ዛሬ የጥምቀት በዓል ነው፡፡ በዓሉም በመላው ኢትዮጵያ በከተማም ሆነ በገጠር በመሐል አገርና በጠረፍ ካሉት አብያተ ክርስቲያናት ታቦታት ከመንበራቸው ተነሥተው ወደተዘጋጀው ባሕረ ጥምቀት በመውረድ አካባቢያቸውን እና ምዕመኑን ከሚባርኩበት ከከተራ ጀምሮ ይከበራል፡፡ በዓሉ ሕፃን አዋቂው አብዝቶ የሚደሰትበት እና በጋራ የሚሳተፍበት ነው፡፡
ታቦታቱ በባሕረ ጥምቀት አካባቢ በሚያድሩበት ድንኳን ውስጥ ማኅሌቱና ሥርዓተ ቅዳሴው ሲከናወን የሚቆይ ሲሆን፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ ብቻ ሳይሆን የውጭ አገር ጎብኚዎች እና የተለያዩ የሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ሳይቀሩ በበዓሉ ታዳሚ የሚሆኑበት ነው፡፡
ካህናት ነጫጭ ልብሰ ተክኗቸውን ተጎናፅፈው በማኅሌትና በመዝሙር፣ በቅዳሴና በልዩ ልዩ ውዳሴ ድምፃቸውን ሲያሰሙ፤ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ተመሳሳይ ቀለማትን የያዙ የሃይማኖቱን ሥርዓት የተከተሉ አልባሳትን በመልበስ እያሸበሸቡ መዝሙር ሲዘምሩ ቀልብን ይስባሉ፡፡
የበዓሉ ታዳሚዎች ወንድ ሴት፤ ሽማግሌና ወጣት እንዲሁም ሕፃናት ሳይቀሩ ሀብት ያለው አዲስ ልብስ ገዝቶ፤ ዓቅም የሌለው ደግሞ በቤት ውስጥ ያለውን አጽድቶ፤ ነጭ በነጭ ለብሶና አሸብርቆ በዝማሬ፣ በሆታና በእልልታ፣ በከበሮ እየተሳተፈ ታቦታቱን አጅቦ በሚያልፉባቸው መንገዶች ሲጓዝ ገሚሱ በታላቅ ድምቀት የሚከብረውን በዓል በተመልካችነት ይታደማል፡፡
ዘንድሮ ደግሞ የጥምቀት በዓል አከባበር በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ የትምህርትና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ሆኖ ታኅሣሥ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ተመዝግቧል፡፡
ይህ ክብረ በዓል ከሃይማኖታዊ ክዋኔው በተጨማሪ በአገር ቅርስነት የተመዘገበ በመሆኑ ሃይማኖታዊ ይዘቱን ሳይለቅ የአገር ሀብት ሆኖ እንዲቀጥል መስራት ያስፈልጋል፡፡
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ለማስመዝገብ እንደተጋው ሁሉ የባህል ሚኒስቴርን ጨምሮ ከበዓሉ ጋር ተያይዞ አገሪቱ በቱሪስት ፍሰት የተሳካላት ሆና ኢኮኖሚዋ እንዲደገፍ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ በዓል ከሰዎች የመንፈስ ደስታ በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲያስገኝ ተግቶ መስራቱ በአንድ ድጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ በበዓሉ አገሪቱ መንግሥትም ሆነ አጠቃላይ ሕዝቡ እንዲጠቀሙ ያስችላል፡፡
በዓሉ ልክ በሌሎች አገሮች እንደሚታዩት ፌስቲቫሎች እውቅናው በዓለም ተንሰራፍቶ፤ የጎብኚዎች ቁጥር ተበራክቶ፤ ታዳሚው አሁን ከሚታዩት ጥቂት የውጭ አገር ዜጎች በላይ ብዙሃን ተሳትፈውበት ከርመው በጎንደር ብቻ ሳይሆን በባሌም ሆነ አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች፤ በገጠር አካባቢዎች ሳይቀር በዓሉ እንደሚከበር በማስተዋወቅ ለቱሪስቶቹ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ትኩረት ሰጥቶ መረባረብ ይገባል፡፡
በዓሉ ሃይማኖታዊ ይዘቱን ሳይለቅ ከዚህም በላይ ማንም ቢሆን ምቾቱ ሳይጎደል፤ ግፊያና ትርምስ ሳይኖር በአግባቡ በፍቃደኛ ወጣቶች አስተባባሪነት ብቻ ሳይሆን መንግሥትም አስቦበት የተደራጀ የበዓል አከባበር እንዲሆን መስራት ይጠበቅበታል፡፡
በዓሉ በተደራጀ መልኩ ደምቆ እንዲከበር ቤተክርስቲያን እና ምእመኑ በእምነት ለሃይማታቸው አስበው ከሚሰሩት በተጨማሪ ጥምቀት የአገር ሀብት ሆኖ መመዝገቡን በማሰብ ሥርዓት ባለው መልኩ ለጎብኚዎች የተመቸ ሆኖ እንዲከበር የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት አለባቸው፡፡
በጊዜው ሆን ብለው ትርምስ የሚፈጥሩ ዘረፋ የሚያካሂዱ ምእመናን እንዲጨናነቁና እንዲተራመሱ የሚያደርጉ በዓሉን የሚያጠለሹትን በመለየት ለፀጥታ ኃይል በማስረከብ በተዋጣ መልኩ እንዲካሄድ የድርሻቸውን ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል፡፡
በዓሉ ደምቆ በተደራጀ መልኩ እንዲካሄድ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አያጠያይቅም፡፡ ይህ የእምነቱ ተከታዮች፣ የቤተክህነት ወይም የአቢያተክርስቲያናት ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን መንግስትም የፀጥታ ሃይሉን በማሰማራት ሁሉም ምቾት እየተሰማው በዓሉ እንዲከበር ማድረግ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 11/2012