የሀገራችን ባለስልጣኖችና መስሪያቤቶች መገለጫ ከሆኑ ጉዳዮች ውስጥ የሀሰት ሪፖርት አንዱ ነው። ያልተሰራውን ተሰራ፤ ስራ ያልያዘውን ያዘ፤ በልቶ ማደር ያልቻለውን አርሶ አደር ባለሃብት ሆነ፤ ከዕለት ጉርሱ መትረፍ ያልቻለውን በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጀውን ወጣት ወደ ባለሃብትነት ተሸጋገረ፤ በዓለም ባንክና በአይ ኤም ኤፍ ጭምር የተረጋገጠውን የ8 በመቶ የሀገራችንን ዕድገት 11 በመቶ ደርሷል የሚሉ የሀሰት ሪፖርቶች በየመገናኛ ብዙሃኑና በየቀበሌው ደጃፍ ያለመሸማቀቅና ያለሃፍረት ሲነገሩ ቆይተዋል።
በተለይም ከለውጡ በፊት የነበረው አገዛዝ ከሚታወቅባቸውና የህዝብንም እምነትና ተቀባይነት ካሳጡት ባህሪዎቹ ውስጥ በድፍረት የሚነገሩ የሀሰት ሪፖርቶች ተጠቃሾች ናቸው። በመልካም አስተዳደር እየተሰቃየ እና እየተማረረ ያለውን ነዋሪ በመልካም አስተዳደር ተንበሽብሸዋል፤ ውሃ የተጠማውን ሀዝብ ጥሙን አርክተንለታል፤ እንደሃምሌ ጸሃይ መብራት ብርቅ የሆነበትን ነዋሪ በብርሃን አጥለቅልቀነዋል የሚሉ የሀሰት ሪፖርቶች በየቀኑ ሲናኙ ኖረዋል።
በዚህም የተነሳ ባለስልጣናት ስኳር በብዛት በገበያው ውስጥ እንዲኖር አድርገናል ሲሉ ህዝቡ በተቃራኒው ስኳር ሊጠፋ እንደሆነ ይጠረጥራል። ዘይት በስፋት እያሰራጨን ሲባል የዘይት እጥረት መኖሩን ያምናል። የመብራት ስርጭቱ ተሻሽሏል ሲባል መብራት ሊጠፋ መሆኑን ቀልቡ ይነግረዋል። የሀሰት ሪፖርት እንደዚህ አድርጎ መንግስትንና ህዝብን በተለያዩ አቅጣጫዎች እንዲነጉዱ አድርጓል።
ዛሬም ይህ በሽታ የለቀቀን አይመስልኝም። ሰሞኑን በአንድ ሚዲያ ያዳመጥኩት ዜናም ከትላንቱ በሽታ ዛሬም እንዳልተፈወስን አረጋግጦልኛል። የአዲስ አበባ የስራ ፈጠራ ኮሚሽን ባለፉት ስድስት ወራት ለወጣቶች ፈጥሬያቸዋለሁ ብሎ ያስተላለፈውን መረጃ መሰረት በማድረግ የከተማው ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት የተባለው ነገር ዕውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ወደ ወረዳዎች በመውረድ መረጃዎችን የመፈተሽ ስራዎችን ሰርተው ተመልሰዋል። ቋሚ ኮሚቴው ባደረገው የማጣራት ስራም በሪፖርቱ ተፈጥሯል ተብሎ ከተጠቀሰው የስራ ዕድል ውስጥ 50 በመቶ ያህሉ በተጨባጭ ወደ መሬት ተወርዶ ሲታይ እንዳልተገኘ በሚዲያ ሲናገሩ አድምጫለሁ።
