ክፍል ሁለት
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
የሞት ቅጣት ዳራ በኢትዮጵያ
የአገራችንን የዘመናት ልማዳዊና ዘመናዊ የሕግ አውድ ስንቃኝ ማህበረሰቡ የሞት ቅጣትን ወሳኝ መቅጫው አድርጎ የተጓዘበትን ጎዳና እስከ ዛሬ አጥብቆ መዝለቁን እንገነዘባለን። “ከባድ” ወንጀል የሠራን ሰው “ይሄማ ሞት ይገባዋል!” ይላል ሕዝቡ ሥር የሰደደውን የአስተሳሰቡን ነጸብራቅ ሲገልጽ።
ከ1949 ዓ.ም. እስከ 1997 ዓ.ም. የነበረው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግን ያረቀቁት ፕሮፌሰር ጂን ግራቭን በሕጉ ዙሪያ በጻፉት መጽሃፋቸው በዚያን ዘመን የሞት ቅጣትን ከኢትዮጵያ ሕግ ማስወጣት የማይታሰብና የማይሞከርም እንደነበር ከትበዋል።
እሳቸው እንዳሉት ለኢትዮጵያውያን የወንጀል ሕግ ሲወጣ የማህበረሰቡን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ብቻ አልነበረም። ሕዝቡ ለፍትህና ለእርምት ሥር የሰደደ ሥሜት ስለነበረውም ጭምር እንጂ። በተለይ የፈጣሪ ሥራ የሆነችዋን ነፍስ “ያጠፋ” ሰው ለክፉ አድራጎቱ የራሱን ነፍስ ልዋጭ አድርጎ ሊሰጥ እንደሚገባው በጽኑ ያምናል።
በዚህም ምክንያት በቀደመው የኢትዮጵያ ሕግ ውስጥ የሞት ቅጣት የማህበረሰባዊ ፍላጎት ነጸብራቅ ተደርጎ ተወስዷል።ፍትሐ-ነገስቱን ጨምሮ የ1923ቱም ሆነ የ1949ኙ የወንጀል ሕግ የሞት ቅጣትን በስፋት መደንገጋቸው የዚሁ ማሳያ ነው። በ1976 ዓ.ም. እና በ1978 ዓ.ም. የተሻሻሉት ልዩ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግጋትም እንዲሁ።
በዘመናችን ለሞት ቅጣት የማዕዘን ድንጋይ የሆነው ኢፌዴሪ ሕገመንግስት ነው። በሕገ መንግስቱ መሰረት ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት አለው፤ በሕግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ህይወቱን አያጣም።
የ1997ቱ የወንጀል ሕግም “…ወንጀሉ እጅግ በጣም ከባድ ከሆነ…” የሞት ቅጣት እንደሚያስከትል ደንግጓል። በዚህ ጠቅላላ መርህ መነሻነት በሕገ መንግስትና በመንግስት ላይ የሚደረጉ ወንጀሎችን ጨምሮ የክደት፣ የመሰለል፣ የከባድ ግድያ፣ ከባድ ውንብድናና ሌሎችም ከ30 በላይ ወንጀሎች በሞት ያስቀጣሉ።
ከወንጀል ሕጉ በተጨማሪ ሌሎች ሕጎችም የሞት ቅጣትን አካተዋል። ከእነዚህ ውስጥ የጸረ-ሽብርተኝነትና የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር አዋጆች ይጠቀሳሉ።
ለሞት ቅጣት የጸና አመለካከት ባለው ሥርዓተ-ማህበርና ሀገረ-መንግስት ውስጥ ከሞት ቅጣት በተቃራኒው መቆም ይከብዳል። ሆኖም ከወንጀል ፖሊሲውና ከሕጉ የቅጣት ዓላማ አንጻር እንዲሁም የሞት ቅጣትን በተመለከተ በአገሪቱ ያለውን ተግባራዊ እውነታ (Practical Realityውን) በማንሳት የሞት ቅጣት ከወንጀል ፍትህ ማዕቀፉ ሊፋቅ እንደሚገባ መሞገት ይቻላል። የዓለምንም ተሞክሮ በማንሳት የተደላደለውን የሞት ቅጣት ወንበር መነቅነቅ ያስፈልጋል።
የሞት ቅጣት የሕጉን ዓላማ አያሳካም
የቅጣት ተቀዳሚ ዓላማ ወንጀለኛን በመቅጣት ማስተማር፣ ማነጽና ማረም (Special Deterrence) እንዲሁም ከተጣለው ቅጣት ሌላው እንዲማርና በሕጉ የተቀመጠው ቅጣትም የማስጠንቀቂያ ደወል እንዲሆንለት (General Deterrence) ስለመሆኑ የቅጣትን ዓላማና ግብ ከሚደነግገው የወንጀል ሕጉ የመጀመሪያ አንቀጽ እናነባለን።
በመሰረቱ “ይሙት በቃ” የተፈረደበት ሰው በሞት ስለሚቀጣ በተጣለበት ቅጣት ከስህተቱ የመማር፣ በስብዕናው የመታነጽ ወይም በባህርዩ የመታረም ዕድል አይኖረውም። እናም የሞት ቅጣት የመጀመሪያውን የቅጣት ዓላማ አያሳካም ማለት ነው።
በሞት ቅጣት ወንጀለኛውን ገድሎ ሌላውን ማህበረሰብ ማስተማር ከሚባለው የቅጣት ዓላማ አንጻር ስንመዝነውም አንጀት የሚያደርስ ማሳመኛ ማቅረብ አይቻልም። እርግጥ ነው ወንጀለኛውን ገድሎ “እሱን ያየ ይቀጣ!” እያሉ መልዕክት ማስተላለፍ የቀደመ የማህበረሰባችን የአስተሳሰብ ውጤት ነው።
ይሁንና በኢትዮጵያ የሞት ቅጣት ከባድ ወንጀሎችን የሚቀንስ ስለመሆኑ በጥናት አልተረጋገጠም። በአንጻሩ የሞት ቅጣት በሌለባቸው አገራት ከባድ ወንጀሎች እየቀነሱ መምጣታቸውን ነው ጥናቶች የሚያሳዩት።
ማህበረሰብና መንግስትም ከደሙ ንጹህ አይደሉም
አጥፊውን እስከ እድሜ ልክ እስራት መቅጣት እየተቻለ ለክፉ አድራጎቱ ብቻውን ተጠያቂ ማድረግ ፍርደ-ገምድልነት ነው። ማህበረሰቡና መንግስት የሞት ቅጣትን በወንጀለኛው ጫንቃ ላይ በመጫን በሕይወት እንዳይኖር ሲከለክሉት የራሳቸውንም ግዴታ ዘንግተዋል።
ወንጀል ማህበረሰባዊ ገጽታ አለው። ወንጀል ፈጻሚዎች ከማህበረሰቡ የሚወጡ፣ በማህበረሰቡ የተንሻፈፉ አስተሳሰቦች የታነጹ፤ ከአስተዳደጋቸው ጀምሮ ቤተሰብ፣ ጓደኛ፣ መምህራንና አካባቢያቸው የዘነጋቸው፣ የሰለቻቸው፣ ያገለላቸው ወይም ማህበረሰቡ ወንጀል መስራትን እንደ ጀብድ እየቆጠረ አግድም እንዲያድጉ አሻራውን ያስቀመጠባቸው ናቸው።
እናም እነዚህ ሰዎች ወንጀል ቢሰሩ ቀጥቶ ማስተማርና ማረም የወግ ሆኖ ሳለ የሞት ፍርድ ማስተላለፍ ግን “ከደሙ ንጹህ ነኝ” አይነት ሽሙጥ ይሆናል። ስለዚህ ለእነሱ ወንጀለኝነት ማህበረሰብም የራሱን ድርሻ ወስዶ የሚመጣባቸውን ኃላፊነት በመጋራት ከሞት ውጭ በሌላ ቅጣት ሊያርማቸው ይገባዋል። “ይሄስ ሞት ይገባዋል” ብሎ ከመፍረድ ይልቅ “ነፍስን ከስጋ ያዋሃዳት ፈጣሪ ብቻ ነው፤ ሊለያትም የሚገባው እሱው ነው” ማለት ያስፈልጋል።
መንግስትም ቢሆን “ከደሙ ንጹህ ነኝ” በሚል በወንጀለኛው ላይ የሞት ቅጣትን ሊጥል አይገባውም። ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ሳይፈጠር፤ ሙስናና የመልካም አስተዳደር እጦት ከድህነት ጋር ተባብረው ሕዝቡን እየደቆሱት፤ ጠንካራ የሕግ ማስከበርና የወንጀል መከላከል አቅም ሳይፈጠር፤ ወንጀል ከተፈጸመም ሕግን ተከትሎ ምርመራ በማድረግ አጥፊ ለፍትህ እንደሚቀርብ ሕዝብ ዕምነት የሚጥልበት ሥርዓት ሳይዘረጋ ሰውን በሞት መቅጣት ቅቡልነት የለውም።
ከዚህም በላይ ያልዳበረና ከብልሹ አሰራር ያልጸዳ፤ ቴክኖሎጂን የማይጠቀም፣ ያልተጻፈና ኋላቀር የማስረጃ ሕግና የምዘና መርህ የሰፈነበት፤ ፍርድ ቢሳሳት እንኳን የፍርድ ክለሳ (Review of Judgment) የሌለበትና ሃሰተኛ ምስክርነት የፍትህን ሚዛን እያንሻፈፈ የሚገኝበት የፍትህ ሥርዓት ያለው መንግስት በወንጀል የተፈረደባቸውን ሰዎች የሚጣልባቸውን ኃላፊነት ሊካፈላቸው ያስፈልጋል። እናም ሕግ አውጥቶ በሞት ሊቀጣቸው አይገባውም።
ሁለት ፍርደኞች ብቻ ተቀጥተው በርካቶቹ “በሕሊና ቶርቸር” ውስጥ
በሕጋችን መሰረት የሞት ቅጣት በአገሪቱ ፕሬዚዳንት ካልጸና ተፈጻሚ አይሆንም። ፕሬዚዳንቱ የሞት ቅጣቱን ወደ ዕድሜ ልክ ጽኑ እስራትም ማሻሻል ይችላል። በሰብዕና ላይ ከሚፈጸሙ (ምሳሌ የዘር ማጥፋት) ወንጀሎች በስተቀር ደግሞ ሞት የተወሰነበት ሰው መንግስት በምህረት (በይቅርታ) ሊፈታው ይችላል።
የሞት ቅጣት በሕዝብ ፊት፣ በአደባባይ በስቅላት ወይም በኢ-ሰብዓዊ መንገድ አይፈጸምም። ይሁንና ቅጣቱ በሰብዓዊ ሁኔታ በማረሚያ ቤት ውስጥ እንደሚፈጸምም ሕጉ ይገልጻል። የአፈጻጸሙ ዘዴም በማረሚያ ቤት የበላይ አካል ይወሰናል። ይሁንና ቅጣቱ የሚፈጸምበት “ሰብዓዊ” የተባለው ሁኔታ ምን እንደሆነ በሕጉ አልተመለከተም።
የሆነው ሆኖ እስካሁን ባለው መረጃ ከደርግ ውድቀት ጀምሮ የሞት ቅጣት የተፈጸመው በሁለት ፍርደኞች ላይ ብቻ ነው። እነዚህም ሜጀር ጄነራል ኃየሎም አርዓያን ገድሏል በተባለው ላይ በ1991 ዓ.ም. እንዲሁም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኃላፊ ክንፈ ገብረ መድህንን ገድሏል በተባለው ላይ በ1999 ዓ.ም. የሞት ቅጣት ተፈጽሞባቸዋል።(በምንና እንዴት ባይታወቅም)
ነገር ግን ፍርድ ቤቶች በየጊዜው የሞት ቅጣት ከመወሰን አልቦዘኑም። “ቅጣቱ ተፈጸመባቸው ወይ?” ከተባለ ግን የሚታወቅ ነገር የለም። Death Penalty Worldwide የተባለ ዓለም-አቀፍ ድርጅት ባስቀመጠው መረጃ መሰረት ከ120 በላይ ፍርደኞች ቅጣቱ ሳይፈጸምባቸው በኢትዮጵያ ማረሚያ ቤቶች ይገኛሉ። አንዳንዶቹም በእስር ከ15 ዓመታት በላይ አስቆጥረዋል።
እርግጥ ነው የሞት ቅጣት የተፈረደበት ሰው ቅጣቱ እስከሚጸናና እስከሚፈጸም ድረስ የጽኑ እስራት እስረኛ ቅጣቱን በሚፈጽምበት ሁኔታ ታስሮ እንደሚቆይ ሕጉ ይገልጻል። ይሁንና “ለፕሬዚዳንቱ እንዲጸና የሚቀርበውና የሚጸድቀውስ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ነው?” የሚለው በሕጉ አልተመለከተም። “ካጸናውስ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ መፈጸም አለበት?” የሚለው እንዲሁ።
