የግብርና ሚኒስቴር ሰሞኑን እንዳስታወቀው፤ በ2011/12 የምርት ዘመኑ 382 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ታቀዶ 329 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ተገኝቷል። ምርቱ የተገኘው በምርት ዘመኑ 13 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን ሲሆን፣ ከእዚህ ውስጥ እስከ አሁን 12 ነጥብ 34 ሚሊዮን ሄክታር ላይ የነበረው ምርት ወይም 90 ከመቶ አዝመራ ተሰብስቧል። ይህም ከአለፈው ምርት ዘመን ከተገኘው 315 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ጋር ሲነጻጸር የ4ነጥብ 33 በመቶ እድገት የታየበት ነው።
ማምረት ብቻውን ግብ አይደለም። ቀጣዩ ስራ ደግሞ ምርቱ ተገቢው ግብይት ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ተጠቃሚ መሆን ያስፈልጋል። ግብይቱ ጤነኛ ሆኖ አርሶ አደሩን እና ሸማቹን በሚገባ ተጠቃሚ እንዲያደርግ በትኩረት መስራት ይኖርበታል። እንደሚታወቀው፤ ምርት በስፋት ገበያ በሚገባበት ወቅት ዋጋ ሊቀንስ ይችላል።
አቅርቦት በስፋት በሚኖርበት ወቅት ዋጋ ላይ ቅናሽ ሊኖር መቻሉ ምክንያታዊ ቢሆንም፣ በህገወጥ ግብይት ፈጻሚዎች ሳቢያ አርሶ አደሩ ከምርቱ ተገቢውን ጥቅም እንዳያገኝ የሚያደርግ ሁኔታ እንዳይፈጠር መስራት ግን ያስፈልጋል።
ወቅቱ ከግለሰብ አንስቶ እስከ የተለያዩ ድርጅቶች ድረስ ለቀጣዩ ዓመት የሚያስፈልጉ የግብርና ምርቶችን ገዝተው የሚያከማቹበት ፣ በሌላም በኩል በእዚህ ወቅት ገዝተው ወደ ዓመቱ መጨረሻ በውድ ዋጋ ለመሸጥ ደላሎችና ስግብግብ ነጋዴዎችም የሚሯሯጡበት ነው። አርሶ አደሩም ለተለያዩ ጉዳዮች ሲል ምርቶቹን በስፋት ገበያ ላይ አውጥቶ የሚሸጥበትም ነው።
አርሶ አደሩ በቀጥታ ለሸማቹ ቢሸጥ በዋጋ ያን ያህል አይጎዳም። በመሀል የሚገቡ ደላሎችና ህገወጥ ነጋዴዎች ናቸው ዋጋውን ሊያራክሱበት የሚችሉት። ለእዚህ ደግሞ የቅርብ አጋሮቹን የአርሶ አደሮች የህብረት ስራ ማህበራትን መጠቀሙን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
ከፌዴራል ህብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ማህበሩ የአርሶ አደሩ ምርት እንዳይወድቅ ከሚያከናውኗቸው በርካታ ስራዎች መካከል አንዱ ከተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር የሚያቀርበው የግብርና ምርት ነው።
የግብርና ምርት ከሚሸምቱ መንግስታዊ ተቋማት መካከል ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች፣ የማረሚያ ተቋማት፣ ሆስፒታሎች እንዲሁም የግብርና ምርትን የሚሰበስቡ እንደ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽንና መሰል ተቋማት ይገኙበታል። የህብረት ስራ ማህበራቱ ከእነዚህ ተቋማት ጋር በገቡት ውል መሰረት እየተሰራ ነው። ይህ የአርሶ አደሩ ምርት ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ በማህበሩ እየተደረገ ያለ ጥረት ሊበረታታ ይገባል።
እነዚህ ተቋማት ቀደም ሲል ምርት የሚያገኙት ከደላሎችና ነጋዴዎች ነበር። አሁን ምርቱ በቀጥታ ከአርሶ አደሩ ለእነዚህ ተቋማት እንዲደርስ ማህበራቱ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።
ማኅበራቱ የአርሶ አደሩን ምርት በመግዛት ለውጭ ገበያም እያቀረቡ ናቸው። ምርቱን በመረከብ ወደ ተለያዩ ገበያዎች ወስደው በመሸጥ አርሶ አደሩን ከገበያው ቀበኞች መታደግ ችለዋል። በተለይም ከከተማ አጋሮቻቸው ከሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት ጋር በመስራት ለእዚህ የሚሆን ከፍተኛ ሀብት በመመደብ ከአርሶ አደሩ እየገዙ ያሉበት ሁኔታም ዘንድሮም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
የምርት እድገት ቀጣይነት እንዲኖረው እንዲሁም የአርሶ አደሩ ኑሮ እንዲቀየር የሚያችሉ ስራዎችን መስራት የማህበራቱ ተልእኮዎች እንደመሆናቸው፣ የምርት ግብአት በማቅረብ የሚያሳዩትን አጋርነት ምርቱ ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ ማድረጋቸውን በማጠናከር ማረጋጋጥ ይኖርባቸዋል። ይህ ሲሆን የአርሶ አደሩም ተጠቃሚነት ይበልጥ ይጎለብታል፤ ምርትና ምርታማነት እያደገ ይሄዳል። ስለሆነም የህብረት ስራ ማህበራት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የአርሶ አደሩ ምርት ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ ሊሰሩ ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥር 19/2012