እንደ መንደርደሪያ
አቤቱታ አቅራቢዎቹ በአማራ ክልል በሜጫ ወረዳ እናምርት ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። የገጠር የእርሻ መሬታቸው (ይዞታቸው) ለቆጋ መስኖ ልማት ግድብ በመፈለጉ ይወሰድባቸዋል። አጋጣሚውም አሁን ለምናነሳው ጉዳይ እና ለባለጉዳዮቹም ለዓመታት የቅሬታ ምንጭ ሆኖ ይቀጥላል። ይዞታቸው ሲወሰድባቸው በወቅቱ ከነበሩት 233 አርሶ አደሮች መካከል ስድስት የሚሆኑት ማረሚያ ቤት ስለነበሩ ካሳ ሳይከፈላቸው ይቀራል። በመሆኑም በየደረጃው ይመለከታቸዋል ያሏቸውን የመንግስት አካላት ይጠይቃሉ። ተገቢ ምላሽ ማግኘት ግን አልቻሉም።
አስፈጻሚውን አካል ማለትም የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርን እንዲከፍላቸው ቢጠይቁትም ሊከፍላቸው ባለመቻሉ አስተዳደራዊ በደል ደርሶብናል በማለት ያቀረቡትን አቤቱታ የዛሬው የፍረዱኝ አምድ ተመልክቶታል። እነዚህ ስድስቱ አቤቱታ አቅራቢዎች አርሶ አደር ዋለ አለባቸው፣ አርሶ አደር ይታይ አቸነፍ፣ አርሶ አደር ምህረት አታላይ፣ አርሶ አደር ማዘንጊያ አለባቸው፣ አርሶ አደር ጋሻው ዋለ እና አርሶ አደር ዘላለም ቸርነት ናቸው።
የቅሬታው ምንጭ
በ1998 ዓ.ም ይዞታቸው ለቆጋ ግድብ ፕሮጀክት ልማት በመፈለጉ 233 አርሶ አደሮች ከይዞታቸው እንዲነሱ ይደረጋል። ከይዞታቸው ሲነሱም የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትን እና ካሳ የሚከፈልበትን ሁኔታ ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 455/ 97 መሰረት እንዲፈጸም ይደረጋል። ፕሮጀክቱ የሚነካቸው እና ከይዞታቸው እንዲነሱ የተደረጉት አርሶ አደሮችም ልማቱን በመቀበል የሚፈለገውን ቦታ ለቅቀው ይነሳሉ።
በእዚህ ምክንያትም በአካባቢው ለሚኖሩት 233 አርሶ አደሮች የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በካሳ ገማች ኮሚቴ አማካኝነት ካሳ የመክፈል ኃላፊነቱ ይኖረዋል። አዋጁን መሰረት በማድረግም ሚኒስቴሩ በየስማቸው የተሰራውን የካሳ ገንዘብ ለእያንዳንዳቸው የማከፋፈል ኃላፊነት ላለበት የወረዳው አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ እንዲከፈላቸው በማሰብ በካቢኔ የጸደቀውን ተመን ለእዚሁ ዓላማ በተከፈተው የባንክ ሂሳብ ገቢ ያደርጋል።
ለእያንዳንዳቸው የማከፋፈል ኃላፊነትን የተረከበው የወረዳው አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ ለአርሶ አደሮቹ ገንዘቡን ያከፋፍላል። ሆኖም ከ233 ቱ አርሶ አደሮች መካከል በክፍያው ጊዜ አልነበርንም የሚገባን ካሳም አልተከፈለንም ሲሉ እነዋለ አለባቸው ስድስት ሰዎች ቅሬታ ያነሳሉ። ላለፉት ዓመታት ይህ ጉዳይ እልባት ሳያገኝ መቆየቱ ተገቢ አይደለም ይላሉ በጉዳዮ ላይ ቅሬቸውን ያቀረቡት እነ አርሶ አደር ዋለ። በ1998 ዓ.ም በቦታው ላይ ቆጠራ ተደርጎ በ2003 እና በ2004 ዓ.ም ካሳ ተሰጥቶ መጠናቀቁንም ያስታውሳሉ። ‹‹በወቅቱ እስር ቤት ስለነበርን ውክልና ሰጥተን ክፍያውን እንዲቀበሉልን አድርገን ነበር›› ሲሉም ይናገራሉ። ሆኖም ውክልና ለሰጧቸው ሰዎች አቤተቱታ አቅራቢዎቹ ይገባቸው የነበረውን የካሳ ክፍያ ሳይሰጡላቸው እንደተዋቸው ይናገራሉ። ሰኔ 8 ቀን 2004 ዓ.ም ከእስር የተፈቱት አቤቱታ አቅራቢዎች በወቅቱ ቀርበው ካሳው እንዲከፈላቸው ቢጠይቁም ምላሽ የሚሰጣቸው ማጣታቸውን ነው የሚናገሩት።
ደግመውም ጥያቄውን በ2005 ዓ.ም የአካባቢውን ጥበቃ ቢሮ በአካል ቀርበው ይጠይቃሉ። ቅሬታው የደረሰው አካልም ጉዳያቸውን ወደ ወረዳው አካባቢ ጥበቃ ቢሮ እንዲያቀርቡ ያስገነዝባቸው እና ይሸኛቸዋል። እነ ዋለም በመጉላላታቸው ሳይታክቱ ጥያቄያቸውን ይዘው ወደ ተባሉት ቦታ ይደርሳሉ። የወረዳው ጥበቃ ቢሮ የአርሶ አደሮቹን አቤቱታ አስመልክቶ ለአባይ ተፋሰስ ጽህፈት ቤት እና ለቆጋ ግድብ ፕሮጀክት ለአቤቱታ አቅራቢዎቹ ካሳው ስለመከፈሉ አጣርተው ምላሽ እንዲልኩ አሳስቦ ደብዳቤ ይልካል።
በስድስቱ አርሶ አደሮች ስም ሒሳቡ ተሰርቶላቸው እንደነበረ በተደረገው ማጣራት ምላሹ አሳውቋቸዋል። ክፍያውም እንዳልተፈጸመላቸው በማጣራቱ ሂደት የተገኘ ውጤት የጠቆመ መሆኑንም ያመለክታሉ። ይህንኑ ውጤት ይዘው ለክልሉ አካባቢ ጥበቃ ቢሮ ያስገባሉ። የክልሉ አካባቢ ጥበቃ ለወረዳው በጻፈው ደብዳቤ ገንዘቡ ለአርሶ አደሮቹ እንዲከፈላቸው እንዲደረግ ትእዛዝ ያስተላልፋል። ግን ወረዳው ተመን አውጭ እንጂ ክፍያውን የሚፈጽም አለመሆኑን ይገልጻል። ክፍያውን የሚፈጽመው የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር መሆኑን ያሳውቃል ይላሉ እነ አርሶ አደር ዋለ።
በእዚህ ሁኔታ ተገቢው ክፍያ አልተፈጸመልንም የሚሉት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ ጉዳዮን ይዘው ለሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ባህር ዳር ቅርንጫፍ አቤት ይላሉ። በማመልከቻቸውም ተገቢው ካሳ ባለመከፈሉ አስተዳደራዊ በደል ደርሶብናል በማለት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ጉዳዮን መርምሮ ምላሽ እንዲሰጣቸው በመፈለግ አቤቱታቸውን ያቀርባሉ።
እንደ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ማብራሪያ፤ ስለጉዳዮ እንዲቀርብ እና እንዲያስረዳ በተደጋጋሚ የተጠየቀው አስፈጻሚው ተቋም በአካል ቀርቦ ምላሽ ሊሰጥ አልቻለም። በእዚህ ምክንያትም የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት እንባ ጠባቂ ተቋም ጉዳዮን መርምሮ የውሳኔ ሃሳብ ያሳውቃል። ሆኖም የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ለቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ይግባኝ አቅርቦ ይከራከራል።
ባቀረበው የመከራከሪያ ሃሳብም ግለሰቦቹ አቤቱታ አቅርበው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱም መርምሮ የሰጠው የመፍትሄ ሃሳብ ተጠሪ መስሪያ ቤት ተካፋይ ባልሆነበት ሁኔታ የተሠጠ በመሆኑ በመሻር በድጋሚ እንዲመረመርለት ያመለክታል። እንባ ጠባቂ ተቋም ባህር ዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በሰጠው የመፍትሄ ሃሳብ ቀርቦ ባለመከራከሩ በድጋሚ እንዲመረመር ወስኖ አዲስ አበባ ወደሚገኘው ዋና መስሪያ ቤቱ መዝገቡን ይልከውና አቤቱታው በድጋሚ እንዲመረመር ይወስናል።
