በሀገራዊ ትውፊት እንንደርደር፤
ስለ ሀገራችን ሲነገሩ የኖሩና ወደፊትም ሲነገሩ የሚኖሩ በርካታ የማሕበራዊ ዕሴቶችና የባህላችን ትሩፋት ትርክቶች እንዳሉን ይታወቃል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደበዘዙና እየወየቡ የሚሄዱ እንዳሉም የሚዘነጋ አይደለም። ለምሳሌ፤ በየትኞቹም ብሔረሰቦቻችን መካከል በዕለት ግጭት፣ በሰነበተ ቁርሾ፣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለተፈጸሙ ጥፋቶችና ስህተቶች በግል፣ ውሱን ቁጥር ባለው ቡድንም ሆነ ሰፋ በሚል ማሕበረሰብ ደረጃ ይቅር መባባልና መታረቅ ሥር የሰደደና የተከበረ ባህላችን ነው።
በየማሕበረሰቡ ውስጥ ስለ እርቅ የሚነገሩ አባባሎች፣ ምሳሌዎች፣ ሥነ ቃላዊ ትርክቶች ለእኛ ኢትዮጵያዊያን እንግዳ አይደሉም። እንዲያውም አብዛኛው ማሕበራዊ መሠረታችን የታነጸው በሥነ ቃሎች ግብዓትነት መሆኑ በብዙ ማስረጃዎች ማሳየት ይቻላል። ከልደት፣ እስከ ልጅነት፣ ከወጣትንት እስከ ጉልምስና፣ ከሽምግልና እስከ ግባ መሬት የምንተርካቸው፣ የምንጠቅሳቸው፣ የምንመስላቸው፣ የምንመክርባቸውና በዕለት ተዕለት ኑሯችን ዘና የምንልባቸው ትውፊታዊና ማሕበራዊ ሀብቶቻችን ዝርዝራቸውም ሆነ ዓይነታቸው ብዙ ነው።
ለምሳሌ፤ ለዛሬው ጽሑፍ በመንደርደሪያነት የተጠቀምኩበትን እርቅ ነክ አባባሎች ከብዙ በጥቂቱ እንደሚከተለው አስታውሳለሁ።
- እርቅ የፈለገን ንጉሥ ገበሬ ያስታርቀዋል።
- እርቅ ያልፈለገን ገበሬ ንጉሥ አያስታርቀውም።
- እርቅ ከወርቅ፤ ዛላ ከምርቅ ይበልጣል።
- እርቅ አይፈርስ፤ ዐይን አይፈስ።
- እርቅ ቢፈርስ ካስታራቂው ድረስ።
- ሀገር ቢጠላህ አልፈህ አልፈህ ታረቅ።
- ታርቄ ተመርቄ፤ ታጥቤ ተለቃልቄ።
- ታርቆ ሙግት፤ በልቶ ስስት የለም።
እነዚህን መሰል እርቅ ተኮር አባባሎች በመላው ሀገሪቱ ውስጥ በሚገኙት ብሔረሰቦች ዘንድ በውብ ቋንቋቸው ውስጥ ማግኘት የሚቻለው በገፍና ያለስስት ነው። በተለይም በእርቅ ሂደት ውስጥ የአስታራቂ ሽማግሌዎች ሚናና ድርሻ ከፍ ያለ ስለመሆኑ ማስታወስ የአደባባዩን በአዋጅ አሰኝቶ አያስተርትም። በአባባሎች ተንደርድሬያለሁና ስለ አስታራቂ ሽማግሌዎች አዘውትረው የሚነገሩ ጥቂት አባባሎችን አስተውሼ ልለፍ።
- ሽማግሌ ካለበት ነገር አይናቅበት።
- ሽማግሌ ይገላግላል፤ የተጠቃ አቤት ይላል።
- ሽማግሌን ከምክርና ከእርቅ መለየት ከምግብ መለየት።
የተቀያየሙ፣ የተጣሉም ሆኑ ደም የተቃቡ ግለሰቦችና ቡድኖች የሚታረቁትና ይቅር የሚባባሉት በዕድሜ በከበሩ፣ በሽበት በደመቁ አዛውንቶች ብቻም ላይሆን ይቻላል። እኒህን መሰል ጎምቱ አበው ማሕበራዊ ቦታቸው ከፍ ያለና ድርሻውም የላቀ ቢሆንም በልጅነታቸው የበሰሉ፣ በጥቁር ጸጉር የሚከበሩ ወጣቶችም ለእርቅና ለሽምግልና ሊፈለጉ አይችሉም ማለት ግን አይደለም። ብስለቱና ማስተዋሉ ይኑራቸው እንጂ በዕድሜ ታናናሽ የሚባሉ ቁመነገረኛ ወጣቶችም ቢሆኑ የማስታረቅ ከባድ ኃላፊነት እንደሚጣልባቸው ውሏችንም ሆነ ተሞክሯችን የሚመሰክሩልን እልፍ አእላፋት ገጠመኞች እንዳሉ ይገባናል። በዕድሜ ያረጁ ሁሉ ፍትሕን በጽድቅ ያስከብራሉ ማለት አይደለም። ለእርቅ ሄደው ጠብ የሚያጋግሉ፣ ለመገላገል ሄደው ዱላ የሚያቀብሉ “አስታራቂዎች” ነን ባዮች በየቦታው እንደማይጠፉ ይታወቃል። ከእህል ውስጥ እንክርዳድ እንዲሉ።
“የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው!”
ግለሰብ ከግለሰብ፣ ብድን ከቡድን፣ ማሕበረሰብ ከማሕበረሰብ ቅሬታቸውን በእርቅና በሽምግልና ፈትተው ሰላም ያሰፈኑባቸው በርካታ ሀገራዊ ታሪኮችንና ተሞክሮዎችን እያጣቀሱ መዘርዘር የሚገድ አይደለም። የታሪክን መዛግብት ብንገልጥና አፋዊ ተረኮቻችንን ብንጠቃቅስ የምንመሰክረው አይቸግረንም። እንደ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ሕዝቦች እኛም ሀገራዊ የመታወቂያ ታሪካችን የሥነ ቃል ብልጽግናችን ስለሆነ።
ከግለሰብ፣ ከቡድንና ከማሕበረሰብ ተሞክሮ ከፍ ብሎ ሀገርና ሕዝብ በስፋት የተቀያየሙባቸውን አጋጣሚዎችንም እንፈላልግ ብንል በጠረናቸው ፖለቲካዊ ሽታ ያላቸውን በርካታ ታሪካዊ ክስተቶችንና ያስከተሉትን ውድቀትና ድቀት መጠቃቀሱም አይከብድም። “ኢትዮጵያዊያን ያልተሰደዱባቸውን ሀገራት መጥቀስ ያዳግታል!” እየተባለ እንደ ጀብድ የምንጠቅሰው ማስረጃም ሰበቡ የሀገርና የሕዝብ ጥል ውጤት ነው። ንፉግና ጨካኝ ሥርዓቶች የፈጠሩት ዳፋ። “እንዴት ሰው ከሀገሩ ጠብ ሊኖረው ይችላል፤ ከሥርዓተ መንግሥታት አንጂ” ተብሎ የሚጠየቅ ከሆነም የየወቅቱን ሥርዓት ወለድ ፖለቲካዊ ብልግና በዋቢነት እያጣቀሱ መከራከር ይቻላል።
የደርግ መንግሥት ሀገርን ከሕዝብ አጋጭቶ እና የእርሱም የግፍ ቁጣ ገንፍሎ እንደምን ባለሀገርነትን ባዕድነት አድርጎ እንዳለፈ አንዘነጋም። ብዙዎች ሀገራቸውንና ሥርዓቱን እየረገሙና እያነቡ ስደትን በመምረጥ መጻተኞችና ስደተኞች ሆነዋል። የባሰበት የኢህአዴግ የሃያ ሰባት ዓመታት አገዛዝ ደግሞ ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨትና ማጣላት ብቻ ሳይሆን ብዙኃንን ከሀገር ጋር በማኳረፍና በማላተም እጅግ የበረታ ጥፋትና ክፋት እንደፈጸመ ያልመሸበት ታሪካችንን ዋቢ መጥራት ይቻላል።
የትናንቱን ትተን በዛሬ እውነታችን ላይ እንቆዝም፤
በሀገሬ ቀደምት ታሪክ መንግሥትና ብዙኃን፣ ቡድን ከቡድን፣ ግለሰብ ከግለሰብ፣ ሃይማኖተኞች ከሃይማኖተኞች፣ የፖለቲከኞች ሸርም ቀላቅሎበት፣ ምንትስ ከምንትስ በጅምላ ተኮራርፈውና ተቀያይመው፣ አልፎም ተርፎ ወደ ከፋ ደረጃ ሲደርሱ በስፋት የሰማነው፣ ያየነውና የተደናገጥነው በዚሁ በእኛው የዕድሜ ጀንበር ላይ ነው። ይህን መሰሉ ክስተት ነባራዊና አሁናዊ ትዕይንት ስለሆነ እንደ ታሪክ የሚጠቀስ አይደለም።
ጉዳዩ “የወደቀ እንጨት ምሳር ይበዛበታል” ካልተባለ በስተቀር ባለፍንባቸው ሦስት ዐሠርት ዓመታት ሆን ተብሎ ሲሠራ የኖረው ሀገርና ሕዝብ እንዲጋጭና እንዲኳረፍ ታቅዶ እስኪመስል ድረስ ያዘመርናቸውንና እያዘመርናቸው ያሉትን ችግሮቻችንን እየመዘዝን በማሳያነት ማስታወስ ይቻላል።
እንዲያው በጠቅሉ ዛሬ እያናወጡን ያሉት ውስብስብ የችግር ሱናሚዎች ያለምንም ማወላወል ምንጫቸው የኢህአዴግ መንግሥት ሤራና ጦስ እንደሆነ ለማንም ግልጥ ነው። እነዚያ የትናንቶቹ መሪዎች ልባቸው እንደምን ለእርቅና ይቅር ለመባባል ደንድኖ እንደነበር ከበርካታ ገጠመኞች መካከል አንዱን ብቻ ለአብነት ማስታወስ ይቻላል። ይህንን ሁኔታ ማስታወሱ የቂም ስንቅ ተደርጎ እንዲታሰብ ከመፈለግ ሳይሆን ምናልባትም አሁን ሀገሪቱን እየመሩ ላሉት መሪዎች ትምህርት ሊሆን ይችል እንደሆን በማሰብ ነው።
ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት (መስከረም 2009 ዓ.ም) ሀገሪቱ በተቃውሞና በሕዝብ ቁጣ በተናጠችባቸው ሰሞን አንድ መቶ አሥር ያህል የሀገር ሽማግሌዎች፣ በመንፈሳዊ መሪነታቸው የፈጣሪን አደራ የተሸከሙ የሃይማኖት አባቶች፣ በላቀ ዕውቀታቸውና ምርምራቸው ትውልድንና ሀገርን ለማገልገል የሚተጉ ምሁራን፣ በተከበረ ምግባራቸውና ለሀገራቸው በፈፀሙት ተግባር የተመሰገኑ ምክር አዋቂ አዛውንቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ በኪነ-ጥበባት ተሰጥኦዋቸው የሕዝብን መንፈስ የገዙ ባለሙያዎችና የመገናኛ ብዙኃን ባልደረቦች የተሰባሰቡበት ጉባዔ በአንድ ሀገር በቀል የሃሳብ አምንጭ ቡድን ተዘጋጅቶ በወቅታዊው አሳሳቢ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ጠንከር ያለ ምክክር ተደርጎ ነበር።
የምክክር ይዘቱን “ጠንከር ያለ” የሚለው ሃሳብ ብቻ አይገልጸውም። ከዚያ ከፍ ያለ ነበር። የሀገሪቱ የጥፋት አቅጣጫ ያስጨነቃቸው ጉባዔተኞች በዕረፍት አልባ ትጋትና መነቃቃት ከማለዳ እስከ ምሽት የተጋጋለ ውይይት ካደረጉ በኋላ በማጠቃለያው ላይ በሀገሪቱ ላይ የተጋረጡትን ወቅታዊ ፈተናዎች ሊታደጉና በሰላም ሊያሳልፉ ይችላሉ ያሏቸውን አሥራ ስድስት ነጥቦችን አንጥረው በማውጣት በየደረጃው ለሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ወሳኝ ተቋማት እንዲቀርብ በመስማማት የሰላም ጉባዔያቸውን አጠናቀቁ።
ከአሥራ ስድስቱ ነጥቦች መካከል አንዱና ዋናው ሃሳብ “በሕዝባችን መካከል በስፋት እየተስተዋለ ያለው ኀዘንና ቅሬታ፣ ