እያንዳንዱ የለውጥ እንቅስቃሴያችን ሀገራዊ ብልፅግናን መሠረት ያደረገ ሊሆን ይገባል!

ጽንፈኝነት ከተዛነፈ አስተሳሰብ እና የልብ ድንዳኔ የሚፈጠር ማኅበራዊ ችግር ነው። ችግሩ ይብዛም ይነስ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ሊፈጥር የሚችለው አደጋ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በተለይም ተገማች የሆኑ ግለሰባዊ እና ቡድናዊ ፍላጎቶችን መሠረት የሚያደርጉ ጽንፈኛ አስተሳሰቦች አጠቃላይ ለሆነው የማኅበረሰብ ፍላጎት ፈተና መሆናቸው የማይቀር ነው።

በአብዛኛው ከአስተዳደግ እና አስተዳደግ ከሚፈጥረው የባሕርይ ችግር የሚቀዳው ጽንፈኝነት፤ የግለሰብን፣ የቤተሰብን ከዛም አልፎ የማኅበረሰብን የዕለት ተዕለት ሕይወት ስጋት ውስጥ ሊከት የሚችል ነው። አስቻይ ሁኔታ ካገኘም አጠቃላይ የሆነውን አንድ ማኅበረሰብ እና ሀገር ዕጣ ፈንታ፤ ብሩህ ነገዎች የሚገድል የከፋ ችግር ነው።

እስካሁን ዓለማችን ያስተናገደቻቸው ትላልቅ ጥፋቶች/የጦርነት እና የግጭት ትርክቶች መነሻቸው ከአስተዳደግ ጋር በተያያዘ የተፈጠረ የባሕርይ መዛነፍ ሰለባ በሆኑ ግለሰቦች ናቸው። በወቅቱ የእነዚህ ግለሰቦች የተዛነፈ ባሕርይ በአግባቡ መግራት የሚያስችል ማኅበረሰባዊ መረዳት ባለመፈጠሩ፤ ዝንፍ ባሕርይዎቻቸው ራሳቸውን፣ ሀገራቸውን እና መላውን ዓለም ብዙ ያልተገባ ዋጋ አስከፍለዋል።

እነዚህ ግለሰቦች በታሪክ አጋጣሚ የሚፈጠሩ የማኅበረሰብ የለውጥ መሻቶችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ፤ የለውጥ መነሳሳቶች ጠልፈው በመውሰድ ለውጦች መስመራቸውን እና ዓላማቸውን ስተው የጥፋት እና የክስረት ምንጭ እንዲሆን አድርገዋል። ለዚህም ሂትለርን፣ መሶሎኒን፣ ኢዲያሚንን የመሳሰሉ አምባገነኖችን መጥቀስ ይቻላል።

ይህ እውነታ በኛ ሀገር በአንድም ይሁን በሌላ የለውጥ ወቅት ዋነኛ ፈተና መሆን ከጀመረ ውሎ አድሯል። የሕዝባችንን የለውጥ መነሳሳት እንደመልካም አጋጣሚ በመቁጠር ግለሰባዊ እና ቡድናዊ ፍላጎቶች በሕዝብ ላይ ለመጫን በተፈጠሩ የተዛነፉ አስተሳሰቦች እና እነሱን ተጨባጭ ለማድረግ በተፈጠሩ ትርክቶች ትውልዶች ብዙ ዋጋ ከፍለዋል።

ባለፉት ሰባት አስርት ዓመታት በሀገራችን የሕዝባችን ተፈጥሯዊ የለውጥ ፍላጎቶች መሠረት ያደረጉ፣ ከአንድም ሁለት ሦስት ሕዝባዊ የለውጥ መነሳሳቶች ተፈጥረዋል። እነዚህ የለውጥ መነሳሳቶች ለሀገር እና ለሕዝብ እንግዳ በሆኑ የፖለቲካ እሳቤዎች እና እሳቤዎቹን ተግባራዊ ለማድረግ በተሞከሩ የተቃርኖ ድርጊቶች ከሽፈዋል።

አስተሳሰቦቹ ለሕዝባችን ማኅበራዊ ዕሴቶች ባዕድ መሆናቸው፣ ቀስ በቀስም በተቃርኖ ተሞልተው ለተለያዩ ግለሰባዊ እና ቡድናዊ ጽንፈኛ አስተሳሰቦች መጠለፋቸው፣ ሕዝባችን የለውጥ መሻቱ መሠረት የሆኑትን ሰላም እና ብልፅግና እውን ሊያደርግ ሳይችል ቀርቷል። ከዚያ ይልቅ ወደከፋ አለመረጋጋት እና ግጭት ውስጥ ገብቶ፤ ላላሰባቸው ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተዳርጓል።

