የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ዋነኛ አንቀሳቃሽ ኃይል መረጃ ስለመሆኑ ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡ የሃያ አንደኛውን ክፍለ ዘመን ልዩ የሚያደርገው ደግሞ መረጃ ኃይል መሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ ኃይሉ የሚገኘው በእያንዳንዱ ሰው እጅ ላይ መሆኑ ነው፡፡ ጥንት አባቶቻችን መረጃ ለማግኘት ብዙ ይደክሙ ነበር፡፡ የመረጃን ጥቅምና ኃይልነት ጠንቅቀው የተረዱት አያት ቅድመ አያቶቻችን በመረጃ ምንጭነት የሚያገለግል መሳሪያ ባይኖራቸውም፣ “ለሁሉም ጊዜ አለው” እንዲል ጠቢቡ ሶሎሞን ወይም እንደ አሁኑ ዘመን በፈለጉት ሰዓት የፈለጉትን መረጃ ለማግኘት የሚያስችል መሳሪያ ለመፈልሰፍ ጊዜያቸው ባይፈቅድላቸውም ያለ መረጃ አንዳችም ሥራ አይሰሩም ነበር፡፡ ምንም ዓይነት ውሳኔ ከመወሰናቸው በፊት በርካታ መረጃዎችን በግብዓትነት ይጠቀማሉ፤ ነገሮችን ግራና ቀኝ ይመለከታሉ(በ “ዘመናዊው” አባባል የአዋጭነት ጥናት(Feasibility study) ያካሂዳሉ፣ አስቀድመው ትርፍና ኪሳራቸውን ያሰላሉ(Cost-Benefit Analysis) ይሰራሉ፡፡ ለዚህም እንደዛሬው መረጃን በፍጥነትና በብዛት ለማግኘት የሚያስችሉ እንደ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ስልክና ኢንተርኔት የመሳሰሉ ዘመናዊ የመረጃ ቴክኖሎጂዎች ባይኖሯቸውም ተፈጥሮን በመረጃ ምንጭነት ይጠቀሙበታል፡፡ እናም ሌላው ይቅርና ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ እንኳን መረጃ ያነፈንፋሉ፤ ጉዞ ለማድረግ ያሰቡበት ጉዳይ ተገቢ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ከተፈጥሮ ጋር ይመካከራሉ፤ “ወፍ ይጠይቃሉ”! አንዳንድ የአዕዋፍና የእንስሳት ዝርያዎች ከሰው የበለጠ በአንድ አካባቢ ሊሆኑ የሚችሉ ሁነቶችን ለመረዳት የሚያስችል ደመ ነፍስ ያላቸው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ የዓለማችን ትልቁ የመረጃና ደህንነት ተቋም ሲ.አይ.ኤ ውሾችን በምርመራ ሥራ ላይ የሚያሰማራው ለምን ይመስልሃል? የአንዳንድ የሁነቶችን ስሪት አጣርቶ በማወቅና ትክክለኛውን መረጃ አነፍንፎ በማሳወቅ ረገድ በተፈጥሯቸው ውሾች ከሰዎች የተሻሉ በመሆናቸው አይደለምን? አባቶቻችን መረጃን የመጠቀም ጥበባቸው እስከ ሥነ ፈለክ ምርምር ድረስ ይዘልቃል፡፡ ሩቅ የሚፈጠርና ዓለምን ሊቀይር የሚችል ክስተትን እንደ ሰብዓ ሰገል በኮከብ ተመርተው መረጃውን ይደርሱበታል::
እየባከነ የሚገኝ በእጅ ያለ ኃይል
በተቃራኒው በእኔ ዘመን ደግሞ ይኸው የኃይል ምንጭ የሆነው መረጃ ከመቸውም ጊዜ የበለጠ እየቀረበ መጥቶ እጃችን ላይ ይገኛል፡፡ “የመረጃ ዘመን” በሚባለው በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሰዎች መረጃ ለማግኘት የትም መድከም፣ ከቤታቸው መውጣት እንኳን አይጠበቅባቸውም፡፡ እጃቸው ላይ አለ፡፡ በአንድ ጉዳይ ላይ መረጃ በሚፈለጉበት ሰዓት በእጅዎ ላይ ያለችውን ትንሽዬ ተንቀሳቃሽ ስልክ መክፈት ብቻ ነው፡፡ ከዚያ የሚፈልጉትን መረጃ በፈለጉት መጠን ያገኛሉ፤ ያውም በፍጥነት፣ ምንም ሳይለፉ በቀላሉ! ግን ምን ያደርጋል “ሰነፍ እጁን ወደ ወጭቱ ይልካል፣ ወደ አፉ ይመልሳት ዘንድ ግን ይታክታል” እንዲል መጽሐፈ ምሳሌ የፈለጉትን ነገር ለማድረግ የሚያስችለውን የመረጃ ኃይል ማግነት እንዲህ ቀላል ቢሆንለትም ስንፍና ቤቱን የሰራበት የእኔ ትውልድ በእጁ ላይ የተቀመጠን ኃይል መጠቀም አልቻለም፡፡
