“ውሃ ህይወት ነው፡፡” የሚለው አባባል አስር ብር ለማግኘት በልቡ አስር ቦታ ለሚሄድ የኔ ቢጤ ድሃ በአስር ብር ከሚሸጥ ግማሽ ሊትር ውሃን የያዘ ፕላስቲክ ላይ እንዳለው አባባል በከንቱ የተባለ ፌዝ እንዳይመስላችሁ፡፡ አባባሉ ትልቅ እውነታ ነው፡፡ ለህይወት ምቹ የምትባለው ፕላኔታችን ምድሯ ሦስት አራተኛ አካሏ የተገነባው ከውሃ ነው፡፡ ስድሳ በመቶ የሚሆነው የደማችን ክፍል ውሃ ሲሆን ከዚህ የተነሳ ይህ የደም ክፍል በአማርኛ “ደመ-ውሃ” የሚል ስም ተሰጥቶታል፡፡ በእንግሊዝኛው “Plazma” ማለት ነው፡፡ ማሰብ እንድንችልና ከእንስሳ እንድንለይ ያደረገን አንጎላችን ከስድሳ አምስት በመቶ በላይ የሚሆነው የተሰራው ከውሃ ነው፡፡ እኛ ራሳችን ሰባ በመቶ የሚሆነው ሥሪታችን ውሃ ነው፡፡
እዚህች ምድር ላይ የሚኖሩ ህይወት ያላቸው ፍጥረታት ሁሉ ዕፅዋት፣ እንስሳትና ሰው በሕይወት እንዲኖሩ ውሃ ግዴታ ነው፡፡ ስልህ! ሁሉም ሰው በህይወት መኖር መተንፈስ ይኖርበታል አይደል፤ ለመተንፈስ ደግሞ ኦክስጅን ያስፈልገዋል፡፡ ታዲያ ሰው መተንፈስ ሳይችል መኖር እንደማይችለው ሁሉ ውሃ በሌለበትም እንዲሁ የሰው ልጅ ከጥቂት ቀናት በቀር በህይወት መቆየት አይችልም፡፡
ለነገሩ ኦክስጅን ራሱ እኮ ውሃ ከተሰራባቸው ንጥረ ነገሮች መካከል አንደኛው ነው፡፡ እናማ “ውሃ ህይወት ነው” ሲባል “እንትና ውሃ” ላይ እንዳለው ለማስታወቂያና ለፕሮፓጋንዳ እንዳይመስላችሁ፡፡ህይወት ሁሉ የተሰራበት ደግሞም ያለ እርሱ መኖር የማይቻልበት ህይወትን ሽጦ ሃብት ለማካበት፣ ትርፍ ለማጋበስ፣ ገበያ ላይ ተወዳጅ ለመሆንና ገዥ ለማግኘት ለማስታወቂያ(ለማጭበርበሪያ) ለጥቅም ታስቦ የሚባል ሳይሆን ስለ ዕውነት ውሃ ህይወት ነው!
