የምርጫ 2012 አጀንዳ፤ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎችን አሁንም ድረስ ለሁለት ጎራ ከፍሎ እንዳነታረከ ነው። ምርጫው ይካሄድ እና አይካሄድ ንትርኩ አሁንም መቋጫ ባያገኝም የምርጫው አስፈጻሚ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግን ሥራውን ቀጥሏል። ምርጫ 2012 የሚካሄድበት ቀን ተቆርጧል። ቦርዱ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ጊዜያዊ የጊዜ ሰሌዳ መሠረትም 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ነሐሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ይካሄዳል። እነሆ ከወዲሁ ዝግጅቱም ተጣጡፏል። የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ለማስፈጸም የሚረዱ ወደ 40 የሚጠጉ መመሪያዎችን የማውጣትና ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር የመወያየት ሥራዎች በምርጫ ቦርድ በኩል እየተከናወኑ ነው። ፓርቲዎች ግን በሙሉ ፊታቸውን ወደ ምርጫ ሥራ ስለማዞራቸው ከጥቃቅን ምልክቶች በስተቀር ጎላ ብሎ የሚታይ ተጨባጭ ነገር እየታየ ነው ለማለት አያስደፍርም። አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ከእርስ በርስ መናከስ፣ መካሰስ፣ መወነጃጀል፣ ጣት መቀሳሰር… ገና አልወጡም። ጥቂቶችም ውስጣዊ አንድነታቸውን ለማስጠበቅ ተስኗቸው ግራና ቀኝ የሚላጉ ሆነዋል። ከመጪው ምርጫ ጋር በተያያዘ ጥቂት ጉዳዮችን ወደመዳሰስ እንለፍ።
የመጪውን ምርጫ መካሄድ አስመልክቶ የሚነሱ የተቃርኖ ሀሳቦች፣
በተወዳዳሪ ፓርቲዎች በኩል መጪውን ምርጫ አስመልክቶ በሁለት ጎራ የሚራመድ አቋም በጉልህ እየታየ ነው። አንዱ ጎራ የዘንድሮ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ሠላማዊ ሁኔታ በአገሪቷ ባለመኖሩ ምርጫ ተራዝሞ ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ፍላጎቱን እያንጸባረቀ ይገኛል። ተቃራኒው ቡድን የመጀመሪያውን ቡድን “ሥልጣን በአቋራጭ ለማግኘት የሚያልሙ ኃይሎች” ሲል ይወርፍና ያሉትን አገራዊ ችግሮች በአስተማማኝ መልኩ ለመቅረፍ የሕገመንግሥቱን ድንጋጌ ተከትሎ በወቅቱ ምርጫ ማካሄድ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም ይላል። ይህም ሆኖ የሁለቱ ወገኖች የልዩነት ሀሳቦች የሚናቁ አይደሉም። ይህን ለማስታረቅ ወይንም ለማቀራረብ የሚያስችል ድባብ መፍጠር በዋንኛነት የመገናኛ ብዙሀን እና የሲቪክ ማህበራት ኃላፊነት ቢሆንም በዚህ ረገድ ከሙከራ ያለፈ አርኪ ሥራ እየተከናወነ ነው ለማለት አያስደፍርም።
ስለውህደት፣ ግንባር፣ ቅንጅት፣
የምርጫው መቃረብን ተከትሎ ውህደት፣ ግንባር እና ቅንጅት… የሚፈጥሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የነበሩ ድርጅቶች አዴፓ፣ ኦዴፓ እና ደኢህአዴን ተዋህደው “ብልጽግና” የተሰኘ አዲስ ፓርቲ መስርተዋል።
ከውህደቱ ያፈነገጠው ህወሓት በበኩሉ “የፌዴራሊስት ኃይሎች” በሚል ግንባር ይሁን ቅንጅት ያልለየለት ስብስብ ፈጥሯል።
አርበኞች ግንቦት ሰባት እና ሰማያዊ ፓርቲ… የፈጠሩት ጥምረት “የኢትዮጵያ ዜጎች ማሕበራዊ ፓርቲ (ኢዜማ)” የተሰኘ አዲስ ፓርቲን ወልዷል።
የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና በሌንጮ ለታ የሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር (ኦዴግ) ጋር ከአንድ ዓመት በፊት ለመዋሀድ የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈጸማቸው የሚታወስ ነው። በሌላ በኩል የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና አምስት በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎች ጥምረት ጋር በጋራ ለመሥራት በቅርቡ ተስማምተዋል።
ታዋቂው አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ ወደ ኦፌኮ መቀላቀል እና እሱን ተከትሎም ኦፌኮ፣ ከኦነግ፣ ከኦብፓ ጋር በትብብር ለመሥራት የሚያስችል ስምምነት ማድረጉ የመጪው ምርጫ ዝግጅት አንድ አካል አድርጎ መውሰድ ይቻላል። ይኸ መሆኑም በቀጣይ በተለይ በኦሮሚያ ክልል የሚኖረውን የምርጫ ውድድር ጠንካራ እንደሚደርገው ይገመታል።
ኢዴፓ (የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ)፣ ኢሀን (የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ) እና ህብር ኢትዮጵያ በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውም ተሰምቷል። ሌሎችም በተመሳሳይ መንገድ እየተሰባሰቡ ያሉ ፓርቲዎች መኖራቸው ይሰማል።
በአዋጁ ትርጉም መሠረት “ውህደት” ማለት ሁለትና ከዚያ በላይ በሕግ የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተናጠል ሕጋዊ ሰውነታቸውን በመተው አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ የሚመሰርቱበት ሒደት ነው።
“ግንባር” ማለት ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተናጠል ሕጋዊ ሕልውናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የጋራ የሆነ ስያሜ፣ የፖለቲካ ፕሮግራም እና መተዳደሪያ ደንብ ይዘው ለመንቀሳቀስ ሲወስኑ የሚመሰርቱት ድርጅት ነው።
“መቀናጀት” ማለት ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተናጠል ሕጋዊ ሰውነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በምርጫ ወቅት ምርጫውን ለማሸነፍ ወይንም ለሌላ መሰል ጊዜያዊ ዓላማ በጋራ ለመሥራት ተስማምተው የመቀናጀት የምስክር ወረቀት የሚያገኙበት ሁኔታ ነው።
አወዛጋቢው የፓርቲዎች የድጋሚ ምዝገባ ጉዳይ፣
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተመዝግበው የሚገኙ ፓርቲዎች በምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሠረት ማሟላት ያሉባቸው ግዴታዎች የሚደነግገው መመሪያ ቁጥር 003/2012 ከታህሣሥ 26 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ወጥቶ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ መመሪያ በምርጫ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 160 ንዑስ አንቀጽ (2) መሠረት አዋጁ ከመውጣቱ በፊት የተመዘገበ የፖለቲካ ፓርቲ በአዋጁ የተቀመጡትን መስፈርቶች ቦርዱ በሚያስቀምጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ማሟላት ያለበት መሆኑን ይደነግጋል። በዚህ መሠረት የአገር አቀፍ ፓርቲ እና የክልል ፓርቲዎች ነባርና እና አዳዲስ ፓርቲዎች ማሟላት ያለባቸው ጉዳዮች በመመሪያው በግልጽ የተቀመጠ ሲሆን ምዝገባው መመሪያው ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚከናወን ቀነ ገድብ ተቀምጦለታል። ከምርጫ ቦርድ በተገኘ መረጃ መሠረትም በመመሪያው መሠረት የተመዘገቡ ፓርቲዎች ትክክለኛ ቁጥር እስከ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ይታወቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በአሁን ሰዓት 139 ገደማ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ የሚነገር ይሁን እንጂ በምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ሠርተፍኬት ያላቸው ፓርቲዎች ቁጥር ግን ከ70 እንደማይበልጥ መረጃዎች ያሳያሉ። በመጪው መጋቢት ወር ይፋ የሚሆነው የአዲሱ ምዝገባ ውጤት የፓርቲዎቹን ቁጥር ከግማሽ በታች ሊቀንሰው እንደሚችል ይገመታል።
ፓርቲዎች ማሟላት ያለባቸው ግዴታዎች ምንድንናቸው?
የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 64 በተደነገገው መሠረት አንድ የፖለቲካ ፓርቲ አገር አቀፍ ፓርቲ ሆኖ የሚመሰረተው ቢያንስ 10 ሺ መሥራች አባላት ሲኖሩት እና ይህንን የሚያረጋግጥ የአባላቶቹን ፊርማ የያዘ ማረጋገጫ ሰነድ ሲያቀርብ ነው። ከእነዚህ መሥራች አባላት ውስጥ የአንድ ክልል ነዋሪዎች ከ40 በመቶ (አራት ሺ) መብለጥ እንደሌለበት በአዋጁ ተቀምጧል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በአዋጁ አንቀጽ 65 በተደነገገው መሠረት አንድ የፖለቲካ ፓርቲ የክልል የፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ የሚመሰረተው ቢያንስ 4 ሺ መሥራች አባላት ሲኖሩት ነው። ከእነዚህ መሥራች አባላት ውስጥ ከ60 በመቶ (2 ሺ 400) በላይ የሆኑት የክልሉ መደበኛ ነዋሪዎች መሆን እንዳለባቸው ተደንግጓል።
ይኸ የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 የተቀመጠ ድንጋጌ በኋላም በመመሪያ ተደግፎ የወጣው ያልተመቻቸው ፓርቲዎች ጥቂት የሚባሉ አልነበሩም።
በተለይ ሕጉ ከጸደቀ በኋላ ሆድ ብሷቸው የጎዳና ላይ አድማ በማድረግ ጭምር የመንግሥትን እጅ ጠምዝዘው ድንጋጌውን ወደሚፈልጉት ለማስቀየር ብዙ ደክመዋል። በየጋዜጣው የፊት ገጽ በመውጣት አቧራ ለማስነሳት ጥረዋል። ቁጥራቸው አንዳንዴ 33፣ አንዳንዴ 70 የሚያደርሱት እነዚሁ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ጥያቄያቸው በአጭሩ “የተቀመጠውን መስፈርት ለማሟላት አቅማችን አይፈቅድም” የሚል ይዘት ያለው ነው። በቦርዱ በኩል አዋጁ በረቂቅ ደረጃ ብዙ ምክክሮችን ያለፈና ብዙ ማሻሻያዎች የተደረጉበት እንደነበረ፣ የማርቀቅ ሒደቱም በገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን መካሄዱን በማስታወስ፣ መመዘኛው እጅግ አነስተኛ መሆኑንና የሚቀየር ነገር አለመኖሩን በተደጋጋሚ ገልጿል። የጎዳና ላይ የረሀብ አድማ እስከመጥራት ደርሰው የነበሩት የፖለቲካ ኃይሎች በመጨረሻም ቁጣና ተቃውሟአቸውን አርግበው፤ ደም በመለገስ በጎ ተግባር ተሳትፈው ወደቤታቸው መመለሳቸውንም በአድናቆት የታዘብነው ነው።
ምርጫ ቦርድ ባወጣው የአፈጻጸም መመሪያ መሠረት በአዋጁ የተቀመጠውን ዝቅተኛ መስፈርት ቁጥር የማሟያ ጊዜ መመሪያ ከጸደቀበት (ማለትም ታህሣሥ 26 ቀን 2012 ዓ.ም) ጀምሮ የሁለት ወራት የጊዜ ገደብን ያስቀምጣል። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ በተለይም ነባር ፓርቲዎች ቀደም ሲል ያስመዘገቡት የአባላት ቁጥር ከተቀመጠው መስፈርት የሚያንስ ከሆነ የጎለደውን እንዲያሟሉ፣ በቂ ከሆነ ደግሞ በቦርዱ ተረጋግጦ ዕውቅና እንደሚሰጣቸው ተደንግጓል። ቦርዱ የቀረበለትን የአባላት ፊርማ ሰነድ የመመርመር ሥልጣንም አለው ተብሏል። በዚህ መመሪያ መሠረት መሀተም በኪሳቸው ይዘው የሚዞሩ አባል አልባ ፓርቲዎች የመቀጠላቸው ነገር ተስፋ ያለው አይመስልም። ቢያንስ አዋጁና መመሪያው ትክክለኛ ፓርቲዎችን አንጥሮ በማውጣት ረገድ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል።
