በኢትዮጵያ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን መጀመር ሳይሆን መጨረሱ ብርቅ ነው። ይህን አባባል የሚያጠናክርልን ደግሞ ባለፉት አምስት አመታት ብቻ በመንግሰት ከተከናወኑ 60 ትላልቅ ፕሮጀክቶች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት በወቅቱ ባለመጠናቀቃቸው መንግስትን ለተጨማሪ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ወጪ መዳረጋቸው ነው። በአጠቃላይም የፕሮጀክቶች መዘግየት እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር ብክነትም አስከትሏል።
በኢትዮጵያ ያለውን የፕሮጀክቶች መጓተት አስመልክቶ በዘርፉ ባለሙያዎች በተደረገ ጥናትም በሀገሪቱ ከ30 እስከ 50 በመቶ የሚጠጉ ፕሮጀክቶች ተጨማሪ ወጪዎችን ጠይቀዋል። ይባሱንም እስከ 400 በመቶ ድረስ ተጨማሪ ወጪን የጠየቁ ፕሮጀክቶች እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል።
በፕላንና ልማት ኮሚሽን የተካሄደ ጥናት እንደሚያሳየውም ባለፉት አስራ አራት ዓመታት በፌዴራል መንግስት የተገነቡ እና እየተገነቡ ያሉ የመስኖ ዘርፍ ፕሮጀክቶች 15 ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪን ጠይቀዋል። በመንገድ ልማት ፕሮጀክቶች ውስጥም ከተገመተው በላይ መንግስት 32 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ አውጥቷል።
በኢትዮጵያ ከተጀመሩ ፕሮጀክቶች ውስጥ የዚህ ችግር ሰለባ ያልሆነ የለም። ከህዳሴው ግድብ ጀምሮ የስኳር ፕሮጀክቶች፤ የባቡር ግንባታዎች፤ የቤት ልማቶች፤ የመንገድ ግንባታዎች፤ ስታዲየሞችና ሆስፒታሎች ግንባታቸው ከተጀመረ ከዓመታት በኋላ እንኳን ተጠናቀው ፍሬያቸውን ማየት አልቻልንም።
እንደ በሽታ ስር ሰዶ የቆየው የፕሮጀክቶች መጓተት የዜጎችን የመልማትና የመጠቀም መብትን የሚያሳጣ ከመሆኑም ባሻገር በብድር የመጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በወቅቱ ባለመከፈሉ ለተጨማሪ ወለድና ዕዳ የሚዳርግ ነው።
በዚህና መሰል ሳንካዎች ምክንያት ኢትዮጵያ በየዓመቱ 20 ቢሊዮን ብር ዕዳ ትገፈግፋለች። ይህ ደግሞ ሀገሪቱን ከድህነት አዙሪት ውስጥ ሊያስወጧት የሚችሉ ልማቶችን እንዳታከናውን የዜጎችም ህይወት እንዳይሻሻል ተጨባጭ ችግር ፈጥሯል።
የፕሮጀክቶች መዘግየት ከወጪ ባሻገርም የጊዜ ብክነትና ተገልጋዩ ህብረተሰብም ማግኘት የሚገባውን ጥቅም እንዳያገኝ የሚያደርግ ነው። አብዛኞቹ ፕሮጀክቶችም ይጠናቀቃሉ ተብሎ ከተያዘላቸው ጊዜ በአማካኝ አራት አመታት ያህል ተጓተዋል። አማካኝ አፈፃፀማቸውም ከ45 በመቶ የዘለለ እንዳልሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከፍተኛ የሀገር ሀብት የፈሰሰባቸው ፕሮጀክቶቹ ለመጓተታቸው ዋነኛ መንስዔዎች ከሆኑት መካከል የዲዛይን ስራዎች መጓደል፣ የኮንትራት አስተዳደርና የክትትል ስራዎች ማነስ፣ የጨረታ ሂደቶች ላይ የታዩ የሙያ ስነምግባር ግድፈቶች፣ የግል ጥቅም ላይ ማተኮር፣ የመረጃ ክፍተቶች እንዲሁም የአቅም ውስንነቶች ጋር የተያያዙ መሆናቸውን በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ጠቁመዋል።
እነዚህንና መሰል ችግሮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የፕሮጀክቶች መዘግየትን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚስችል አዋጅ መዘጋጀቱን ከሰሞኑ ተሰምቷል። አዋጁ የመንግስት ፕሮጀክቶች ከጅማሬ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሚያልፉባቸውን ሂደቶችን ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መልኩ ለመተግባር እንደሚያስችል ታምኖበታል።
በመሆኑም መንግስት በፕሮጀክቶች መዘግየት ምክንያት በሀገርና በዜጎች ላይ እየደረሱ ያሉ ኪሳራዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች ይበል የሚያሰኙ በመሆናቸው በቀጣይም ተገቢው ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊተገበሩ ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥር 16/2012