ይሁን እንጂ በዓለም የሙቀት መጨመር፣ እየተስፋፋ በመጣው ድርቅ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የውኃ ብክለት ምክንያት ከዓመት ዓመት ቁጥሩ እያሻቀበ ለሚሄደው የዓለም ህዝብ የበቂ ንጹህ ውሃ አቅርቦት እጥረት በዚህ ዘመን እጅግ አስጨናቂ ከሆኑ የሰው ልጆች ፈተናዎች መካከል አንዱ ሆኗል፡፡ እ.ኤ.አ. በ 2015 በዓለም ላይ የግብርና ምርት በመጨመሩ ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የውሃ ፍላጎት በ17 በመቶ ሊጨምር ችሏል፡፡ በተመሳሳይ በመላው ዓለም እየጨመረ በሚሄደው የዓለም ህዝብ ቁጥር የተነሳ በአውሮፓውኑ 2025 የውሃፍጆታ ፍላጎትን በ 40 በመቶ ሊያሳድገው እንደሚችል ተተንብይዋል፡፡
በዚህም ግማሽ የሚሆነው የዓለም ህዝብ ከውሃ ችግር ጋር ተያይዞ ውጥረት በነገሰባቸው አካባቢዎች ለመኖር ሊገደድ እንደሚችል የዓለም የጤና ድርጅት ከአምስት ወር በፊት ያወጣው መረጃ ያመላክታል፡፡ በመሆኑም ይላሉ እዮሃኪም ሃጎፒያን የተባሉ የግሎባል ሪሰርች ጸሃፊ “እስከ ሃያኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ነዳጅ ወሳኙን ሚና ሲጫወት እንደቆየው ሁሉ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ ውሃ እጅግ በጣም ውዱ የዓለማችን የተፈጥሮ ሃብት ይሆናል”፡፡
ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት ከዓመታት በፊት የተባበሩት መንግስታት ንፁህ የመጠጥ ውሃ ማግኘት ዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት መሆኑን ደንግጓል፡፡የዚህ ድንጋጌ ቀጣይ ማስፈጸሚያ የሆነው የዘላቂ ልማት አጀንዳ 2030 በበኩሉ በግብ ቁጥር 6 ነጥብ 1 ላይ “አቅምን ታሳቢ ያደረገ፣ ከብክለት የጸዳ፣ ለጤና ተስማሚ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ለሁሉም ሰው” በማለት ለዓለም መንግስታት ጥሪ አቅርቧል፡፡ በተቃራኒው ይህንን መብት አለመቀበል ወይም ጥሰት መፈጸም ህይወትን እራሷን የመካድ ያህል የሚከብድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደመፈጸም ይቆጠራል፡፡ እናም የሰው ልጆችን በህይወት የመኖር መብት ለማሳጣት ሆን ተብሎ የሚደረግ ማንኛውም ውሳኔ ከግድያ፣ ሰብዓዊነት የሌለው በሰው ልጆች ላይ ከሚፈጸም አሳፋሪ ወንጀል አይተናነስም፡፡
