የሰውን ልጅ በእውቀት የሚወልድ የሙያ ሁሉ አባት ነው፤ መምህርነት። እውቀትና ትምህርት ባለበት ሁሉ መምህር አሻራው በአንድም በሌላም መልኩ ይገኛል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ደግሞ መምህራንን እንደ ዋርካ ናችሁ አሏቸው። ጥላ ከለላ፤ ኃላፊነትና አደራም ያለባችሁ ናችሁ ሲሏቸው ነው።
ታድያ በትላንትናው እለት ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ዘጠና ስድስት ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች የተውጣጡ እነዚህ ዋርካ የተባሉ መምህራን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ግቢ ተሰባስው ነበር። የመሰባሰባቸው ምክንያት ለአገር አቀፉ የመምህራን ጉባኤ ሲሆን፤ በአጋጣሚውም በየጊዜው ከሚገጥማቸው ችግር መፍትሄን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሻት ጥያቄዎቻቸውን አቅርበዋል።
ለትምህርት ዘርፍ ከተሰጠው ትኩረት፣ ከትምህርት ጥራት፣ ከመምህራን ጥቅማጥቅም፣ ከአገር ሰላም እንዲሁም ከአካል ጉዳተኞች ተካታችነት ጋር የተያያዙና ሌሎች በርካታ ጥያቄዎች ተነስተዋል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩልም ምላሽና ገንቢ አስተያየት ተሰጥቶባቸዋል።
መምህራን አንዱ ችግራችን ነው ያሉት የጥቅማ ጥቅም ጉዳይ ነው። ጥቅማጥቅሙ ዝቅተኛ ከመሆኑ በላይ በተመሳሳይ እውቀትና ደረጃ የተለያየ ክፍያ መከፈሉም በምክንያትነት ተነስቷል። የመምህራንን አገልግሎት ዋጋ የማይተመንለት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደመወዝና ጥቅማጥቅም ጥያቄ እንደአገር የበርካታ ተቋማት ችግር መሆኑን በምሳሌ አሳይተዋል። በተመሳሳይ ደረጃና እውቀት ላሉ ግን ወጥ የሆነ አሠራር ሊኖር ይገባል ብለዋል።
በመምህራንና በትምህርት ዘርፍ በኩል ሲነሱ የቆዩ ችግሮች ቀላል ባለመሆናቸው ችግሩን ለመፍታት ጊዜ ይወስዳል። ሆኖም ለትምህርት ጥራት የተሰጠውን ትኩረትና በአወቃቀር፣ በእቅድና በአሠራር እየተኬደባቸው ያሉ ሥራዎችንም ልብ ብሎ ማጤን ይገባል። «በሚጠበቀው ልክ ምላሽ ያልተሰጠ ይሆናል፤ ነገር ግን የትምህርት ሥርዓቱን ማዘመንን በተመለከተ አጥብቀን እየሠራን ነው» ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በጉባኤው በአሁኑ ጊዜ እያሳሰበ ያለው የሰላም ጉዳይም ተነስቷል። በተለይም ከታሪክ ትምህርት ጋር በተገናኘ የማስተካከል አቅሙ በመምህራን እጅ ላይ መሆኑም ተጠቁሟል። «በአገራችን ያለውን ችግር ለመቅረፍ ከእናንተ ወዲያ ከማንም ጋር ትክክለኛ መሠረት መጣል አይቻልም» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በመምህራን በአገራቸው እንደማይደራደሩና ያላቸውን መተማመን ግልጽ አድርገዋል። እናም «ታሪክ መማሪያ እንጂ መዋጊያ እንዳይደለ ማስተማር ይገባል» ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የእውቀት ምንጭን መፈለግ ላይ መሥራት እንደሚገባም አንስተዋል። ይህም በተለይ ማኅበራዊ ድረ ገጽን አስመልክቶ፤ ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆን እንዴት መጠቀም እንዳለበት የሚያውቅ ትውልድ ማፍራትን የተመለከተ ነው። በዚህም ላይ የሃሳብ ልዕልናን እንዲሁም ኅብራዊነትን በማስተማር፤ ዋርካነታቸው እንዲገለጥ አንጥሮ የማየት አቅማቸውን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል። በዚህም ትኩረትን በትብብር አገር መገንባት ላይ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በጉባኤው ላይ ተሳታፊ ከሆኑ መምህራን መካከል ከሻሸመኔ ምዕራብ አርሲ የመጡት መምህር ንጉሤ ሀብተማርያም ይገኙበታል። መምህር ንጉሤ የቋንቋ መምህር ሲሆኑ፤ ሰላሳ ስድስት ዓመታትን በመምህርነትና በተያያዥ ኃላፊነቶች ላይ አገልግለዋል።
በአሁኑ ጊዜ በትምህርት ዘርፉ የተነሱ ችግሮችን ለመቅረፍና በዛም አገርን ከፍ ለማድረግ የሰላም ዋጋ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ባይላሉ። «አገርን ለመገንባትና ለማሳደግ መጀመሪያ አንድነትና ኅብረት ሊኖር ይገባል» ያሉት መምህር ንጉሴ፤ በጉባኤው አገራችንን እንዴት ማሳደግ እንደሚቻልና የመምህራን ኃላፊነት በዛ ውስጥ ምን እንደሆነ ተረድተዋል።
የሰላምን ዋጋ ከፍ አድርገው ያነሱት መምህር ንጉሤ፤ የኑሮ ሁኔታ አለመመቻቸት ተማሪን በትክክል ከመቅረጽ እንደማይገድብና እንደአገርም ሰላም የማስከበር ሥርዓቱን እንደማያስተጓጉል ይገልጻሉ። እርሳቸው ባሉበት አካባቢ የመማር ማስተማሩ ሂደት መልካም መሆኑን ያነሱ ሲሆን፤ ከጉባኤው የተገኘውን መልካም ተሞክሮ ሁሉም መምህራን በየአካባቢውና በሚያስተምርበት የጀመረውን ለማጠናከርና የዘነጋውንም እንዲያስታውስ ያግዘዋል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 28/2011
በሊድያ ተስፋዬ