ራሱን፣ አካባቢውንና ዓለሙን ሊለውጥበት የሚችለውን የመረጃ እና የእውቀት ኃይል በቸልተኝነት እያባከነው ይገኛል፡፡ ይች የኪስ ቦርሳ የማታክል ትንሽ ዕቃ ትንሽ እንዳትመስልዎት፤ በአሁኑ ሰዓት በዓለም ላይ ትልቁ ቤተ መጽሐፍት የሚገኘው እሷ ውስጥ ነው፡፡ ከመረጃ ምንጭነቷ አንጻር “ቤተ መጽሐፍት” አልን እንጅ በዚች ትንሽ የቴክኖሎጂ ደብተር ውስጥ “ዓለም” ራሷ አለች፡፡ ታዲያ ምን ያደርጋል ሃያ አራት ሰዓት ኢንተርኔት ላይ ተጥዶ የሚውለው የእኔ ትውልድ ሙሉ ጊዜውን እና ትኩረቱን የሚያጠፋው መረጃው ላይ ሳይሆን “ፌዙ” ላይ ማለቴ “ፌዝ ቡኩ” ላይ ሆነ እንጂ፡፡ አብዛኞቹ የሃገሬ ሰዎች የሚጠቀሙበት መረጃ ለማግኘትና ራስን ለመለወጥ ሳይሆን ርባና ቢስ ቧልቶችን ለመለዋወጥ በመሆኑ “ፌዝ ቡክ” ተባለ እንጅ ፌስ ቡክ ዘመናችን ካፈራቸው ምርጥ የመረጃ ምንጭ ቴክኖሎጂዎች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው፡፡
በረከተ መርገም ወመረጃ
ከላይ እንደተገለጸው ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ለዓለማችን ካበረከታቸው መልካም ዕድሎች ዋነኛው መረጃን እንደልብ ማግኘትና መለዋወጥ መቻሉ ነው። በዚህ ረገድ እንደ ፌስ ቡክ፣ ትዊተር፣ ቴሌግራምና ዩትዩብ የመሳሰሉት ማህበራዊ ሚዲያ የሚባሉት የመገናኛ ዘዴዎች የመረጃ አብዮት እየፈጠሩ ይገኛሉ። በዓለማችን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይም ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆነዋል፡፡ ይሁን እንጅ ደግነቱ አጠቃቀሙ በእኛ አስተሳሰብ በቁጥጥር ሥር ሆኖ የሚመራ መሆኑ እንጂ የቱንም ያህል ጠቃሚና አስፈላጊ ቢሆን እንኳን ማንኛውም ነገር የራሱ የሆነ አሉታዊ ጎን አለው፡፡ ጥቅም እንዳለው ሁሉ ጉዳትም ይኖረዋል፤ ለልማት ሊውል እንደሚችል ሁሉ ለጥፋትም ሊውል ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ እንደ ትልቅ አብነት ሊጠቀስ የሚችለው ፌስቡክ ነው፡፡
ፌስቡክ ሁሉም ሰው ሃሳቡን በነጻነት እንዲገልፅና ዲሞክሲያዊ ውይይት እንዲኖር በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ ቢሆንም በዚያው ልክ ለጥፋትም እያገለገለ ይገኛል፡፡ መጥፎ አስተሳሰብና አመለካከት ይዘው ለሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ቡድኖች ከመደበኛ የመገናኛ ብዙሀኖች ይልቅ ማህበራዊ ሚዲያው ለእኩይ ዓላማ የመዋል ዕድሉ ሰፊ መሆኑን ደጋግመን ታዝበናል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያውን ብዙውን ጊዜ ነጻና ቁጥጥር የማይደረግበት በመሆኑ ትልልቅ የሚባሉ የአሸባሪ ድርጅቶች ሳይቀር የራሳቸውን አባላቶቻቸውን ለመመልመልና የጥፋት ዓላማ ለማስፈጸም እንደሚጠቀሙበት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ በመሆኑም አገራት እንደየአቅማቸው በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ቁጥጥር ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል። ለአብነትም ጀርመን እስከ ሃምሳ ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ከፍተኛ ወጭ በመመደብ በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ ሃሰተኛ የጥፋት መረጃዎችን የመቆጣጠር ሥራ እንደምትሰራ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ በእኛም ሃገር በቅርቡ ለምክር ቤት የቀረበው የጥላቻ ንግግርና ሃሰተኛ መረጃ ለመከላከል ረቂቅ አዋጅ በማህበራዊ ሚዲያው አማካኝነት እየደረሰ ያለውን ጥፋትና በህዝብ ደህንነት ላይ እየፈጠረ ያለውን ስጋት ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ በእርግጥ ባደጉት ሃገራት በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁና የሚዘዋወሩ አውዳሚ መረጃዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችም አሉ፡፡
በእንደእኛ ዓይነት ታዳጊ አገራት ግን የቴክኖሎጂው ባለቤት ስላልሆንንና ገዝተን እንኳን እንጠቀም ቢባል ዋጋውም ውድ ከመሆኑ የተነሳ የጠፉ መረጃዎችን በዚህ መልኩ ለመቆጣጠር አይቻልም፡፡ ሆኖም ራሱ የማህበራዊ ሚዲያው ባለቤት የፈጠረውን የመቆጣጠሪያ ስልት በመጠቀም በሃሰት የሚሰራጩ የጥፋት መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካውንቶችን ለኩባንያው ሪፖርት በማድረግ ማዘጋት የሚቻልበት አሰራር በእኛም ሃገር አለ:: ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያም የራሷ የሆነ የመረጃ ነጻነት አዋጅና ህግ ያላት በመሆኑ በህጉ ላይም ለጥፋት የሚያነሳሱ መረጃዎችን ማሰራጨት የተከለከለ በመሆኑ በተለይም በትክክለኛ አካውንታቸው ይህን መሰል መረጃ የሚያሰራጩና አድራሻቸው በሚታወቁት ላይ ርምጃ መውሰድ የሚቻልበት ሁኔታ መኖሩ አደጋውን መቀነስ እንደሚቻል የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡
ሃሰተኛ አካውንትን የሚጠቀሙና አድራሻቸው የማይታወቁትም ቢሆን ይህንን ለመለየት የሚያስችል ቴክኖሎጂ እየመጣ በመሆኑ ከተጠያቂነት ማምለጥ የማይቻልበት ሁኔታ እየመጣ መሆኑም ለዓለማችን መልካም ዜና ነው፡፡ የጥፋት ድርጊታቸው መታቀብ እንደሚገባቸውም ያስጠነቅቃሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት የሚደርሰውን ጥፋት ለመቀነስና ከናካቴውም ለማስቀረት ከተፈለገ ህብረተሰቡ ራሱ ንቃተ ህሊናውን ከፍ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህም በፌስቡክ የሚሰራጩ ዜናዎችን ከመውደዱና ከማጋራቱ በፊት ቆም ብሎ ማሰብና ምንጫቸው ከወዴት እንደሆነ ማወቅ፣ ለምን ዓላማ እንደተሰራጩ ማጤን ይገባል፡፡ በዚህም በፌስቡክ የሚሰራጩ የሃሰትና የጥፋት መረጃዎችን ዓላማ ማምከን የሚቻልበት ዕድል ሰፊ ነው::
