በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ በየአመቱ በደማቅ ስነስርእት የሚከበረው የጥምቀት በአል ትናንት በመላ ኢትዮጵያ በድምቀት ተከብሯል።በአሉ በአዲስ አበባ እና በተለያዩ ክልሎችም በተመሳሳይ ተከብሮ የዋለ ሲሆን፣በአዲስ አበባ ጃንሜዳና በጎንደር ደግሞ በአሉ የተከበረው በርካታ ምእመናንና የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገሮች ጎብኚዎች በተገኙበት ነው ።
በአሉ በጃን ሜዳ በተከበረበት ስነስርእት ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሀይማኖት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ባስተላለፉት መእልክት፤በዓለ ጥምቀቱ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት በተመዘገበ ማግስት መከበሩ ለኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንና ለአገር ትልቅ ትርጉም እንዳለው ጠቅሰው፣እንደ ጥምቀት ያሉ በዓላት የአንድነትና ፍቅር አስተምሮት ያዘሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የጥምቀት በአል በእርግጥም አንድነትና ፍቅር የተንጸባረቀበት ነው።ማንም እንደሚገነዘበው፤ በአሉ ከመንፈሳዊ በአልነቱ በተጨማሪ የተለያዩ ፋይዳዎች አሉት።በበአሉ አከባበር ወቅት የሚታዩ ትዕይንቶችም ይህንኑ ያረጋገጡ ናቸው።በተለይ የእምነቱ ተከታይ ወጣቶች ፣ሙስሊሞች እና ሌሎች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ታቦታቱ ወደ ጥምቀተ ባህር የሚሄዱባቸው መንገዶችና የጥምቀተ ባህሩን አካባቢ ጭምር በማጽዳት የሚያሳዩት ርብርብ የህዝቡ አብሮ መኖር ማሳያ ነው።ህዝቡ የቱንም ያህል ፈተና ቢገጥመው አንድ በሚያደርገው ሁሉ አብሮ ከመሆን የሚያግደው እንደሌለ ያመለክታል።
ህብረተሰቡ በአጠቃላይ በተለይ ወጣቶች ህዝቡ በአሉን በሰላም አክብሮ ወደ ቤቱ እንዲገባ ተቀናጅተው ያከናውኗቸው ተግባሮች አድናቆት ሊቸራቸው ይገባል።እንደሚታወቀው የአደባባይ በአሎች ሲከበሩ በህዝብ ብዛት እና መጨናነቅ ሳቢያ ብዙ ጉዳቶች ይደርሳሉ።
ይሀን አጋጣሚ እንደ ሰርግና ምላሽ የሚጠቀሙ አካላት ሲኖሩ ደግሞ ችግሩ ምን ያህል ሊባባስ እንደሚችል መገመት አይከብድም። ወጣቶቹ ይህን አይነት ችግሮች እንዳይደርሱ በሚል ያከናወኑት ተግባር በሌሎች የአዘቦት ቀናትም ሊደጋገም ይገባል። መንግስትም ይህን የወጣቶቹን ተግባር ሀገሪቱ ሰላምንና ልማትን ለማረጋገጥ ለምታከናውናቸው ተግባሮች ቀምሮ መጠቀም ይኖርበታል።
በአሉ የማያሳትፈው የህብረተሰብ ክፍል የለም። የእምነቱ አባቶች ፣ ካህናት ፣ቀሳውስት፣ምእመናን ህጻናት፣ ወጣቶች፣ ጎልማሶች፣አዛውንቶች፣የእምነቱ ተከታዮች ፣የእምነቱ ተከታይ ያልሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ወዘተ … በበአሉ ላይ ይገኛሉ።ይህን ያህል ህዝብ አብሮ ስለአንድ ጉዳይ እያሰበ ይውላል።ይህም አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ አብረን እንደምንሆን ያመለክታል።ስለሆነም ሌሎች የሚያስተሳስሩንን ሀብቶችም በመጠቀም ለሀገር ሰላምና ልማት ማዋል ይኖርብናል።
በበአሉ ላይ የታደሙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በአሉ ከሃይማኖታዊ ትሩፋቱ ባሻገር ለአገሪቱ የሃብት ምንጭ በተለይ አዲስ አበባ ከተማ ከቱሪዝሙ ዘርፍ ይበልጥ ተጠቃሚ እንድትሆን እንደሚያስችል ጠቅሰው ፣መላ ኢትዮጵያውያን የአለም ሃብት ለመሆን የበቃውን ይህን በአል እንዲያሳድጉትና እንዲያስተዋውቁት አሳስበዋል።
በአሉ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊው ፋይዳውም ከፍተኛ ነው። ከፍተኛ ሀብት የሚንቀሳቀስበትም ነው። ስለሆነም የዚህን በዓል ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ማሳደግ ይገባል። በተለይ በአሉ በዩኒስኮ መመዝገቡ በቀጣይ ብዙ በመስራት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መስራት ያስፈልጋል።
ጥምቀት ብዙ ጥበቦች የሚታዩበትም ነው።ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በባህላዊ ልብሶች አጊጦ አደባባይ የሚወጣበት ነው።የባህል ልብስ በአይነት በአይነት ይታያል።ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ መባሉስ ለዚህ አይደል። በርካታ ጥበብ የሚታይበት ነው፤ የሀገራችን የባህል ልብስ ዲዛይነሮች አቅም ምን ያህል እያደገ እንደመጣም በበአሉ የሚታዩት አልባሳት ያመለክታሉ።
ከእነዚህ ዲዛይነሮች በስተጀርባ በዚያው ልክ በማምረቱ እና በግብይቱ በኩልም ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን መታወቅ አለበት።ይህ አለባበስ በቀጣይም የእለት ተእለት እንዲሆን በማድረግ የሀገራችንን ምርት ተጠቃሚነት ማሳደግ ይኖርብናል።
መንግሥት ይህን የህዝብ ትስስር የጎላበት በአል ለሀገር ልማትና ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ግንባታ ለማዋል መስራት ይኖርበታል።በተለይ የጥምቀት በአል ድምቀት የሆኑት ወጣቶች ይህን አርአያነት ያለው ተግባራቸውን የዕለት ተዕለት በማድረግ ለሀገራቸው ሰላምና ልማት መስራት ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 12/2012