ባለፉት ሠላሳ ዓመታት እጅግ ውድ በሆነው የምድራችን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ በትክክል እየሆነ ያለው ይኸው ነው፡፡ “የዓለም ባንክ በህይወት ለመኖር እጂግ አስፈላጊ የሆነውን ንጹህ የመጠጥ ውሃ የግል ይዞታን በገንዘብ ሲደግፍ ቆይቷል፡፡ ይህም የመጠጥ ውሃን በከፍተኛ ዋጋ ተገዝቶ ካልሆነ በስተቀር ለማግኘት የማይቻል ውድ የግል ንብረት እያደረገው በመሆኑ በዓለም ላይ የሚኖሩ እጅግ በጣም ድሃ ህዝቦች የሚጠጡት ውሃ እንኳን እንዳያገኙ እያደረጋቸው ይገኛል”፡፡ እንደ እርሳቸው ገለጻ በእነኝህ ከመጠን ያለፈ ትርፍን ለማጋበስና ቁሳዊ ሃብትን ለማካበት በሰው ልጆች ህይወትና ደህንነት ላይ ስርቆትና ዝርፊያን በሚፈጽሙ ስግብግብ ኮርፖሬሽኖች ፍጹም ሰብዓዊነት የሌለው አረመኔያዊ ተግባር የተነሳ ድሆች በውሃ ጥም እየሞቱ ነው፡፡
በአየር ብክለት ሳቢያ የሰው ልጅ ለረጅም ጊዜ ሳንባው እየቆሸሸ ቢሆንም፣ የዓለም ሙቀት መጨመር፣ የአየር ንብረት ለውጥንና ሌሎች አስከፊ የተፈጥሮ አደጋዎችን ጨምሮ በሰው ልጆች ላይ እየደረሰ ያለውን ዓለም አቀፋዊ የጤና ችግር ሳይገልጹ ስለ ንጹህ አየር ግንባታ የሚያወሩ “አዛኝ ቅቤ አንጓች” ገንዘብ አምላኪ ቱጃሮች ባለፉት ዓመታት አየርን እንደ ግል ንብረታቸው ቆጥረው እንደ ሸቀጥ አሽገው ለመሸጥና ከፍተኛ ትርፍ ለማግኘት ሲታትሩ ቆይተዋል፡፡
ስግብግቦቹ አሁን ኮምፓሳቸውን ዋነኛው የህይወት መዘውር-ውሃ ላይ አነጣጥረዋል፡፡ “ንጹህ ውሃን ለማዳረስ” በሚል ሽፋን ውሃንም እንደ አየር በፕላስቲክ አሽጎ መሸጥ ላይ በስፋት ተሰማርተዋል፡፡ ይህም የዓለምን ህዝብ ቁጥር አሁን ካለው ሰባት ቢሊዮን ወደ ግማሽ ቢሊዮን ለመቀነስና ቱጃሮች ብቻ ተንደላቀው የሚኖሩባት፣ ድህነት፣ ረሃብና በሽታ የሌለባት ዓለምን ለመፍጠር ሌት ተቀን እየለፉ የሚገኙ “ሉላውያን” አጀንዳ ነው፡፡
ይህም ማለት ይላሉ ሃጎፒያን “ይህ ማለት በእነዚህ የጥቂት ሃብታሞች ብቻ የሆነች ዓለም ለመመስረት የሚፈልጉ እኩያን ሰይጣናዊ ዕቅድ መሰረት አሁን ካለው የዓለም ህዝብ መካከል ከየ አስራ አራት ሰዎች ስብስብ አስራ ሦስቱ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ መሞት አለባቸው፡፡” እናም የህዝብ ቁጥርን በፍጥነት ለመቀነስ ለሰው ልጆች ህይወት እጀግ አስፈላጊ በሆነው የምድራችን ውስን የውሃ አቅርቦት ላይ ሙሉ ባለቤትነት እና ቁጥጥር ከመውሰድና የሰውን ልጅ በገፍ እንዲያልቅ ከማድረግ ምን የተሻለ መንገድ ይገኛል፡፡