“ለማጽደቅ ወይም ላለማጽደቅስ ምክንያቶቹ ምንድን ናቸው?” የሚለውም ባለመቀመጡ ለፕሬዚዳንቱ ያልተገደበ ሥልጣን ተሰጥቷል። ይህም ኃላፊነትና ተጠያቂነት የሌለበት በዘፈቀደ የተገመደለ ነው።
የህጉ ክፍተት እንደተጠበቀ ሆኖ “ፍርደኞቹ የሞት ቅጣት ከተወሰነባቸው በኋላ ሳይፈጸምባቸው ለዓመታት በእስር የሚቆዩት ለፕሬዚዳንቱ ሳይቀርብ በመቅረቱ ነው ወይንስ ቀርቦለት ይጽና/አይጽና የሚለውን ባለመወሰኑ ነው?” የሚለው አይታወቅም።
የሞት ቅጣቱ ወደ ዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት የተቀየረለት ፍርደኛ ስለመኖሩም መረጃ የለም። (በሽብርተኝነት ሞት ተፈርዶባቸው በምህረትና በይቅርታ የተፈቱትን ሳንዘነጋ) ከዚህ የምንረዳው ታዲያ የሞት ቅጣት እንደማይፈጸም እየታወቀ “የወረቀት ነብር” ሆኖ ሕጎቻችንን እያስጨነቀ እንደሚገኝ ነው።
ከሁሉም በላይ ፍርደኞቹ ቅጣቱ ሳይፈጸምባቸው በእስር በማቆየት “ካሉት በታች ከሞቱት በላይ” እንደሚባለው “ዛሬ እሞት? ነገ እሞት?” እያሉ መጨረሻው የማይታወቅና ተስፋ የሌለበት ሕይወት እንዲኖሩ ማድረግ የሥነ-ልቡናና የሕሊና ስቃይ (Torture) ነው። ይህም በመንግስት የሚፈጸም ኢ-ሕገመንግስታዊ ድርጊት ነው።
“ከመሞት መሰንበት” ከሚል ማህበረሰብ አብራክ የተከፈሉ በመሆናቸው ያደርጉታል ተብሎ ባይጠበቅም ፍርደኞቹ ራሳቸው ወይም ቤተሰቦቻቸው ጉዳዩን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ-መንግስታዊ መብት አቤቱታ አስገብተው ለፍትሕ አደባባይ ማውጣትም ያስፈልጋቸው ነበር።
በሁለቱ ላይ ብቻ ቅጣቱን በማስፈጸም በመቶዎች የሚቆጠሩትን በእስር ማቆየት በፍርደኞች መካከል የልዩነት አሠራር መኖሩን ያሳያል። ቁንጮ ሹመኞችን የገደሉት ቅጣቱ ተፈጽሞባቸው ተራ ዜጋ የገደሉቱ ወይም ሌሎቹ የሞት ፍርደኞች ደግሞ ታስረው መቆየታቸው በሰዎች መካከል ልዩነትን ይፈጥራል። ይህም በሕገ-መንግስቱ የተቀመጠውን የእኩልነት መብት ይጋፋል።
የሆነው ሆኖ አገሪቱ የሞት ቅጣትን በሕጓ ብታስቀምጥም እነዚህ ሁሉ ተጨባጭ ሀቆች ግን የሞት ቅጣት በነባራዊው ሁኔታ (De facto) የተደመሰሰ ስለመሆኑ ማረጋገጫዎች ናቸው። በመሆኑም የሞት ቅጣትን አሁንም ድረስ በሕግ መደንገግ “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” እንደሚባለው ነው።
ዓለም-አቀፋዊ ሁኔታዎች
በኢትዮጵያ የሞት ቅጣት ከሕግ እንዲነቀል የሚሞግት የተደራጀ አካል የለም። በጉዳዩ ዙሪያ ነባራዊ፣ ሕጋዊ፣ ዓለም-አቀፋዊና ያለንበትን ዘመን የዋጀ ጠንካራ አመክንዮ በማንሳት ጉዳዩ የፖሊሲ አውጭዎች አጀንዳ እንዲሆን የሚያደርግ ሃሳብም ሲፈልቅ አይስተዋልም።
