የትምህርትን ጥራትና ተደራሽነት እውን ለማድረግ ከሚያስፈልጉ ወሳኝ ግብዓቶች መካከል አንዱ ቴክኖሎጂ ነው። ዘርፉን በቴክኖሎጂ መደገፍ ተማሪዎች ዓለም አቀፋዊ እውቀትን እንዲያገኙና ከሌሎች የዓለም ባለሙያዎች ጋር እንዲግባቡ ያስችላቸዋል። ተማሪዎች በጊዜና በቦታ ሳይገደቡ መደበኛ ትምህርትና ከመደበኛ ትምህርት ውጭ ያሉ እውቀቶችን በፍጥነትና በጥራት እንዲጨብጡም ያስችላቸዋል። የመማር ማስተማር ሥራውንም ቢሆን በተግባር ተኮር እውቀት ለመደገፍ ያስችላል። ሥራንም ፈጣን ያደርገዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ሥራ ፈጣሪ ትውልድን ለማፍራት ይረዳል።
በኢትዮጵያም በቴክኖሎጂ በመታገዝ የትምህርት ዘርፉ ዘላቂ እድገት እንዲያስመዘግብ ለማድረግ የሚረዱ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ። ይህን ተግባር የሚደግፉ በርካታ አጋር የልማት ተቋማትም በሀገሪቱ ተሰማርተዋል። የትምህርት ሚኒስቴር ከእነዚህ ተቋማት ጋር በመተባበር የሚተገብራቸው ዘርፈ ብዙ የትምህርት ቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶች አሉ። እነዚህ ተግባራት ደግሞ የዘርፉን እድገት ዘላቂ የማድረግ አወንታዊ ሚና እንዲኖራቸው ይጠበቃል።
ቴክኖሎጂን በመጠቀም የትምህርትን ዘርፉን በማዘመን ተግባር ላይ የተሰማሩ ሥራ ፈጣሪዎችን ከሚደግፉ ተቋማት መካከል አንዱ ‹‹ሪች ፎር ቼንጅ›› (Reach For Change) የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው። የድርጅቱ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ወይዘሮ መቅድም ጉልላት እንደሚያስረዱት፣ ተቋሙ ማኅበራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ሥራዎችን ያከናውናል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ሥራ ፈጣሪዎችን (Social Entrepreneurs) የመደግፍ ተግባር አንዱ ነው።
ድርጅቱ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰሠራባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ ትምህርት እንደሆነ የጠቆሙት ዳይሬክተሯ፣ ከ‹‹ማስተርካርድ ፋውንዴሽን›› (Mastercard Foundation) ጋር በመተባበር የሚያከናውነው ‹‹ኤድቴክ (EdTech/Education Technology) ፌሎውሽፕ›› ደግሞ በትምህርት ዘርፍ ከሚሠራቸው ውስጥ እንደሚጠቀስ ያነሳሉ። በፋውንዴሽኑ የገንዘብ ድጋፍ የሚከናወነው ፕሮግራሙ፣ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ትምህርትን የሚያግዙና የሚያዘምኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የሠሩ ሥራ ፈጣሪዎችን ያበረታታል፣ ሥራዎቻቸውን እንዲያሳድጉ ያግዛልም።
ፕሮጀክቱ በሦስት ዙሮች ለአምስት ዓመታት የሚተገበር ሲሆን፣ በመጀመሪያው ዙር መርሃ ግብር 11 የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል። በድርጅቱ ድጋፍ የተደረገላቸው ሥራ ፈጣሪዎች ትምህርትን በቴክኖሎጂ በታገዘ አሠራር በመደገፍ ውጤት ማስመዝገብ ችለዋልም። ሥራ ፈጣሪዎቹ ከ255ሺህ በላይ ተጠቃሚዎችን ተደራሽ መሆን የቻለ አገልግሎት ሰጥተዋል። ከአዲስ አበባ አልፈው በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎችንና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችንም ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል። በሁለተኛው ዙር የሚሳተፉ ሥራ ፈጣሪዎች ተለይተው ድጋፍ የማድረጉ ሥራ እንደተጀመረ ዳይሬክተሯ አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የቴክኖሎጂዎቹን ተደራሽነት ለማስፋትና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ የፋይናንስ ድጋፍ ወሳኝ በመሆኑ የፈጠራ ባለቤቶቹን አብረዋቸው ሊሠሩ ፈቃደኛ ከሆኑ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ለማገናኘት ጥረት ተደርጓል። ‹‹የእኛ ዓላማ በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን መሙላት ነው›› የሚሉት ወ/ሮ መቅድም፣ የ‹‹ሪች ፎር ቼንጅ›› ሥራዎች ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት አሰጣጥን ለማዘመን የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያግዝም ይገልፃሉ።
እ.አ.አ በ2006 የተቋቋመው ‹‹ማስተርካርድ ፋውንዴሽን››፣ ትምህርትን የማዘመን እና የፋይናንስ አካታችነትን በማረጋገጥ በታዳጊ ሀገራት ብልጽግናን እውን የማድረግ ዓላማ አለው። ፋውንዴሽኑ ከስድስት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ቢሮ መክፈቱን የሚያስታውሱት በማስተርካርድ ፋውንዴሽን ኢትዮጵያ የሠራተኛ ልማት ኃላፊ ፍቃዱ ሙሉጌታ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ ከሚያከናውናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት መካከል የትምህርት ቴክኖሎጂ ልማት አንዱ እንደሆነ ያስረዳሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፣ በፋይናንስ አካታችነት፣ በትምህርትና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ልማት በሚያከናውናቸው ሥራዎች በርካታ ወጣት ኢትዮጵያውን የሥራ እድል እንዲያገኙ አስችሏል።
‹‹ትምህርት ለሁሉም በፍትሃዊነት መዳረስ እንደሚገባው እናምናለን፤ ለዚህም ነው ከስድስት ዓመታት በፊት ባቋቋምነው የፈጠራ ተኮር መማር ማስማር ማዕከል በኩል የማስተርካርድ ፋውንዴሽን ኤድቴክ ፌሎውሺፕን የጀመርነው። መርሃ ግብሩ የትምህርት ዘርፍ ቴክኖሎጂዎችን ለመለየት፣ ለመደገፍና ለማሳደግ የተቀረፀ ፕሮጀክት ነው›› ይላሉ።
እንደሳቸው ማብራሪያ፣ የፋውንዴሽኑ የመማር ማስተማር ማዕከል በትምህርት ዘርፍ ዘላቂ ለውጥ መፍጠር የሚያስችል ምቹ የትምህርት ቴክኖሎጂ ምህዳርን የሚያሰፋ ነው። በዚህም ለዘርፉ ችግሮች መፍትሄ ሊሆኑ በሚችሉ ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ላይ የፋይናንስ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
ማስተርካርድ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ከሚያከናውናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት መካከል የትምህርት ቴክኖሎጂ ልማት አንዱ እንደሆነ የጠቆሙት ፍቃዱ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ የሚያከናውነውን የኤድቴክ ፕሮግራም የሚተገብረው ከ‹ሪች ፎር ቼንጅ› ጋር በመተባበር እንደሆነ ይናገራሉ። በዚህም ትምህርት ለማዘመን በሚረዱ የፈጠራ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ያስረዳሉ።
በማስተርካርድ ፋውንዴሽን የኤድቴክ ፌሎውሺፕ ተጠቃሚ ከሆኑ የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጣሪዎች መካከል አንዱ ‹‹እንጫት ጌምስ›› የተሰኘው የቴክኖሎጂ ድርጅት ነው። የድርጅቱ መስራች ሰርክዝናው ሲራክ እንደሚገልፀው፣ ‹‹እንጫወት ጌምስ›› ልጆች ጨዋታ እየተጫወቱ የሚማሩባቸውን፣ መጽሐፍና ስልክ አንድ ላይ በማቀናጀት እውቀት የሚቀስሙባቸውን እና የተለያዩ መዝሙሮችንና ጨዋታዎችን የሚያገኙባቸውን የቴክኖሎጂ አማራጮችን ያቀረበ ድርጅት ነው። በፕሮጀክቱ ያገኙት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ ሥራቸውን በአጭር ጊዜ ለማቀላጠፍና የሰው ኃይላቸውን ለመጨመር እንዳገዛቸው ይናገራል።
‹‹በፌሎውሺፑ የተደረገልን ድጋፍ ሥራችንን አፋጥኖልናል፤ ሰፋ ያለ የሰው ኃይል እንዲኖረንም አግዞናል›› የሚለው ሰርክዝናው፣ ድርጅታቸው ባገኘነው ድጋፍ በመታገዝ ሥራዎቹን ለማስፋትና በብዙ ቋንቋዎች ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ እንደሆነም ይገልፃል።
የትምህርት ሚኒስቴር በትምህርት ዘርፍ የሚተገበሩ ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት የዘርፉን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የሚያከናውናቸው በርካታ ሥራዎች አሉ። ሚኒስቴሩ ከአጋር ተቋማት ጋር በመተባበር የሚተገበሩ የትምህርት ቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶችን የሚያስተባብር ሲሆን፣ ፕሮጀክቶቹ የትምህርት ተደራሽነትን በማሳደግ ዘመናዊ የትምህርት አቀራረብን እውን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስለማበርከታቸው ተገልጿል።
በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የትምህርት ሚኒስቴር አማካሪ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት፣ ‹‹የትምህርት ቴክኖሎጂዎች የትምህርት ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ በማገዝ የዘርፉን እድገት ለማፋጠን የሚያስችሉ በመሆናቸው የቅንጦት መሣሪያዎች ሳይሆኑ አስፈላጊ ግብዓቶች ናቸው›› ይላሉ።
ፕሮፌሰር ክንደያ እንደሚናገሩት፣ በአሁኑ ወቅት በትምህርት ዘርፍ አገልግሎት ላይ የዋሉ ቴክኖሎጂዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ለዘርፉ መሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። ለአብነት ያህልም ተማሪዎች በፍጥነትና በጥራት ትምህርት እንዲያገኙ አግዘዋል፤ የፈተና አሰጣጥና ምዘና ሥርዓቱን እንዲዘምን አድርገዋል፤ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ተደራሽነት ለማሳደግ አስችለዋል። በዚህም የትምህርት ዘርፉ ተወዳዳሪ የሰው ኃይል በማፍራት ዘላቂ እድገት እንዲኖረው እገዛ አድርገዋል።
‹‹የትምህርት ቴክኖሎጂዎች ለሀገራዊ የትምህርት ተደራሽነት፣ ጥራትና ፍትሃዊነት ከፍተኛ አወንታዊ አስተዋፅኦ አላቸው። ትምህርት ሚኒስቴርም ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ትምህርትን በቴክኖሎጂ ለማገዝ የሚከናወኑ ተግባራትን ለማስፋፋት የሚሠራቸውን ተግባራት አጠናክሮ ይቀጥላል›› በማለትም ፕሮፌሰር ክንደያ ያስረዳሉ።
አሁን የትምህርት ዘርፍ በቴክኖሎጂ ካልታገዘ ጥራት ያለውና ተወዳዳሪ የሆነ የተማረ የሰው ኃይል ማፍራት የማይታሰብበት ዘመን ሆኗል። በመሆኑም የትምህርት ዘርፍ ቴክኖሎጂዎች ከአማራጭነት ወደ አስገዳጅነት እየተሸጋገሩ ነው። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) እንደሚያብራሩት፣ በትምህርት ዘርፍ አገልግሎት ላይ የሚውሉ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች በአማራጭነት የሚተገበሩ ሳይሆኑ ለዘርፉ እድገት እጅግ አስፈላጊ ግብዓቶች ሆነዋል። የመማር ማስተማር ሥራዎችን የሚያቀላጥፉ ዲጂታል የትምህርት ግብዓቶች የትምህርት ዘርፉን ዘመኑን በሚመጥን ፍጥነት ለመምራት እና እድገቱን ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ ወሳኝ ሚና አላቸው። በመሆኑም ቴክኖሎጂዎቹን ማሳደግና በስፋት መጠቀም ይገባል።
ሚኒስትሩ እንደሚሉት፣ የትምህርት ዘርፉ በቴክኖሎጂዎች መደገፉ በትምህርት ዘርፍ የተስተዋሉ ታሪካዊ ክፍተቶችን ለመሙላት፣ የተማሪዎችን ብቃት ለማሳደግ፣ ግላዊ የትምህርት ተሞክሮን ለማስፋፋትና ትስስርን ለማጠናከር ያስችለዋል። ዘመኑ የደረሰበት የቴክኖሎጂ ደረጃ ላይ የኢትዮጵያ ወጣቶች እንዲደርሱ እድል ይሰጣቸዋል። ከዚያም ባሻገር ወጣቱ ኅብረተሰብ የቴክኖሎጂ ፍላጎቱን ደምሮበት የትምህርት ቴክኖሎጂዎችን ከአማራጭነት ወደ አስፈላጊነት ለማሸጋገርም እድል ይሰጠዋል። ይህ ደግሞ በስፋት እየታየ ይገኛል።
የቴክኖሎጂ ውጤቶች የትምህርት ዘርፉን ወደላቀ ደረጃ በማሳደግ የኢትዮጵያን የዲጂታል ሽግግር እቅድ ለማሳካት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ የሚገልፁት በለጠ (ዶ/ር)፣ የሕግ ማሕቀፎችን በአግባቡ በመቅረጽና በፍትሃዊነት በመተግበር ለትምህርት ዘርፍ ቴክኖሎጂዎች ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግም ይናገራሉ። ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከፍተኛ የወጣት ቁጥር ያላት ሀገር በመሆኗ ወጣቶችን ከቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ማፋጠን እንደሚገባም ያስገነዝባሉ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የትምህርት ዘርፍ ቴክኖሎጂዎችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋት ከአጋር አካላት ጋር በጋራ እየሠራ ይገኛል። በዚህም ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ለማሳደግ፣ የትምህርት ቴክኖሎጂዎችን ከሕዝብ አገልግሎት ተግባራት ጋር ለማስተሳሰር፣ አካታች የኢኖቬሽን ምህዳር በመፍጠር ወጣቶችን፣ ሴቶችንና ተጠቃሚ ሳይሆኑ የቆዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲሁም የግልና የመንግሥት አጋርነትን ለማጠናከር በትኩረት እየተሠራ ስለመሆኑም ያነሳሉ።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም