ባህል ነክ አሟጋች መከራከሪያዎች
“ባህል” የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ለማንም ሰው እንግዳ አይደለም። የቃሉ ቤተኛነት እንደተጠበቀ ይሁን እንጂ ሁሉንም በጋራ የሚያስማማ ድንጋጌ ለመስጠት ግን ለምሁራኑ እጅግ አስቸጋሪ የሆነ ይመስላል። ሬመንድ ዊሊያምስ የተባሉ ምሁር የባህልን ድንጋጌ በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፣ “በእንግሊዝኛ ቋንቋ ውስጥ ሁለት ወይንም ሦስት ለትርጉምና ለፍቺ አዳጋች ከሆኑት ቃላት መካከል አንዱ ባህል የሚለው ነው። ” የሥነ-ሰብ (Anthropologists) ተመራማሪዎች ለባህል የተሠጡ ድንጋጌዎችን ከየዕውቀት ዘርፉ በመልቀም ቁጥራቸው 150 ያህል እንደሚደርስ ለማመልከት ሞክረዋል።
ምሁራኑ በሰጧቸውና እየሰጧቸው ባሉት ብያኔዎች፣ ትንተናዎችና መከራከሪያዎች ዙሪያ “የእኔ ልክ፣ የአንተ ልክ” እየተባባሉ እንኳንስ ተግባብተው አንድ ስምምነት ላይ ሊደርሱ ቀርቶ ውዝግባቸው ራሱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ ሄዷል። በዚሁ ምክንያትም የሚፈጥሯቸው ድንጋጌዎች ዛሬም ቢሆን ቁጥራቸው እያሻቀበ መሄዱ አልቀረም። ለባህል የሚሠጠው ድንጋጌ አስቸጋሪ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ቃሉ የተሸከመው ጽንሰ ሃሳብ በራሱ ውስብስብ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ምሁራኑና ያገባኛል ባዩ ሁሉ “ባህል” የሚለውን ቃል በተለያዩ ጽንፎች ላይ ቆመው ፍች ለመስጠት ስለሚሞክሩ ጭምር ነው።
የባህልን ጽንሰ ሃሳብ ምንነት ብቻ ሳይሆን ከባህል ጋር የተያያዙ መከራከሪያዎችም ዓይነታቸው ብዙ ነው። ለምሳሌ፣ ካለፈው አስራ አምስት ቀናት ጀምሮ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደትና የጥምቀት በዓላትን በድምቀት እያከበርን እንገኛለን። የክርክሩ መነሻ በዓላቱን ባይመለከትም አምላክና ሰው የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በተመለከተ ግን ምሁራኑ ለዘመናት ሲከራከሩበት የኖሩትን አንድ ሃሳብ ቀጥሎ እንጠቅሳለን።
ክርስቶስ ሰው ሆኖ በምድር ላይ በተመላለሰባቸው በሰላሳ ሦስት ዓመታት ውስጥ የተገኘበትን ማሕበረሰብ ባህል በተመለከተ የኖረው እንዴት ነው?
* ከባህሉ በላይ ሆኖ?
* ከባህሉ በታች ሆኖ?
* ለባህሉ ራሱን አስገዝቶ?