በነዚህ ጽንፍ የረገጡ አስተሳሰቦች፣ ለዘመናት አብሮነቱ መሠረት የሆኑ ማኅበራዊ ዕሴቶቹን ተሸርሽረው ሀገራዊ አንድነቱ ስጋት ውስጥ የወደቀበት ሁኔታዎች ተፈጥረው አልፈዋል። ችግሩ የሕዝባችንን ተስማምቶ እና ተቻቻሎ የመኖር ዘመን ተሻጋሪ ዕሴቶችን በማደብዘዝ ጥርጣሬ እና አለመተማመንን ፈጥሯል። ከዛም አልፎ ሀገርን እንደ ሀገር የባሕር በር እና ወደብ አልባ አድርጓል።

ይህ በለውጥ ወቅት የሚፈጠርን የሕዝብ መነሳሳት ጠልፎ ለግል እና ለቡድን ፍላጎት ማስፈጸሚያ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት እና ከዚህ ጥረት የሚመነጭ ጽንፈኛ አስተሳሰብ ትናንት እንደ ሀገር የተጀመሩ የለውጥ መነሳሳቶችን በብዙ ፈትኗል፤ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሀገራዊ ሰላም እና መረጋጋት ተግዳሮት ሆኗል። የለውጥ ትውልድንም ብዙ ያልተገባ ዋጋ አስከፍሏል።

ችግሩ በተመሳሳይ መንገድ በቅርቡ እንደሀገር የጀመርነውን ለውጥ ፈትኗል። የለውጥ መነሳሳቱን ለግለሰቦች እና ቡድናዊ ፍላጎቶች መጠቀሚያ ማድረግ የሚያስችል አቅም ለመፍጠር፣ የተለያዩ ጽንፈኛ አስተሳሰቦች ተፈጥረው፤ የሕዝባችንን የለውጥ ተስፋ አደብዝዘዋል። እንደ ሀገር ዳግም ያልተገባ ዋጋ እንድንከፍል ሆነናል።

ታሪክን ያለዓውዱ በሚተረጉሙ፤ የሕዝቦችን የአብሮነት ታሪክ በሚያሳንሱ፤ የሀገርን ሰላም እና አንድነት አደጋ ውስጥ በሚከቱ ትርክቶች ፤ ጽንፈኛ አስተሳሰቦችን በሕዝብ ውስጥ አቅም አግኝተው የፖለቲካ አጀንዳ እንዲሆኑ ብዙ ተሞክሯል። ሙከራዎች በራሳቸው ለውጡን በብዙ ፈትነውታል።

አንዳንዶችም ጽንፍ የወጡ አስተሳሰቦቻቸውን ተጨባጭ ለማድረግ በሀገር እና በሕዝብ ላይ ጦርነት አውጀዋል፤ በገዛ ሕዝባቸው የለውጥ ፍላጎት ላይ በተቃርኖ በመቆም የዕለት ተዕለት ሕይወታቸውን በጣር የተሞላ ያደረጉም ቡድኖችም በስፋት ተፈጥረው ታይተዋል፤ ከጽንፈኛ አስተሳሰቦች ተጠቃሚ ለመሆን በዲጂታል ሚዲያው ሰልፈኛ የሆኑም ጥቂቶች አይደሉም።

በዚህ ሁሉ ሕዝባችን ብዙ ያልተገባ ዋጋ ከፍሏል። ከዚህ ከትውልድ ትውልድ እየተሻገረ፤ የትውልዶችን ተስፋ ከሚናጠቅ ከዚህ የፖለቲካ ባህል ለመውጣት፤ ሕዝባችን ከሁሉም በላይ በለውጥ ወቅት ከሚፈጠሩ የተሳሳቱ አሰላለፎች እና አስተሳሰቦች ሊፈጥሩ ከሚችሉት ግራ መጋባት እና ስሜታዊነት ራሱን ማቀብ ይጠበቅበታል።

እያንዳንዱ የለውጥ እንቅስቃሴው የሀገሩን አንድነት እና ብሔራዊ ጥቅሞችን የማይፈታተኑ፤ እንደ ሕዝብ ለዘመናት ይዞት የመጣውን አብሮነቱን የማይገዳደሩ፤ ተሻጋሪ ማኅበረሰባዊ እሴቶቹን የማያደበዝዙ፤ ቀደም ባሉት ዘመናት ጀምሮ ትውልዶች ብዙ ዋጋ የከፈሉበትን ሀገራዊ መነሳት፣ ብልፅግናን መሠረት ያደረጉ እና ለእሱ ብቻ የተገዙ ሊሆኑ ይገባል!

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You