
የሰው ልጅ በየፈርጁ የኑሮ ዘይቤውን፣ አመለካከቱን እና የስልጣኔ ደረጃውን ከጊዜ ጋር እየተሽቀዳደመ ይቀያይራል። ይህ ብቻ አይደለም። በተፈጥሮ ኡደት የሚከሰቱ አስቸጋሪ ለውጦችን የሚቋቋምበት ብልሃትም ይዘይዳል። ስሪቱም እራሱን ከሁኔታዎች ጋር አላምዶ እንዲኖር ይፈቅዳል። ይህ ስጦታው ደግሞ በርካታ ዘመናትን አሻግሮች አሁን ያለንበት አስደናቂ የኑሮ ደረጃ ላይ አድርሶታል።
ለዛሬ የፋሽን አምዳችን በዚህ ኡደት ደመቀውና ጎልተው ስለተገኙ ጉዳዮች ለማንሳት ይወዳል። ስለ “ፊልምና የቀይ ምንጣፍ ፋሽን ትርኢት” ጥቂት እንላለን። እንደሚታወቀው ዓለማችን ላይ የሰው ልጆች ጥበብ፣ የስልጣኔና የውስጥ ስሜት መገለጫ ነፀብራቅ እንደሆነ ተደርጎ የሚወሰደው የፊልም ኢንዱስትሪ ነው። ይሄ ዘርፍ ደግሞ ብቻውን የማይቆምና በብዙ መሰል ሙያዎች የሚደገፍ ነው። ከዚህ መካከል ደግሞ የፋሽን ኢንዱስትሪው ከፊልም ሙያ ጋር ቀዳሚ ቁርኝት እንዳለው ባለሙያዎች ይገልፃሉ።
“ፊልምና ፋሽን ምን አገናኛቸው?” በማለት የጠየቃችሁ እንደሆን የሚከተለውን ሃሳብ ለማንሳት ይገደናል። ባለፉት ዘመናት በዓለማችን ላይ የፊልም ኢንዱስትሪ ከእለት እለት እያደገ የሰው ልጆችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን እየዳሰሰ እዚህ ደርሷል። ፊልም የነበሩና የሚታዩ ጉዳዮችን አጉልቶ በአዝናኝና አሳዛኝ መንገድ ከማንፀባረቅ ባሻገር አዳዲስ መላምቶችን በቴክኖሎጂ ታግዞ በማመላከት ቀጣይ የስልጣኔ ጉዞው ምን እንደሚመስል ዓይንና ጆሮ በመሆን የሚያሳይ ጭምር ነው።
ሁለቱ ዘርፎች ተመጋጋቢና ጥብቅ ቁርኝ ያላቸው መሆኑን ሙያው ውስጥ የሌለ ማንኛውም ሰው ሊያውቀው የሚችለው ጉዳይ ነው። ይህን ለመረዳት ጥሩ ፊልም ተከታታይ ብቻ መሆን በቂ ሳይሆን አይቀርም። ምክንያቱ ደግሞ ግልፅ ነው በፋሽን ዘርፉ የሚተዋወቁ አዳዲስ የመዋቢያ አልባሳት፣ ጌጣጌጦች እንዲሁም መሰል ቁሳቁሶች በቀዳሚነት የሚተዋወቁት በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ አጠንጥነው በሚሠሩ ፊልሞች ላይ ነው። ፊልሞች በዲዛይነሮች በተሠሩና ባጌጡ አልባሳት የተዋቡ ተዋኒያን ከሌሉበት ባዶ ነው። አልባሳቱም ያለ ተዋኒያኑ ነብስ ያጣሉ። በሲኒማ ቤቶች ውስጥ የሚታዩ አዳዲስ የፈጠራ ውጤት የታከለባቸው መዋቢያዎች ከተማውን በፍጥነት ያዳርሱታል። የወጣቶችን ቀልብም ይሰቡበታል። ምን ይሄ ብቻ በፊልሙ የተለያዩ ሀገራት፣ ብሄረሰቦችና የማንነት መገለጫ የሆኑ ባህላዊ አልባሳትም ይተዋወቁበታል። በዚህ የተነሳ ፊልምና ፋሽን ይተለየ ግንኙነት እንዳላቸው ይገለፃል።
የቀይ ምንጣፍ ፋሽን ትርኢት
