የፌዴራል ፖሊስ መረጃ እንደሚያመለክተው በትራፊክ አደጋ ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ከ20 ሺህ ያላነሱ ዜጎች ሕይወታቸው አልፏል:: በአንድ ዓመት ብቻ 4ሺ 500 ዜጎች በመኪና አደጋ ህይወታቸውን የሚያጡ ሲሆን ከ7 ሺ ያላነሱ ሰዎች ደግሞ ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል:: በንብረትም ላይ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል::
የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ የተሽከርካሪ አደጋ 3ኛ ወገን መድን አዋጅ ቁጥር 799/2005 ለማስፈፀም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 300/ 2006 የተቋቋመ የፌዴራል መንግሥት መስሪያ ቤት ነው:: ኤጀንሲው በተሽከርካሪ አደጋ የሚደርሰውን የሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ኪሳራ የሚያስከትለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለማቃለል ሁሉም ተሽከርካሪዎች የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን እንዲኖራቸው ያስቀምጣል፡፡
የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አስአኳይ ህክምና ዕርዳታን በነፃ እንዲያገኙና ለሞትና ለአካል ጉዳት እንዲሁም ለንብረት ጉዳት ካሳ እንዲያገኙ በማድረግ አገራዊ ተልዕኮውን በመወጣት ላይ ከመሆኑም ባሻገር ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ የተሽከርካሪ አደጋ አድርሰው በተሰወሩ 350 ግለሰቦች ምክንያት ዘጠኝ ሚሊየን ብር ካሳ ለተጎጂዎች ከፍሏል::
ተቋሙ ይህንን ያህል ከባድ ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም ሥራውን በሚፈለገው ልክ እንዳይሠራ የተለያዩ አሳሪ ምክንያቶች እንዳሉበት ደግሞ ይነገራል:: እኛም ኤጀንሲው እያከናወነ ባለው ተግባርና ባጋጠሙት መሰናክሎች ዙሪያ ከምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ከአቶ ሽመልስ ታምራት ጋር ቆይታ አድርገን እንዲህ አቅርበነዋል::
አዲስ ዘመን፦ ለኤጀንሲው የተሰጡት ተግባርና ኃላፊነቶች ምንድን ናቸው?
አቶ ሽመልስ፦ መንግሥት እንደ አንድ ተቋም ሲያቋቁመው ታሳቢ ያደረጋቸው ነገሮች አሉ፤ ዋናው ግን በተሽከርካሪ አደጋ ምክንያት ተጎጂ የሆኑ ሰዎች የሚደርስባቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር መቅረፍ ነው:: ተቋሙ የዛሬ 9 ዓመት ገደማ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን በእነዚህ ዓመታት ውስጥም በርካታ ተግባራትን አከናውኗል::
አዲስ ዘመን፦ በርካታ ብለው የጠቀሷቸውን ተግባራት ማወቅ ይቻል ይሆን?
አቶ ሽመልስ፦ ያከናወናቸው ተግባራት ተሽከርካ ሪዎች ሦስተኛ ወገን ሽፋን እንዲኖራቸው ማድረግ ነው:: በዚህም ማንኛውም ተሽከርካሪ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን በመግባት ምልክቱን (ስቲከሩን) ለጥፎ መጓዝ ስላለበት ይህንን እንዲያደርጉ ማስቻል ነው፡፡ ይህ በሌሎች አገራት በጣም ረጅም ርቀት የተሄደበት ተግባር ሲሆን በአገራችን ግን ዘግይተን ነው የጀመርነው፡፡ ቢሆንም ኤጀንሲው የተሰጠው ትልቁ ተግባርና ኃላፊነት በመሆኑ ለሥራው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ላይ ነው::
እንደ ኤጀንሲ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን በሌላቸው ተሽከርካሪዎች የሚገጩ ዜጎችን የአካል ጉዳት፣ የሞት ካሳ እንዲያገኙ የማድረግ ተልዕኮውንም በአግባቡ እየተወጣ ነው:: ሌላው በማንኛውም ተሽከርካሪ ተገጭቶ ጉዳት የደረሰበት ሰው የአስቸኳይ ህክምና አገልግሎትን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እስከ ሁለት ሺህ ብር ድረስ እንዲያገኝ ማስቻልም ነው::
አዲስ ዘመን፦ እዚህ ላይ ግን የሦስትኛ ወገን የመድን ሽፋን ባለው ተሽከርካሪም ጉዳት የደረሰበት ሰው የህክምና ዕርዳታውን በነፃ ማግኘት ይችላል ማለት ነው?
