ባለፈው ሳምንት ስለሀርሞኒካ በሰፊው አስነብበናል። የመገናኛ ብዙኃን ከአገራችን ባህላዊ ነገሮች ይልቅ የውጭውን ማስተዋወቃቸው ለባህላዊ ነገሮች መረሳት ምክንያት መሆናቸውንም ወቀስ አድርገን ነበር። ታዲያ ይህን የወቀሰ ጋዜጠኛ ራሱስ ምን አስተዋዋቂ አደረገው ማሰኘቱ አይቀርም። ለመሆኑ ስለአታሞ ስንቶቻችሁ ታውቁ ይሆን? በሉ ከሀርሞኒካው ድባብ ውጡና ስለአታሞም እናውራ። በነገራችን ላይ አታሞ ለጥምቀት ብቻ ሳይሆን እንደ እንቁጣጣሽና መስቀል ባሉ በዓላትም ልጃገረዶች የሚጫወቱበት የሙዚቃ መሳሪያ ነው። በዋናነት ግን ለጥምቀትና ለሰርግ ነው። መቼስ እንግዲህ የጥር ወር የሰርግ አይደል?
በነገራችን ላይ ጥምቀቱ ሎሚ ወርወራ ከአታሞው ጨዋታ የመጣ ነው (በእርግጥ ሎሚ ወርወራ ባህላዊ እንደሆነ ማንም ያውቃል)። ለልጃገረዶችና ጎረምሶች ሎሚ የፍቅር መገለጫ ነው። ሎሚ ወረወረባት ማለት በቃ ቀልቤ አርፎብሻል እንደማለት ነው። በዘመንኛው እንተርጉመው ከተባለ ለከፋ መሆኑ ነው። ይሄ የሎሚ ጨዋታ ታዲያ የሚደምቀው በአታሞ ነበር። በሀርሞኒካ፤ ክብር ሰርተው፣ ወገብ ለወገብ ተቃቅፈው፣ አንዳንዴም ከዳሌ አካባቢ በመነካካት በአስቂኝና አዋቂዎችንም እስከማሳፈር በሚደርስ ትዕይንት ይከወናል። በአታሞው ጨዋታ ግን እንዲህ ብሎ ነገር የለም። ልጃገረዶች ክብ ሰርተው ይቆመማሉ፤ ጎረምሶች ከኋላ ያጅባሉ። በሀርሞኒካው እርስበርስ መወዳደስ የለም፤ እንዲያውም የዘለፋ፣ የተስፋ መቁረጥና የሱስ ግጥሞች ይበዛሉ። በአታሞ ግን እንዲህ ብሎ ነገር የለም። የአታሞ ጨዋታ መወዳደስ ነው፤ መደናነቅ ነው።
አታሞ የምት የሙዚቃ መሳሪያ ነው። የሚዘጋጀውም ከቆዳና ከሸክላ ድስት ነው። በፎቶው ላይ እንደሚታየው አታሞ ቅርጹም የድስት ቅርጽ ነው(ክብ ማለት ነው)። ለአታሞ የሚመረጠው ቆዳ የፍየል፣ የተኩላ፣ የድኩላና ፍየል መሰል እንስሳት ነው። የዚህ ምክንያቱ ሌላ ሳይሆን ስስነቱ ስለሚፈለግ ነው። የተሰራበት ቆዳ ስስ ከሆነ ነው ድምጸ መረዋ የሚሆነው። የተዘጋጀው ቆዳም ከድስቱ አፍ ላይ ተወጥሮ በድስቱ ዙሪያ ይተበተባል። ይህን የሚሰሩት እናቶች ናቸው። አልፎ አልፎም ኮረዶች ራሳቸው ሊሰሩት ይችላሉ።
ድምጸ መረዋነቱ እንደየ አታሞው ይለያያል። እንዳልኳችሁ ዋናው አሰራሩ ነው። ቆዳው በደንብ መወጠር አለበት። በሌላ በኩል ደግሞ እንደ አታሞ መችዋም ይለያያል። አታሞ መችዋ ዝም ብላ እንዶፍ እንዶፍ የምታደርገው ከሆነ ይቀበሏታል። አለበለዚያ በዘፈን ይነግሯታል።
አታሞውን ምችው
አርጊው ደምቧ ደምቧ፤
እንደ ወለደች ላም
አታሰኝው እምቧ።
በጨዋታው ውስጥ ከመወዳደሱ ጋር ሎሚ መወራወሩ ይጀምራል። በእርግጥ ሎሚ ወርወራው ከገጠር ይልቅ በከተሞች አካባቢ ነው የበለጠ የሚታየው። ገጠር ውስጥ ከመወራወር ይልቅ በስጦታ መልክ ነው የሚሰጠው። ሌላው ልዩነት ደግሞ ሴቷ ለወደደችው ወንድ ሎሚ የምትሰጥ መሆኑ ነው። በከተማ አካባቢ የሚታወቀው ወንዱ ሲወረውር ነው፤ በገጠሩ ባህል ግን ሴቷ ለከንፈር ወዳጇ ወይም ቀልቧ ለወደደው ሎሚ ትሰጣለች። ምናልባት ከአካባቢ አካባቢ ሊለያይ ስለሚችል በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የተገለጸው በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳና በደቡብ ወሎ አካባቢዎች ያስተዋልኩትን ነው።
የጥምቀት በዓል በተለይም ጎረምሶችና ኮረዶች በጉጉት የሚጠብቁት ነው። ይህ እንግዲህ የከንፈር ወዳጆች ለሆኑትም ለሌላቸውም ነው። የከንፈር ወዳጅ የሆኑት የዚህን ዕለት ተገናኝተው ይጫወታሉ፤ የሌላቸውም የሚያገኙት በጥምቀት ጨዋታ ላይ ነው። የከንፈር ወዳጅ ብቻ ሳይሆን የትዳር አጋርም የሚታጨው የጥምቀት በዓል ላይ ነው። ከዚያ መሀል የመረጣትን ለጓደኞቹ ይናገራል። ጓደኞቹም ነገሩ የልጁ ቤተሰብ ጋ እንዲደርስ ያደርጋሉ። በቃ የጥምቀት ዕለት ቀልቡ ያረፈባትን ያገባል ማለት ነው።
በነገራችን ላይ ካሕሳይ ገብረእግዚአብሔር በአንድ መጽሐፋቸው ላይ(ሕብረ ብዕር) እንደ ጥምቀትና አሸንዳ ያሉ የልጃገረዶች በዓል ላይ ሚስት ማጨት አጉል እንደሆነ ጽፈው ነበር። ምክንያታቸው ደግሞ በእንዲህ አይነት በዓላት ላይ ሁሉም ቆንጆ ስለሚሆኑ ነው(በኋላ ጣጣ እንዳይመጣ ማለታቸው ነው)።
ይህ በሎሚ የሚገለጸው የኮረዶችና ጎረምሶች ፍቅር ዘፈናቸውን እንኳን ሎሚ ሎሚ እንዲል አድርጎታል። እዚሁ ጥምቀት ላይ እንኳን አንዲት ኮረዳ ጓደኛዋን ዓመት ዓመቱ ያድርሰን ለማለት በሎሚ ግጥም ነው።
የከረረች ሎሚ የከረረች ሎሚ
እከልዬ እከሌ በደህና ክረሚ።
ይህ የሎሚ ጨዋታ በጥምቀት ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም። በሰርግ ሰሞን በሚደረግ የአጫዋች (ተበችሳ) የልጃገረዶችና ጎረምሶች ጨዋታ ላይም በስፋት ይታያል። አጫዋች (በወሎ አካባቢ ተበችሳ) ማለት ከሰርጉ ቀን በፊት የሚደረግ ጨዋታ ነው (ለዝርዝሩ ሌላ ቀን እመለሳለሁ)።
ጽሑፌን ፍትሐዊ ለማድረግ ስለአዲስ አበባውም (ይሄኛውን እንኳን ቴሌቪዥኑ ሁሉ ሲያሳያችሁ ይውላል ብዬ ነው) ያስተዋልኩትን ልናገር። የከተራ ዕለትና የጥምቀት ዕለት ጃንሜዳ የነበረ ሰው እዚህም እዚያም ክብ ሰርተው አንገት ለአንገት ተቆላልፈው የሚደንሱ ወጣቶችን አይቷል። በተለይም ሴትና ወንድ ሆነው ሲደንሱ ደግሞ ተመልካቹ ይበዛል። አንዳንዶቹ እንዲያውም ነጠላ የተሸፋፈኑም ነበሩ። ነጠላው ውስጥ ምን ያደርጉ እንደነበር እንግዲህ እግዜር ይወቀው። ሴትና ወንድ ሆነው ሲደንሱ ብዙ ተመልካች ቢኖረውም ሴቶች ግን በጣም ሲግደረደሩ ነበር። በግድ ተጎትታ የገባች እንኳን ብትኖር እንደምንም አዘናግታ አፈትልካ ትወጣለች። እርግጥ ነው አንዳንድ ሴቶች በራሳቸው ተነሳሽነትም ወንዶችን ይዘው ገብተው የደነሱ መኖራቸውን አይቻለሁ።
በሀርሞኒካው ጨዋታ ውስጥ ደግሞ ጭራሮ እና ረገጣ የሚባሉ የአጨዋወት ዘዴዎችንም ሰምቻለሁ። እንግዲህ ሀርሞኒካ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የራሱን ስልት ፈጥረውለታል ማለት ነው። ወይም ደግሞ ወጣቶቹ የራሳቸው ትርጉም ሰጥተውታል ማለት ነው። እንደዚያ መሆን አለበት እንጂ መቼም ይህ የፈረንጅ የሙዚቃ መሳሪያ ጭራሮ እና ረገጣ የሚሉ ቃላትን ፈረንጆች ሊያውቋቸው አይችሉም።
ሌላው የጃንሜዳ ድባብ የነበረው ደግሞ የቁማር ጨዋታ ነበር(ይህን እንኳን ድባብ ማለት ይከብዳል)። በገንዘብ የሚደረጉ የተለያዩ አይነት ጨዋታዎች ነበሩ። በጨዋታው ውስጥ ወይ ገንዘብ ታገኛለህ ወይም ታጣለህ። እንግዲህ በአጭሩ ያው ቁማር ማለት አይደል?
ስለአዲስ አበባው ጥምቀት አንድ የማደንቀው ነገር አለኝ። እኔ እምለው ግን አዲስ አበባ ውስጥ ይህን ያህል ሴት የባህል ቀሚስ ነበረው እንዴ? ይሄ ‹‹ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ›› የሚባል አባባል ትልቅ ተፅዕኖ ሳይፈጥር አልቀረም። እንኳን ወደ ዋናው በዓል ያለበት ጃንሜዳ ግሮሰሪዎች ሁሉ ቀሚስ በቀሚስ ነበሩ። በመንገድ ላይ ሁሉ ቀሚስ፣ ካፌ ብገባ ቀሚስ፣ ግሮሰሪ ብገባ ቀሚስ፣ ቢሮ ብገባ ቀሚስ በቃ ሰሞኑን ቀሚስ በቀሚስ ነበር። የምር ሴቶች ከባህል አለባበስ እያፈነገጡ ነው የሚባለው ሀሜት ውድቅ ሊሆን ነው። ሴቶች ይልመድባችሁ ብያለሁ! በጥምቀት ብቻም ሳይሆን በአዘቦቱም ቀን።
አታሞና ሎሚ በወርሃ ጥር ትልቅ ቦታ አላቸው። አንድ የሚገርመኝ ነገር ግን አታሞ በባህል ዘፋኞች እንኳን ብዙም የማይታወቅ መሆኑ ነው። እነ ከበሮ፣ ዋሽንት፣ ማሲንቆና ክራር ቢያንስ በስም እንኳን ይታወቃሉ። አታሞ ግን እስከአሁን ድረስ ገጠር ውስጥ ናት፤ ይባስ ብሎ ደግሞ እዚያም እየቀረች ነው። በባህል ላይ የተሰሩ ብዙ ጥናቶችንም ለመቃኘት ሞክሬያለሁ፤ ስለአታሞ ግን ስሟን ከመጥቀስ የዘለለ የተብራራ ነገር አላገኘሁም። ባህል እንዲህ እየሆነ ነውና የሚረሳ ባህሎቻችንን እናስታውስ!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 16/2012
ዋለልኝ አየለ