በኢትዮጵያ የህብረት ስራ ከተጀመረ ረዘም ያለ ጊዜ ተቆጥሯል። ከዕድሜው አንጻር ውጤቱ ሲታይ ግን እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ይነገራል። ዘርፉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተነቃቃ ቢሆንም ካለው አገራዊ አቅም አንጻር ገና ብዙ የሚቀረው ነው።
ዘርፉ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ለእድገቱ ማነቆ የሆነበትስ ምንድን ነው? ያሉት የአሰራር ክፍተቶች እንዴት ይገለጻሉ? በቀጣይ ስኬታማ ለመሆንስ ምን መስራት አለበት? በሚሉትና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ከአቶ ዑስማን ሱሩር ጋር ቆይታን አድርገን እንደሚከተለው አቅርበናል።
አዲስ ዘመን፤ ወደ ኤጀንሲው የስራ ሀላፊነት መቼ ተቀላቀሉ?
አቶ ዑስማን፡- በኤጀንሲው ስራ የጀመርኩት በ 2005 ዓ.ም ሲሆን አሁን ሰባት ዓመት ሆኖኛል።
አዲስ ዘመን፦ በወቅቱ ኤጀንሲውንና ዘርፉን በምን ደረጃ ላይ ነበር ያገኟቸው?
አቶ ዑስማን፦ በወቅቱ ዘርፉ ሞቶ ስርዓተ ቀብሩ ሊፈጸም ጫፍ ላይ ነበር። መንግስት ማህበራቱን እናፍርስ ወይስ ኤጀንሲውን በማስተካከል ችግሩን እንፍታ በሚል እስከመምከር ደርሶም ነበር። በመጨረሻም አሰራሩን ብናስተካክል ችግሩ ይፈታል የሚል ውሳኔ ላይ ነው የተደረሰው። ለእኔም ዘርፉን አፍርሼ እንድሰራ ነው ሀላፊነት የተሰጠኝ።
አዲስ ዘመን፦ አፍርሰው ለመስራት ምን እርምጃ ወሰዱ?
አቶ ዑስማን፦ ስራው ብዙ ውጣ ውረድ ነበረው። በመጀመሪያ የተወሰደው እርምጃ የኤጀንሲው አሰራርና አስተዳደር ችግር በአሜሪካ ድርጅት ማስጠናት ነው። በጥናቱም ኤጀንሲው መንሳፈፊያው ተቀዶ በመስመጥ ላይ እንዳለ መርከብ ሆኖ ነው የተገኘው። ከዚህ በመነሳት የለውጥ መፍትሄ አስቀምጠን ወደ ስራ ነው የገባነው።
አዲስ ዘመን፦ በተቀመጠው መፍትሄ ምን ውጤት አመጣችሁ?
አቶ ዑስማን፦ ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት የማህበራቱ ቁጥር 38 ሺ ሲሆን አባላቱ 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን እንዲሁም ካፒታላቸው ደግሞ 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ነበር። ዛሬ ላይ 90 ሺ ማህበራት፣ 21 ሚሊዮን አባላትና 26 ቢሊዮን ብር ካፒታል ተመዝግቦ ይገኛል።
ይህም ማለት ካፒታላቸው በ2005 ዓ.ም ከነበረበት ተጨማሪ 22 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ብልጫ ማሳየቱን የሚያመላክት ሲሆን በኢኮኖሚው ዕድገት ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ከዚህም በተጨማሪ አንድ አገር ከድህነት ለመውጣት ዋናው መሳሪያ ቁጠባ ነው። ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት ማህበራት የነበራቸው ቁጠባ ከአንድ ቢሊዮን ብር በታች ነበር። ዛሬ 19 ቢሊዮን ብር ደርሷል።
ከዚህም በላይ የህብረት ስራ ማህበራት በስራ ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት በ 2005 ዓ.ም ከነበረበት 240 ሺ አሁን ከ አንድ ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ወደ ስራ አስገብተዋል።
የህብረት ስራ ማህበራት ከፈጠሩት ካፒታልና የስራ ዕድል በላይ ዋናው ስኬታቸው ኢ-ፍትሃዊነትን መቀነስ ነው፤ በዚህም ዜጎች የህብረት ስራ ማህበራት ሲቆጥቡ ማሲያዥያቸው መተማመን ነው። እርስ በእርስ ዋስ በመሆን ብድር ወስደው ድህነትን ድል ያደርጋሉ። በህብረት ስራ ጉልት የሚነግዱ እናቶች ጥቂት በመቆጠብ ብድር ማግኘት ይችላሉ። በዚህም ድህነትን ድል ያደረጉ የልማት አርበኞች በርካታ ናቸው።
በአገሪቱ ኢ-ፍትሃዊነት በማስወገድ ሁሉም በኢኮኖሚው ተሳታፊ መሆኑ በልማት ብቻ ሳይሆን በፖለቲካና በማህበራዊ ተሰሚነትንም እንዲጨምር ያደርጋል። በመንግስትና ኢ- መንግስታዊ አደረጃጀቶች በመግባትም ዜጎች እራሳቸውና አገራቸውን ጠቅመዋል። የህብረት ስራ ማህበራት ተቋማት የመሪዎች ማፍሪያ ጭምር ሆነዋል። ባለፉት ዓመታት ትንሽ ስራ በመስራታችን በርካታ ለውጦች መጥተዋል። በአጠቃላይ በድህነት ቅነሳና ሁሉን አቀፍ ለውጥ በማምጣት ከፍተኛ አስተዋጽኦ መጥቷል። ለዚህም እንደ ተቋምና በግል ጭምር ከፍተኛ መስዋዕትነት ተከፍሏል።
አዲስ ዘመን፦ የአንድ ተቋም ሀላፊ ከሚወጣው ሀላፊነት የተለየ ምን መስዋዕት ከፈሉ?
አቶ ዑስማን፦ ኤጀንሲውን ለመለወጥ ከስራ ባልደረቦቼ ጋር በመሆን በከፍተኛ የስራ ጫና ውስጥ ማለፌ ለከፍተኛ ህመም አጋልጦኝ ነበር። ነገር ግን ህክምና በመከታተል ተርፌያለሁ።
ዋናው የእኔ መሞት አይደለም። ምክንያቱም ሰው በተለያየ ነገር ህይወቱን ሊያጣ ስለሚችል ዋናው ግን አቅም በፈቀደ ልክ ሰርቶ ማለፍ ነው። ለአገርና ለህዝብ የአቅምን ሁሉ ሰርቶ ማለፍን የመሰለ ነገር የለም። በተለይ ደግሞ መንገድ ላይ ጉልት የሚነግዱ እናቶችንና ወጣቶችን ህይወት ለመለወጥ እንዲሁም የብዙሃንን ችግር ለመፍታት ሰርቶ ማለፍ ትልቅ ኩራት ነው። በዚህ ሁሉ ውስጥ አልፌ ዛሬ ላይ የምኮራባቸውን ተጨባጭ ውጤቶች አይቻለሁ።
አዲስ ዘመን፦ አገሪቱ በህብረት ስራ ማህበራት ካላት ጸጋ አንጻር ተሰርቷል የሚሉት የተለየ ነገር ምንድነው?