“የቀይ ምንጣፍ ፋሽን” የሚለው ስም ለአንዳንዶቻችን አዲስ ሊሆን ይችላል። የፊልም ሽልማት ሥነሥርዓቶችን የሚከታተሉ አድናቂዎች ግን በዚህ ስም ብዙም ላይገረሙና ምንነቱን ላይጠይቁ ይችላሉ። ምክንያቱም በዓለማችን ላይ በዓመቱ ምርጥ ፊልም፣ ተዋኒያን በሚሸለሙበት ሰዓት የሚካሄድ እጅግ ተወዳጅ ሥነሥርዓት ስለሆነ ነው።
የቀይ ምንጣፍ ሥነሥርዓት በተለይ በግራሚ፣ ኦስካርና ጎልደን ግሎብን በመሳሰሉ ታላላቅ የፊልምና የሙዚቃ ሽልማት ሥነሥርዓቶች ላይ የሚደረግ ቀዳሚ ዝግጅት ነው። ተዋኒያን ተፅኖ ፈጣሪ ሰዎች፣ እንዲሁም በሙዚቃና ፊልም ኢንዱስትሪው ላይ ዝናን ያተረፉ ባለሙያዎች እጅግ ውብ በሆኑ ሥብዕናቸውን በሚገልፁ አልባሳት ተውበው በቀይ ምንጣፍ ላይ የፎቶና የቃለ መጠይቅ ሥነሥርዓት የሚያካሂዱበት ነው።
በዚህ ዝጅግት ላይ የዓለማችን ታዋቂ የፋሽን ዲዛይነሮች በታዋቂና ተወዳጅ ተዋኒያንና ተፅኖ ፈጣሪ ሰዎች አማካኝነት ሥራዎቻቸውን የሚያስተዋውቁበት ነው። ታዲያ በዲዛይን ሥራዎቻቸው ተወዳጅም ተነቃፊም ሲሆኑ ማስተዋል አዲስ አይደለም። በቀይ ምንጣፍ ሥነሥርዓቱ ላይ በተለይ ታላላቅ የሚዲያ ተቋማትና ጋዜጠኞች ስለሚገኙ አዳዲስ ፋሽን የሚያስተዋውቁ ተዋንያን ልዩ ትኩረት ያገኛሉ። በዚህ ወቅት ከፍተኛ አድናቆት የሚያስገኙ አልባሳት ትኩረት እንደሚያገኙ ሁሉ ከሥነ ምግባር አንፃር ደግሞ ነቀፌታን የሚያስተናግዱትም በተመሳሳይ የመገናኛ ብዙሃን አፍ ውስጥ ገብተው ሲብጠለጠሉ ማየት የተለመደ ነው።
ፈልምና ፋሽን በመግቢያችን ላይ ካስቀመጥነው ጉዳይ በዘለለ “በቀይ ምንጣፍ ፋሽን” ትርኢትም ጥብቅ ግንኙነት አላቸው ማለት ነው። እንዲያውም ሁለቱ ዘርፎች የአንድ ሳንቲም ገፅታ ናቸው ብንል ማጋነን የሚሆን አይመስለንም። ይሄን ካልን ዘንዳ ከዚህ በሚከተሉት ምእራፎች ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ይሄ ልምድ ምን ይመስላል የሚለውን ጉዳይ ለመመልከት እንሞክር።
እንደ እድል ሆኖ ሁለቱም ዘርፎች በኢትዮጵያ ውስጥ ገና በማደግ ላይ የሚገኙ ዘርፎች ናቸው። ይሁን እንጂ ጅምር ሂደቱ ግን የተስፋ ብልጭታ የሚታይበት ነው። ፊልሙ ሄድ መለስ እያለም ቢሆን የሚያበረታቱ ይበል የሚያሰኙ የጥበብ ውጤቶችን እያሳየ ነው። የፋሽን ዘርፉም እንደዚያው። ነገር ግን አንድ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ሁለቱም ዘርፎች በተገነቡና በደረጁ ተቋማት ሳይሆን በግለሰቦች ጥረትና ጥንካሬ የሚመሩ መሆናቸው ነው። ወደፊት ግን በዘርፉ የተደራጁ አካላት የሚያደርጉት ጥረት መልካም ውጤት ይዞ እንደሚመጣ ከወዲሁ የሚያመላክቱ እንቅስቃሴዎች እየታዩ መሆኑም የሚካድ ሃቅ አይደለም።
