ደጃዝማች በዝብዝ ካሳ ዓፄ ዮሐንስ አራተኛ ንጉሠ ነገሥት ኢትዮጵያ ተብለው የነገሡት ከዛሬ 148 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 13 ቀን 1864 ዓ.ም ነበር።
ዓፄ ዮሐንስ አራተኛ የተንቤን ባላባት ከነበሩት የራስ ሳህለ ሚካኤል የልጅ ልጅ ሹም ተንቤን ምርጫ እና ከእናታቸው የእንደርታው ገዢ የራስ አርአያ እህት ወይዘሮ ሥላስ ድምፁ ሐምሌ 5 ቀን 1825 ዓ.ም በትግራይ ተምቤን ልዩ ስሙ ማይ በሀ ተብሎ በሚታወቀው ሥፍራ ተወለዱ።
ርዕሰ መኳንንት ደጃዝማች በዝብዝ ካሳ ሐምሌ 6 ቀን 1863 ዓ.ም ዓፄ ተክለ ጊዮርጊስን አድዋ አካባቢ አሳም የሚባል ሥፍራ ላይ ወግተው ድል ካደረጉ በኋላ ጥር 13 ቀን 1864 ዓ.ም አክሱም ላይ ሥርዓተ ንግሣቸው ተፈጽሞ ዓፄ ዮሐንስ አራተኛ ንጉሠ ነገሥት ኢትዮጵያ ተብለው ነገሡ።
በዝብዝ ካሳ በሐምሌ ወር መጀመሪያ 1863 ዓ.ም. አፄ ተክለ ጊዮርጊስን ድል ካደረጉ በኋላ ለስድስት ወራት ለሥርዓተ ንግሥ ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ‹‹አፄ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንድነት›› በሚለው መጽሐፋቸው ስለድግሱ እንዲህ ብለዋል።
‹‹…ድግሱም ሲሰናዳ ቆይቶ በጥር 13 ቀን 1864 ዓ.ም. በአክሱም ቤተ ክርስቲያን ስመ መንግሥታቸው ‹ዮሐንስ አራተኛ› ተብሎ በጳጳሱ በአቡነ አትናቴዎስ እጅ ተቀብተው በሥርዓተ መንግሥት ነገሡ። በዚሁ ንግሥ ምክንያት ሦስት ቀን በዓል ሆኖ ለግብር 4ሺ ሠንጋ ታርዶና 50 ጉንዶ ማር የፈጀ 150ሺ ገንቦ ጠጅ ቀርቦ በደስታ ሲበላ ሲጠጣ እንደ ሰነበተ ሙሴ ጂ. ዲወ በዝርዝር ጽፎ አትሞታል። የአገራችንም ጸሐፊ አለቃ ዘዮሐንስ የንግሡን ሁኔታ በመጥቀስ ከነገሡ በኋላ በቤተ መቅደስ ወርቅ መበተናቸውን 30 ቀን ሙሉ የደስታ በዓል መደረጉን ጠቅሰውታል። ››
ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ‹‹Innovation and Misoneism during the Reign of Emperor Yohannes IV(1872.1889)›› በተሰኘ ጥናታቸው እንደገለጹት አፄ ዮሐንስ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ በሥርዓት በማዘጋጀትና በማስተዋወቅ ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው። ደብረ ታቦርና ደሴን የመሰሉ ከተሞችን በማልማት፤ በጎንደርና አድዋ ክሊኒክ በመመስረትና በክትባት ዘመናዊ ሕክምና በማስፋፋት፤ ክብረ ነገሥትና ዕደ ጥበባትን የመሰሉ ቅርሶችን ከእንግሊዝ በማስመለስና የባርያ ንግድን የሚያስቆም ድንጋጌን በማውጣት ተጠቃሽ ስራዎችን አከናውነዋል።