የምርጫ ክንውን ጊዜያዊ የጊዜ ሰሌዳን በተመለከተ፣
የ2012 ምርጫን አስመልክቶ ቦርዱ ባወጣው ጊዜያዊ መርሃግብር መሠረት የዘንድሮ ምርጫ ድምጽ መስጫ ዕለት ነሐሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚሆን ተመልክቷል። በተጨማሪም የመራጮች ምዝገባ ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዚያ 28 ቀን 2012 ዓ.ም፣ የእጩዎች ምዝገባ ጊዜ ከሚያዚያ 13 ቀን እስከ ሚያዚያ 26 ቀን 2012 ዓ.ም፣ የምረጡኝ ዘመቻ ጊዜ ከሚያዚያ 27 እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም፣ የምርጫ ድምጽ መስጫ ዕለት ነሐሴ 10 ቀን ሲሆን ቦርዱ የተረጋገጠ ውጤት ማሳወቂያ ቀን ከነሐሴ 11 እስከ 20 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚሆን ተጠቅሷል። በጊዜ ሰሌዳው እና አፈፃፀሙ ላይ በተካሄደው ውይይት ከተነሱ ዋና ዋና ጥያቄዎች እና አስተያየቶች መካከል የሚከተሉት እንደሚገኙበት ከቦርዱ ያገኘሁት መረጃ ይጠቁማል።
የመራጮች ምዝገባ ጊዜ ከ30 ቀናት እንደሚያንስ፣ የእጩ ምዝገባ ቀናት አንሷል፣ ቢታሰብበት፣ ቀኑ ክረምት ላይ በመዋሉ ለማስፈፀም ያስቸግራል፣ ጥቅምት ወይንም ህዳር 2013 ዓ.ም ለምን አይሆንም? በምርጫ ዘመቻ ወቅት ወከባ እንዳይፈጠር ቦርዱ ዝግጅት ቢያደርግ? የምረጡኝ ቅስቀሳ ቀናት ያንሳሉ፣ ከአሁን ጀምሮ ቅስቀሳ የጀመሩ ፓርቲዎችም አሉ፣ ቦርዱ ምን ይላል? ፓርቲዎች የድምፅ መስጫ ወረቀቱ ላይ የሚደረደሩበት ቅደም ተከተል በእጣ ይሆናል ማለት ምን ማለት ነው?
በምርጫ ቦርድ አመራር አካላት ለቀረቡት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ የመራጮች ምዝገባ በሕግ የተቀመጠ 30 ቀን መሆኑን፣ የእጩ ምዝገባ ቀናት በህግ በተቀመጠው መልኩ እንደሚታይ፣ አስፈላጊ ከሆነ ቀናት መጨመሩን ቦርዱ ሊያየው ይችላል ግን በእቅዱ ላይ የተቀመጠው ቀን ለፓርቲዎች እንደማያንስ እንደውም ጫና የሚሆነው ቦርዱ ላይ መሆኑን ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ነሐሴ ላይ ምርጫው መካሄዱ ቦርዱ ፈልጎ የገባበት አይደለም፣ ግንቦት ለማድረግ ስላልተቻለ ነው ተብሏል። ስለዚህ በግንቦት ወር ላይ ማድረግ የሚቻል አይደለም። አፈፃፀሙ ክረምት በመሆኑ ብዙ ችግር እንደሚገጥመው እሙን ነው። ከክልል መንግስታት፣ ከፌዴራል መንግስትና ሌሎች ተቋማት ቦርዱ የሎጅስቲክስ ድጋፍ ጠይቆ ለማስፈፀም ጥረት ያደርጋል። ከመስከረም ካለፈ ደግሞ የህግ ጥሰት ይፈጥራል። ስለዚህ ወደፊት መግፋት አለመቻሉ ተነግሯል።