መረጃን ለጥፋት መጠቀምና የጥፋት አንቂዎች
ስሙ ራሱ እንደሚያመለክተው አንቂነት ወይም በእንግሊዝኛው አክቲቪስትነት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ህዝብን ማስተማር፣ መቀስቀስና ማስተማር ነው፡፡ ይህም “ማህበራዊ ወይም ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት የሚደረግ ጠንካራ የፖሊሲ ወይም የተግባር ዘመቻ” ከሚለው የኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት የአክቲቪስትነት ትርጉም ጋር አብሮ የሚሄድ ነው። ስለሆነም የአክቲቪስትነትን ሥራ የሚሰራ ማለትም በአንድ የተወሰነ ማህበራዊ ወይም ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ ህዝብን የሚቀሰቅስና የሚያነቃ ሰው ነው አክቲቪስት የሚባለው፡፡
ይሁን እንጂ “አክቲቪስት” የሚለውን ስም ማግኘት ያለበት ምን ዓይነት ሰው ነው የሚለው የራሱ የሆነ አካሄድ ያለው መሆኑን የፖለቲካል ሳይንስ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ስንመለከተው በተለይም አሁን በእኛ አገር ላይ እየተስተዋለ የሚገኘው “የአክቲቪስትና የአክቲቪስትነት ጉዳይ” ግን ከዚህ ፍጹም ተቃራኒ መሆኑን እንታዘባለን። ትክክለኛውን አካሄድ ያልተከተለና ችግር ያለበት ነው፡፡ ምክንያቱም አክቲቪስትነት ሃሳብ ነው፤ አንድ ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርጎ፤ ሃሳብ ይዞ የሚደረግ ዓላማ ያለው እንቅስቃሴ ነው፡፡
በእኛ ሃገር ግን በአብዛኛው አንድ ሰው አክቲቪስት የሚባለው ግለሰቡ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ባለው የተከታይ ብዛት እንጂ በሚያነሳው ሃሳብ አይደለም። ከዚህም በአሻገር አክቲቪስትነት ግለሰቦች ከምንም ተነስተው ለራሳቸው የሚሰጡት ማዕረግ ሆኗል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በእኛ ሃገር አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የፌስቡክ ተጠቃሚ መኖሩን መረጃዎች ያመለክታሉ፣ ሁሉም ራሱን አክቲቪስት ብሎ ስለሚጠራ አራት ነጥብ አምስት አክቲቭስት ተፈጥሯል ማለት ነው፡፡ ተመልከቱ እንግዲህ ትናንትና ማታ እራቱን ምን እንደበላ ለማሳየት የበየዓይነት ፎቶ የሚለጥፈውም፣ አባቴ ሞተብኝ ብሎ ፌስቡክ ላይ የሚፅፈውም፣ ትልቅ ሃሳብ ይዞ ለለውጥ የሚሰራውም ሁሉም አክቲቪስት ሆነዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይሄ ፈጽሞ አንቂ ሊሆን አይችልም፤ በሃሳብ ላይ ያልተመሰረተ አንቂነት የለም፤ ተከታይ እንጂ የሚያነሳው ሃሳብ የሌለውም አንቂ ሊሆን፣ ሊባልም አይችልም፡፡
የአንድ አንቂ ሃሳብ ለበርካታ ሰዎች የሚዳረስና በአዎንታዊም ይሁን በአሉታዊ ጎኑ በብዙሃኑ ላይ ተፅዕኖን የመፍጠር ባህርይ ያለው እንደመሆኑ መጠን ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ከእያንዳንዱ ተግባራቸው ጀርባ ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ሆኖም አሁን በእኛ አገር ያለው አንቂነት ከማህበራዊ ኃላፊነት የተነጠለ ነው። ስለሆነም አገር ሁሉ ሊያፈርስ የሚደርስ ጽሁፍ እየጻፉ ራሳቸውን እንደ አክቲቪስት የሚቆጥሩ አካላት አንቂዎች ሳይሆኑ አጥፊዎች ናቸው፡፡ በሰለጠኑ አገራት ያሉ አክቲቪስቶች ለእያንዳንዷ ነገር ይጠነቀቃሉ፡፡ አብዛኞቹ የእኛ አገር አክቲቪስቶች ግን የሚጽፉት ይቀሰቅስልኛል ያሉትን ነገር ብቻ ነው፤ የሚያነሱት ጉዳይ በሃገርና በህዝብ ላይ ሊያመጣው የሚችለውን ጉዳት አያስቡትም፤ ማህበራዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው ረስተውታል፤ አያውቁም ወይም ሆን ብለው እያወቁ አገር ያጠፋሉ፡፡
በዚህ ረገድ የመረጃ ማሰራጫ ዘዴው በራሱ ማህበራዊ ኃላፊነት እንዳይኖር ከፍተኛውን ሚና ተጫውቷል። ምክንያቱም አብዛኞቹ በአክቲቪስት ስም የሚለቀቁ መረጃዎች ባለቤታቸው ማን እንደሆነ አይታወቁም፡፡ ባለቤት በሌለበት ሁኔታ ደግሞ ማህበራዊ ተጠያቂነትን ለመፍጠር አስቸጋሪ ነው፡፡ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሥርዓታችን ነው እንጂ አክቲቪስትነት በእኛ ሃገርም ብዙ መልካም ለውጦችን አምጥቷል፡፡ አሁንም ቢሆን በኃላፊነት ከተሰራበት ፋይዳው የላቀ መሆኑን ሁሉም የሚስማማበት ነው፡፡ ለዚህም በቅርቡ በታጣቂ ኃይሎች የታገቱ ተማሪዎችን ለማስፈታት በፌስ ቡክ ላይ የተደረገን ዘመቻ ጨምሮ በርካታ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡
እውነተኛ ንቃትና ያልተጠቀምንበት የመረጃ ኃይል
እውነተኛ ንቃት መጠየቅ ነው፡፡ እውነተኛ አንቂነትም መረጃን በመጠቀም ሃገርና ህዝብን ሊጠቅሙ የሚችሉ ሥራዎችን መሥራት፣ ብሎም አዎንታዊ ለውጥ እንዲመጣ ከፊት ሆኖ መምራት ነው፡፡ የሃገርና የህዝብን ጥቅም የሚጎዱ አድሏዊ አሰራሮችን መጠየቅ ነው እውነተኛ ንቃትና አንቂነት፡፡ ህብረተሰብን በገንዘብ፣ በስልጣን፣ በሌላም መንገድ ባገኙት አቅም ሌሎችን የሚበድሉ አካላትን መጠየቅ አንባገነኖችን መሟገት ነው ንቃት፡፡ ዋነኛ ዓላማውም ለህዝብና ሃገር ጥቅም ዘብ መቆም ነው፡፡ በእኛ ሃገር እንደሚደረገው መረጃንና የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም አገርን ለማፍረስ፣ ህዝብን ለማባላት መቀስቀስ ሳይሆን እውነተኛ አንቂዎች በተቋም፣ በመንግስትና በግለሰብም ሊሆን ይችላል የሚከናወኑ ፍትሃዊ ያልሆኑ አሰራሮች እንዲስተካከሉና ማናቸውም ዓይነት በደል በህዝብ ላይ እንዳይፈጸም ህብረተሰቡ መብቱንና ጥቅሙን እንዲያስከብር ግንዛቤን የሚፈጥሩና ህዝብን የሚያነቁ ናቸው፡፡ እውነተኛ አንቂ ፍትሃዊ ያልሆኑ አሰራሮች ሲፈጸሙ ለምን ብሎ ይጠይቃል፣ የመንግስት ባለስልጣናትም ይሁኑ ሌሎች በደል ፈጻሚ አካላትንም በህይወቱ ላይ አደጋ የሚያስከትል እንኳን ቢሆን በፍርሃት አያልፍም፣ ለህግ እንዲቀርቡና በጥፋታቸውም እንዲቀጡ ፍትህ እንዲሰፍን ህይወቱን አደጋ ላይ እስከመጣል ድረስ በጽናት ይታገላል፡፡