በኢትዮጵያ አሁን አሁን ተለያዩ ዘርፎች ላይ ውጤታማ ሥራ ለሠሩ ግለሰቦችም ሆነ ተቋማት እውቅናና ሽልማቶችን መስጠት እየተለመደ ነው። ይሄ ሥነሥርዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገት እያሳየ መሆኑንም የሚያመላክቱ ዝግጅቶችን ማስተዋል እንችላለን። በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ሽልማቶችን ማንሳት እንችላለን። በፊልሙ ዘርፍ ጉማ፣ በሙዚቃው ለዛ እንዲሁም በሥነ ፅሁፍና መሰል የኪነ ጥበብ ጉዳዮች ላይ “ሆሄ” አዋርድን ማንሳት እንችላለን። ታዲያ በእነዚህ ዝግጅቶች ላይ በሚደረጉ የቀይ ምንጣፍ ሥነሥርዓቶች የፋሽን ዲዛይነሮች የፈጠራ ውጤት የሆኑ አልባሳት በተዋኒያንና የኪነ ጥበቡ ዓለም ተፅኖ ፈጣሪዎች ተሽቀርቅረው መታየት ጀምረዋል። በዚህም የሁለቱ ዘርፍ ትስስርና የጋራ ውጤቶችንም ማየት እየቻልን ነው። ዲዛይነሮችም ሥራዎቻቸውን ለሕዝብ ይፋ የሚያደርጉበት ሁነኛ አማራጭ ያገኛሉ። ተወዳጅና የራስ ማንነትን ያልለቀቁ ሥራዎች ሠርተው ሲገኙ ይሞገሳሉ። በተቃራኒው ደግሞ የሚያስነቅፍና አፈንጋጭ ሥራዎች ሲያስተዋውቁ ከማህበረሰቡ ነቀፌታ አያመልጡም። እስካሁን ድረስ ላነሳነው ሃሳብ ማጠናከሪያ እንዲሆነን በሚከተለው የመውጫ አንቀፅ ላይ የቅርብ ጊዜ ትዝታን አንስተን ለመሰነባበት እንሞክር።
በሰባተኛው ጉማ ሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ የታደሙ ባለሙያዎች ለብሰዋቸው የነበሩት አልባሳት በተለይ በማኅበራዊው ሚዲያ ላይ ባለፈው ሳምንት ዋነኛ መነጋገሪያ ሆነው ነበር። በሽልማቱ ላይ ታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰዎች ታዳሚ የነበሩ ሲሆን ከመካከላቸውም ጥቂት የማይባሉት የተገኙት ለየት ባሉ ባሕላዊ እና ዘመናዊ አልባሳት ተውበው ነበር። በተለይ አንዳንዶች የለበሷቸው ለየት ያሉ አልባሳት አድናቆትን ሲያስገኝላቸው የአንዳንዶቹ ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ከመጋራቱ በተጨማሪ ትችትም ገጥሟቸዋል። ይሄ የሽልማት ሥነሥርዓት የፊልምና የፋሽን ትስስርን ያሳየ፣ በየአመቱ እያደገ የመጣ እንዲሁም ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ተወዳጅ ዝግጅት መሆኑን ግን ከመሰናዶው ጥራትና ከገነባው እውቅና አንፃር መዝኖ መፍረድ ለማንም ከባድ አይሆንም።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም