የዓለም አትሌቲክስ ከሚያዘጋጃቸው ዓመታዊ የዙር ውድድሮ መካከል አንዱ የዓለም ቤት ውስጥ የዙር ውድድር ነው። እኤአ በ2016 መካሄድ የጀመረው ይህ ውድድር በትራክና በሜዳ ተግባራት የውድድር ዓይነቶችን ማሳደግ ዓላማው ሲሆን፤ የዳይመንድ ሊግን አካሄድ የሚከተልም ነው። በዳይመንድ ሊግ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ተሳታፊ ለመሆን መስፈርት እንደሚሆነው ሁሉ፤ በዚህ የዙር ውድድር ውጤታማ መሆንም በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና መሸጋገሪያ በመሆን ያገለግላል።
ሲጀመር በአራት ዙር የሚካሄደው ይህ ውድድር ሁለት አህጉራትን በማካለል ሶስቱን በአውሮፓ አንዱን ደግሞ በአሜሪካዋ ፖርትላንድ በማድረግ ይከናወን ነበር። ከቀናት በኋላ በሚጀመረው በዘንድሮው የቤት ውስጥ የዙር ውድድርም ሁለት መዳረሻዎችን በመጨመር ስድስት ዙሮችን የሚያካልል ይሆናል። በዚህ ውድድር ላይ የሚካፈሉ አትሌቶችም በዚህ ዓመት በናንጂንግ በሚካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ለመካፈል ከማስቻሉም በላይ የ20 ሺ የአሜሪካ ዶላር ተሸላሚ ያደርጋቸዋል።
ከሶስት ቀናት በኋላ በሚጀመረው በዚህ ውድድር ላይም እጅግ ተጠባቂ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አስር የሚሆኑትን የዓለም አትሌቲክስ በድረ ገጹ አስፍሯል። ከተጠባቂዎቹም ውስጥ ኢትዮጵያዊው የ1 ሺ 500 ሜትር አትሌት ሳሙኤል ተፈራ ይገኝበታል። የ22 ዓመቱ ወጣት አትሌት በባለፈው ዓመት ተሳትፎው የራሱን ምርጥ ሰዓት በሶስት ሰከንዶች ካሻሻለ ከቀናት በኋላ በበርሚንግሃም የዓለም የቤት ውስጥ ክብረወሰንን ማሻሻሉ የሚታወስ ነው። ሳሙኤል በሞሮኳዊው ሂቻም ኤል ጉሩዥ ለረጅም ዓመታት ተይዞ የቆየው ሰዓት 3 ደቂቃ ከ32 ሰከንድ ከ01 ማይክሮ ሰከንድ ነበር። ኢትዮጵያዊው አትሌት ግን ርቀቱን በ3 ደቂቃ ከ31 ከ04 ማይክሮ ሰከንዶች ክብረወሰኑን ሲረከብ የርቀቱ ፈጣን አትሌትም ተሰኝቷል። ይህም አትሌቱን በዚህ ዓመት በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ተጠባቂ አትሌት አድርጎታል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 13/2012
ብርሃን ፈይሳ