ይሁን እንጂ ይላሉ አቤቱታ አቅራቢዎች አሁንም ምርመራው ተጠናቅቆ የካሳ ክፍያው እንዲከፈል፤ ክፍያው ባይፈጸም እንኳን ካሳ ክፍያው የማይፈጸምበትን ምክንያት አሳውቆ ምላሽ እንዲሰጡ ተብለው እንደነበር ይናገራሉ። እነ አርሶ አደር ዋለ ግን ከፍያው ‹‹የውሃ ሽታ›› ሆኗል ሲሉ ቅሬቸውን ይገልጻሉ። አቶ ዋለ ሁለት ቃዳ ተኩል፣ ዘላለም ሶስት ቃዳ፣ ማዘንጊ ስድስት ቃዳ፣ መሰረት ለስድስት ቃዳ እሩብ ጉዳይ፣ ጋሻው አንድ ቃዳ ከሩብ እና ይታይ ሁለት ቃዳ የእርሻ መሬት ለልማቱ መተዋቸውን ይናገራሉ።
የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች መሆናቸውን የሚናገሩት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ ልጆቻችንን ባግባቡ ለማሳደግ እና ለማስተማር ተቸግረናል ይላሉ። ከእህሉ ተርፎ ገለባው እንኳን ለከብቶቻቸው መኖ በቂ እንደነበር ያስታውሳሉ። አሁን ከብት ለማርባት እንኳን የገለባ ዋጋም ንሯል በማለት ያማርራሉ። በእርሻ መሬታቸው ማሽላ፣ ዳጉሳ፣ ጤፍ፣ ገብስ፣ ጓያ እንዲሁም ኑግ ያመርቱ እንደነበር ያስታውሳሉ። አቶ ዋለ ሁለት ቃዳ ተኩል በነበረው የእርሻ መሬታቸው እንደ አብነት ሲጠቅሱም ማሽላ ካመረቱ እስከ 40 ኩንታል ያመርቱ እንደነበር፣ ኑግ አምስት ኩንታል፣ ጤፍ ሲሆን ደግሞ እስከ 12 ኩንታል ያመርቱ እንደነበር ያስታውሳሉ።
እንደ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገለጻ፤ መንግስት የተመነልን የካሳ ክፍያ አልተከፈለንም። በእዚህ ምክንያት ደግሞ ለከፍተኛ እንግልት ተዳርገናል። ልጆቻችንን በአግባቡ ለማስተዳደር ተቸግረናል። በመሆኑም በተሰላልን የሂሳብ ስሌት መሰረት ሊከፈለን የሚገባው ካሳ እስካሁን የተጉላላንበት ተጨምሮ ይከፈለን ሲሉ አቤቱታቸውን ያቀርባሉ።
የቆጋ ግድብ ፕሮጀክት ልማት
ከውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የቆጋ ግድብ ፕሮጀክት ልማት ህዳር 1997 ዓ.ም ነው። ፕሮጀክቱ የተጠናቀቀው ደግሞ ግንቦት 2003 ዓ.ም ነው። ግድቡ 83 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሜትር ኪዮብ ውሃ መያዝ ይችላል። ሰባት ሺ ሁለት አካባቢ ሄክታር ያለማል። 14 ሺ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል ነው። 800 ሚሊዮን ብር አካባቢ ወጪ ተደርጎበታል።
የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር
ተጠሪ መስሪያ ቤቱ ለአቤት ባዮች ሐምሌ 01 ቀን 2011 ዓ.ም በተጻፈ ለቆጋ ግድብ ፕሮጀክት በመፈለጉ ከይዞታቸው እንዲነሱ እንደተደረገ በማስታወስ ምላሽ ሰጥቷል። ከይዞታቸው ሲነሱም ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትን እና ካሳ የሚከፈልበትን ሁኔታ ለመወሰን በወጣው አዋጅ (አዋጅ ቁጥር 455/97) መሰረት መፈጸሙን ጠቅሷል።