በሥነ መለኮት የሙያ ዘርፍ ላይ ባሉት ምሁራን መካከልም ሆነ በሌሎች የዕውቀት ዘርፎች ላይ በተሰማሩ ልሂቃን መካከል በምላሹ ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ ስላልተደረሰ ይህ ጸሐፊ “አቋሜ ይህ ነው” ለማለት ድፍረት አላገኘም። ርዕሱ በራሱ ውስብስብና አከራካሪም ስለሆነ።
በዚያም ተባለ በዚህ የሰው ልጅ ከባህሉ ጋር ያለውን ትሥሥር በተመለከተ በርካታ ምሁራን ታላላቅ የመጻሕፍት ጥራዞችን እንዲጽፉ ክርክሮቹ ጥሩ ግብዓት ሆነዋቸዋል። እንደ ብዙ ተመራማሪዎች እምነት ማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር በየትኛውም የኑሮ ደረጃና የሕይወት አቋም ላይ ቢገኝ ወይንም ምንም ዓይነት ፍልስፍና ቢኖረው ራሱን ከባህሉ ነጥሎ ለማውጣት ግን አይችልም። ምክንያቱም ባህሉ እንደ አንድ የዘርፉ ምሁር አገላለጽ “ከነርቩ ንዝረት ጋር የተቆራኘ የስብዕናው መገለጫ ስለሆነ። ”
ከላይ በተጠቀሱት ምሁር አገላለጽ፤ “በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረው የሰው ልጅ በሥጋና በነፍስ የተሸረበው ማንነቱ እንዳለ ሆኖ ከዚሁ እውነታ ባልተናነሰ መልኩ ያለ ባህል ስብዕናው ትርጉም አይኖረውም። የሰውን ልጅ ከሌሎች እንስሳት ልዩና ክቡር የሚያሰኘውም የሥጋ፣ የመንፈስና የነፍስ ህልውናው ብቻ ሳይሆን ባህል መፍጠሩና በባህሉ ውስጥ ለመኖር የመገደዱ ምሥጢር ጭምር ነው። ”
የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኰ) እ.ኤ.አ በ1982 ዓ.ም ሜክሲኮ ላይ ባደረገው ጉባኤ የተደረሰበት የጋራ ስምምነት ከላይ ለጠቀስነው እውነታ ጥሩ ማብራሪያ ይሆናል።
“ባህል፣ የሰው ልጅ ሰብአዊና ምክንያታዊ ፍጡር እንዲሆን ያስቻሉት ወይም ከሌሎች ፍጡራን ለመለየት ያበቁት ማንኛቸውም ምሁራዊ፣ ሥነምግባራዊ፣ አካላዊ፣ ቴክኒካዊና ሌሎችም ሥራዎች ሁሉ፣ እንዲሁም የሰው ልጅን የመማር፣ በሞራል፣ በቴክኒክና በአዕምሮ እውቀት ራሱን የማሠልጠን ሁኔታዎችን የሚያጠቃልል ጽንሰ ሐሳብ ነው። አንድ ሕዝብ ከሌላው ተለይቶ የሚታወቅባቸውን ሁኔታዎች፤ ማለትም የአኗኗር ዘይቤዎቹን፣ እምነቶቹን፣ ትውፊቶቹን፣ በአጠቃላይም ቁሳዊና ኅሊናዊ ሀብቶቹን የሚያካትት ሰፊ ጽንሰ ሐሳብ ነው። ”
አንድ ባህል በኅብረተሰቡ ውስጥ ቅቡልነት አግኝቶ ህልው የሚሆንባቸው መንገዶችና ሰበቦች እጅግ ውስብስብና ረቂቅ ናቸው። ባህል በዓመታትና በዘመናት መካከል በንብርብር ማህበራዊ እውነታዎች የመገንባቱን ያህል ለመለወጥና ለመሻሻልም የዚያኑ ያህል የዕድሜ ርቀት ይጠይቃል።