ልዩ ልዩ ጥናቶችና መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ከሆነ በዓለም ላይ እስከ ዛሬ ድረስ በተደረጉ ጦርነቶች ከሞቱት ሰዎች ይልቅ በአሁኑ ሰዓት በውሃ ወለድ በሽታዎች ምክንያት እየሞተ ያለው የህዝብ ቁጥር ይበልጣል፡፡ ከንጹህ ውሃ እጥረት ጋር በተያያዘ በዓለም ላይ በያንዳንዷ ሰዓት 240 ህጻናት ይሞታሉ፡፡ በንጽህና ጉድለት ሳቢያ በየዓመቱ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ህጻናት በኮሌራና በታይፎይድ በሽታዎች ይሞታሉ፡፡እነኝህ የማይታመኑ የሚመስሉ አሳዛኝና አስደንጋጭ ሃቆች በምድር ላይ በህይወት ለመቆየት የንጹህ ውሃ አቅርቦት ምን ያህል ወሳኝና አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡
ታዲያ እንደ ጸሃፊው ገለጻ እነኝህ የፕላኔቷን ንጹህ ውሃ በመቆጣጠር የህዝብ ብዛትን በፍጥነት ለመቀነስና የምድርን ሃብት በብቸኝነት ጠቅለው ለመያዝና በጥቂት ቱጃሮች አገዛዝ ሥር የዋለች “አዲስ ዓለም”ን ለመመስረት እየተሯሯጡ ያሉ የኮርፖሬት ኃይሎች ዓላማቸውን ለማሳካት የሚከተሉት ስልት ውሃን ከተፈጥሮ ስጦታነት አውጥተው በግል ንብረትነት የሚያዝ የንግድ ሸቀጥ በማድረግ ነው፡፡ ያኔም ውሃ ለሁሉም ሰው በነጻ የተበረከተ የእግዜር ስጦታ መሆኑ ይቀርና ጥቂት የናጠጡ ቱጃሮችና የዓለምን መዋዕለ ንዋይ የሚያንቀሳቅሱ ታላላቅ ባንኮችና ኮርፖሬሽኖች ብቻ ሊገዙት የሚችሉ የቅንጦት ዕቃ ይሆናል፡፡ በእኛም አገር እየሆነ ያለው ከዚህ የሚተናነስ አይደለም፡፡
ጉዞ ለማድረግ አውቶቢስ ተራ ሰባተኛ አቅንቼ ነበር፡፡ በዚያም በአንድ ምግብ ቤት ውስጥ ከጓደኛዬ ጋር ምግብ አዘን ተቀመጥን፡፡ መቼም ያለ ውሃ ምግቡም ከጉሮሮ መውረድ አይችልምና አስተናጋጁን ጠርተን ውሃ አምጣልን ስንለው፤ “ውሃ የለችም” አለን፡፡ ታዲያ መታነቅ የለብንምና ግዴታ ስለሆነብን አቅማችንን አይተን ለእያዳንዳችን ግማሽ ሊትር የታሸገ ውሃ እንዲያመጣልን ነገርነው፡፡ መጨረሻ ላይ ሂሳቡ ሲሰላ ስንት ቢሆን ጥሩ ነው? አንዱ ግማሽ ሊትር ውሃ አስር ብር፤ ለሁለቱ ማለትም ለአንድ ሊትሩ ውሃ ሃያ ብር፡፡
አስቡት አሁን ጽሁፍ እያዘጋጀሁ ባለሁበት ወቅት ከሁለት ቀናት በፊት የአፍሪካ የውሃ ማማ በሆነችው የአፍሪካ መዲና ላይ አንድ ብርጭቆ ውሃ አስር ብር ሲሸጥ፤ ለዚያውም ሳንፈልግ በግዴታ፡፡ አስገድደው ሲሸጡልን፤ ይህ ከአስገድዶ ከመድፈር በምን ይሻላል? ታዲያ ይኼ በእርግጥም ውሃም የብዙሃኑ መሆኑ ቀርቶ እንደ ውስኪ የሃብታሞች ብቻ ወደ መሆን እየተሸጋገረ አይደለም ትላላችሁ? እውነቴን እኮ ነው፡፡ እስኪ እኔስ የመንግስት ሰራተኛ በመሆኔ ቢያንስ ድሃ በሚለው ምድብ ውስጥ ስለሆንኩ እንደምንም ብዬ ግማሽ ሊትር ውሃ በአስር ብር ገዝቼ ጠጣሁ፡፡ ቆይ ከእኔ ያነሰ ገቢ ያላቸውስ፤ ማለቴ ይች አገር እኮ ከድሃም ያነሰ “የድሃ ድሃ” የሚባሉ ዜጎች የሚበዙባት አገር ናት፡፡ ታዲያ ቢቀር ቢቀር ውሃም “ጥቁር ውሃ”ም ይወደድብን እንዴ?
እናም “ያልጠረጠረ ተመነጠረ” እንዲል የአገሬ ሰው እዮሃኪም ሃጎፒያን እንደሚሉት የእኛዎቹ ውሃ ሻጭ ቱጃሮችም የዓለም አቀፉ “ውሃን በሞኖፖል የመያዝ” ሰይጣናዊ ሴራ አካል እንዳልሆኑ በምን እርግጠኛ እንሆናለን፡፡ ውሃን በግል ይዞታ ስር የመቆጣጠርና የህዝብ ቁጥርን በፍጥነት የመቀነስና ዓለምን ለራሳቸው ብቻ በሚመች መልኩ አፍርሶ ለመስራት ከመጋረጃው በስተጀርባ እየተካሄደ ያለው የሰይጣናውያን አጀንዳ የኃያላን አገራት መንግስታት ድጋፍም ያለው መሆኑንም እኮ ተንታኙ እየተናገሩ ነው፡፡ እናም ተራው የዓለም ህዝብ በአንድነት ሆ ብሎ ተነስቶ ካልተቃወመውና ካላስቆመው በስተቀር በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕቅዳቸው እንደሚሳካ እየተነገረ ነው፡፡
በዚህ ረገድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ላይ የውሃን የግል ይዞታነት የሚቃወሙ ድምጾች እየተበራከቱ መምጣታቸው የመጥፋት አደጋ ለተጋረጠበት ብዙሃኑ የዓለማችን ምስኪን ህዝብ መልካም ዜና ነው ይላሉ እዮሃኪም ሃጎፒያን፡፡ ዓላማቸውም ይኸው ነው-የውሃ አቅርቦት በእነሱ ቁጥጥር ሥር ይውላል፣ ገንዘብ የሌለው ብዙሃኑ ድሃ የሚጠጣው ውሃ ስለማያገኝ በውሃ ጥም፣ የሚታጠብበትና ንጽህናውን የሚጠብቅበት ውሃ ስለማይኖረው በወረርሽኝ በሽታ እንዲያልቅ ማድረግ፤ ከዚያም እንደተመኙት “በሃብታሞች፣ ለሃብታሞችና የሃብታሞች ብቻ የሆነች አዲስ ዓለም መፍጠር(Realizing their dream of creating the New World Order)”!
ለዚህም ከሁለት ዓመት በፊት የዓለም ባንክ ዓመታዊ ጉባኤውን በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ባካሄደበት ወቅት ከህንድና ከአሜሪካ የተውጣጡ የውሃ የግል ይዞታን የሚቃወሙ ፀረ ኮርፖሬታውያን ዓለም አቀፍ ጥምረቶች “የዓለም ባንክ በታዳጊ አገራት ላይ በልማት ስም ውሃ በግል ይዞታ ሥር እንዲውል የሚያደርገውን ዘመቻ እንዲያቆም እንጠይቃለን” በማለት በግልጽ ደብዳቤ መጠየቃቸውና ለዓለም ህዝብ መልዕክት ማስተላለፋቸው አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ምክንያቱም እንደ እርሳቸው አባባል በዓለም ባንክ ስር የሚተዳደረው “ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን” በያመቱ በርካታ ሚሊዮን ዶላሮችን በብድርና በርዳታ መልክ የሚሰጥ በተለይም በድሃ አገራት የውሃን የግል ይዞታነት ለማስፋፋት ለሚካሄዱ ፕሮጀክቶች በዓለም ላይ ትልቁ የገንዘብ ምንጫቸው ነው፡፡
እናም ብዙሃኑ ድሃ ህዝብ ኮርፖሬታውያኑ ከቃጡበት ጥፋት ራሱን በፍጥነት መታደግ ከፈለገ ከላይ እንደተጠቀሱት የህንድና የአሜሪካ የጋራ ጥምረት አባላት በንቃት ሊታገል ይገባል፡፡ ሰፊው ህዝብ እንዲህ በአንድነት ሆ ብሎ ከተነሳና ከተባበረ ደግሞ ለሰው ልጆች ህይወትና ደህንነት ሁሌም ከኮርፖሬታውያኑ ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው እኩይ ሴራቸውን በድፍረት እያጋለጡና በፅናት እየታገሉ የሚገኙት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት አርበኞችና የመብትና የደህንነት ተሟጋቾች ከጎኑ ናቸው፡፡ እናም የቀድሞው የጦር መኮንን ሚስተር ኢዮሃኪም ሃጎፒያን ግሎባል ሪሰርች ላይ በጻፉት ጽሁፋቸው “ምስኪኑ ድሃ ወገኔ ሆይ ራስህን ለማዳን ጊዜው አሁን ነው፡፡ በተባበረ ክንድህ ፈጥነህ የሰይጣናውያኑን የጥፋት ሴራ አክሽፍ!” የሚል የህይወት አድን ጥሪ ለዓለም ህዝብ ያስተላልፋሉ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 6/2012
ይበል ካሳ