አቶ ዑስማን፡- አገሪቱ በህብረት ስራ ካላት ጸጋ አንጻር ከተነሳ እስካሁን የተሰራው ከባህር ላይ በማንኪያ እንደመጨለፍ ነው። አሁን የደረስንበት ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው ሀብት በጣም ጥቂቱን ነው። በአዲስ አበባ አንዲት አዋጭ የምትባል የገንዘብ ቁጠባ ህብረት ስራ አለች። በ33 ሴቶችና በስምንት ወንዶች በድምሩ በ 41 ሰዎች ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት የተመሰረተች ናት። ከአባላቶቹ አብዛኞቹ ሴቶች ጉልት የሚነግዱ ነበሩ። ወደ ስራ ሲገቡም በ 15 ሺ ብር ቁጠባ ነበር ።
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ድጋፍ በማድረጋችን አሁን ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 10 ቅርንጫፎች ተከፍተዋል። ከ 500 ሚሊዮን ብር በላይ ቁጠባ ሰብስባለች። 21 ሺ አባላትም አፍርታለች። ይህ የሆነው በአምስት ዓመት ውስጥ ነው።
አገሪቱ ያላትን ጸጋ ከባህር ላይ በማንኪያ ያህል መሆኑን ከዚህ ማህበር መረዳት ይቻላል። ከዚህ አንጻር ገና ብዙ መስራት ይገባል። አሁን ግን ስኬታማ ነን የምንለው በዘርፉ ውስጥ ያለውን ፈተና ተቋቁመን ሊፈርስ የነበረን ዘርፍ በሰባት ዓመት እዚህ ደረጃ ላይ ማድረሳችን ነው።
አዲስ ዘመን፦ ፈተናው ምንድን ነው?
አቶ ዑስማን፦ የእስካሁን ውጤት በብዙ ፈተና ውስጥ የተገኘ ነው። በዘርፉ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ገና ብዙ መስራት ይጠይቃል። የኢትዮጵያ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ኪራይ ሰብሳቢነትና ሌብነት የበላይነት የያዘበት ከመሆኑ አንጻር ከሚገነባ መንገድ፣ ህንጻ ወይም ሌላ አገልግሎት ሰርቆ መኪናና ቤት የገዛን ጀግናና ብልህ የሚያደርግ ነው። የህብረት ስራ ደግሞ ሀብት ወደ ብዙሃን እንዲሄድ የሚያደርግ በመሆኑ ብዙ ፍጭትና ፈተና አለ። ውጤቱ የመጣው በዚህ ትልቅ ፈተና ውስጥ ትግል ተደርጎ ነው። ስለ ህብረት ስራ ማህበር ጥቅም በህዝብ ዘንድ ያለው ግንዛቤ አለማደጉ ሌላው ክፍተት ነው። ፈተናውንም ከፍተኛ እንዲሆን አድርጎታል።
አዲስ ዘመን፦ ምን አይነት የግንዛቤ ችግር ነው ያለው?
አቶ ዑስማን፦ የህብረት ስራ ማህበራት ትልቁ ግባቸው የሰው ልጅ ክብር እንዲኖረውና ችግርን በጋራ መፍታት ነው። ሰዎች በተፈጥሯችን ሙሉ ካለመሆናችን አንጻር ሰው ለሰው መፍትሄ ሲሆን ይታያል። የአንዱን ጉድለት በሌላ በመሙላት በህብረት በመስራት ደግሞ ለዚህ ማሳያው ነው። መጨረሻ የሌለውን የሰው ልጅ ፍላጎት አንዱ ለሌላው ጊዜውን፣ ገንዘብን፣ እውቀቱንና ሌሎች ሀብቶችን አስተባብሮ በመስራት ማሟላት ነው። ከዚህ አንፃር ከአመራሩ እስከ ግለሰቦች በህብረት ስራ ሰው ለሰው ነው የሚሰራው የሚለው በብዙዎች ዘንድ
ግንዛቤ የተሟላ አይደለም።
አዲስ ዘመን፦ የህብረት ስራ ማህበራት በገንዘብ ቁጠባ ያላቸው አስተዋጽኦ በምን ደረጃ ላይ ነው?
አቶ ዑስማን፦ በአገሪቱ 21ሺ የገንዘብ ቁጠባና ብድር መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራትና 128 ዩኒየኖች አሉ። እነዚህ ማህበራት እያንዳንዳቸው 100 ሚሊዮን ብር ቢያፈሩ አገሪቱ በትሪሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚዋ ታስገባለች፤ ከፍተኛ ሀብትም ይኖራታል። በገጠርና በከተማ ያሉ የህብረት ስራ ማህበራት ቢጠናከሩ፣ ግንዛቤ ቢፈጠርና ቢደገፉ አገሪቱ ብድር ፍለጋ ወደ ውጭ አትሄድም። ነገር ግን ገና ብዙም አልተሰራም። የኤጀንሲው አደረጃጀት እንኳን ለዚህ ምቹ በሚሆን ደረጃ ላይ አልተቀመጠም። ይህን እየቀየርን ከሄድን ለውጥ እናመጣለን።
እስካሁን ቁጠባ ላይ በተሰራው ስራ በህብረት ስራ ማህበራት ብቻ ያለው አራት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ደርሷል። ይህ በብሔራዊ ባንክና በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጭምር እውቅና የተሰጠው ቢሆንም አገሪቱ ከምታመነጨው ሀብት አንጻር በጣም ዝቅተኛ ነው። በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን እቅዱ ሲቀርብ ክልሎችም ሆኑ መንግስት አይሳካም ብቻ ሳይሆን ደንግጠው ነበር። እቅዳችንን ግን እያሳካን ነው።
ገንዘቡ መቆጠብ ብቻ ሳይሆን የቁጠባና የመበደር ባህሉም እየተቀየረ መጥቷል። አርሶ አደሮች በመቶ ሺዎች ብር ይበደራሉ። መበደር ብቻም ሳይሆን የብድር አመላለሳቸው መቶ በመቶ ነው። ብድሩ የሚሰጠው እርስ በእርስ ዋስ በመሆኑ ለማሲያዣም አይቸገሩም። ይህ እየሰፋ ከሄደ አገር በአጭር ጊዜ ውስጥ ይለወጣል።
አዲስ ዘመን፦ በህብረት ስራ ህፃናት እንዲቆጥቡ ትሰራላችሁ? ምን ያህል ውጤታማ ነው?
አቶ ዑስማን፦ ልምዱ የተወሰደው ከትግራይ ክልል እምበማህያ ከተባለች የህብረት ስራ ማህበር ሲሆን በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እንዲሆን አድርገናል። ስራው ቁጠባ ሳይሆን ህፃናት የማህበረሰቡን ልምድና ስነምግባር ማስረጽ ነው። ድግስና የመሳሰሉትን ወጪ በማስቀረትም አሉታዊ የሆኑ ባህሎችንም እንዲቀረፍ ማድረግ ነው። ህፃናት በቆጠቡት ብር አድገው ወጣት ሲሆኑ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲሄዱ የትምህርት መሳሪያና አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ይገዛላቸዋል። የቁጠባው ዓላማ አምራችና ተወዳዳሪ ዜጋን መገንባት ነው።
በቁጠባ ስርዓቱ እስከ አሁን ከ 700ሺ በላይ ህጻናት በቤተሰቦቻቸው አማካኝነት እየቆጠቡ ነው። በዚህ መንገድ የሚያድጉ ህጻናት ችግርን ድንጋይ ወርውሮ ከመፍታት ይልቅ በስራና በቁጠባ መፍታትን እየተለማመዱ ያድጋሉ። ስራው በመላ አገሪቱ እንደየአካባቢው ሁኔታ ተግባራዊ እንዲደረግ እየተሰራ ነው። ስራው እየተስፋፋ ከሄደ ውጤታማ ይሆናል።
የህብረት ስራ ማህበራት ዋና ዓላማው ጤናማ፣ ደስተኛና የበለጸጉ ቤተሰቦችን መፍጠር ነው። እነዚህ የበለጸጉ ማህበረሰቦች አገርን ይፈጥራሉ። በሁሉም ደረጃ የምንሰራው ይህን እውን ለማድረግ ነው።
አዲስ ዘመን፦ አዲሱ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለህብረት ስራ ማህበራት ምን አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል?
አቶ ዑስማን፦ ህብረት አንዱ የጎደለውን ከሌላው ጋር በመደመር ችግርን በጋራ መፍታት ነው። የመደመር ፍልስፍናም ያለውን አብሮ በማሰባሰብ ውጤት ማምጣት ነው። በመሆኑም አዲሱ ሪፎርም ከህብረት ስራ ጋር ተጣጥሞ የሚሄድ ነው። በደንብ ከተሰራበት አገሪቱን በኢኮኖሚ ወደ ማይቀለበስ የዕድገት ደረጃ የሚያደርስ ነው።
የህብረት ስራ ግን ውጤታማ እንዲሆንና ዓላማውን እንዲያሳካ በርካታ ጥረት ይጠይቃል። ተገዳዳሪ ሀይልም ያለበት ነው። ዜጎች በህብረት ሆነው የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ ከሌሎች ዘርፎች ነጥሎ በማየት መስራት ያስፈልጋል። ይህ ከሆነ የተጀመረው ለውጥ ወደኋላ እንዳይመለስ ትልቅ መሳሪያ ይሆናሉ።
የአገር በቀል ኢኮኖሚ መሰረቱ ግብርና ሲሆን በዚህ በርካታ የህብረት ሥራ ማህበራት ተደራጀተዋል። ሁለተኛው ኢንዱስትሪ ሲሆን 900 መካከለኛና ዝቅተኛ ኢንዱስትሪዎች በህብረት ሥራ ተገንብተዋል። እነዚህ የህብረት ሥራ ማህበራት እየተሻሻሉና እየተደገፉ ከመጡ በቀጣይ ወደ መሪነት መምጣት ይችላል። ያሉት ማህበራት ኢንዱስትሪውን ወደ ከፍተኛ ያሳድጋሉ፤ ግብርናውንም ወደ መካናይዜሽን ያሳድጉታል። በገበያ ተወዳዳሪና ጥራት ያለው ምርትና አገልግሎት ይሰጣሉ። ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያም ምርትና አገልግሎታቸውን ያቀርባሉ። ማህበራቱ እያደጉ ሲመጡ የኢኖቬሽን፣ የምርምርና የስርጸት ማዕከል ይሆናሉ።
እዚህ ደረጃ እንዲደርሱ የአደረጃጀት፣ አሰራር መበልጸግ አለበት። የአመራር ቁርጠኝነትም ወሳኝ ነው። የህብራት ስራ አመራር ወሳኝ ነው። ጠንካራ አመራር በሌለበት ህብረት ስራ መፈለግ “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” ነው። አመራርና ህብረት ሥራ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ብዙ የሚያወራ ምንም የማይሰራ ባለበት የህብረት ሥራ አይኖርም። ህብረት ሥራ በንግግር ሳይሆን በተግባር የሚፈጥራቸው ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- በህብረት ሥራ የሚካሄደው ግብይት ችግር እንዳለበት ይነሳል። ለዚህ መልስዎ ምንድን ነው?
