በዘመነ መሳፍንት ተከፋፍሎ የነበረውን የኢትዮጵያ ግዛት አንድ በማድረግ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ የተወለዱት ከዛሬ 201 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 6 ቀን 1811 ዓ.ም ነበር።
በትውልድ ስማቸው ካሳ ሀይሉ፤ በፈረስ ስማቸው አባ ታጠቅ፤ በጦር ሜዳ ውሏቸው መይሳው ካሳ ተብለው የሚጠሩት አጼ ቴዎድሮስ በ1811 ዓ.ም ከአባታቸው ደጃዝማች ሃይሉ ወልደ ጊዮርጊስና ከእናታቸው ወይዘሮ አትጠገብ ወንድወሰን ከጎንደር ከተማ ደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ በምትገኘው ዳዋ ቀበሌ ተወለዱ።
አባታቸው ከሱዳን ጋር በተደረገ ጦርነት ሲያልፉ ፣ ወይዘሮ አትጠገብ በ1813 ዓ.ም ህጻኑን ቴዎድሮስ ይዘው ወደ ተወለዱበት ጎንደር ከተማ ተመለሱ። ወይዘሮ አትጠገብ ባለቤታቸው እንደሞቱ ቆርበው ስለነበር ሌላ ልጅ አልወለዱም። ቴዎድሮስ አንድ ለናቱ የተባሉት በዚህ ምክንያት ነው። ጳውሎስ ኞኞ አጼ ቴዎድሮስ በተሰኘ መጽሐፉ ወይዘሮዋ የጎንደር ባላባት ዘር ናቸው እንጂ በታሪክ እንደሚታወቀው ኮሶ ሻጭ አልነበሩም። ነገር ግን ጠላቶቻቸው አፄ ቴዎድሮስን ለማዋረድ የኮሶ ሻጭ ልጅ ሲሉ እንደጠሯቸው ጽፏል።
ካሳ በህጻንነታቸው የቄስ ትምህርት ከቀሰሙ በኋላ፣ የአጎታቸውንና በኋላም ለጥቂት ጊዜ የጎጃሙን ጦር መሪ የጎሹ ዘውዴን ጦር ተቀላቀሉ። በዚሁ የውትድርና ዘመናቸው ጀግንነታቸውን ስላስመሰከሩና ዝናቸው ስለተስፋፋ በ1839 ዓ.ም የራስ አሊ አሉላ ልጅ ተዋበች አሊ ተዳሩላቸው። በኋላም በደጃዝማችነት ማዕረግ የቋራ አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ። ለካሳ ይህ በቂ አልነበረምና በ1844 ዓ.ም አጠቃላይ የዘመነ መሳፍንት ሥርዓትን በመቃወም በሰሜናዊ ባላባቶች ላይ ዘመቻ ጀመሩ።
ካሣ በራስ ዓሊ ሥልጣን ሥር የሚተዳደሩትን የዘመነ መሣፍንት የአካባቢ ገዥዎችን ተራ በተራ ድል በማድረግ ከፍተኛ ተሰሚነትና ዝና አተረፉ። በመጨረሻ ከራስ ዓሊ ጋር ውጊያ ለማድረግ የጦርነቱ ቀንና ቦታ ተቆረጠ። የጦሩ አውድማ “አይሻል”፣ የግጥሚያው ቀንም ሰኔ 23 ቀን 1846 ዓ.ም ሆነ። በጦርነቱ ሁለቱም ወገኖች የሞት የሽረት ፍልሚያ ስላደረጉ ከፍተኛ የሆነ ደም መፋሰስ ሆነ። ከሁለቱም ጎራ ጀግኖች ወደቁ። የማታ ማታ ድሉ ግን የካሣ ሆነ። ዓፄ ቴዎድሮስ አንድ ለማድረግ የሞከሩት ሰሜናዊውን የኢትዮጵያ ክፍል ብቻ አልነበረም። ወደ ወሎና ሸዋ ያደረጓቸው ዘመቻዎች በታሪክ የሚታወቀውን አጠቃላይ የኢትዮጵያ ክፍል አንድ ለማድረግ ለመነሳታቸው አስረጅዎች ናቸው።
ካሳ ሃይሉ የካቲት 11 ቀን 1847 ዓ.ም ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብለው ዘውድ ጫኑ ፣ ስማቸውም ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ተባለ። የዙፋን ስማቸውን የመረጡት ከፍካሬ እየሱስ ሲሆን ይህ መጽሃፍ የሚያትተው ስለሚመጣው አለምና በ15ኛው ክፍለ ዘመን ስለነበረው በኢትዮጵያውያን ዘንድ እጅግ ተወዳጁ የነበረ ንጉስ ቀዳማዊ አጼ ቴወድሮስ ስርዓት እንደገና በኢትዮጵያ መንሰራፋት ነበር። ይሄው የጥንቱ ንጉስ በጥንቶቹ ኢትዮጵያውን ዘንድ ተወዳጅ ንጉስ ነበር። ከሰራቸው ስራዎች አንዱ ከይኩኖ አምላክ ጀምሮ ለቤተክርስቲያን ሲወርድ ሲዋርድ የመጣውን የቤተክርስቲያን መሬት ለገበሬዎች ማከፋፈሉ ነበር። በፍካሬእየሱስ መሰረት፣ ቀዳማዊ ቴዎድሮስ እንደገና ከሞት ይነሳና ፍትህና ሰላም አስፍኖ “ሁሉም ከሚፈጠረው ደስታና ሰላም ተካፋይ” ሚሆንበት ግዛት ያንሰራፋል።
በ1830ዎቹ የዘመነ መሳፍንት ጦርነቶች በተሰቃየው ህዝብ ዘንድ ይህ የ ፍካሬ እየሱስ ትንቢት ከመንደር መንደር የገነነ ነበር። አጼ ቴዎድሮስ፣ ይህ “የአገሪቱን የታሪክ አቅጣጫ የሚቀይር” የሚመጣው ንጉስ ነኝ ብለው ያምኑ ነበር። ቴዎድሮስ የሚለው ስያሜ ጣዎስ ድሮስ ከሚል የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም የአምላክ ስጦታ ማለት ነው።
አጼ ቴዎድሮስ 1852 ዓ.ም የቤተ ክርስቲያንን መሬት በከፊል ለገበሬወች አከፈፋሉ። ይህም በፍካሬ እየሱስ ላይ እንደተጠቀሰው ቀዳማዊ ቴዎድሮስ ስራ ነበር። በዚሁ አመት የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ከሁለት ቄሶችና ሶስት ዲያቆኖች በላይ እንዳይሆን ደነገጉ። በተጨማሪም ደብተራነትን ከነአካቴው ለማጥፋት እንዳሰቡ ገለጹ። በዚህም ከቤተ ክርስቲያን ጋር ቅራኔ ውስጥ ገቡ።
በ1850ዎቹ ንግሡ በዛ ያሉ አመጾችን በትግራይና በበጌምድር አስተናግደዋል። ታህሳስ 1852 ዓ.ም የሰሜኑ ክፍል አመጽ ዋና አዛዥ የነበረውን አገው ንጉሴን ወግተው ገድለዋል። በ1857 መቅደላ ያደገው ወጣቱ ምኒልክ ከመቅደላ አምልጦ ሸዋ በመግባት የግዛቱን ነጻነት አወጀ። ትግራይም እንዲሁ በካሳ ምርጫ ስር ሆነ። ከ1858 እስከ 1859 ዓ.ም ንጉሱ የተለያዩ ኃይሎችን ለመቆጣጠር ብዙ ዘመቻዎችን አካሄዱ። በዘመቻዎቹ ብዙ ወታደሮች ከንጉሱ እየከዱ አመለጡ። የንጉሱ በጣም ጠንካራ ወታደራዊ ዲሲፕሊን ብዙዎቹ ወታደሮች እንዲከዱ አደረገ። ባንድ ወቅት የአጼው ሰራዊት ከመቶ ሺህ በላይ የነበር ሲሆን በ1858 ከአስር ሺህ ብዙ አይበልጥም ነበር። በ1859 ዓ.ም በንጉሱ ሙሉ ቁጥጥር ስር የነበረ አካባቢ ቢኖር በጌምድር ነበር ። ጥቅምት 1860 ላይ ቴዎድሮስ ደብረታቦርን አቃጥለው ወደ መቅደላ በመሄድ እስከ እለተ ሞታቸው ድረስ ኑሮአቸውን በዚያ አደረጉ። በአገሪቱ የነበረው የተቃውሞ መጠን ከማየሉ የተነሳ አጼ ቴዎድሮስ ከደብረታቦር መቅደላ ባሰሩት መንገድ እንኳ በሰላም መንቀሳቀስ ስላልቻሉ በመቅደላ ተወሰኑ።