የባህል መፀነሻ ምክንያት አንድና “ይህ ብቻ ነው” የሚባል ውሱን ክስተት አይደለም። የሚፋፋባቸው ማህፀኖች በርካታ ናቸው። ቤተሰብ፣ ማሕበረሰብ፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ሀገራዊ የትምህርት ስርዓት፣ ተምሳሌታዊ ትርጉም ያላቸው ምልክቶች፣ በማሕበረሰቡ ውስጥ አንቱታን ያተረፉ ግለሰቦች፣ ከባዕዳን ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ሀገራት ጋር የሚደረጉ መስተጋብሮችና ግንኙነቶች ወዘተ. ከዝርዝሮቹ መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። እነዚህ ዝርዝሮች በዋነኛነትም የባህሉ መገለጫ በመሆንም ያገለግላሉ።
በዓላትና ባህሎች የተወሰነ መመሳሰሎች ቢኖራቸው እንጂ አንድ ዓይነት ፍቺና ትርጉም ያላቸው የአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽታዎች ተደርገው ሊቆጠሩ አይገባም። ባህልን በውቂያኖስ ብንመስል፤ በዓላትን ደግሞ በመጋቢ ወንዞች መመሰሉ ጥቂት ፍንጭ ሊሰጥ ይችላል። በዓላት ባህሎች ውስጥ ሊካተቱ ይችሉ ካልሆነ በስተቀር ባህሎች ሁሉ በዓላት ውስጥ አይካተቱም።
አንድ ሀገራዊ ጉዳይ ጠቅሰን ሃሳቡን እናብራራ።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በብሔራዊ ደረጃ የምናከብራቸው የሕዝብ በዓላት በቁጥር አስራ ሦስት ይደርሳሉ። ከእነዚህ በዓላት መካከል ስምንቱ (መስቀል፣ መውሊድ፣ የኢየሱስ የልደት ቀን (ገና)፣ ጥምቀት፣ ስቅለት፣ ፋሲካ፣ ኢድ አል ፈጥር፣ ኢድ አል አደሀ) ሃይማኖታዊ በዓላት ናቸው። አራቱ (የአድዋ ድል በዓል፣ የላብ አደሮች ቀን፣ የድል ቀን፣ የደርግ መንግሥት የወደቀበት ቀን) ታሪካዊ መነሻ ኖሯቸው ወይንም የፖለቲካ ክብር ተሰጥቷቸው የሚከበሩ ናቸው። መስከረም አንድ ቀን የምናከብረው የዘመን መለወጫም የራሱ ትርጉም አለው። በርካታ ብሔረሰቦች የራሳቸው የዘመን መለወጫ በዓላት እንዳላቸው ሳይዘጋ።
ታሪካዊና ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው በዓላት አብዛኛውን ጊዜ ከመንግሥታት መነሳትና መውደቅ ጋር ትስስር ስላላቸው መሻርና የመለወጥ ባህርይ ስላላቸው የባህልን መስፈርት አያሟሉም። በደርግ ዘመን መስከረም ሁለት ቀን ሲከበር የኖረው ንጉሡ ከሥልጣን የወረዱበትን ታሪካዊ ክስተት ለማስታወስ ነበር። የኢህአዴግ መንግሥት ስልጣን በያዘ ዋዜም ይህንን ቀን አፋጥኖ በመለወጥ ከጫካ የመጣው ኃይል አዲስ አበባ ከተማን የተቆጣጠረበትን ግንቦት 20 ቀንን ብሔራዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር አደረገ። የፋሽስት ኢጣሊያ ሠራዊት ድል የተመታበት ታሪካዊ ቀንም አንዲሁ ከሚያዝያ 27 ቀን ወደ መጋቢት 28 ቀን እንዲለወጥ በደርግ መንግሥት ተወስኖ ሲከበር የቆየ ቢሆንም ኢህአዴግ ሥልጣን እንደያዘ ወደ ቀድሞ ቀኑ ሚያዝያ 27 ቀን እንዲመለስ መደረጉ አይዘነጋም።
አንዳንድ ጊዜ ረጅም ዘመናት ያስቆጠሩ ሃይማኖታዊ በዓላትም የፖለቲካ ሥልጣኑን በጨበጠ መንግሥት ትዕዛዝ እንዲለወጡ ሙከራ መደረጉ አይቀርም። ከሀገራችን ጉዳይ ጋር የተያያዘ አንድ አጋጣሚ እናስታውስ። አምላክ የለሹ “ኮሞኒስት ነኝ ባዩ” የደርግ መንግሥት በአንድ ወቅት በተከታታይ ቀናት በሚከበሩት የጥምቀት በዓላት ላይ አንድ እርምጃ ለመውሰድ ሞክሮ ሳይሳካለት ቀርቷል። ታሪኩ እንዲህ ነበር። በሀገሪቱ የሚገኙት አርባ አራቱ ታቦታት ለበዓለ ጥምቀቱ ከማደሪያቸው ወጥተው ጥምቀተ ባህር የሚያድሩት ጥር አስር ቀን መሆኑ በሚገባ ይታወቃል። ከአነዚህ ታቦታት መካከል ብዙዎቹ ጥር 11 ቀን ወደ መንበረ መኖሪያቸው ሲመለሱ ሁለቱን ብቻ ለአብነት እንጥቀስና (ሌሎችም ሊኖሩ ይችላሉ) የቅዱስ ሚካኤል ታቦት ጥር 12 ቀን፣ የቅዱስ ሩፋኤል ታቦት ጥር 13 ቀን እንደሚገቡ ይታወቃል። ይህም ከዘመን ዘመን ሲወርድ የመጣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖታዊ ቀኖና ነው። ነገር ግን ደፋሩ የደርግ መንግሥት ሁሉም ታቦታት ጥር 11 ቀን ተሰባስበው እንዲገቡ ቢወስንም ሙከራው በሃይማኖቱ መሪዎች ቆራጥ ውሳኔና በምዕመኑ ተጋድሎ ውሳኔው ሳይፀና ቀርቷል። አንዳንድ ጊዜ በድፍረትም ይሁን ባለማወቅ በሃይማኖታዊ በዓላት አከባበር ላይ የሚሞከሩ አንዳንድ ጥፋቶችና ስህተቶች በቀላሉ የሚበርዱ ስላልሆኑ የመሪዎችን ማስተዋል በእጅጉ ይጠይቃል።
የአንድ ባህል መገለጫዎች በርካቶች እንደሆኑ ቀደም ሲል ለመግለጥ ተሞክሯል። አንዳንድ ባህሎች በተምሳሌታዊ ምልክቶች፣ በአካላዊ የመግባቢያ እንቅስቃሴዎች፣ በስዕሎችና በሙዚቃዎች ወዘተ. ሊገለጡ ይችላሉ። የኢትዮጵያን ብሔረሰቦች የሚወክሉ አለባበሶች፣ ሰላምታዎች፣ ምግቦች፣ መጠጦች፣ የቡና ስነ ሥርዓቶች፣ የቤት አሰራር ጥበቦች ወዘተ. የጎሉ የባህሎቻችን መገለጫዎች ናቸው።
ማሕበረሰባቸው ያከበራቸው በሕይወት ያሉና የሌሉ አልፎም ተርፎም በምናብ የሚፈጠሩ ጀግኖች አርበኞች፣ የኪነ ጥበባት ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና በጥቅሉ የመልካም ተግባራት “አንቱዎች”ም (Role Models) እንዲሁ ባህሉ ገዝፎና ደምቆ እንዲተዋወቅ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው።