አመልካቾችን ጨምሮ ለ233 አርሶ አደሮች በካሳ ገማች ኮሚቴ አማካኝነት በየስማቸው የተሰራውን የካሳ ገንዘብ በካቢኔ ጸድቆ የሚገባውን ካሳ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለእዚሁ በተከፈተው የባንክ ሂሳብ ገቢ ማድረጉን አሳውቋል። ይህንኑ ገንዘብ ለእያንዳንዳቸው የማከፋፈል ኃላፊነት ያለበት የወረዳው አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ ስለመሆኑ ጠቅሶ በስማቸው የተዘጋጀውን የካሳ ክፍያ ለማን እንደሰጠ እንዲጠየቅላቸው አሳስበዋል። ፕሮጀክቱን ተረክቦ እያስተዳደረ የሚገኘው የአባይ ተፋሰስ ጽህፈት ቤት ምላሹን እንዲያቀርብም ጠይቀዋል። የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የስድስቱን የካሳ ገንዘብ ቀንሶ ሊያስቀር የሚችልበት ህጋዊ ምክንያት አለመኖሩንም ጠቅሷል። ገንዘቡ ገቢ ስለመደረጉ በወረዳው ገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ጽህፈት ቤት እና የወረዳው ካሳ ገማች ኮሚቴ በሚያቀርበው ማስረጃ ሊረጋገጥ እንደሚችል ምላሽ ሰጥቷል።
ሕገ መንግስቱ እና አዋጅ ቁጥር 455/97
ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትን እና ለንብረት ካሳ የሚከፈልበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 455/97 ለአዋጁ መደንገግ ምክንያት ያለውን በመግቢያው ላይ እንዳመለከተው፤ መንግስት ለሕዝብ አገልግሎት ለሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች መሬትን መጠቀሙ አስፈላጊ በመሆኑ ነው።
የአገሪቱ ከተሞች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉና የነዋሪዎችም ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ በከተሞቹ ፕላን መሰረት ለመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ ለመሰረተ ልማት፣ መሬትን ማልማት በማስፈለጉ እንዲሁም በገጠር ለሚከናወኑ የልማት ስራዎች መሬት አዘጋጅቶ ማቅረብ ስለተፈለገ ለአዋጁ መውጣት ምክንያት መሆኑን አስቀምጧል።
የመሬት ይዞታ እንዲለቀቅ ሲደረግ ለባለይዞታው የሚከፈለውን ካሳ ለመተመን እንዲቻል ግምት ውስጥ የሚገቡ መሰረታዊ መርሆዎችን ለመወሰን አስፈላጊ በመሆኑም አዋጁ እንዲወጣ መደረጉንም በተጨማሪነት ጠቅሶ አዋጁ በመግቢያ ላይ ዓላማውን ያመለክታል።
የፌዴራል መንግስቱ የመሬት አጠቃቀም ሕግ የማውጣት ስልጣን እንዳለው በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 51 (5) የፌዴራል መንግስት ስልጣን እና ተግባር በሚለው ስር የመሬት፣ የተፈጥሮ ሀብት እና የታሪክ ቅርሶች አጠቃቀም እና ጥበቃን በተመለከተ ሕግ እንደሚያወጣ ተደንግጓል።
የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት የንብረት መብትን አስመልክቶ በአንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ 08 ያስቀመጠው አለ። በድንጋጌው ላይ እንደተመለከተውም፤ የግል ንብረት ባለቤትነት መብት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ መንግስት ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ተመጣጣኝ ካሳ በቅድሚያ በመክፈል የግል ንብረትን ለመውሰድ ይችላል። ይህንን ሃሳብ በመመርኮዝም ነው አዋጅ ቁጥር 455/ 97 በዝርዝር ሊደነገግ የበቃው።