አቶ ዑስማን፡- ኤጀንሲው የውጭና የአገር ውስጥ ግብይት እንዲከናወን ከተሰጡት ኃላፊነቶች አንዱ ነው። ሆኖም የግብይት ስርዓቱ መዋቅር እንኳን የለውም። መዋቅር ለማስተካከል እየሰራን ነው። እንዲያም ሆኖ የገጠርና የከተማውን ትስስር ጤናማ ለማድረግ ጥረናል።
ገዥና ሻጭ ፍትሃዊ ግብይት እንዲያካሄዱ ሰርተናል። በአገር ውስጥ ከሚደረገው የግብርና ምርት ግብይት ከ13 በመቶ በላይ የሚካሄደው በህብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት ነው። ተጽዕኖውም ትልቅ ነው። በአንድ ኩንታል ጤፍ ከ500 እስከ 1500 ብር ልዩነት አለው ሽያጩ። በገዥና ሻጭ መካከል ያለውን ደላላ በማስቀረት ገበያው ጤናማ እንዲሆን ስንሰራ ነበር።
በውጭ ገበያም ተሳትፏችን እያደገ መጥቷል። ቀደም ሲል በሁለት ምርት ብቻ የነበረው ተሳትፏችን አሁን ላይ የተለያዩ ምርቶች በህብረት ስራ በኩል እየተሸጡ ነው። ለውጭ ገበያ ያቀርቡ የነበሩ አምስትና ስድስት ማህበራት አሁን ላይ ቁጥራቸው ከ40 በላይ ደርሷል። ኤክስፖርት የሚያደርጉት ምርት በመጠንና በጥራትም እያደገ መጥቷል። ለውጭ ገበያ ከሚቀርበው ምርት በመጠን የ8 በመቶ በገንዘብ የ14 በመቶ ድርሻ አላቸው።
አዲስ ዘመን፡- የህብረት ሥራ የሚያቀርቡት ምርትና አገልግሎት የጥራት ችግር አለበት። ይህን ለምን ማስተካከል አልቻላችሁም?
ዑስማን፡- የህብረት ሥራ መለያ ጥራት፣ ዋጋና ቅልጥፍና ነው። በየትም ዓለም ያሉ የህብረት ሥራ ማህበራት መለያ መስፈርቶቻቸው ናቸው። በእኛ አገርም በጥራት፣ በዋጋና በቅልጥፍና መለያቸው የሆኑ አሉ። ከዚህ በተቃራኒው የሆኑ ጥራትና ቅልጥፍና የሌላቸውም አሉ። እነዚህ በአመለካከት ችግር፣ ባለማወቅ ወይም በማወቅ የሚፈጥሩ ችግሮች ናቸው።
የህብረት ሥራ ማህበራት ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ወጥተው የተለዩ አይሆኑም። ህብረት ሥራ ላይ በሁሉም ተቋማት ያለ ችግር አልፎ አልፎ ሊኖር ይችላል። ከዚህ ውጭ ግን የህብረት ሥራ ማህበራት ሲጠናከሩ የንግድ ስርዓቱን ጤናማ ያደርጉታል በሚል ተቀጭተው ከገበያ እንዲወጡ አቅደው ፕሮፖጋንዳ የሚሰሩባቸውም አሉ። በዚህም በህብረት ሥራ የሚፈጠሩ ትናንሽ ችግሮች ተጋነው ሰለሚነገሩ ካለው ችግር በላይ ይጋነናል። በመሆኑም በመጠኑ ማየት ይገባል። ያለውን ችግር ግን አንድም ቢሆን ሊከሰት አይገባም። ይህን እያስተካከልን ነው።
አዲስ ዘመን፡- የህብረት ሥራ ማህበራት የሚፈርሱት ለምንድን ነው?
አቶ ዑስማን፡- የማህበራት መፍረስ ምክንያቱ “ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል” እንደሚባለው ነው። የሚፈርሱት ማህበራት አዋጭነታቸው ሳይጠና የሚቋቋሙት ናቸው። በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ ሳይጠና በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ማህበራት በርካታዎቹ ፈርሰዋል። ወደፊትም መፍረስ ያለባቸው ማህበራት ይፈርሳሉ። እኛ የምንፈለገው ውጤታማ የሚሆኑ በሚሊዮን ህዝብ አሳታፊ የሚያደርጉና ትልቅ ኢኮኖሚ የሚፈጥሩትን ነው። ወደፊት ትናንሾቹን እያዋሀድን ትላልቅ ማህበራትን መፍጠር ነው የምንሰራው።
በዓለም ላይ ያሉ የህብረት ስራ በቁጥር ትንሽ ናቸው። ግን ከአገራቸው አልፈው ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ናቸው። የእኛ አገር ማህበራት በጋራ በመደራጀት እና ከጎረቤት አገራት ጭምር በጋራ በመስራት ትላልቅ ማህበራትን ለመፍጠር እንሰራለን።
አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ ምን ላይ ለመስራት አቅዳችኋል?