የእምነትና የአምልኮ ሥነ ሥርዓቶች፣ ማሕበራዊ መስተጋብሮች፣ የተለያዩ ክንዋኔዎችና ትዕይንቶችም እንዲሁ አንድን ባህል በሚገባ ገልፀው ማራኪ የማድረግ ብርታታቸው ከፍ ያለ ነው። የሚዳሰሱትም ሆኑ የማይ ዳሰሱት የአንድ ሀገር ባህሎች የዚያ ሀገር ሀብት ብቻ ሳይሆኑ የዓለም ማሕበረሰብም ጭምር የሚሆኑበት አጋጣሚዎች ብዙ ነው። ዩኔስኮ በማይዳሰሱ ቅርስነት የመዘገባቸውን የመስቀል፣ የገዳና የጥምቀት በዓላትን በአብነት ማስታወስ ይቻላል። ሌሎች በርካታ የሀገራችን የሚዳሰሱ ቅርሶችም በዚሁ ድርጅት አማካይነት በዓለም ቅርስነት መመዝገባቸው ይታወሳል።
ማሕበረሰቡ ይሁነኝ ብሎ ባፀደቃቸው ዕሴቶች ውስጥም ባህሉ እንደሚንፀባረቅ ጠቁሞ ማለፍ ይቻላል።
ለምሳሌ ክፋትና ደግነት፣ ቸርነትና ንፍገት ወዘተ. የአንድ ባህል መገለጫዎች የሚሆኑባቸው ጊዜያትም አሉ። ምንም እንኳ ዛሬ ዛሬ እውነታው ፈታኝ ቢሆንም “ኢትዮጵያዊነት ደግነትና ርህሩሁነት ነው። ያለስስት ተካፍሎ ይበላል። እንግዳ ተቀባይ ደግ ሕዝብ ነው። ወዘተ.” እያልን የኖርነው ባህላችንን ለማስተዋወቅ ጭምር ትልቅ ድርሻ ነበረው። የዛሬው አቋማችን እንኳ በተከድኖ ይብሰል ትዝብት ቢታለፍ ይሻላል።
አንድ ባህል በራሱ የሚመሰገነውም ሆነ የሚነቀፈው አቅፎ በያዛቸው ዕሴቶች ሲመዘን እንደሆነ የዘርፉ ጠበብት አበክረው ያስገነዝባሉ። በአንድ ባህል ውስጥ አድገውና ዳብረው ማሕበረሰቡ በአሜንታ የሚቀበላቸው እሴቶች በአይነትም ሆነ በብዛት መልካቸው ዝንጉርጉር ነው። ለምሳሌ አንድ ባህል “የሰው ለሰው ግንኙነትን የሚመለከተው አንዴት ነው?” “ሰው ለሰው መድኃኒቱ ነው” እያሰኘ ነው ወይንስ “ለሰው ሞት አነሰው” የሚል ፍልስፍና ለባለባህሉ ሕዝብ እያስተማረ? ወይንስ “ሰው ክፉም ነው ደግም ነው” እያሰኝ ሚዛን በማስጠበቅ።
ሌላም ምሳሌ እናክል። የሰውና የተፈጥሮን ግንኙነት በተመለከተ ባህሉ በማሕበረሰቡ ውስጥ ምን ዓይነት እሴት አዳብሯል? “ተፈጥሮ ከሰው ቁጥጥር በላይ ነው!”፣ “የለም ሰው ከተፈጥሮ በላይ ነው!”፣ ወይንም “ሰውና ተፈጥሮ ተደጋጋፊ ናቸው። ” ይህ ጥልቅ ትንታኔ የሚፈልግ ጭምቅ ሃሳብ ነው። ዘመነ ደርግ ሲያስፎክረን የኖረው “ተፈጥሮን በቁጥጥር ሥር እናደርጋለን” እያለ እንደነበር የምናስታውሰው ነው። ይህ ማለት ደርግ ሊያሰርፅ የሞከረው “ተፈጥሮ ከሰው በታች ነው” የሚል እሴትን ነበር። ሀገራዊ ርሃቡ ፍልስፍናውን ፉርሽ አድርጎበት ተሸናፊ ባያደርገው ኖሮ። በአሁኑ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሚቀነቀነው እሴት ደግሞ “ሰውና ተፈጥሮ ተደጋጋፊ ናቸው” የሚል መሆኑን የቅርብ ጊዜው የችግኝ ተከላ ዘመቻችን ጥሩ ማሳያ ነው።