አዋጁ የአስፈጻሚው መስሪያ ቤት ኃላፊነት በሚል ያስቀመጠው ድንጋጌ አለ። እንደ ድንጋጌው ከሆነ የአዋጁ አንቀጽ 06 ንዑስ ቁጥር (2) ላይ የመሬት ይዞታቸውን እንዲለቅቁ ለተደረጉ ባለይዞታዎች በእዚህ አዋጅ (በአዋጅ ቁጥር 455/ 1997) መሰረት ተገቢውን ካሳ የመክፈል ኃላፊነትን ጥሏል።
የተያዘ ጭብጥ
እንባ ጠባቂው ለአቤቱታ አቅራቢዎቹ (ለእነዋለ አለባቸው ስድስት ሰዎች) የካሳ ክፍያ የመፈጸም ግዴታ ወይም ኃላፊነት ያለበት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ካሳ ክፍያውን ከመፈጸም አንጻር ግዴታውን ፈጽሟል ወይስ አልፈጸመም ? የሚለውን በጭብጥነት ይዞ መዝገቡን ተገቢነት ካላቸው ህጎች ጋር አገናዝቧል።
የተደረገ ምርመራ እና ግኝት
ዕንባ ጠባቂው አቤቱታውን መርምሮ ተገቢውን የመፍትሄ ሐሳብ ለመስጠት እንዲያስችለው ከተጠሪ መስሪያ ቤት ኃላፊዎች ጋር ውይይት አካሂዷል። ከጉዳዮ ጋር አግባብነት ያላቸውንም ህጎች ተመልክቷል። ተጠሪ መስሪያ ቤቱ ‹‹ካሳ ይከፈለን ጥያቄን›› ተቀብሎ ለ233 የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የካሳ ገንዘብ በአካውንት ገቢ ማድረጉን አሳውቋል። ለአቤት ባዮቹ በተጠሪው መስሪያ ቤት በኩል ግን በሰነድ ተደግፎ ይህንን አላስረዳም። በመሆኑም አቤቱታ አቅራቢዎቹ ካሳ እንዳልተከፈላቸው የምርመራ ውጤቱ አረጋግጧል።
ስድስቱ አቤቱታ አቅራቢዎች እነዋለ አለባቸው ካሳ ተከፍሏቸዋል አልተከፈላቸውም የሚለው ጉዳይ አከራካሪ አልሆነም። አርሶ አደሮቹ ከማረሚያ ቤት ከወጡ በኋላ ካሳ ለምን አልተከፈላቸውም ? የሚለውን መመርመር አስፈላጊ መሆኑን ዕንባ ጠባቂው አምኖበት መርምሮታል። የወረዳው ፋይናንስ ቢሮ እንዳሳወቀው በወቅቱ ካሳ የተከፈለው ወረዳው ላይ አይደለም። ካሳው የተከፈለው ከተማ አስተዳደሩ ላይ ነው።
በመሆኑም ወረዳው በአርሶ አደሮቹ ካሳ ክፍያ ጉዳይ ምንም አይነት ኃላፊነት የለበትም ሲል አሳውቋል። የወረዳው ገጠር መሬት አስተዳደርም ቢሆን ካሳ እንዲከፈላቸው ማስተላለፍ እንጂ ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ ከአሰራር አንጻር ኃላፊነት የሌለበት መሆኑን ገልጿል። የአባይ ተፋሰስ ጽህፈት ቤት በበኩሉ በ2003 ዓ.ም እና በ2004 ዓ.ም ካሳ ክፍያ በቆጋ ፕሮጀክት በኩል ክፍያው እንደተፈጸመ አሳውቋል። ሆኖም ለስድስቱ አርሶ አደሮች በተለያየ ምክንያት ካሳ ሊከፈላቸው እየተገባ ሳይከፈላቸው ከቀረ ግን ገንዘቡ ወደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተመላሽ ሊደረግ እንደሚችል አሳውቋል።
ዕንባ ጠባቂው ከላይ በተገለጹት ምክንያቶም አቤቱታ አቅራቢዎቹ ከማረሚያ ቤት ከወጡ በኋላ የካሳ ክፍያው ሳይፈጸምላቸው እንደቀረ መረዳት ችሏል። በተዘረዘሩት ምክንያቶች ለአርሶ አደሮቹ ካሳ ካልተከፈለ ካሳ የመክፈል ግዴታ እና ኃላፊነት ያለበት የአርሶ አደሮቹን ይዞታ ለግንባታው ያዋለው አካል መሆኑንም ይገነዘባል። ካሳውን መክፈል እንዳለበትም ያምናል።