አቶ ዑስማን፡- ሥራው እያደገ ነው። አንዱ ሲያልቅ ሌላው ትልቅ ስራ ይወልዳል። አሁን ላይ ይህን ታሳቢ በማድረግ ከቁጥቁጥ ወጥተን በሰፊው አስበን እየሰራን ነው። ባለፉት ሶስት ዓመታት አገር በፖለቲካ ነውጥ ውስጥ ሆና እኛ ስራችንን ስንሰራ ነበር። ለፖለቲካው ነውጥ ብዙም ትኩረት አልሰጠንም። የፖለቲካው አለመረጋጋቱ በኢኮኖሚው ከታገዘ አገር ወደማትመለስበት አደጋ ትገባለች የሚል ግምገማ ነበርን። የፖለቲካውን ሥራ የሚሰሩ እያሉ እኛም ስራችንን ስንሰራ ነበረ።
ባለፉት ሶሰት ዓመታት የህብረት ሥራ በቀጣይ ዓመታት ወዴት መሄድ እንዳለበት አቅጣጫ የሚያሳይ ፖሊስ አዘጋጅተናል። ፖሊሲውን ስናዘጋጅ አንዳንዶች አገር በችግር ውስጥ ስለፖሊሲ ታወራላችሁ በሚል ሲዘባበቱብን ነበር። እኛ በወቅቱ “መንግስትና ፓርቲ ይቀያየራል፤ ህዝብና አገር ግን ሁልጊዜም ይኖራል። ህዝብ እስካለ ችግር አለ። ችግር ካለ ደግሞ ህብረት ሥራ ያስፈልጋል። ማንም ቢመጣ ፖሊሲውን ይጠቀምበታል። የተሻለ ነገር ካለውም የእኛን አሻሽሎ ይጠቀመበታል” እንል ነበር። ፖሊሲ ብቻ ሳይሆን የ15 ዓመታት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅተናል።
በ15 ዓመታት በአገሪቱ ሊደራጅ ከሚችለው ህብረተሰብ በከተማ 75 እና በገጠር 85 በመቶ እናደርሳለን ብለን አስቀምጠናል። ህብረት ሥራ ማህበራቱ ለአባሎቻቸው የግብርና፣ የፋይናንስ፣ የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ለአባሎቻቸው መቶ በመቶ፣ ለሌላው ህብረተሰብ 90 በመቶ የኤክስቴንሽን አገልግሎት እንዲሰጡ አቅደናል። ከሚቀርበው የግብርና ምርት በማህበራት 75 በመቶውን እሴት ጨምረው ያቀርባሉ። ወደ ውጭ ኤክስፖርት ከሚደረገው የግብርና ምርት 60 ከመቶው የህብረት ሥራ ማህበራት ድርሻ እንዲኖራቸው በፍኖተ ካርታው ግብ አስቀምጠናል።
የግብርና ምርቶችን በጥራትና በደረጃ አሽጎ በማቅረብ ደረጃውን የጠበቀና ጥራት ያለው ምርት እንዲሸጥ ለማድረግ ታቅዷል። ፖሊሲውና ፍኖተ ካርታው ለግብርና ሚኒስቴር ቀርቧል። ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያጸድቀው ወደ ሥራ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ለቃለ ምልልሱ ፈቃደኛ ስለሆኑ አመሰግናለሁ።
አቶ ዑስማን፡- እኔም እድሉ ስለተሰጠኝ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 13/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