በውጭ አገር የሰሙት ስልጣኔ በአገራቸው እንዲስፋፋ በመመኘት ይሄው ህልማቸው እንዲሳካ ለእንግሊዟ ንግስት ቪክቶሪያ ደብዳቤ የጻፉት ቴዎድሮስ ለጻፉት ደብዳቤ አንድ አመት ሙሉ መልሱን ሲጠባበቁ ቢቆዩም ምንም መልስ ባለማግኘታቸው ተቆጥተው ጥር አራት ቀን 1856 ዓ.ም የእንግሊዝ የዲፕሎማቶችን በመቅደላ አሰሩ።
የእንግሊዝ መንግስት እስሩን ተከትሎ በላከው ደብዳቤ እስረኞቹ እንዲፈቱና ይህ ሲሆን እርዳታ እንደሚሰጥ አስታወቀ። በዚህ መልስ ያልረኩት አጼ ቴዎድሮስ መልዕክተኛውን አሰሩ። የመልዕክት ልውውጡ ቀጥሎ ጥር 1859 ላይ ንጉሰ ነገሥቱ እስረኞቹን ፈተው ወደ ምጽዋ ከተወሰዱ በምትኩ የእንግሊዝ መንግስት ወታደራዊ እርዳታ እንደሚያደርግ ደብዳቤ ከእንግሊዝ መንግስት ደረሳቸው። በዚህ ወቅት ንጉሰ ነገሥቱ በማያባራ ዘመቻና አመጽ ተጠምደው ስለነበር ከመቅደላ ምጽዋ ያለውን መንገድ መቆጣጠር አይችሉም ነበር። ስለዚህ ሚያዝያ 1859 ከእንግሊዝ ለደረሳቸው ዛቻ መልስ ሳይሰጡ ችላ አሉት።
የእንግሊዝ መንግስትም እስረኞቹን ለማስፈታት ዘመቻ ለማድረግ ወሰነ። ነሐሴ 1859 እንግሊዞች በ ሮበርት ናፒየር የሚመራ 32 ሺ ጦር ሰራዊት አዘመቱ። እንግሊዞቹ በዚህ ወቅት ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በቂ መረጃ ነበራቸው። የቴዎድሮስ ሰራዊት በ1859 ከ5 እስከ 10 ሺ የሚገመት ነበር። ንጉሰ ነገሥቱ ፣ከናፒየር ሰራዊት ሁለት ሳምንት ቀድመው ጥቅምት 1860 ላይ መቅደላ ደርሰው ነበር። የእንግሊዝ ሠራዊት ምጽዋ ላይ አርፎ በቂ የመጓጓዣና የምግብ እርዳታ ከካሳ ምርጫ በማግኘት ያለ ችግር ወደ መቅደላ ተመመ።
በአጼ ቴዎድሮስ ሰራዊትና በናፒየር ሰራዊት መካከል ውጊያ ተካሄደ። በጦርነቱ የኢትዮጵያ ሰራዊት ተሸንፎ አፈገፈገ። ጦርነቱ በተካሄደበት ቀን ማግስት ናፒየር ለቴዎድሮስ በጻፈው ደብዳቤ ንጉሡ እስረኞቹን ከፈቱና ለእንግሊዟ ንግሥት እጅ ከሰጡ በክብር እንደሚያዙ አሳወቃቸው። ንጉሰ ነገሥቱ ይህን አይነት ውርደት እንደማይቀበሉ ለናፒርየር በደብዳቤ አሳወቁ።
ሚያዚያ 6 ቀን ሦስት ሰዓት ላይ እንግሊዞች በመቅደላ ምሽግ ላይ መጨረሻ ጥቃት አደረሱ። ንጉሱ፣ የሃይል ሚዛኑ ወደ እንግሊዞቹ ሙሉ በሙሉ አንዳጋደለ ከንግስት ቪክቶሪያ በተላከላቸው ሽጉጥ በገዛ እጃቸው በጀግንነት አለፉ።እንግሊዞች ምሽጉን ሲሰበር ንጉሱ ሞተው ስላገኟቸው እጅጉን ተናደው መቅደላ እንዲመዘብርና የተረፈው በእሳት እንዲጋይ አደረጉ። ሚያዚያ 18 ቀን 1860 ዓ.ም እንግሊዞች አገሩን ለቀው ወጡ። የአጼ ቴዎድሮስን ህልፈት ተከትሎ በወቅቱ ከተገጠሙት ግጥሞች አንዱ ተከታዩ ነው።
መቅደላ አፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ
የሴቱን አናውቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ
የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ የአጼ ቴዎድሮስ 150ኛ ዝክር በዓል በሚከበርበት ወቅት ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ ስለ ንጉሡ ተከታዩን ብለዋል።
“አፄ ቴዎድሮስን እንደ ገፀ ባህሪ ካየነው የሚስብ ነው። ከምንም ተነስቶ ነው አገር እስከ መምራት የደረሰው። እሱም ከትቢያ አንስቶኝ ነው የሚለው። በንግግሮቹና ለተለያዩ ጉዳዮች በሚፅፋቸው ደብዳቤዎች መጨረሻ ላይ በተደጋጋሚ “በእግዚአብሔር ኃይል” ይላል። በእንግሊዝኛው “A man of Destiny” ወይም ለአንድ ትልቅ ነገር የታጨ ሰው መሆኑ ይሰማው ነበር። በዚያ ሁኔታና ራዕይ ይንቀሳቀስ የነበረ ሰው ነው። ሁለተኛውና ዋናው ጉዳይ የተነሳባቸው አላማዎች ፣ ቋሚ የሆኑ አላማዎች ናቸው። … አፄ ቴዎድሮስ አነሳሱም አወዳደቁም እንዳይረሳ ያደርገዋል።
ኢትዮጵያን አንድ አደርጋለሁ ብሎ የተነሳ አንበሳ ፤ የማታ ማታ ሁሉ ነገር ከሽፎበት ብቻውን ምድረ በዳ ላይ መሽጎ ፣ በመጨረሻ ራሱን መሰዋቱ ህይወቱን በድራማ የታጀበ ያደርገዋል። …ቴዎድሮስ ትልቅ ራዕይ ቢያነግብም ራዕይና ህልሙን እውን ለማድረግ ትዕግስትና ሆደ ሰፊነት ይጎድለዋል። ያነሳው አላማ ከባድ ነው። የዓላማውን ከባድነት መረዳት ነበረበት ነው የምለው። ከባድነቱን እሱ ተረድቶ አንዳንድ ሰዎች ካልተረዱም ለማስረዳት የሚችልበትን ስልት መፈለግ ነበረበት እንጂ አንተ ካልተረዳህ ፣ ያሰብኩትን የማትቀበል ከሆነ … እያለ መግደልና ማስወገድ አልነበረበትም።”
ቴዎድሮስ ከእቴጌ ተዋበች ዓሊ በፊት አቶ እንግዳወርቅ የተባሉ በሽፍትነት የታወቁ ሰው ልጅ ወይዘሮ ገሠሠች እንግዳወርቅ የተባሉትን አግብተው መሸሻ ካሣና አልጣሽ ካሣን ወልደዋል። በኋላ ላይም ከቤተ መንግሥቱ ጋር የጋብቻ ዝምድና የመሠረቱባትን ተዋበች ዓሊን አግብተዋል። ተዋበች በሞት ሲለይዋቸው የደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያምን ልጅ እቴጌ ጥሩወርቅን አግብተዋል። በተጨማሪም በዘመኑ ባህል በርካታ ቅምጦች (ቁባቶች) እንደነበራቸውው የተለያዩ መረጃዎች ያስረዳሉ።
ቴዎድሮስ ከሕግ ሚስታቸው ከጥሩወርቅ በናፒየር ጦር እንግሊዝ አገር ተወስዶ ከዚያው በዘመድ ወገን ልልት የሞተውን ልዑል ዓለማየሁ መውለዳቸው ይታወቃል። በአጠቃላይ ቴዎድሮስ ራስ መሸሻ ፣ ልጅ ኃይሉ ፣ ልጅ ተሰማ ፣ ልጅ ይማም እና ወይዘሮ አልጣሽ የተባሉ ልጆች ወልደዋል። ሆኖም በታሪክ ተጠቃሽ በመሆናቸው በጉልህ የሚታወቁት ልጆቻቸው ዓለማየሁ ፣ መሸሻና አልጣሽ ናቸው። የዚህም ምክንያቱ ዓለማየሁ ምርኮኛ ሆኖ ተወስዶ በዚያው መሞቱና ታሪኩ ለታሪክ ጸሐፊዎች ቅርብ መሆኑ ነው። መሻሻ በዳግማዊ ምኒልክ ራስ ተብለው፣ በእርሳቸው ዘመን ከነበሩት መኳንንቶች አንዱ መሆናቸውና ልጃቸው ደጃዝማች ካሣ መሸሻ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በጎንደር ከነበሩት መኳንንቶች አንዱና የስመ ጥር ልጆች ወላጅ መሆናቸው ነው። አልጣሽ ደግሞ የዳግማዊ ምኒልክ የመጀመሪያ ሚስት ነበሩ።
አዲስ ዘመን ጥር 6/2012
የትናየት ፈሩ