አቶ ሽመልስ፦ በማንኛውም ተሽከርካሪ የተጎዳን ያካትታል፡፡ ሽፋን ያላቸው የሌላቸው ብለን የለየነው ለካሳ አከፋፈሉ እንዲመች ነው እንጂ ህክምናውን አይመለከትም::
አዲስ ዘመን፦ ይህ የነፃ የህክምና ዕርዳታ የመንግሥት ሆስፒታሎች ላይ ብቻ ነው የሚገኘው?
አቶ ሽመልስ፦ አገልግሎቱ የሚሰጠው ወይም ህጉ የሚያዘው በሁሉም ማለትም በግልም በመንግሥትም ጤና ተቋማት ላይ ነው:: በአዋጁ መሰረትም ሁሉም ይገደዳሉ:: ኤጀንሲው ደግሞ አገልግሎቱ በአግባቡ መሰጠት አለመሰጠቱን ያጣራል:: ከዚህ ውጪ ግን የሦስተኛ ወገን ሽፋን ባላቸው የሚገጩትን ኢንሹራንሶች ወጪውን መሸፈን ስለሚገባቸው ይህንንም ተከታትሎ ማስፈጸም የኤጀንሲው ሥራ ይሆናል ማለት ነው:: ይህንን ለመፈጸም ደግሞ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ይጠቀማል:: ከእነሱም ጋር የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር እየተንቀሳቀሰ ነው::
አዲስ ዘመን፦ ከዚህ አንጻር ተልዕኮውን በማስፈጸም በኩል ተሳክቶለታል ማለት ይቻላል?
አቶ ሽመልስ፦ በመጀመሪያ ደረጃ ኤጀንሲው እያከናወነ ባለው ተግባር እያስመዘገበ ያለው ውጤት መጥፎ ነው የሚባል አይደለም፤ ግን ደግሞ በተለያየ መንገድ ከህብረተሰቡ߹ ከአሽከርካሪው߹ ከተሽከርካሪውና ከባለንብረቱም በኩል ካለው የግንዛቤ እጥረት ምክንያት ረጅም ርቀት ተሂዷል ለማለት ግን አይቻልም::
አዲስ ዘመን፦ ለማሻሸልስ በእናንት በኩል የተሞከሩ ሥራዎች የሉም?
አቶ ሽመልስ፦ በእኛ በኩል ከዓመት ዓመት የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች እየጨመሩ በመምጣታ ቸው፣ ሌሎቹም ትኩረት ሲሰጡት ባለድርሻ አካላትም በኔነት ስሜት መሥራት ሲጀምሩ አሁን ላይ የተለያዩ የንቅናቄ መድረኮችን እያዘጋጀን መገናኛ ብዙሃንን እየተጠቀምን ትንሽ መሻሻል ፈጥረናል:: በተለይም በባለፈው ዓመት የሠራናቸው ሥራዎች ጥሩ ነበሩ::
ይህም ቢሆን ግን ኤጀንሲው በአዋጅ የተሰጠውን ሥራ በማከናወን በኩል ተሳክቶለታል ማለት ግን አይቻልም:: ለውጥ አለው ብሎ መውሰዱ ይሻላል:: አሁንም ጥረት እያደረግን ያለነው የህይወት ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆን አለበት የሚለው ላይ ነው:: አደጋ ቢቀንስ አምራች ዜጎች ወደ ምርታማነት ስለሚገቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሩ ይቀንሳል፤ እንደ አገር እየወደመ ያለው ሀብትና እየጠፋ ያለውን የሰው ህይወት መታደግ ያስችላል::
ኤጀንሲው በአብዛኛው የሚሠራው ከአደጋ በኋላ የሚፈጠረውን የተጎጂዎችን ችግር ማቃለል ላይ ቢሆንም ከአደጋ በፊት ግን አደጋን መከላከሉ ትኩረት ሊያገኝ ይገባል በማለት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ ነው::
አዲስ ዘመን፦ አደጋ የደረሰባቸውን የህብረ ተሰብ ክፍሎች አስቸኳይ የህክምና ዕርዳታ በሁሉም ጤና ተቋማት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲያገኙ ህጉ ያዛል፤ ግን እናንተ በግምገማችሁ ይህ ሥራ በአግባቡ እየተሠራ ነው ብላችሁ ትላላችሁ? ምክንያቱም የሚታዩት ነገሮች እንደዛ ስላልሆኑ፤
አቶ ሽመልስ፦ አስቸኳይ የህክምና ዕርዳታን ሁሉም የጤና ተቋማት በሚፈለገው ወይም ህጉ በሚያዘው መሰረት እየሰጡ አይደለም:: ምንድነው ምክንያቱ ስንል ትልቁ የግንዛቤ ክፍተት ነው፤ ህብረተሰቡም መብቴ ነው ብሎ አይጠይቅም፤ ይህ ችግር ደግሞ ኤጀንሲው በሚሠራቸው ወይም በሚፈጥራቸው መድረኮች ብቻ ሊፈታ የሚችል አይደለም:: ይህንን ያልኩበት ዋና ምክንያትም ባለፉት ዓመታት ኤጀንሲው በመላው አገሪቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ ግንዛቤ እፈጥራለሁ ብሎ የተለያዩ መድረኮችን ሲያዘጋጅ ነበር፤ ግን ለውጥ አላመጣም:: ስለዚህ አሁን ያለው አማራጭ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሥራውን በባለቤትነት ይዘው መንቀሳቀስ አለባቸው የሚል ነው::
አዲስ ዘመን፦ ለምሳሌ የትኞቹ ተቋማት ናቸው ከእናንተ የተሻለ ለሥራው ቅርበት ኖሯቸው ሊሠሩ ይችላሉ የሚባሉት?