በአንጻሩ በዓለም-አቀፍ ደረጃ የሞት ቅጣት ከአገራት ሕጎች እንዲፋቅ፤ ሥሙ እስኪደመሰስ ድረስም የሞት ቅጣት ያለባቸው አገራት ሕጎቻቸውንና ያስተላለፏቸውን ውሳኔዎች እንዳይፈጸሙ እገዳ እንዲጥሉባቸው የተጠናከረ ንቅናቄ ይካሄዳል። በየዓመቱም ዓለም-አቀፍ ጸረ-የሞት ቅጣት ቀን በተለያዩ መርሐግብሮች ይከበራል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን (ተመድ) ጨምሮ ያገባናል ባዮችና አገራት ንቅናቄውን ይደግፋሉ።
እኤአ የ1966ቱ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለምአቀፍ ሥምምነት አገራት የሞት ቅጣትን ከሕጋቸው እንዲፍቁ አረንጓዴ መብራት ካበራ በኋላ ተመድ እኤአ በ1989 አገራት የሞት ቅጣትን እንዲያስወግዱ የሚያስገድድ ፕሮቶኮል አውጥቷል። ኢትዮጵያ ግን አልተቀበለችውም።
በተጨማሪም የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ የሞት ቅጣት እንዲጠፋ፤ እስከዚያም ሕግና ውሳኔዎች ተፈጻሚ እንዳይሆኑ የሚከለክሉ አራት ውሳኔዎችን እኤአ ከ2007 እስከ 2013 ባሉት ዓመታት ማስተላለፉን የድርጅቱ ድረ-ገጽ ያሳያል።
ኢትዮጵያ ሁለት የሞት ቅጣትን ብቻ የፈጸመች ቢሆንም ቅሉ በየዓመቱ በበርካታ ፍርደኞች ላይ የሞት ቅጣትን በመፈጸም ስመ-ጥር ከሆኑት ቻይና፣ ኢራን፣ ሳዑዲና መሰል አገራት ጎን ተሰልፋ የተመድ አራቱም ውሳኔዎች ሲጸድቁ ተቃውሞዋን በመዝገብ ላይ አስፍራለች።
ከዓለምአቀፍ ጥረቶቹ ማግስት ከ160 የሚልቁ አገራት የሞት ቅጣትን ከሕጋቸው መፋቃቸውን ነው የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር መረጃ የሚያሳየው። ከ50 በላይ የሆኑ አገራት ግን አሁንም የሞት ቅጣትን ይተገብራሉ።
በአፍሪካ 15 አገራት የሞት ቅጣት አላቸው። እኤአ በ2018 ብቻ በ43 ፍርደኞች ላይ የሞት ቅጣትን በመፈጸም ግብጽ ቁንጮ በሆነችበት በዚሁ ካምፕ ውስጥ በ30 ዓመታት ሁለት ሰዎችን በሞት የቀጣችው ኢትዮጵያም ትገኝበታለች። ተራማጆቹ ርዋንዳ፣ ኮትዲቮር፣ ጋምቢያና ጋቦንን የመሳሰሉ አገራት ግን በቅርቡ የሞት ቅጣትን በመፋቅ ከነግብጽ ካምፕ ወጥተዋል።
ይህ የሚያሳየው ኢትዮጵያ የሞት ቅጣትን በሕጎቿ ውስጥ በማካተቷ ብቻ በተግባር ከሌለችበት ካርታ ውስጥ ራሷን ማስቀመጧን ነው።
ከረቂቅ አዋጁ የሞት ቅጣት እንዲፋቅ
በሰው የመነገድና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው ረቂቅ አዋጅ መሰረት በወንጀሎቹ ምክንያት ተጎጂው ከሞተ ከ15 እስከ 25 ዓመት ወይም እድሜ ልክ ፅኑ እስራት ወይም የሞት ቅጣት እና ከሃምሳ ሺህ እስከ ሁለት መቶ ሺህ ብር መቀጮ ይጣላል።
ነባሩ አዋጅ ቁጥር 909/2007ም በተመሳሳይ የሞት ቅጣትን አካትቶ ነበር። ይሁንና ባለፈው ሳምንት እንዳየነው ሕጉ ባለመተግበሩና አገሪቱ በሌሎች ከባድ ችግሮች ውስጥ ተወጥራ በነበረበት ወቅት በመጽደቁ ጉዳዩ አንገብጋቢ አጀንዳ አልነበረም።
በብዙ መስኮች መሰረታዊ ማሻሻያዎች በሚደረጉበት በአሁኑ ወቅት ግን የሞት ቅጣትን የያዘ የሕግ ረቂቅ መዘጋጀቱ ዓይነተኛ መነጋገሪያ ሊሆን ይገባዋል።
