል ማደግን የሚያሳየው የምርጫ ምልክት) በሰላማዊ ሠልፍ፣ በስብሰባዎች፣ በጐዳናዎች እና ከቤት ወደ ቤት በመዘዋወር ጭምር ሰፊ የምርጫ ቅስቀሳ አድርገዋል፤ እንዲሁም በሲዳማ ዞን መንገዶች እና አደባባዮች ልዩ ልዩ የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክቶችን ሰቅለዋል። እነዚህ የምርጫ ቅስቀሳ ፖስተሮችም የምርጫ ቅስቀሳው ጊዜ ከአለፈ በኋላም በየመንገዱ ይታዩ ነበር።
የኢሰመኮ የክትትል ቡድን አባላት በጎበኙት አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች አካባቢ የተወሰኑ የወጣት ቡድኖች ድምፅ ለመስጠት ለተሰለፉ ሰዎች የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ታይተዋል። ለአማራጩ የጎጆ ቡድን የምርጫ ቅስቀሳ በይፋ የተከለከለ ነገር ባይኖርም፣ በርካታ አስተያየት ሰጭዎች ለኢሰመኮ ታዛቢዎች እንደገለጹት፤ በሲዳማ የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታ አማራጩን ሐሳብ በይፋ ለመቀስቀስ ስጋት እና ፍራቻ ነበር።
የጎጆን አማራጭ ሊያቀርብ ይችላል ተብሎ የተጠበቀው በመጀመሪያ ያቀረበው የደቡብ ክልል መስተዳድር የምርጫ ቅስቀሳ አላደረገም። የሲዳማ ዞን አስተዳደር በአንጻሩ የሻፌታ ምርጫ ቅስቀሳን ድጋፍ የሰጠ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ለአማራጭ ሐሳብ የፖለቲካ ምህዳሩ ለማንኛውም ሰው ክፍት መሆኑን ገልጿል። በቅድመ-ምርጫ ወቅት ሀሳብ የመግለፅ፣ የመሰብሰብ ነጻነት እና የመንቀሳቀስ ነጻነት ላይ ምንም ዓይነት ገደብ አልተደረገም። የምርጫ አስተዳደር አዲስ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተጨናነቀ የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ሰላማዊ ምርጫን ለማደራጀት እና ለማስፈጸም የተቀናጀ ጥረት ያደረገ ሲሆን፤ በሌላ በኩል በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ብቻ የሚከተሉትን ጨምሮ አነስተኛ የሥነ ሥርዓት ችግሮች ታይቷል።
ብዛት ያላቸው መራጮች የተመዘገቡባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ሥራ አፈጻጻም አስቸጋሪ መሆኑ፤ (በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ከሁለት ሺ የሚበልጡ መራጮች ተመዝግበዋል፣ ቢያንስ በአንድ የምርጫ ጣቢያ አምስት ሺ675 መራጮች መመዝገባቸውን የኢሰመኮ የክትትል ቡድን ተመልክቷል።)
የተሟላ ምርጫ አስፈጻሚዎች የሌላቸው የምርጫ ጣቢያዎች፤ (በኢሰመኮ ታዛቢዎች የተጎበኙ አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች 1 ወይም 2 ብቻ የምርጫ አስፈጻሚዎች ነበሯቸው)
እንደ የድምፅ መስጫ ሳጥን፣ የምርጫ ወረቀቶች እና እንደ ቀለም ያሉ የምርጫ ቁሳቁስ አቅርቦት እጥረት መኖር (የኢሰመኮ ታዛቢዎች በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ቦርድ የጐደሉ የምርጫ ቁሳቁስ በሟሟላት ምላሽ እንደሰጠ ተመልክተዋል።)
አብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ አለመሆን (የኢሰመኮ ታዛቢዎች የተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች የተንቀሳቃሽ ወንበር መግቢያ (ራምፕ) ያላቸው እንደሆኑ ተመልክተዋል።
አዲሱ የኢትዮጵያ የምርጫ ህግ አንድ የምርጫ ጣቢያ ለ1500 ሰዎች እንደሚያገለግል ይደነግጋል። ይህ ቁጥር ከአለም አቀፍ ደረጃ አንጻር ሲታይ ከፍተኛ ነው። ከሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ተሞክሮ አንጻር ሲታይም ይህን ያህል መጠን ያለው የምርጫ ጣቢያ በአግባቡ ሥራውን ለማከናወን አስቸጋሪ መሆኑ ታይቷል። በአጠቃላይ በምርጫ ወቅት አንድ የምርጫ ጣቢያ 5 የምርጫ አስፈጻሚዎች የሚኖሩት እና የምርጫ ጣቢያዎች ቁጥርን ለመጨመር ሀብት የሚጠይቅ ቢሆንም የምርጫ ቦርድ ይህን አንቀጽ በመፈተሽ በአንድ የምርጫ ጣቢያ የሰው ብዛት ከ 750 እስከ 1000 ብቻ በማድረግ ሊያሻሽለው ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥር 20/ 2012