አቶ ሽመልስ፦ ከአስቸኳይ የህክምና ዕርዳታ ጋር በተያያዘ ጤና ሚኒስቴር ነው:: ምክንያቱም በሰፊው ጉዳዩ የሚመለከተው በመሆኑ፤ ፖሊስ ገጭቶ የሚያመልጠውን ከመያዝ አኳያ ይመለከተዋል፤ ትራፊክ ፖሊስ ህገ ወጥ የሆኑና የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን ያልያዙ ተሽከርካሪዎች በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ከመቆጣጠር አንጻር ይመለከተዋል፤ እነዚህ አካላት ባለቤት ነን ብለው ካልተንቀሳቀሱ ኤጀንሲው ብቻውን የሚያመጣው ለውጥ የለም::
አዲስ ዘመን፦ እንዳሉት እነዚህ አካላት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ጉዳዩ የሚመለ ከታቸው ናቸው፤ ግን በእናንተ በኩል ኃላፊነታቸውን አሳውቃችሁ የጋራ መግባባት ላይ ደርሳችኋል ወይስ እነሱም መሥራት አለባቸው ብቻ ብላችሁ ነው ቁጭ ያላችሁት?
አቶ ሽመልስ፦ አሁን ላይ ትራንስፖርት ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ሳይቀሩ በሥራው ላይ ተሳትፎ እያደረጉ ነው ፤የትራንስፖርት ሚኒስትሯም ራሳቸው መድረኮችን እየፈጠሩ እየመሩ አቅጣጫ እየሰጡ ነው:: የጤና ሚኒስቴር እየተሳተፈ ነው:: ትልቁና ዋናው ደግሞ ኤጀንሲውን የሚከታተለው ቦርድ ከኢንሹራንሶች ፣ከጤና ሚኒስቴር፣ከፖሊስ የተውጣጡ አካላትን በአባልነት እንዲይዝ መደረጉ ትልቅ ዕርምጃ ነው:: ውጤቱ ደግሞ በቀጣይ የሚታይ ይሆናል::
አዲስ ዘመን፦ እዚህ ላይ ለትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና ዕርዳታን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሆስፒታሎች በነፃ እንዲሰጡ ህጉ ያስገድዳል፤ በቂም ባይሆን ደግሞ ተቋማቱም አገልግሎቱን እየሰጡ ነው፤ ግን እነዚህ ተቋማት ያወጡትን ገንዘብ በወቅቱ ካለማግኘት ጋር በተያያዘ የሚያነሱት ቅሬታ አለ፤ አገልግሎቱን ከሰጡ ለምንድን ነው በወቅቱ ወጪያቸው የማይሸፈንላቸው?
አቶ ሽመልስ፦ ይህ ትክክል ነው፤ ይህ ተዘዋዋሪ የሦስተኛ ወገን የመድን ፈንድ ገንዘብ ዋና ዓላማው በተሽከርካሪ አደጋ ምክንያት የተጎዱ ሰዎች አስቸኳይ የህክምና ዕርዳታን እንዲያገኙ ማድረግ ነው:: ስለዚህ ገንዘቡ ከኢንሹራንሶች ይሰባሰብና በጤና ሚኒስቴር የባንክ ቁጥር ገቢ ይደረጋል:: ሚኒስቴሩ ደግሞ መረጃዎችን በማየት ገንዘቡን አገልግሎቱን በትክክል ላደረሱ የጤና ተቋማት የመክፈል ኃላፊነት ተሰጥቶታል:: ግን ዋናው ችግር ገንዘቡን ማስመለሱ ላይ አይደለም፤ አገልግሎቱን የሚሰጡት ተቋማት በሚኒስቴሩ በኩል ተገቢው ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው ያወጡትንም ወጪ ኦዲት እያስደረጉ ማቅረብና በፍጥነት መሄድ ላይ ነው ፤ ይህንን እንዲቆጣጠር ስልጣን የተሰጠው ተቋም ደግሞ የችግሩ ባለቤት መሆን አለበት ባይ ነን እኛ፡፡
ኤጀንሲው ገንዘቡን ከኢንሹራንሶች ሰብስቦ በሚኒስ ቴር መስሪያ ቤቱ የባንክ ቁጥር ያስገባል፤ እርሱ ደግሞ ከላይ በተጠቀሰው መሰረት ማስረጃዎችን እያጣራ ቶሎ ቶሎ መልቀቅና ሲያልቅም መጠየቅ ሥራው ነው::
ሌላው እዚህ ላይ ያለው ችግር አንዳንድ ሆስፒታሎች ሥራውን በአግባቡ ሠርተው ማስረጃቸውን አደራጅተው ያቀርባሉ፤ ሌሎች ደግም ጭራሹኑ ካለመሥራታቸውም በላይ ከሌላ ሥራቸው ጋር ይደበላልቁታል:: በአዋጅ የተቀመጠላቸውን የመጀመሪያ ህክምና ዕርዳታ ወጪ እንዳለ ሆኖ ሌሎች ሥራዎቻቸውን በመደበላለቅ አንድ ላይ ገንዘብ ይጠይቃሉ:: ይህ ደግም ተገቢ ካለመሆኑም በላይ ወንጀል ነው:: ስለዚህ ጤና ሚኒስቴር የሚመልሰው መልስ ኦዲት ለማድረግ ተቸገርኩ ነው::
እንዲህ አይነት ነገር ሊገጥም ይችላል:: ግን አስቀድሞ መደገፍ በአግባቡ ክትትል ማድረግ ይጠይቃል:: እኛም ለቁጥጥር ስንወጣ ብዙ ችግሮችን እናገኛለን ፤ ችግሮቹን ግን ለሚመለከተው አካል ከማቅረብ የዘለለ ሚና አይኖረንም፤ ምክንያቱም ያንን ፈንድ አሰባስበን ከማስገባት ባለፈ የማንቀሳቀስ መብት የለንም::
እዚህ ላይ ግን አንዳንዶቹ ሆስፒታሎች ሳይሠሩ ነው የሚጠይቁት:: ሲጠየቁም ገንዘቡ የለንም ይላሉ:: ግን በአዋጅ ከተቀመጠና ሥራው ከተጀመረ ረዘም ያለ ጊዜን አስቆጥሯል:: ጤና ቢሮዎች ይህንን አውርደው ተቋማቱ አገልግሎቱን በአግባቡ እንዲሰጡ በማድረግ߹ ለቦታው ትክክለኛውን ሰው በመመደብ በኩል ሰፊ ክፍተት አለ:: ይህ ደግሞ ትክክል አይደለም::
አዲስ ዘመን፦ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ክልሎች ለመጀ መሪያ ደረጃ ህክምና ዕርዳታ እንዲጠቀሙበት የተመደበላቸውን ገንዘብ ለሌላ ዓላማ የማዋል ሁኔታ አለ ይባላልና እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ሽመልስ፦ የአንዳንድ ክልሎች መሰረታዊ ችግር ሆኖ ሲቀርብልን የነበረው ገንዘቡን ለሌላ ዓላማ ማዋል ነው:: በእርግጥ በዚህ ዓመት አላገኘንም፤ ባለፉት ዓመታት ግን ሲቀርብ የነበረው ሪፖረት የሚላክላቸው ገንዘብ አጠቃቀም ላይ ችግር የሚያሳይ በመሆኑ ገንዘቡ አይከፋፈልም ነበር:: ኤጀንሲውም ገንዘቡ ገቢ ከሆነ ለምንድን ነው የማይለቀቅላቸው ብሎ ጥያቄ ሲያቀርብ ላልተገባ ዓላማ የማዋል ጉዳይ አለ የሚል ምክንያት
ችግሩን ያባብሰዋል::
አዲስ ዘመን፦ ከዚህ ቀደም የእናንተም ኤጀንሲ ሲያቀርብ የነበረው ቅሬታ በተለይም ገጭተው የሚያመልጡ አሽከርካሪዎችን አድኖ በመያዝና ተጠያቂ በማድረግ በኩል ፖሊስ ሚናውን አልተወጣም የሚል ነበርና አሁን ላይ መሻሻል አለ?
አቶ ሽመልስ፦ አሁን ትልቅ ለውጥ አለ:: በተለይም ባለፈው አንድ ዓመትና ከዚያ በፊት ለውጥ እየታየ ነው:: ለለውጡ መምጣት ትልቅ አስተዋጽዖ ያበረከተው ደግም ኤጀንሲው በየመገናኛ ብዙሃኑ ባደረገው ረጅም የንቅናቄ ሥራ ሲሆን በዚህ ሂደት ውስጥ ታሳቢ ተደርጎ የተሠራው ደግሞ ባለድርሻ አካላትን ነው:: ስለዚህ የፌዴራልና የከተማ ፖሊሶችን፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችንና የጤና ባለሙያዎችን አሳትፈናል:: በፊት የነበረው አሠራርም እሩቅ ለሩቅ ሆነን አዋጁን አስፈጽም አታስፈጽም ነበር፤ አሁን ያ አሠራር እንዲቀር ሆኖ ተቀራርበን በመወያየት እየሠራን ነው::
በነገራችን ላይ ገጭቶ የማምለጥ ጉዳይ የተከማቸ ነው:: ኤጀንሲው ወንጀልን የመከላከል ሥራ አይሠራም፤ ግን ወንጀል አይመለከተንም ብለን እጃችንን አጣጥፈን ከተቀመጥን የሚመለከተውም አካል ሥራውን ላይወጣ ይችላል፡፡ በመሆኑም ሥራው የጋራ ነው ብሎ በመቀናጀት እንዲሁም በመገፋፋት እየተሠራ ያለው ሥራ ጥሩ ነው::
አዲስ ዘመን፦ ጥሩ ነው ሲሉ ግን በተጨባጭ ውጤት አይታችሁበታል?
አቶ ሽመልስ፦ አዎ ውጤት እየታየበት ነው:: ባለፉት ዓመታት እኮ ገጭቶ ያመለጠን ተሽከርካሪ መያዝ ላይ በጣም ችግር ነበር:: አሁን ባሳለፍነው ስድስት ወር ውስጥ እንኳን ሦሰት ገጭተው ያመለጡ አሽከርካሪዎች ተይዘው ፍርድ ቤት ቀርበው ቅጣታቸውን ተቀብለው ኤጀንሲውም የከፈለውን ገንዘብ ለማስመለስ ችሏል:: ይህ ቁጥር ትንሽ ሊመስል ይችላል፡፡ ሆኖም ምንም ካልነበረበት እዚህ መድረስ ለእኛ ትልቅ ስኬት ነው:: ስለዚህ ባለድርሻ አካላት በተለይ ፖሊስ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶታል ማለት ነው:: ወንጀለኛን አድኖ ከመያዝ ባሻገር አሁን ላይ የቁጥጥር ሥራውም ትልቅ ለውጥ እየታየበት ያለ ነው::
አዲስ ዘመን፦ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን ባለውም በሌለውም ተሽከርካሪ ጉዳት የደረሰበት ሰው በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ነው የካሳ ክፍያውን ማግኘት የሚችለው? ይህንን ያልኩት በክፍያው ሂደት መርዘምና መንዛዛት አንዳንዶች የሚተውትም አሉ የሚባል ነገር ስላለ ነው?
አቶ ሽመልስ ፦ ወደ ኤጀንሲው ከደረሰ ያን ያህል የሚፈጀው ጊዜ የለም:: ምክንያቱም ኤጀንሲው ይህንን ታሳቢ በማድረግ ከተለያዩ አካላት የተውጣጡ ኮሚቴዎችን አቋቁሟል፡፡ ሰነዱ እንደቀረበለትም ቁጭ ብሎ በመወያየትና የሰነዶችን ትክክለኛነት በማረጋገጥ ያጸድቃል::
እዚህ ላይ ግን የሚቆየው መጀመሪያ አካባቢ ያለው ሂደት ነው:: ሟች ከሆነ ወራሾች የአካል ጉዳት ከሆነም ካሳ የሚያገኘው ሰው የትራፊክ መረጃው ተጠናቅሮ እስኪቀርብ ቀናት ይወስዳል::
የምንክሰው ካሳ አመርቂ አይደለም:: ትንሹ አምስት ሺ ብር ሲሆን ትልቁ 40 ሺ ብር ነው:: አምስት ሺ ብር የሚካሰው ሰውዬ ከክልል ተነስቶ አዲስ አበባ መጥቶ ጉዳዩን አመልክቶ ምንልባትም ቀጠሮ ሊሰጠው ይችላል፡፡ ተመልሶ አገሩ ሄዶ በቀጠሮው ቀን መጥቶ እስኪያስፈጽም ድረስ ስንት ሺ ብር ይጨርሳል:: ስለዚህ ይተወዋል ማለት ነው:: ትልቅ የተባለው 40 ሺ ብርም እኮ እንደዚያው ነው፤ ስለዚህ ሁኔታው ትንሽ መታየት አለበት::
አዲስ ዘመን፦ መፍትሔውስ ምንድን ነው?
አቶ ሽመልስ፦ እዚህ ላይ ሁለት አማራጮች አሉ፤ አንደኛው ሥራውን ማቅለል ነው፤ ይህ ሲባል እንግዲህ አደጋ በመላው አገሪቱ የሚደርስ ከመሆኑ አንጻር ተጎጂዎች ጉዳያቸውን በአቅራቢያቸው እንዲከታተሉ የካሳ ገንዘባቸውንም እዚያው ባሉበት የሚሰጥበትን አሠራር ማበጀት ነው:: ሌላው ደግሞ አሁን ላይ ያለውን የኢኮኖሚ እድገት እንዲሁም የኑሮ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ ሰዎችንም ሊስብ የሚችል የካሳ ክፍያን ማመቻቸት ነው::
ኤጀንሲው ገንዘቡ እንኳን ከአገሪቱ ጫፍ ሊመጣበት ይቅርና ከተማ ውስጥ ጉዳዩን ተከታትሎ አስፈጽሞ ለመከፈል የሚያነሳሳ አለመሆኑን አምኖበት እንዲሻሻልም ጥያቄን አቅርቧል፤ ግን ደግሞ ጉዳዩ የሰውን ህይወት ፣ የአገርን የኢኮኖሚ ሁኔታ እንዲሁም የአሽከርካሪዎችን አቅም ማገናዘብ ያለበት በመሆኑ ዝም ብሎ የሚጠና አይደለም:: በዘርፉ እውቀት የሥራ ልምድ ያላቸው ከፍተኛ ባለሙያዎችን ተሳትፎም ይጠይቃል::
ስለዚህ ቀድሞ ሲጠና ምን ታይቶ ነበር አሁን ደግሞ ለድጋሚ ጥናቱ ምን ዓይነት ነገሮችን ከግምት ውስጥ እናስገባ የሚለውን ታሳቢ ተደርጎ የካሳ መጠኑ መሻሻል አለበት የሚል ነው የኤጀንሲው አቋም::
አንድ ሰው ምንም አልተጉላላም ቢባል እንኳን የቤተሰቡን አባወራ ያጣ ሰው 40 ሺ ብር ካሳ ምንድን ነው የሚያደርግለት:: ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ከግምት ውስጥ መግባት አለባቸው:: በተጨማሪም የማስፈጸሚያ ሂደቱም በጣም ማጠር አለበት::
አዲስ ዘመን፦ ኤጀንሲው በካሳ መጠኑ ማነስና በሂደቱ መርዘም ላይ ግንዛቤ ወስዶ እንዲሻሻል ቢሠራም የሌሎች ባለድርሻ አካላት ለምሳሌ የኢንሹራንሶች ሃሳብ ምንድን ነው? ትወያዩበታላችሁ?
አቶ ሽመልስ፦ ኢንሹራንሶች፣ ፖሊስና የጤና ተቋማት የተካተቱበት የምክክር ፎረም አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ክልልሎች አሉን፤ በውይይት ላይም እነዚህ ነገሮች በተደጋጋሚ ይነሳሉ:: ከመወያየትም ባለፈ አቅጣጫ እየተቀመጠ ነው፤ የእነዚህ ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ጥሩ ነው:: የተቋሙን መዋቅር ለመለወጥ ስናስብም እነዚህን ታሳቢ አድርገናል:: ለምሳሌ የቀድሞውን ቦርድ አፍርሰን አዲስ ስንመሰርት በአገሪቱ ትልቁን ድርሻ የሚይዙ የኢንሹራንስ ካምፓኒዎችን ህብረት ፕሬዚዳንትን ጨምሮ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል፣የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ አባል እንዲሆኑ ሆኗል:: ምክንያቱም የምንወስናቸውን ውሳኔዎች ታሳቢ በማድረግ::
አዲስ ዘመን፦ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ለንብረታቸውም ለሚያደርሱት ወይም ለሚደርስ ባቸው ጉዳት ሙሉ ኢንሹራንስ ይገባሉ፤ ከዚያ ጎን ለጎን ደግሞ ሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን እንዲገቡ ይገደዳሉ፤ ግን ጥቂት ባለንብረቶች እኛን ለማስቸገር ካልሆነ ጥቅም የለውም ይላሉና በዚህ ላይ ምን ሃሳብ አለዎት?
