ክፍል አንድ
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
የሞት ቅጣት ከኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አውድ ውስጥ መወገድ አለበት ወይስ የለበትም? የሚለው እሰጥ አገባ አንድ ጊዜ ሞቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቀዝቀዝ እያለ ነው የሚደመጠው።
የሞት ቅጣት ከአገራት ሕጎች እንዲፋቅ እንዲሁም ሥሙ እስኪደመሰስ ድረስ የሞት ቅጣት ያጸደቁ አገራት ሕጎቻቸውንና ያስተላለፏቸውን የሞት ቅጣት ውሳኔዎች እንዳይፈጸሙ እገዳ እንዲጥሉባቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጠናከረ ንቅናቄ ይካሄዳል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ ያገባናል ባዮችና አገራት ሳይቀሩ የንቅናቄው ደጋፊዎች ናቸው። በየዓመቱም ዓለም-አቀፍ ጸረ-የሞት ቅጣት ቀን በተለያዩ መርሃግብሮች ይከበራል።
በአንጻሩ በኢትዮጵያ የሞት ቅጣት ከአገሪቱ ሕግ እንዲነቀል የሚሞግት የተደራጀ አካል የለም። በጉዳዩ ዙሪያ ነባራዊ፣ ሕጋዊ፣ ዓለም-አቀፋዊና ያለንበትን ዘመን በዋጀ መልኩ ጠንካራ አመክንዮዎችን በማንሳት የፖሊሲ አውጭዎች አጀንዳ እንዲሆን የሚያደርግ ሃሳብም ሲፈልቅ አይስተዋልም።
በዚህም ምክንያት የሞት ቅጣት በኢትዮጵያ ሕጎች ውስጥ የያዘውን ጠንካራ ወንበር መነቅነቅ የማይታሰብ ሆኗል። በረዥሙ የአገራችን የመንግስትነትና የሕግ ታሪክ ውስጥ የተቆናጠጠውን ጠንካራ ይዞታ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም አስጠብቆ ቀጥሏል። ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያው በቅርቡ የተሰናዳው በሰዎች የመነገድ ረቂቅ አዋጅ የሞት ቅጣትን ማካተቱ ነው።
እኛም ይህንኑ ሰበብ በማድረግ በአጠቃላይ ከኢትዮጵያ ሕግ ውስጥ የሞት ቅጣት ሊፋቅ ይገባል አይገባም የሚለውን እንዲሁም በአዋጁ ውስጥስ መካተቱ አስፈላጊ ነው ወይስ አይደለም በሚለው ላይ ትኩረታችንን በማድረግ በዚህና በቀጣዩ ሳምንት ጽሁፋችን ሞጋች ሃሳቦችን እናቀርባለን።
በሰዎች የመነገድ የሕግ ማዕቀፍ
በሰዎች መነገድ፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርና ሕገ-ወጥ የሥራ ሥምሪት ወንጀሎች ተያያዥና ሰፋፊ ጉዳዮች ናቸው። በአገራችን እነዚህን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች አሉ።
የመጀመሪያው ሕገ መንግስቱ ሲሆን፤ ማንኛውም ሰው በባርነት ወይም በግዴታ አገልጋይነት ሊያዝ እንደማይችል እንዲሁም ለማንኛውም ዓላማ ቢሆን በሰው መነገድ የተከለከለ መሆኑን በአጽንኦት አስቀምጧል።
በሰዎች መነገድ በተለይም የሴቶችና ሕጻናት ዝውውር ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ወንጀል ፈጻሚዎችን ለመቅጣት እንዲሁም ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ በየብስ፣ በባህርና በአየር ማስወጣትና ማስገባት ለመከላከል የወጡትን ዓለም አቀፍ ፕሮቶኮሎችንም በአዋጆች አጽድቃለች።
የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ ሰውን አገልጋይ ማድረግን፣ በሴቶችና በሕጻናት መነገድን፣ ሴቶችንና ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን ለዝሙት አዳሪነት በማቃጠር መነገድን፤ በሕገ-ወጥ መንገድ ኢትዮጵያውያንን ለሥራ ወደ ውጭ አገር መላክንና ሌሎችንም ድርጊቶች ደንግጓል። የዜጎችን የውጭ አገራት የሥራ ሥምሪትን የተመለከቱ አዋጆችም ወጥተዋል፤ ሥምምነቶችም ተፈርመዋል።
ከእነዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጉዳዩ አሳሳቢ በመሆኑ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደተኞችን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያለመ አዋጅ ቁጥር 909/2007 ወጥቷል።
እንደሚታወቀው በሰዎች መነገድም ሆነ ሰዎችን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎች በአብዛኛው በተደራጁ የወንጀል ቡድኖችና ድንበር ተሻገሪ በሆነ ሁኔታ ስለሚፈጸም እንዲሁም በቢሊዮኖች ዶላር ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት በመሆኑ አፈጻጸሙ ውስብስብ፣ አስከፊና አደገኛ ነው።
በዚሁ መነሻ አገራት በጋራ ከሚያደርጉት ጥረት በተጨማሪ በየግላቸው የሚዘረጓቸው የሕግ ማዕቀፎች በዚያው ልክ ጠንካራና ለችግሩ ስፋት፣ ጥልቀትና ውስብስብነት የሚመጥን ምላሽ የሚሰጡ መሆን አለባቸው።
ይሁንና ከላይ የጠቃቀስኳቸው የአገራችን ሕጎች አንዳቸውም የሚመጥን ምላሽ የመስጠት አቅም የላቸውም። በተለይም አዋጅ ቁጥር 909/2007 በቂና ግልጽ ካለመሆኑም በላይ ከሥያሜው ጀምሮም ሆነ በውስጡ ያካተታቸው የወንጀል ድንጋጌዎች እንዲሁም የመከላከልና የመቆጣጠር አቅጣጫዎቹ መሰረታዊ ችግሮች ነበሩበት።
አዋጁ ምንም ሳይተገበር ለማለት በሚቻል ደረጃ ለሥም ብቻ ከአገሪቱ አዋጆች ተርታ ተሰልፎ ዓመታትን አስቆጥሯል። በተለይም በዚህና በተከታዩ ጽሁፍ ለመዳሰስ እንደምንሞክረው የወንጀል ድንጋጌዎቹ በሕጸጽ የተሞሉ በመሆናቸው የወንጀል ምርመራ ለማድረግ፣ ክስ ለማቅረብና ተከራክሮ ለማስቀጣት እንቅፋት ሆኗል። እናም መንግስት ዘግይቶም ቢሆን ሕጉን በማሻሻል ረቂቅ ሕግ ለፓርላማው አቅርቧል።
በሰዎች መነገድ ምንድን ነው?
ነባሩ አዋጅ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደተኞችን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ ነው። ይህ በሥያሜ ረገድ በተለይም “ስደተኞችን” የሚል ቃል በመጠቀም ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ሰደተኛ ያልሆኑ ሰዎች የችግሩ ሰለባ ቢሆኑ የማይመለከት ሆኖ መውጣቱ ችግር ፈጥሯል።
በመሆኑም ረቂቅ ሕጉ “በሰው የመነገድና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ” በሚል ነው የተሰናዳው። ረቂቅ አዋጁ የተለያዩ ክፍሎች አሉት። ከእነዚህ ውስጥ ዋነኛው የወንጀል ድርጊቶችን የተመለከተው ሲሆን፤ ወንጀሎቹ በሶስት ዓበይት ዘውጎች ተከፍለዋል።
እነዚህም በሰዎች መነገድ፣ ሰዎችን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና ህገ-ወጥ የውጭ አገር የስራ ስምሪት ወንጀሎች ናቸው። በእነዚህ ሥርም የተለያየ ቅጣትን የሚያስክሉ ዝርዝር ወንጀሎች ተቀምጠዋል። ተያያዥ ወንጀሎች በሚል አርዕስት ሥር ደግሞ ወንጀልን አለማስታወቅ፣ በወንጀል ጠቋሚዎችና ምስክሮች ላይ ወንጀል መፈጸም፤ ማስረጃን ማጥፋት፣ ተጠርጣሪ እንዳይከሰስ መርዳት እንዲሁም ንብረት የመሰወር ድርጊቶችም ተካተዋል።