የጾታ እኩልነትን በተመለከተም ባህሉ በማሕበረ ሰባችን ውስጥ ምን እሴት አሳድጎልናል? ብለንም መጠየቅ እንችላለን። “ሴቶች ከወንዶች በላይ ናቸው!”፣ “ወንዶች ከሴቶች በላይ ናቸው!” “አይደለም ሴቶችና ወንዶች አኩል ናቸው” የሀገራዊ ባህላዊ እሴታችን የቱን ፍልስፍና እንድናቀነቅን ሲያስተምረንና ማሕበረሰቡም ሲያለማምደን እንደኖረ ጠለቅ አድርገን ብንመረምር መልሱን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል።
ባህላችን ያዳበረውን የጊዜ አጠቃቀም እሴትን ልብ ብለን ብናጤንም ብዙ ማለት ይቻላል። ለምሳሌ፤ የአንዳንድ ሀገር ባህሎች ጊዜን በተመለከተ እሴታቸው “ትናንት ከዛሬ ይሻላል” የሚል አይነት ነው። አንዳንዶች ደግሞ “ዛሬ ከትናንት ይሻላል” ባዮች ናቸው። ከሁለቱ ያፈነገጡት ደግሞ “ነገ ከዛሬም ሆነ ከትናንት የተሻለ ይሆናል” በማለት ይከራከራሉ። እኛ ለጊዜ አጠቃቀም ያዳበርነው እሴት በተመለከተ ምን እንደሚመስል ሶስት ሰዓት የተጠራ ስብሰባ አምስት ሰዓት መከፈቱን፣ አራት ሰዓት እንዲገኝ ፕሮግራም የተያዘለት የክብር እንግዳ ስድስት ሰዓት መድረሱን እያጣቀስን ራሳችንን መውቀስ እንችላለን።
ባህል በጥቅሉ ቁሳዊና መንፈሳዊ ወይንም የሚዳሰስና የማይዳሰስ ተብሎ ሊመደብ ይቻላል። ባህል የማይነካው የሕይወት ክፍል የለም። ከጥንት እስከ ዛሬ ሰብዓዊነት የተገመደውና የሰው ልጅ ባህርይውም ሆነ መስተጋብሩ የሚሸመነው በባህል ውስጥ ነው።
የሰው ልጅ ባህል ባይኖረውስ?
ይህ ጥያቄ የዘርፉን ልሂቃን ለዘመናት ሲያነታርክ የኖረ መሆኑ ከላይ ተጠቅሷል። ይሁን እንጂ ብዙዎች የተስማሙበት የጋራ ሃሳብ የሰው ልጅ ያለባህል መኖር ያለመቻሉን ነው። ዓሣን ከባህር አውጥቶ ማኖር እንደማይቻል ሁሉ የሰውን ልጅም ከባህል ውጭ አንዲኖር መፍረድ ወደ እንስሳ ባህርይ የመመለስ ያህል የከበደ ነው። ባህል ሰብዓዊነትን ገንብቷል። ያለ ባህል ሕይወት ጣዕምና ትርጉም አልባ ነው። ባህል ተከልሎና ለብቻው አድፍጦ የሚኖር ክስተት ሳይሆን ከሌሎች ባህሎች የሚዋሰው፣ የሚያውሰው፣ የሚጥለውም ሆነ የሚያነሳው ብዙ ጉዳዮች አሉት። በተቻለ መጠን ሀገራዊ ባህሎቻችን በይዘታቸውና በቅርጻቸው በድንበር ዘለል ተፅእኖዎች ሙሉ ለሙሉ እንዳይወረሱና እንዳይመሰቃቀሉ ልዩ ጥበቃ ማድረጉ ላይ መበርታት እንጂ “ቱባ ባህሌ በጭራሽ አይነካም!” ብሎ አፍኖ ለማኖር መሞከሩ እጅግም ውጤት ላያስገኝ ይችላል። መልካም የሰሞነ ጥምቀት በዓላት። ሰላም ይሁን!!!
ይህ ዓምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ አስተያየታቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሑፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 13/2012
በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