«የአእምሮ ህመም የእግዜር ቁጣም፤ እርግማንም አይደለም» ፕሮፌሰር አታላይ ዓለም የአእምሮ ህክምና ስፔሻሊስት

«አንዲት የመንግሥት ሠራተኛ ሴት ናት፤ አንድን የሃይማኖት አገልጋይ ሊያገባኝ ይፈልገኛል ፤ እግዚአብሄርም ፈቅዷል እያለች ሁልጊዜ በሚሠራበት ቦታ ጠዋት ጠዋት በመሄድ ሳታየው ወደ ሥራዋ አትገባም። ነገር ግን ሰውየው ይሸሻታል። እሷ ግን እሱን ለማየት በሚገባበት የሥራ ቦታ እና ሰዓት በር ላይ ቆማ ጠብቃው ሰላምታ ሳትሰጠው ወደ ሥራዋ አትሄድም። ይሄ ሁኔታ በሥራዋ ላይ ማርፈድን አስከተለ። ከሥራ ማርፈድ ደግሞ ተያይዞ የሚመጡ ነገሮች ይኖራሉ። እናም ወደ ችግር ውስጥ ገባች። ይሄን የሴትየዋን ሁኔታ ሰዎች አይተው ወደ አእምሮ ጤና ህክምና ባለሙያዎች በማድረሳቸው ምክንያት ሴትየዋ መታከምና መዳን ቻለች። ሴትየዋ ፍቅር ይዟት ሳይሆን ከአእምሮ ህመም አንዱ ገጥሟት ነው፤ አንዳንዶች ግን ፍቅር ይዟት ነው የሚል አስተሳሰብ ነበራቸው» ይላሉ የአእምሮ ህክምና ስፔሻሊስቱ ፕሮፌሰር አታላይ ዓለም።

ብዙ ሰዎች ስለ አእምሮ ህመም ያላቸው ግንዛቤ የተዛባ ነው። የእግዜር ቁጣ ወይም እርግማን አድርገው የሚቆጥሩ እንዲሁም በህክምና የማይድን የሚመስላቸው ቁጥራቸው ቀላል የሚባሉ አይደሉም። ወደ እምነት ተቋማት በመውሰድ ብቻ መፍትሄ የሚገኝ የሚመስላቸው ብዙዎች ናቸው። ህሙማኑን አስረውና ደብቀው በቤታቸው የሚያስቀምጡም አሉ፤ በዚህ ብዙ ህሙማን መጎዳትና መጎሳቆል ይደርስባቸዋል። የአእምሮ ህመም መነሻ ምክንያቱ የተለያየ ቢሆንም እንደማንኛውም ህመም ሁሉ የሚታከምና የሚድን ነው። እያንዳንዱ ሰው አካላዊ ህመም ሲያጋጥመው በሽታው የሚጠራው በራሱ በህመሙ ነው። ለምሳሌ አንድ ልቡን ወይም ኩላሊቱን የታመመ ሰው ምኑን ታሞ ነው የሚል ጥያቄ ቢነሳ የልብ ወይም የኩላሊት ህመምተኛ ነው ይባላል። ነገር ግን የአእምሮ ጤና ችግር የገጠውን ሰው ግን የአእምሮ መታወክ ህመም ሳይሆን የሚባለው «እብድ» የሚል ህመሙን የማይገልጽ መጠሪያ ይሰጠዋል። ይሄ መጠሪያው ህመምተኛውንና ቤተሰቡን የሚያሸማቅቅ ጭምር ነው። በሁሉም ማህበረሰብ ዘንድ የአእምሮ ጤናን አስመልክቶ ያለው የግንዛቤ ክፍተት ከአጠራሩ ጀምሮ የሚታይ መሆኑን ይሄ ያሳያል ያሉን በሥነ አእምሮ ህክምና ረጅም ልምድ ያካበቱት ስፔሻሊስት ሀኪሙ ፕሮፌሰር አታላይ ዓለም ናቸው።

የአእምሮ ጤና የአእምሮ ህመም የሚባለው መቼ ነው? የአእምሮ ጤና ምክንያቶች ተብለው የሚጠቀሱ ምንድናቸው? የአእምሮ ህመም መነሻ ምክንያቶች፣ በእነዚህና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ፕሮፌሰር አታላይ ማብራሪያ ሰጥተውናል።

የዓለም ጤና ድርጅት እአአ በ1948 ሲቋቋም ኤክስፐርቶች ተሰብስበው የአእምሮ ጤና ምንድነው? ብለው በሰጡት ትርጉም መሠረት ጤና ማለት በአካል ላይ የሚከሰት በሽታ አለመኖር ብቻ አይደለም። እሱን ጨምሮ የማህበራዊ ፣ የሥነልቦናዊ እና የመንፈሳዊ ጤንነትን ጭምር የሚያጠቃልል ነው በማለት ነው ያስቀመጠው።