ለወንጀሎቹም እንደየክብደታቸው ልክ እስከ 25 ዓመት ወይም የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም የሞት ቅጣት እና እስከ 200 ሺ ብር የገንዘብ ቅጣቶች ተቀምጠዋል። ወንጀሎቹን የፈጸመው የሕግ ሰውነት ያለው አካል ከሆነ ደግሞ እንደወንጀሎቹ ክብደት እስከ ሶስት ሚሊዮን ብር ቅጣት እንዲሁም የድርጅት መፍረስና የንብረት መወረስ ቅጣቶች ይጣላሉ።
የመጀመሪያው የወንጀል ዘውግ በሰዎች መነገድ ነው። በረቂቅ ሕጉ የተካተቱት በሰዎች የመነገድ ድርጊቶች ከወንጀል ሕጉና በሰዎች መነገድ በተለይም የሴቶችና ሕጻናት ዝውውር ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ወንጀል ፈጻሚዎችን ለመቅጣት በተባበሩት መንግስታት ከወጣው ፕሮቶኮል ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ጥረት ተደርጓል።
ፕሮቶኮሉ የሚያተኩረው የወንጀሎቹ ሂደት ላይ ማለትም ለብዝበዛ ዓላማ ሰውን መመልመል፣ ማጓጓዝ፣ ማስጠለል፣ ዛቻ ወዘተ ላይ ነው። የወንጀል ህጉ ድንጋጌዎች ደግሞ ከነችግራቸውም ቢሆን ሂደቱንም ሆነ የሚፈጸመውን ብዝበዛ (አገልጋይ ማድረግ፣ ዝሙት፣ ልመና ወዘተ) ያጠቃልላሉ።
ነባሩ አዋጅ ቁጥር 909/2007 በበኩሉ ልክ እንደ ፕሮቶኮሉ የወንጀሎቹ ሂደት ላይ የሚያተኩሩ አድራጎቶችን ይዘረዝራል። ይህ በመሆኑም አገሪቱን በተመሳሳይ ጉዳይ ሁለት የተለያየ ህግ (ለሂደቱ አዋጁ ለብዝበዛው ደግሞ የወንጀል ሕጉ) ያላት አገር አድርጓታል።
በዚሁ መነሻ ረቂቅ ሕጉ በአንድ በኩል እንደ ፕሮቶኮሉ የብዝበዛ ሂደቶቹን አካቷል። በሌላ በኩል ደግሞ በወንጀል ሕጉ የተመለከቱንና ሌሎች የብዝበዛ ተግባራትን በማካተትና በወንጀል ሕጉም የነበሩትን በማሻሻልና ይበልጥ ዝርዝርና ግልጽ በማድረግ ተቀርጿል። ይህም የሕግ ማዕቀፉን ከተበታተነበት እንዲሰበሰብ አድርጎታል።
በመሆኑም በሰዎች የመነገድ ወንጀልን የሚያቋቁሙት የብዝበዛ አድራጎቶች ሌላውን ሰው በባርነት ወይም በባርነት መሰል ተግባር፣ በአገልጋይነት ወይም በዕዳ መያዣነት መያዝ፤ አካሉን በማውጣት ወይም በዝሙት አዳሪነት ወይም መሰል የወሲብ ተግባር ብዝበዛ መፈጸም፤ በግዳጅ ሥራ ወይም አገልግሎት፣ በልመና፣ በወንጀል ተግባር፣ በግዳጅ ጋብቻ ወይም በማህጸን ኪራይ ማሰማራት ወይም ህጻናትን በጉልበት ሥራ መበዝበዝ ወይም እነዚህን መሰል ተግባራት ናቸው። እነዚህን መፈጸምም ከ7-15 ዓመት ጽኑ እስራትና ከሃያ ሺህ እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር ያስቀጣል።
በሌላ በኩል የብዝበዛ ሂደቶች የሚባሉት በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ ውጭ ወደ መዳረሻ ቦታ ለመውሰድ በዛቻ፣ በኃይል፣ በማገት፣ በመጥለፍ ወይም ሌላ የማስገደጃ ዘዴ በመጠቀም፣ በማታለል፣ የተስፋ ቃል በመስጠት፣ ሥልጣንን አላግባብ በመጠቀም፣ የሰውን ተጋላጭነት በመጠቀም ወይም ስለሌላ ሰው ኃላፊነት ያለበትን ሰው ፈቃድ ለማግኘት መደለያ ወይም ጥቅም በመስጠት ወይም በመቀበል ሌላውን ሰው መመልመል፣ ማጓጓዝ፣ ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፍ፣ ማስጠለል፣ መደበቅ ወይም መቀበል ናቸው። እነዚህም ከ7-12 ዓመት ፅኑ እስራትና ከሃያ ሺህ እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር ያስቀጣሉ።
በሰዎች የመነገድ ድርጊት እንደሚያስቀጣው ሁሉ ድርጊቱን በማስፈጸም ምቹ ሁኔታ በመፍጠር መተባበርና መደገፍም ያስቀጣል። ይህም በዋናነት ለወንጀሎቹ መስፋፋት አስተዋጽዎ የሚያደርጉ የቤት አከራዮችንና የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎችን እንዲሁም በሕገወጥ መንገድ መታወቂያ ወይም የጉዞ ሰነድ የሚያዘጋጁና የሚሰጡትን አደብ እንደሚያስገዛ ይጠበቃል።
በሰዎች የመነገድ ወንጀል ከባድ ቅጣት የሚያስከትልባቸው ሁኔታዎችንም ረቂቅ ሕጉ አስቀምጧል። እነዚህም ድርጊቱ የተፈጸመው በሕጻናት፣ በአዕምሮ ህመምተኛ ወይም በአካል ጉዳተኛ ላይ ከሆነ፤ አደንዛዥ ዕፅ፣ መድሃኒት ወይም የጦር መሣሪያ በመጠቀም እንደሆነ፤ የመንግስት ሠራተኛ (በባለሥልጣን) የተሰጠውን ኃላፊነት መከታ በማድረግ ወይም የሥራ ስምሪት ፈቃድ ያለው አካል ፈቃዱን ሽፋን በማድረግ የፈጸመው እንደሆነ የሚሉ ናቸው። እነዚህም ከ10-20 ዓመት ፅኑ እስራትና ከሰላሳ ሺህ እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር ያስቀጣሉ።
ከዚህ በተጨማሪ ድርጊቱ የተፈጸመው የተደራጀ የወንጀል ቡድን አባል በመሆን ወይም ቡድኑን በመምራት ወይም በማስተባበር እንደሆነ ወይም በተጎጂው ላይ የማይድን በሽታ ያስከተለ ወይም የተጎጂው ህይወት ወይም ደህንነት አደጋ ላይ የወደቀ ወይም በተጎጂው ላይ ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰበት ወይም ለኢ-ሰብአዊ አያያዝ የተዳረገ እንደሆነ ቅጣቱ ከ15-25 ዓመት ጽኑ እስራትና ከሀምሳ ሺህ እስከ አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ ብር ይደርሳል።
በረቂቅ አዋጁ መሰረት በሰው የመነገድ ድርጊቱ (ሂደቱም ይሁን ብዝበዛው) በተጎጂው ላይ ሞት አስከትሎ እንደሆነ ከ15-25 ዓመት ወይም እድሜ ልክ ፅኑ እስራት ወይም የሞት ቅጣት እና ከሃምሳ ሺህ እስከ ሁለት መቶ ሺህ ብር መቀጮ ይጣላል።
በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር
ሁለተኛው የወንጀል ዘውግ በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ነው። ይህም ወንጀል በነባሩ አዋጅ ለአፈጻጸም አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል። በተለይም ሕጉ “ስደተኞችን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል” በማለቱ ምክንያት ኢትዮጵያውያን ወይም ሌሎች ስደተኛ ያልሆኑ ሰዎች የድርጊቱ ሰለባዎች በሚሆኑበት ጊዜ “ስደተኛ” በሚለው አንድምታ ውስጥ ሊካተቱ ስለማይችሉ በተከሳሾች ላይ ክስ ማቅረብ አልተቻለም።
ረቂቅ አዋጁ ታዲያ ይህን ለማስተካከል “ስደተኛ” የሚለውን “ሰውን” በሚል ቃል በመተካት ችግሩን አስወግዶታል። እናም በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር የሚባለው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የገንዘብ (ቁሳዊ) ጥቅም ለማግኘት (ለሌላ ሰው ለማስገኘት) በማሰብ ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ፤ ከኢትዮጵያ እንዲወጣ፤ በኢትዮጵያ ግዛት እንዲተላለፍ ማድረግ ነው። ሰውን ከኢትዮጵያ ለማስወጣት ዝግጅት ማድረግ፣ በሂደት ላይ መገኘት፣ ማጓጓዝ ወይም መቀበልም የወንጀሉ አካል ነው።