ሌሎች ዘርፎችም በዚህ አግባብ ቢፈተሹ ተመሳሳይ ችግሮች ይጠፋባቸዋል ብዬ አላምንም። ስለዚህም ያልሰራነውን ሰራን ብለው ህዝብና መንግስትን የሚያራርቁና የራሳቸውን ስልጣን ዘመን ለማራዘም ሲሉ በሀሰተኛ ሪፖርት የሚተዳደሩ ባለስልጣናትን እየተከታተሉ የእርምት እርምጃ መውሰዱ ከሚመለከታቸው አካላት በሙሉ የሚጠበቅ ተግባር ነው። እዚህ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ያከናወኑትን የማረጋገጥ ተግባር ሳላደንቅ ማለፍ አልፈልግም። ሌሎችም አካላት ይህንኑ አርአያነት ያለው ተግባር በመከተል የሀሰተኛ ሪፖርት ቀበኞችን ሊያጋልጡና የተሰራው ስራ በልኩ ህዝብ እንዲያውቀው ማድረግ ይገባል። በተለይ ወቅቱ በርካታ ተቋማት የስድስት ወራት አፈጻጸማቸውን የሚያቀርቡበት ወቅት በመሆኑ ለሀሰተኛ ሪፖርቶች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ምርቱን ከገለባው መለየት ያስፈልጋል።
ተሰሩ ተብለው ሪፖርት የተደረገባቸው መረጃዎች በእውነት መሬት ላይ አሉ ወይ ? ስራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነዋል ተብለው የተጠቀሱት ወጣቶችና ሴቶች የሚቆጠሩና ሲጠየቁም ምስክርነት የሚሰጡ ናቸው ወይ ? የሚለውን መፈተሽ ይገባል። በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ለወጣቶችና ለሴቶች ተፈጠረ የተባለው የስራ ዕድል ሪፖርት ሲደረግ ከአጠቃላይ የከተማዋ ነዋሪው ቁጥር በላይ ሆኖ መገኘቱን አስታውሳለሁ።
በአንድ ወቅት ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ከተማ አስተዳደሩ ድረስ ያሉ ኃላፊዎች በተግባር የሰሩትን ሳይሆን ምናባቸው ያመነጨውንና ለጊዜው ስልጣኔን ያቆይልኛል ብለው ያሰቡትን ቁጥር እንዳሻቸው በሪፖርታቸው ውስጥ አካተው ‹‹ይሄን ያህል የስራ ዕድል ፈጥሬያለሁ፤ ይህም ዕቅዴን ከ100 ፐርሰንት በላይ ማሳካት መቻሌን ያሳያል፤ የከተማዋን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት መቶ በመቶ ማሳካት ችያለሁ፤ የመብራት አቅርቦትን ለሁሉም የከተማዋ ነዋሪ አዳርሻለሁ፤ ስኳርና ዘይትን ጨምሮ ሁሉንም መሰረታዊ ፍጆታዎች ለነዋሪው አቅርቤአለሁ›› ወዘተ የሚሉ የሀሰት ሪፖርቶች ከተማዋን እንዳጥለቀለቋት አስታውሳለሁ።
በዚህ ወቅት ግን የከተማዋ ነዋሪ በኑሮ ውድነት ወገቡ የጎበጠበት፤ በውሃና በመብራት ችግር የተማረረበትና አቤቱታውን እንኳን ለማዳመጥ ሰሚ የታጣበት፤ ስኳርና ዘይት እንደቅንጦት ዕቃ የተቆጠሩበት ጊዜ ነበር። የህብረተሰቡን ኑሮ መመልከት ያልቻለው የከተማዋ አስተዳደር የሚደርሱት ሪፖርቶችና የነዋሪው ዕሮሮ ለየቅል መሆኑን ለመረዳት አልቻለም። ስለዚህም መሰል ችግሮች እንዳይፈጠሩና ዛሬም የሀሰተኛ ሪፖርቶች ሰለባ እንዳንሆን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። የአበራሽን ጠበሳ ያየ በእሳት አይጫወትምና !
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 16/2012
እስማኤል አረቦ