አቶ ሽመልስ፦ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን መግባት በጣም ጠቃሚ እንጂ እንደሚሉት የሚያስቸግራቸው አሊያም ጫና የሚያሳድርባቸው አይደለም:: አንድ አሽከርካሪ ወይም መኪና ያለው ሰው በዓመት ለሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን የሚያወጣው እኮ ከሦስት መቶ እስከ አምስት መቶ ብር ነው :: ለዚያውም እንደ መኪናው ሁኔታ ተገናዝቦ:: አደጋ እኮ አይደርስም ብሎ ማለት በጣም ከባድ ነው፡፡ ተሽከርትካሪ ሰው ሠራሽ ነው፡፡ ምንም አሽከርካሪው ጠንቃቃ ቢሆን በመካከል የሚገጥሙ ቴክኒካል ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ:: በዚህ ምክንያት ደግሞ አደጋ በየትኛውም አጋጣሚ ይከሰታል:: የሚከፍሉት ክፍያ ደግሞ በጣም አነስተኛ የሚባል ነው:: ይህንን ባለመክፈል ግን ከዚህ በላይ በጣም ከፍተኛ ወጪን ሊያወጣ ይችላል:: ሦስተኛ ወገን ያለው ተሽከርካሪ ግን አደጋ ቢያደርስ ከሦስተኛ ወገን ጋር ነው የሚያገናኘው:: ስለዚህ እርሱ በዓመት በከፈላት መጠነኛ ገንዘብ ተጎጂው ይታከምለታል ፤ ችግሩም እንዲቀረፍ ይሆናል::
አንዳንድ ጊዜ ለቁጥጥር ስንወጣ ሐሰተኛ (ፎርጅድ)߹ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ማስረጃዎች በተሽከርካሪ ላይ ተለጥፎ እናገኛለን:: ይህ በጣም አሳዛኝም፤ አሳፋሪም ነው:: ዝም ብለሽ ብታስቢው ሐሰተኛ ማስረጃ ለማሠራት ስንት ብር ይወጣል? በጣም የሚገርም ነው::
ከሚደርሰው አደጋ አንጻር የሚከፈለው ገንዘብ የተጋነነ አይደለም፤ አደጋው ሲደርስ ግን ከባድ ነው፤ አደጋ ካቆመ እኮ ተቋሙም ብዙ የሚያከናውናቸው ሥራዎች አሉበት ፤ ግን አሁንም የሚካሰው ካሳ ብዙ ነው፤ ኢንሹራንሶች የሚክሱትም በተመሳሳይ በጣም ብዙ ነው:: ይህ እስካልተወገደ ድረስ የሦስተኛ ወገን አልከፍልም ማለት ለራስ አለማሰብ ነው::
አዲስ ዘመን፦ የእርስዎ ኤጀንሲ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በጎዳናዎች ላይ ተሽከርካሪዎችን ይቆጣጠራሉና፤ በዚህ ሥራ ምን ተመለከታችሁ? ይህን ያልኩት አንዳንድ ተሽከርካሪዎች እንዴት የቴክኒክ ምርመራውን አልፈው መንገድ ላይ ወጡ የሚያስብሉ በመሆናቸው ነው?
አቶ ሽመልስ፦ አዎ ፤ በተለይ አሁን በቅርቡ በነበረን የንቅናቄ ጊዜ ከፌዴራል ትራንስፖርት ባለስል ጣንና ከፖሊስ ጋር በጋራ ሠርተናል:: ምንም እንኳን የሥራ ኃላፊነቶቻችን ቢለያዩም የሚያገናኙን ነገሮች ደግሞ አሉ:: አደጋን በመከላከል ዙሪያ ደግሞ እንኳን እኛ ተመጋጋቢ ሥራ የምንሠራው ቀርቶ የትኛውም ተቋም እንዲሁም ግለሰብ ይመለከተዋል:: በዚህ መሰረት ከትራንስፖርት ባለስልጣን ጋር የጋራ እቅድ አቅደን ነው የተንቀሳቀስነው፡፡ በእቅዱም ውስጥ አንደኛው ሽፋን ሲሆን ሌላው የተሽከርካሪው ቴክኒካዊ ብቃትን የተመለከተ ነበር፤ ለሥራውም በርካታ የትራፊክ ፖሊስ ተሽከርካሪዎችና አባላት እንዲሁም የኤጀንሲውና የትራንስፖርት ባለስልጣን ባለሙያዎች በየክልል ተንቀሳቅሰው ሠርተዋል፤ ጥሩ ውጤትም ታይቶበታል::
አዲስ ዘመን፦ እዚህ ላይ ግን ውጤቱ እንዳለ ሆኖ የትራፊክ አደጋ መንስኤ ናቸው፤ መከላከያ መንገዱ ይህ ሊሆን ይችላል ብላችሁ የደረሳችሁበት ግኝት የለም?