ይሁን እንጂ አሁን በተጨባጭ እየታየ እንዳለው የአንቂነት ሥራ ሁሉም እንደፈለገ ዘሎ የሚገባበት አጥር የሌለው ሙያ ሆኗል፡፡ በዚህ የተነሳም ለራሳቸው ጥቅምና ለግል ፖለቲካዊ ፍላጎቶቻቸው የሚሰሩ አካላት በአንቂነት ስም በአጥቂነት ተሰማርተዋል፡፡ ይህም ለህዝብ ጥቅምና ፍላጎት ያሰቡ በማስመሰል ህዝብና ህዝብን የሚያጋጩና በአገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ ሃሰተኛ መረጃዎች በብዛት እንዲያሰራጩ ዕድል በመፍጠሩ ሥራውን ከፍተኛ የተዓማኒነት ችግር ውስጥ ከቶታል። ለህዝብ ጥቅም ከቆመው ትክክለኛው የአንቂነት ዓላማ በተቃራኒው የተሰለፈ በመሆኑ ለአንቂውና ለሙያው ትልቅ ፈተና ሆኗል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሃሰት አካውንቶችን በመጠቀምና ማንነታቸውን በመደበቅ አክቲቪስት መስለው የፕሮፓጋንዳ ሥራ የሚሰሩ አካላትም መኖራቸውም ሌላው ዘርፉን እየፈተነ የሚገኝ ችግር መሆኑን የዘርፉ ተመራማሪዎች ይመሰክራሉ፡፡
ጠያቂነት ወይም አንቂነት ትልቅ ኃላፊነት የሚያስፈልገው ሥራ ነው፤ ከራስ አልፎ ለሌሎች መጠየቅም ከሁሉም የላቀ ተግባር በመሆኑ አንቂ ከማንም በላይ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህንን ኃላፊነቱን የማይወጣና ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚሰራ ማንኛውም አካል አንቂ ሳይሆን “አጥቂ” በመሆኑ በሥራው ሊያፍር ይገባል፡፡ ምክንያቱም ጥፋት አያኮራም፣ ክፋት አያስከብርም፡፡ ይሁን እንጂ በህዝብ ላይ የሚያሴሩና ራሳቸው አድሏዊ አሰራርን እየተከተሉ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ ፖለቲከኞችንና የመንግስት ባለስልጣናትን የሚያጋልጡ ትክክለኛ አንቂዎችን ከሃሰተኞቹ ጥቅመኛ አንቂ ነን ባዮች ጋር አንድ ላይ ፈርጆ ሙያውን በጅምላ መኮነንም ሌላው በአሁኑ ሰዓት የምንታዘበው ሃቅ ነው። ስህተትም ነው፡፡ በዚህ ረገድ ህግንና ሥርዓትን ጠብቆ በኃላፊነት የሚሰሩ አንቂዎች መኖራቸው ከምንም በላይ ለሃገርና ለህዝብ፣ ለመንግስትም አስፈላጊ ነውና ማበረታታትም ያስፈልጋል፡፡ ከራስ አልፎ ለሌሎች ጥቅም ማሰብ፣ ለመልካም ነገር ከፊት መሰለፍ፣ ዘመኑ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም እጃችን ላይ እንደ ልብ የሚገኘውን የመረጃንና ዕውቀትን ኃይል ለመልካም ነገር መጠቀም እውነተኛ ጀግንነት ነውና ሁላችንም ልናስብበት ይገባል እላለሁ፡፡ ዘመናችን የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም እጃችን ላይ ያለውን የመረጃ ኃይል በከንቱ አናባክነው፣ ለመልካም ነገር እንጠቀምበት፣ ራሳችንን፣ ሃገራችንን እና ዓለማችንን በአዎንታ ለመለወጥ እንጠቀምበት በተለይም ለትውልድ ተጋሪ አቻዎቼ ለወጣቶች የማስተላልፈው መልዕክት ነው፡፡
ከዚህ አኳያ ሁለቱም ባለሙያዎች በሁለቱም ወገን በመገናኛ ዘዴውም በአክቲቪስቱም በኩል የሚስተዋሉ ችግሮችን አስተካክሎ መሄድ ከተቻለ በእርግጥም ለሃገርና ለህዝብ ጥቅም ዘብ የቆመውን የአራተኛው መንግስት አካል የሆነውን የአክቲቪስትነት ሙያ ለአዎንታዊ ለውጥ ማዋልና ለመልካም ነገር ብቻ መጠቀም ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 13/2012
ይበል ካሳ