አንድ ሰው ሲመረመር በአካሉ ላይ ምንም አይነት የጤና ጉድለት የሌለው ሆኖ ነገር ግን ከማህበረሰቡ፣ ከጎረቤቱ እና ከቤተሰቡ ጋር ስምምነት የሌለው፤ ሁልጊዜ ችግር የሚፈጥር ከሆነ ጤነኛ ነው ማለት አይቻልም። ለምሳሌ አንድ ወንድ ሚስቱን የሚደበድብ ወይም ደግሞ አንዲት ሴት ባሏንም የምትደበድብ ብትሆን እንደነዚህ አይነት ሰዎችን የዓለም ጤና ድርጅት እንደጤነኛ አድርጎ አይቆጥራቸውም።

የአእምሮ ጤናም ማህበራዊ፣ ሥነልቦናዊ እና መንፈሳዊ ጤንነትን ያጠቃልላል። ለምሳሌ አንድ ሰው ስኳር፤ ደም ግፊት፣ ኩላሊት ወይም ሌላ ህመም ተመርምሮ ምንም አይነት ህመም የሌለበት መሆኑ ቢረጋገጥ ጤነኛ ነው ማለት አይደለም።

የአእምሮ ጤና ምን አይነት ነው?

የአእምሮ ጤና ማለት የማሰብ ፣ የስሜትና የባህሪ ጤንነት ማለት ነው። ማሰብ ሲባል ማሰላሰል፣ ማቀድ፣ የአዲስ ነገር ግኝት፣ ውሳኔ መወሰን ፣ የሚጠቅምና የማይጠቅም ነገርን ለይቶ ማወቅና መረዳት፣ እንዲሁም ከልምድ ተነስቶ ማቀድ እና ከሁኔታዎች ጋር አገናዝቦ ጎጂ ከሆኑት ነገሮች መራቅ፤ ጠቃሚ የሆኑት ላይ ደግሞ መወሰንን የሚያጠቃልል መሆኑን ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ።

ስሜት የሚባለው ደግሞ ኀዘን ፣ደስታ፣ ሳቅ፣ ጨዋታ፣ ለቅሶ፣ ቁጣንና ፍቅርን ሁሉ የሚያጠቃልል ነው። ባህሪ ሲባል ደግሞ ሃሳብ እና ስሜት ኖሮም በተግባር የሚገለጥ ፤ በድርጊት የሚገለጹ ሁሉ ባህሪ ነው። የአእምሮ ጤንነት ሲባልም የእነዚህ ነገሮች ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ በአንድ ሰው ላይ ሲገኙና ሲኖሩ ያ ሰው አእምሮ ጤነኛ ነው ተብሎ ይገለጻል ይላሉ። ከእነዚህ ውጪ የአስተሳሰብ የስሜት ወይም የባህሪ ችግር ከተከሰተ የአእምሮ ጤንነቱ የተጓደለ ሊሆን ይችላል ብሎ መጠርጠርና ማሰብ ይቻላል።

አንድ ሰው የአእምሮ ህመም ሊኖርበት ይችላል ተብሎ እንዲጠረጠር የሚያደርጉ ምልክቶች አሉ። ነገር ግን እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ፕሮፌሰር አታላይ እንዳሉት ፤ አንድ ሰው የአእምሮ ህመም ሊኖርበት ይችላል ተብሎ እንዲጠረጠር የሚያደርጉ አምስት መስፈርቶች አሉ። እነዚህን በማየት የአእምሮ ጤና መኖር አለመኖሩን ለማወቅ ጥረት ይደረጋል። ነገር ግን አንድ ሰው ሌላ ህመም ቢያጋጥመው ህመሙ ምን አይነት ነው ወይም ምኑን ነው ብሎ ለመናገር የሚደረጉ የምርመራ አይነቶች አሉ። በላቦራቶሪ የደም ምርመራ ፤ በኤክስሬይ፤ በኤም አይ አር… ምርመራ ይደረጋል። የተለያዩ ናሙና ተወስዶ ይመረመርና የተለያዩ ምልክቶች ይታያሉ። በዚህ መሠረት ይሄ ሰው እዚህ ቦታ ላይ እንዲህ አይነት ችግር አለበት ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል።

በአብዛኛው የአእምሮ ህመም ግን በእንደዚህ አይነት ምርመራ የሚገኝ አይደለም። ሆኖም ግን እንደነዚህ አይነት ምርመራዎች የሚጠቁሙት ነገር ይኖራል። ለምሳሌ በአካል ህመም ምክንያት የተፈጠረ የአእምሮ ህመም ሊከሰት ስለሚችል የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን መርምሮ ህመሙን ለመረዳት ያግዛል። ነገር ግን በአብዛኛው የአእምሮ ህመም ከህመምተኛው ጋር በሚደረግ ግንኙነት የሚገኘው መረጃ ነው ለአእምሮ ህመም መኖር አለመኖር ጠቋሚ የሚሆነው ይላሉ።

የአእምሮ ህመም ጠቋሚ ምልክቶች

የአእምሮ ህመም ጠቋሚ ምልክቶች ተብለው በዋነኛነት የተለዩት አምስት ናቸው። እነሱም አንደኛ ግለሰቡ በውስጡ የሚሰማው የሥነልቡና መቸገር ፣ መረበሽ፣ መጠበብ፣ አለመረጋጋት ፤ በውስጥ ለግለሰቡ የሚታይ ለሌላ የማይታይ ነገር መኖር፣… የመጀመሪያ መነሻ ነው።

ሁለተኛው ደረጃ በእነዚህ ነገሮች የተነሳ የተለያዩ ድርጊቶችን ማድረግ ነው። ለምሳሌ መደረግ የሌላባቸውን ማድረግ ፤ በሥራ ውጤታማነት ላይ እየተቸገሩ መሄድ ይሆናል። አንድ ሰው በአንድ ቀን በቀላሉ ሲያከናውናቸው የነበሩ ተግባራቶችን ማከናወን ያቅተዋል። የሥራ አፈጻጸሙ ሊቀንስ ወይም ጭራሽ ሊቆም ይችላል፤ ተማሪ ከሆነ መማር ያቅተዋል፣ ገበሬ ከሆነ ማረስ ይሳነዋል …ይሄ ሌላው መለኪያ ነው።

በሶስተኛነት የሚታየው የአእምሮ ህመም ምልክት ደግሞ ማህበራዊ ግንኙነት ነው። እዚህ ላይ ከሰዎች ጋር በሚኖር ግንኙነት ላይ መቸገር ይታያል። ከሰዎች በጣም መሸሽ ፣ ብቸኝነትን መምረጥ ወይም በሰው ጉዳይ አላግባብ መግባት እና ድንበር ያልጠበቀ ግንኙነት መኖር ፤ አልፎ አልፎ ደግም ከሰዎች ጋር መጣላት፣ ቁጡ መሆን ፣ ጮክ ብሎ መናገር የመሳሰሉት የህመሙ ማሳያ ምልክቶች ናቸው። በአጠቃላይ ሰዎቹ ቀደም ሲል ከነበራቸው ማህበራዊ ግንኙነት ወጣ ሲሉ ማለት ነው።

በአራተኛነት የሚታየው ራስን መንከባከብ ወይም መጠበቅ ማቃት፤ ራስን ለማኖር እያንዳንዱ ሰው ጠዋት ተነስቶ የሚያደርገው ነገር አለ። ለጤንነት፣ ለኑሮ፣ ለሕይወታችን የሚሆኑ ተገቢ የሆኑ ነገሮችን ያደርጋል። መደበኛ የሆኑትን ነገሮች ለራሳችን ለአካላችን የሚጠቅሙንን በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረንና ተስማምተን እንድንኖር ማድረግ ያለብንን እናደርጋለን። ይሄ ንጽህና መጠበቅ፣ አለባበስ፣ ጸጉር ማበጠር … የመሳሰሉትን በማህበረሰቡ ተቀባይነት ለማግኘት የሚያስችሉትን ማድረግ ማቃት ሌላው ምልክት ነው። በማህበረሰቡ ውስጥም ይሄን አይነት ምልክት ሲኖር እከሌ እከሊት ራሱን ጥሏል/ጥላለች ይባላል።

አምስተኛው ምልክት ደግሞ በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ባህሪ ማሳየት ነው፤ ቀደም ሲል ያልነበረን ማድረግ ይህም የማንነት መታወቂያ ባህሪይ ሲቀየር ነው። እነዚህ ሁሉ መረጃዎች ተሰብስበው ነው የአእምሮ ህመም አለ የለም የሚለውን ለመወሰን የሚቻለው።

የአእምሮ ህመም ስንት አይነት ናቸው?