አቶ ሽመልስ፦ የአደጋ መንስኤዎች ግልጽ ናቸው፤የአሽከርካሪ ስነ ባህርይ ደግሞ ዋናውን ድርሻ ይይዛል:: በመሆኑም ይህ ጉዳይ ልዩ ትኩረትን ይሻል፤ በእኛ አገር በጣም አደጋ እያደረሰ ንብረት እያወደመ ግን ደግሞ ቸል የተባለ ጉዳይ የትራፊክ አደጋ ነው:: በጣም ብዙ ህዝብ እየጨረሰ ኢኮኖሚን እያደቀቀ ግን ደግሞ ትኩረት ያልተሰጠው ነው:: ስለዚህ የአሽከርካሪ ስነምግባር ለውጥ ወሳኝ መሆኑን ተረድተናል::
ሌላው እንዳልሽው ቴክኒካል ምርመራ በሚያደርጉ የቁጥጥር ባለሙያዎች በኩል በትኩረት የሚታይ አይደለም:: አንዳንድ ተሽከርካሪዎች እኮ በተለይ አደጋ አድርሰው ሲታዩ እውነት ይህ ተሽከርካሪ ጎዳና ላይ መታየት ነበረበት ያስብላሉ:: ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ጠበቅ ማለት አለባቸው ብለን እናስባለን::
የእኛ ተቋም አደጋው ከደረሰ በኋላ በተለይም ገጭተው በሚያመልጡና የመድን ሽፋን በሌላቸው ላይ ትኩረቱን ያድርግ እንጂ ቅድመ አደጋም ከፍተኛ የሆነ ትኩረት ማግኘት አለበት ብለን ነው የምናስበው:: ከዚህ አንጻር ሥራዎቻችን ለምን ይበጣጠሳሉ የሚል አቋም አለን፡፡ ለምንስ ነው ወደ አንድ አምጥተን ሥራውን የማንሠራው በማለት ከአደጋ በፊት ያሉትንም ሥራዎች ጭምር ወደ አንድ ለማምጣት የተጀመረ እንቅስቃሴ አለ::
አዲስ ዘመን፦ እንቅስቃሴው ላይ በተለይ ኤጀንሲው በምን መልኩ ነው ተሳትፎ ያደርጋል ብላችሁ ያሰባችሁት?
አቶ ሽመልስ፦ ተቋማችንን ከፍ ወዳለ ኮሚሽን ደረጃ የማሳደግና ሥራዎቹንም ከትራፊክ ቁጥጥሩ ጀምሮ እስከ አደጋው ድረስ ያለውን ጉዳይ መከታተል የሚያስችል ሥራ መሥራት ነው:: ይህ ምንልባትም አደጋን በመቀነስ በኩል ሚና ይኖረዋል ብለን ስላሰብን አማራጩን እየተከተልን ነው:: ከጸደቀም በቀጥታ ሥራችን ይሆናል ማለት ነው::
አዲስ ዘመን፦ ይህ ኤጀንሲ ባይኖር ኖሮ ብለው የሚሉት ነገር አለ?
አቶ ሽመልስ፦ የኤጀንሲው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም ፤ አሁን ላይ መድረኮች እየተፈጠሩ መገናኛ ብዙሃንም ለኤጀንሲው ሥራ ትኩረት እየሰጡ ሲመጡ እንዲሁም የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና አገልግሎት ለተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች መብት ነው የሚለው ነገር መታወቅ ሲጀምር ኤጀንሲው ከመቋቋሙ በፊትና ከተቋቋመ በኋላም ባለማወቅ ጉዳት ደርሶባቸው እቤታቸው የተቀመጡ ሰዎች ሁሉ እየመጡ ነው:: በመሆኑም መኖሩ ችግርን ይቀርፋል፤ ምንም የሚያከራክር ነገር የለውም:: ባይኖር ደግም በተለይም ገጭተው በሚያመልጡና የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን በሌላቸው ተሽከርካሪዎች ጉዳት የሚደርስባቸው ሰዎች ከፍተኛ የሆነ ችግር ውስጥ ይገቡ ነበር::
ተሽከርካሪ እስካለ ድረስ አደጋ አለ ፤ ስለዚህ የኤጀንሲው መኖር ወሳኝ ነው ብለን እናስባለን፤ ግን አሁንም አሠራሮቹን ማሻሻልና አቅሙን ማጠናከር ቢችል የበለጠ ጠቃሚ ይሆናል::
አዲስ ዘመን፦ የቀጣይ እቅዳችሁ ምንድን ነው? ምንስ አዲስ ነገር ይጠበቃል?
አቶ ሽመልስ፦ አገልግሎታችንን ቀልጣፋ በማድ ረግ የሚንዛዙ አሠራሮችን መቀነስ ላይ ሰፊ ሥራ መሥራት አለብን ብለን እያሰብን ቢሆንም ይህንን ሥራ ግን ብቻችንንን ማከናወን የለብንም የሚል ነው አዲሱ አቋማችን በመሆኑም ባለድርሻ አካላት አብረውን እንዲሠሩ እናደርጋለን::
ከዚህ በተጨማሪም የኤጀንሲውን አቅም ከፍ በማድረግና ወደ ኮሚሽን ደረጃ የሚያድግበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየታሰበ ነው:: እዚህ ላይ ሳልገልጽ የማላልፈው ነገር መንግሥት ለትራፊክ አደጋ የሰጠው ትኩረት ላቅ ያለ መሆኑን ነው ፤ ከዚህ አንጻር ኤጀንሲው የበለጠ ተደራሽ ለመሆን መሥራት አለበት ብዬ አስባለሁ::
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይት በጣም አመሰግናለሁ::
አቶ ሽመልስ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 6/2012
እፀገነት አክሊሉ