አፄ ዮሐንስ በተለያዩ ጦርነቶች አገር ለመውረር የመጣ ጠላትን አሳፍረው በመመለስ የአገራቸውን ድንበር አስከብረዋል። በዘመናቸው ከነበሩት ጦርነቶች በጉንደት፣ ጉራዕና ዶግዓሊ የተካሄዱት ይጠቀሳሉ። የጉንደትና ጉራዕ ጦርነቶች መንሥኤ የግብፅ መሪ ከዲቭ ኢስማኤል ነበር። በርካታ የአውሮፓ ተወላጆች በገንዘብ እየቀጠረ ማዕረግ በመስጠት የግብፁ ወታደር ላይ መሪ አድርጎ ራሱ በቱርክ እየተገዛ ኢትዮጵያን ወሮ ከሱዳንና ሱማልያ ጋር በመቀላቀል ግዛቱን ከሜዲትራንያን ባህር እስከ ህንድ ውቅያኖስ የማስፋት ምኞት ነበረው። አባ በዝብዝ ካሳ አፄ ዮሐንስ አከሸፉበት እንጂ።
ተክለ ጻድቅ ይህን ሁኔታ እንደሚከተለው ይገልጹታል ‹‹በዚህ ጊዜ አንደኛ በአገር ውስጥ የነበረው መከፋፈል፣ ሁለተኛ የኢትዮጵያ በሥልጣኔ ኋላ ቀርነት፣ ሦስተኛ የስዊዝ ቦይ መከፈት አደፋፍሮት ይህ ሰፊ ምኞት አያዋጣህም፣ በከንቱ አትክሰር የሚለው የዘመድ መካሪም አላገኘም። ይልቁንም ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ‹ይገባሃል ያስፈልግሃል ግፋ በርታ› የሚሉት የውጭና የአገር ተወላጆች በረከቱለት። ይኽን የወረራ ምኞቱን ወደ ፍፃሜ ለማድረስ በ1866 ዓ.ም. በኅዳር ወር ጉንደት ላይ በ1868 ዓ.ም በየካቲት ወር ጉራዕ ላይ ‹ያልሠለጠነ መንጋ ወታደር ነው› ብሎ በናቀው በአፄ ዮሐንስ ጦር ድል ተመታ። የተማረከውን የግብጽ ልዑልን በሁለት ሳጥን ወርቅ ብቻ አልመለሱትም ‹‹ያገሬን አፈር ይዞ እንዳይሄድ›› ብለው እግሩን አሳጥበው አስሻገሩት። ››
አፄ ዮሐንስ ሁለት ጊዜ ግብፆችን ድል በማድረጋቸው ስማቸው ገናና ሆኖ ነበር። የንግስና ዘመናቸውን በጦርነቶች ያሳለፉት አጼ ዮሐንስ ህይወታቸውን ያጡትም ከደርቡሾች ጋር በተደረገ ጦርነት ከጠላት ጋር እየተዋጉ ነው። በ1881 ዓ.ም በመጋቢት መባቻ በውጊያው የሚመሩት ጦር ድል እየተቀዳጀ ባለበት ወቅት ንጉሡ ተመተው ወድቀው በማግስቱ ህይወታቸው አለፈ። የአጼ ዮሐንስን ሞት የሰማች አንዲት አልቃሽ ተከታዩን ግጥም መደርደሯ በታሪክ ይጠቀሳል።
አጼ ዮሐንስ ይዋሻሉ፣
መጠጥ አልጠጣም እያሉ፤
ሲጠጡም አይተናል በርግጥ፣
ራስ የሚያዞር መጠጥ፤
በጎንደር መተኮስ፣
በደምቢያ መታረድ አዝኖ ዮሐንስ፣
ደሙን አፈሰሰ እንደ ክርስቶስ፤
እንዳያምረው ብሎ ደሃ ወዳጁን፣
መተማ አፈሰሰው ዮሐንስ ጠጁን፤
የጎንደር ሃይማኖት ቆማ ስታለቅስ፣
አንገቱን ሰጠላት ዳግማይ ዮሐንስ።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 13/2012
የትናየት ፈሩ