የዘመቻ ጊዜ ከወከባ እና ችግር እንዳይኖር ቦርዱ ጥረት ያደርጋል፣ ከዚህ በፊት ፓርቲዎች ችግር ሲገጥማቸው ቦርዱ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፣ አሁን ይህንን ድጋፍ ለማስፋት በምርጫ ዘመቻ ወቅት የራሱ ዴስክ አዘጋጅቶ ተቋማዊ ድጋፍ እንደሚያደርግ የቦርድ አባላቱ ጠቅሰዋል።
የምረጡኝ ቅስቅሳ አሁን መጀመር አይቻልም፣ የተሰጠው ሶስት ወር በላይ ግን በቂ ነው፣ ከአሁኑ ቅስቀሳ የጀመሩ አሉ ለተባለው ውይይት እና ንግግር ከህዝብ ጋር ማድረግ ይቻላል፣ እኔን ምረጡኝ የሚል ዘመቻ ግን መጀመር አይቻልም፣ ያንን የሚያደርጉ ፓርቲዎች ላይ ቦርዱ ማጣራት ያደርጋል።
ፓርቲዎች የድምፅ መስጫ ወረቀት ቅደም ተከተል ሲባል የሚደረደሩበት መንገድ በእጣ የሚወሰን ይሆናል እንጂ ከዚህ በፊት እንደነበረው አይሆንም። እጣው ላይ በሚደርሳቸው ቅደም ተከተል መሰረት ፓርቲዎች የድምፅ መስጫ ወረቀቱ ላይ በቅደም ተከተል እንደሚቀመጡ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
የድምጽ መስጫ ዕለት (ነሐሴ 10) አስመልክቶ ከሚሰጡ ሌሎች ተጨማሪ አስተያየቶች አንዱና ከፍተኛ ግምት ሊሰጠው ከሚገባው አንዱ ጊዜው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ የጾም ወቅት (ፍልሰታ/ጾመ ማርያም) መሆኑ ነው። እንደሚታውቀው የፍልሰታ ጾም ከነሐሴ አንድ እስከ አሥራ አምስት የሚከናወን ነው። በዚህ ወቅት ምርጫ ማካሄድ ሕዝብ በምርጫ ላይ ያለውን ተሳትፎ እንዲቀንስ ምክንያት ሊሆን ስለሚችል ቢያንስ የድምጽ መስጫው ዕለት በአንድ ሳምንት ወደፊት ቢራዘም የተሻለ ሊሆን እንደሚችል የሚነሳው ሀሳብ ቦርዱ ሊያየው ይገባል።
የፓርቲዎች ቅስቀሳና ትንኮሳ አዘል ዲስኩሮችን በሚመለከት፣
ቦርዱ ባወጣው ጊዜያዊ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ፓርቲዎች አባሎቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን ሰብስበው የምረጡኝ ቅስቀሳ የሚደርጉበት ጊዜ ከሚያዚያ 27 እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ ነው። ይህም ሆኖ አንዳንድ ፓርቲዎች ከወዲሁ ቀጥተኛ ያልሆነ የቅስቀሳ ሥራ የጀመሩበት ሁኔታ የምንታዘበው ነው። ሌሎች ደግሞ እጅግ አስደንጋጭ በሆነ መልኩ አባልና ደጋፊዎቻቸውን ሰብስበው ግልጽ የምርጫ ቅስቀሳ ከማካሄድ በላይ ተቀናቃኞቻቸውን እና የሌሎች ሃይማኖት ተከታዮችን በአደባባይ በማንቋሸሽ፣ በመዝለፍ፣ ደጋፊዎቻቸውንም ለሁከትና ብጥብጥ በማነሳሳት ረገድ ያሳዩት የሕግ ጥሰት እና ነውረኛ ድርጊት በቀጣይ የቦርዱ ጠንካራና ቆንጣጭ እርምት የሚሻ ነው።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 13/2012
ፍሬው አበበ