ፍትህ የነፃነት ምልክት እንደመሆኑ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ፍትህ ለሁሉም ህብረተሰብ ተደራሽ ሊሆን ይገባል። ይህን የነፃነት አርማና ምልክት የሆነውን ፍትህ ለማስፈን ደግሞ የአንበሳውን ድርሻ ሊወስድ የሚገባው መንግስት ነው። መንግስት ለፍትህ ዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ህብረተሰቡ ለሕገወጥነት ቦታ አይኖረውም::
ከዚህም በላይ ፍትህ እና ሰላም የሰፈነለት ዜጋ ለአገሩ የሚኖረው ስሜት ከፍተኛ ይሆናል:: ዜጎች በአገራቸው ጉዳይ ላይ የባለቤትነት ስሜት ሲሰማቸው ጤናማ አስተሳሰብ ይኖራቸዋል። በዚህም አገር እንደ አገር በብዙ እጥፍ ማትረፍ ትችላለች።
በአሁን ወቅት በአገሪቷ እየታየ ያለውን ለውጥ ተከትሎ መንግስት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ የሚገኝ ቢሆንም ዋጋ ሊያስከፍሉ የሚችሉ ክፍተቶችም በግልፅ ይታያሉ። ታዲያ ዛሬ እዚህም እዚያም ብልጭ ድርግም የሚሉ የህግ ጥሰቶችን መንግስት በወቅቱ ማረምና ማስተካከል ካልቻለ ነገ ከነገ ወዲያ የአገርን ህልውና ከመፈታተን አልፈው ትልቅ ዋጋ ያስከፍላሉ። መንግስት እንደ መንግስትነቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዛሬ በአገሪቷ ፍትህ እና ሰላምን ለማረጋገጥ አበክሮ ሊሰራ ይገባል።
እርግጥ ነው ባለፉት ጊዜያት የፍትህ ዘርፉን ጨምሮ በታራሚ ዜጎች ላይ ይደርስ የነበረውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች እንዲሁም የተለያዩ አስከፊ የታሪክ ምዕራፎች አልፈዋል። በመሆኑም መንግስት እነዚህንና መሰል ታሪኮችን ለማደስ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል። ይሁንና አሁንም በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች የፍትህ ዘርፉን የሚያደነቃቅፉ በርካታ እንቅፋቶች በመኖራቸው ምክንያት የፍትህ ዘርፉን በአግባቡ ለመምራት አዳጋች መሆኑን በርካቶች ይናገራሉ።
ፍርድ ቤቶች ባላቸው ሰፊ ድርሻ የዳኝነት ስርዓቱን ወይም የፍትህ አሰጣጥ ሂደቱን ነፃ፣ ገለልተኛ ቀልጣፋ እንዲሁም ተገማች በማድረግ የህዝብ አመኔታን ማትረፍ እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ ሊፈጠርላቸው ይገባል።
ይህም ሲባል ምቹ የሆኑ የፍርድ ሂደቶች የሚስተናገዱበት ቦታዎች፣ ለስራ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁስ፣ የቋንቋ አጠቃቀም፣ የባለሙያዎች እጥረትና የመሳሰሉ ችግሮች በስፋት ይስተዋላሉ። እነዚህ ችግሮች ሊፈቱ ይገባል::
የዳኝነት ጉዳይ በተለይም የፍትህ ጉዳይ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በየትም አገር ቢሆን በዋናነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባና ትልቅ ስልጣን፣ ሀይል እና ጉልበት ያለው የመንግስት ተቋም ነው። በመሆኑም ትልቅ ትኩረት የሚያስፈልገው መሆኑ ዕሙን ነው። እርግጥ ነው ከተለያዩ አቅጣጫዎች፣ ከቡድኖች እንዲሁም ከባለሙያው ግላዊ ባህሪ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ጉዳዮች የፍትህ ስርዓቱን ሊያዛቡት እንደሚችሉ ይታመናል።
ይሁንና የፍትህ ተቋማትን ነፃና ገለልተኛ በማድረግ ዳኞች ገለልተኛና ነፃ ሆነው ጉዳዮችን ማየትና መወሰን እንዲችሉ ለስራው አስፈላጊ የሆኑ ማናቸውም ጥያቄዎች መመለስ ይገባቸዋል። ከዚህ ባለፈም ወደ ፍትህ ተቋማቱ የሚገቡ ሰዎች ከተራ የስራ ዕድል መክፈት ባለፈ የፍትህ አገልግሎት ማለት የሕይወት ጥሪ መሆኑን በመገንዘብ የተለያዩ ግፊቶችን ተቋቁመው ለፍትህ መቆም ይጠበቅባቸዋል።
በፍትህ ተቋማት አካባቢ የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ እንዲሁም ባለሙያዎች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ሁሉ አቅም በፈቀደ መጠን አፋጣኝ መልስ በመስጠት የነፃነት አርማ የሆነውን የፍትህ ዘርፉ ነፃ፣ ገለልተኛና የህዝቦች አመኔታን ያተረፈ እንዲሆን ማድረግ ይገባል።
በመጨረሻም አንድ የሕግ ሊቅ “ለሰው ልጅ በምድር ላይ ሀሴትን የሚሰጥ ትልቅ ነገር ቢኖር ፍትህ ነው” እንዳለው አሁን በአገሪቷ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ በማስቀጠል አስተማማኝ የሆነ የፍትህ ስርዓት ተገንብቶ መጭው ትውልድ ብሩህ ተስፋ እንዲኖረው እንዲሁም ፍትህ የሰፈነባትና ደህንነቷ የተጠበቀች አገር ሆና፤ ዜጎች በአገራቸው በነፃነት አንገታቸውን ቀና አድርገው መራመድ እንዲችሉ መንግስት ለፍትህ ዘርፉ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል እንላለን።
አዲስ ዘመን ጥር 18/2012