ለአርሶ አደሮቹ ካሳ ክፍያው እንዲፈጸም የተላለፈላቸው አካላትን ሚኒስቴሩ ተገቢውን ማጣራት አድርጎ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እንደሚኖርበት እንባ ጠባቂው ባካሄደው ምርመራ ማረጋገጡን አመልክቷል። ወይም ለሚመለከተው የህግ አካል ተላልፈው እንዲሰጡ በማድረግ በህግ እንዲጠየቁ ማድረግ እንዳለበት በምርመራው ማጣራቱን እና ይህንኑ ለተቋሙ ማሳወቁን ይጠቁማል።
በጉዳዮ ላይ በቀጥታ በሚመለከታቸው አካላት ቸልተኝነት ወይም ጉዳዮን እንደማያውቁትና እንደማይመለከታቸው በማሰብ እየተፈጸመ የሚገኘው ተግባር ተገቢ እንዳልሆነ ይጠቅሳል። ዜጎች ለሕዝብ ጥቅም በሚል ከይዞታቸው ሲነሱ ሊያገኙ የሚገባቸውን ተገቢ ካሳ እንዳያገኙ የሚያደርግ ተግባር መሆኑንም የምርመራ ውጤቱ ይጠቁማል። በህገ መንግስቱ እና በሌሎች ዝርዝር ህጎች የተሰጣቸውን ካሳ ክፍያ የማግኘት መብትም የሚያሳጣ ሆኖ ማግኘቱንም ያትታል። በእዚህ ምክንያትም ተጠሪ መስሪያ ቤቱ በአቤት ባዮች ላይ አስተዳደራዊ በደል መፈጸሙን እንዳረጋገጠ ነው የሚጠቁመው።
የመፍትሄ ሃሳብ
የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በተሻሻለው አዋጅ 1142/2011 በዜጎች ላይ በዘፈቀደ የሚፈጸሙ የአስተዳደር በደሎችን የመከላከል ተግባር አለበት። ተፈጽሞ ከተገኘም እንዲታረም የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎበታል። ለዜጎች በህገ መንግስቱ እና በሌሎች ህጎች የተሰጣቸውን መብቶች ወይም ጥቅሞች በአስፈጻሚው አካል ተግባራዊ መደረጋቸውን በምርመራ ሂደት በማረጋገጥ የአሰራርም ሆነ የህግ ክፍተት ካለ አስፈላጊው የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ የመፍትሄ ሃሳብ ይሰጣል።
አሁን በተያዘው የእነ ዋለ አለባቸው ስድስቱ ሰዎች ካሳ የማግኘት መብታቸው ህግ የሚያስፈጽመው አካል ማለትም የውሃ መስኖ እና ኢርጂ ሚኒስቴር አላከበረላቸውም። በምርመራ ሂደትም ዕንባ ጠባቂው ይህንን ማረጋገጥ ችሏል። ስለሆነም ለአርሶ አደሮቹ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትን እና ካሳ የሚከፈልበትን ሁኔታ ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 455/97 እና ሌሎች አግባብነት ባላቸው ሕጎች መሰረት ካሳ ሊከፈል ይገባል በማለት ወስኗል። አስፈጻሚው አካል በተሰጠው የመፍትሄ ሃሳብ መሰረት ፈጽሞ የደረሰበትን ወጤት በአንድ ወር ውስጥ እንዲያሳውቀው ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም ልኳል።
የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ምን ይላል?
በጉዳዮ ምላሽ ለማግኘት የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርን በተደጋጋሚ ጠይቀን ነበር። ግን ለሕትመት እስከገባንበት ጊዜ ድረስ ምላሹን ሊያሳውቀን አልፈቀደም። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ምላሽ በሠጠን በማንኛውም ጊዜ የምናስተናግድ መሆኑን ዝግጅት ክፍሉ ያሣውቃል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 13/2012
ዘላለም ግዛው