እርግጥ ነው በሰዎች የመነገድና በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ጉዳይ ዓለምን ሰቅዞ የያዘ ችግር ነው። ኢትዮጵያም ከምትገኝበት ጂኦ-ፖሊቲክስ የተነሳ የችግሩ ጡጫ ጠንክሮባታል። እናም የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀቷ አግባብ ነው።
ይሁንና ችግሩ የተለያዩ መነሻዎች ያሉት ሆኖ ሳለ ጥፋት ፈጻሚዎችን በሞት መቅጣት ቅቡልነት ባለው አመክንዮ የሚደገፍ መፍትሄ አይደለም።
“ዜጎቻችን በውጭ አገር ለብዝበዛ እንዲጋለጡ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ ስራ-አጥነት ነው። ህገ-ወጥ ድንበር አሻጋሪዎችም የዜጎችን ስራ-አጥነትንና መሰል ተጋላጭነትን በመጠቀም የተሻለ ህይወት እንደሚያገኙ በመስበክና በመልመል ለእነዚህ ወንጀሎች እየዳረጓቸው ይገኛሉ” ይላል ለፓርላማው የቀረበው የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ። ይህ በግልጽ የሚያሳየው መንስዔዎቹ ብዙ የሆኑትን ችግር ለመቅረፍ ወንጀለኞችን በሞት ከመቅጣት በላይ ሌሎች ቁልፍ መፍትሔዎችን ማስቀመጥ እንደሚገባ ነው።
ዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት እንደሚመክረውም በጥናት በተለዩ አካባቢዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠት፤ የሥራ ስምሪትን ማሻሻል፤ የሥራ ዕድልን ማስፋት፤ መልካም አስተዳደር፣ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን፤ የድንበር ቁጥጥርን ማጥበቅና የጎረቤት አገራት ትብብርን ማጠናከር እንዲሁም ተመላሾችን ማቋቋም ዓይነተኛ መፍትሔዎች ናቸው።
ከዚህ ውጭ ግን የሞት ቅጣት ከሌሎች አማራጭ ከባድ ቅጣቶች በበለጠ ወንጀሉን እንደሚቀንሰው ውሃ የሚያነሳ ማረጋገጫ ማቅረብ በማይቻልበት ሁኔታ የሞት ቅጣትን በአዋጁ ውስጥ ማካተት አግባብነት የለውም። የአገሪቱን የሞት ቅጣት አፈጻጸም ተጨባጭ ሁኔታና ዓለም የደረሰበትን ደረጃም ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው።
“ወንጀሉን ለመከላከል ረቂቅ ሕጉ አስፈላጊ ቢሆንም የሞት ቅጣት መያዙ ግን ስህተት ነው። የሞት ፍርድ ጨካኝና ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ሊመለስ የማይችል ቅጣት በመሆኑ ተፈጻሚነቱ ሊታቀብና ለወደፊቱም ሊቀር ይገባዋል” ሲሉ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በትዊተር ገጻቸው አዋጁን መኮነናቸውን ስናስብ ደግሞ ሕጉ አገሪቱ የሰብዓዊ መብቶችን አያያዝ ለማሻሻል የምታደርገውን ጥረት የሚያጎድፍ ስለመሆኑ መናገር እንችላለን።
ደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 13/2012
ገብረክርስቶስ