ብዙ ጊዜ ሰዎች የአእምሮ ህመምተኛ ብለው የሚያስቡት ወደ ጎዳና የወጡትን፣ ልብስ ያወለቁትን፣ ብቻቸውን የሚያወሩና ንጽህናቸውን መጠበቅ አቅቷቸው ወይም ለየት ያለ ባህሪ የሚያሳዩትን ብቻ ነው። ነገር ግን የዓለም ጤና ድርጅት በሚያወጣው መረጃ መሠረት በአእምሮ ህመም ውስጥ የተጠቃለሉት ወደ 300 የሚደርሱ መሆናቸውን ፕሮፌሰር አታላይ ይጠቅሳሉ። ጽኑ እና ጽኑ ያልሆኑ ተብሎ የአእምሮ ህመም በሁለት ይከፈላል። ጽኑ የሆነ የአእምሮ ህመም የሚባለው ከነባራዊ ሁኔታ ለየት ያለ አስተሳሰብና ሁኔታ ውስጥ ሲገባ ነው። በራስ ዓለም ውስጥ መግባት፤ ሌላው የማይሰማውን ድምጽ መስማት፣ ስለ ራስ ስለ አከባቢና ስለ ዓለም ያለው አስተሳሰብ የተለየ መሆን፤ የራስን ንጽህና አለመጠበቅ ፤ የዓለም ሁሉ ሸክም ነኝ ብሎ ራስን ማሰብ ወይም በተቃራኒው የዓለም ሁሉ ገዢ ነኝ ብሎ ማሰብና በዚህ ላይ ጽኑ እምነት መኖር ነው። ጽኑ ያልሆነ የአእምሮ ህመም ደግሞ ሌሎች መረበሾች ሲኖሩ ነው።

የአእምሮ ህመም መንስኤዎች

የአእምሮ ህመም መንስኤዎች በጣም ብዙ መሆናቸውን ባለሙያው ይናገራሉ። ሆኖም እስካሁን በተካሄዱ በጣም ብዙ ምርምሮች ይሄ ነው የሚባል ተጨባጭነት ያለው ምክንያት ተለይቶ አልወጣም። ሆኖም ግን ተጓዳኝ ምክንያት በሚል የሚጠቀሱት ሶስቱ መለየታቸውን ይጠቅሳሉ። እነሱም ሥነ ሕይወታዊ፣ ሥነልቦናዊ እና ማህበራዊ ምክንያቶች ተብለው ተጠቃለዋል። አሁን አሁን ደግሞ መንፈሳዊም ይታከላል።

ሥነ ሕይወታዊ የሚባሉት በአካል ላይ የሚመጣ አንጎል ላይ የሚከሰት ሲሆን ይሄም የተለያዩ ዕጽ እና አልኮል በመጠቀም የሚመጣ ነው። የአካል በሽታዎች ፣ ከዘረመል ጋር የሚከሰትም አለ።

ማህበራዊ የሚባለው ኢኮኖሚያዊ፣ ድህነት፣ መፈናቀል፣ ስደት ፣ ረሃብ፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ያለ ቀውስ በጠቅላላ ነው። ሌላው ሥነልቦናዊ ሲሆን ከልጅነት አስተዳደግ እና ከሥብዕና ጋር የተገናኙ ናቸው። እንደ አጠቃላይ ግን የአካልን ጤንነት በትክክል መጠበቅ የአእምሮ ጤናንም መጠበቅ መሆኑም ይናገራሉ።

የአእምሮ ህመም በሚመለከት በኢትዮጵያ ውስጥ በከተማ በገጠር በሁሉም ጾታ፤ በሁሉም ስፍራዎች ላለፉት 30 ዓመታት ጥናት መደረሩን ፕሮፌሰር አታላይ ይናገራሉ። በተካሄደው ጥናት መሠረት የተገኘው ውጤት የሚያመለክተውም በተለያዩ ሀገራት የታዩ ችግሮች በእኛም ሀገር መኖራቸው ነው። የአእምሮ ህመም እንደሌሎች የህመም አይነቶች ገዳይ በሽታ አይደለም። ሆኖም ግን ለገዳይ ምክንያቶች ያጋልጣል፤ እድሜንም ይቀንሳል። የአእምሮ ህመምተኛ ሰው የአእምሮ ህመምተኛ ካልሆነው ሰው ከ 10 እስከ 30 ዓመት እድሜው ያጥራል። ጫናን በተመለከተም የኢኮኖሚ ጫናው ድህነት በራሱም ሆነ በቤተሰቡ ብሎም በሀገር ደረጃ ያስከትላል።

የአእምሮ ጤናን በተመለከተ በተለይ በታዳጊ ሀገሮች ውስጥ ገዳይ ለሆኑ የጤና ህመሞች የሚሰጠውን ያክል ትኩረት አይሰጥም። በመሆኑም እንደሀገርም ለአእምሮ ህመም የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው። በዚህም ምክንያት የአእምሮ ጤና የሌለ ይመስላል እንጂ ጫናው ግን ከፍተኛ መሆኑን ነው የሚገልጹት።

አልማዝ አያሌው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You