ኢትዮጵያዊ ያልሆነ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር ወይም ለመቆየት የሚያስችል የፀና ፈቃድ የሌለውን ሰው በአገር ውስጥ እንዲቆይ መርዳት እንዲሁም ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ለማሻገር እንዲውል ሀሰተኛ የጉዞ ወይም የማንነት መታወቂያ ሰነድ ማዘጋጀት፣ ይዞ መገኘት፣ ማቅረብ ወይም ማስተላለፍም ወንጀል ነው።
ከሁሉም በላይ ደግሞ በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ድርጊቱ በተጎጂው ላይ ሞት አስከትሎ እንደሆነ ከ15-25 ዓመት ወይም እድሜ ልክ ፅኑ እስራት ወይም የሞት ቅጣት እና ከሃምሳ ሺህ እስከ ሁለት መቶ ሺህ ብር ያስቀጣል።
ሕገ-ወጥ የውጭ አገር የስራ ስምሪት
ይህ ሶስተኛው የወንጀል ዘውግ ነው። በአሁኑ ወቅት የውጭ አገር የስራ ስምሪት ጉዳይ የሚመራው በውጭ አገር የሥራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2008 ነው። ነገር ግን አዋጁ የወንጀል ድንጋጌ የለውም።
ከዚህ አዋጅ አስቀድሞ ከስራ ስምሪት ጋር በተያያዘ የሚፈጸም ወንጀል ሥለ ሥራና ሰራተኛ ማገናኘት አገልግሎት በወጣው አዋጅ ቁጥር 632/2001 የተሸፈነ ነበር። አዋጁ ኢትዮጵያውያንን ለስራ ወደ ውጭ አገር በህገ-ወጥ መንገድ መላክ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 598 እንደሚያስቀጣ ይገልጻል።
ይሁንና የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር አዋጅ ቁጥር 909/2007 ከአዋጁ ጋር በተገናኙ ጉዳዮች የወንጀል ህጉን አንቀጽ 598ን ተፈጻሚ እንዳይሆን አግዶታል። እናም አዋጅ 632/2001 ቀድሞ የወጣና የወንጀል ህጉን የሚያጣቅስ በመሆኑና አዋጅ ቁጥር 909/2007 ደግሞ በኋላ የወጣና የወንጀል ሕጉን አንቀጽ 598ን ተፈጻሚነት ያገደ በመሆኑ የወንጀል ሕጉ አፈጻጸም አከራካሪ ሆኗል።
በዚህ መነሻ በሕገ-ወጥ መንገድ ኢትዮጵያውያንን ለስራ ወደ ውጭ አገር ከመላክ ወንጀል ጋር በተያያዘ የህግ ክፍተት ስለመፈጠሩ የሚሞግቱም አሉ። የሆነው ሆኖ በሥራ ላይ ያለውንና የወንጀል ድንጋጌ የሌለውን አዋጅ ቁጥር 923/2008ን እና የአዋጅ ቁጥር 909/2007ን ክፍተቶች ለመሙላት የአሁኑ ረቂቅ አዋጅ ህገ-ወጥ የውጭ አገር የስራ ስምሪት ወንጀሎችን በዝርዝር ማካተቱ መልካም ነው።
ህገ-ወጥ የስራ ስምሪት በሰዎች የመነገድና ሰዎችን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን ለመፈጸም ከሚያመቹ ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ ነው። ረቂቅ ሕጉም ይህንን ማካተቱ ችግሩን ለመከላከል ያግዛል። ፈቃድ የሌለው ብቻ ሳይሆን አሰሪና ሰራተኛ ለማገናኘት ፍቃድ ያለው ሰውም ቢሆን የሚፈጽማቸውን ወንጀሎች በግልጽ ማስቀመጡም ያስመሰግነዋል።
ይ ቀ ጥ ላ ል…
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ጥር 6/2012
ገብረክርስቶስ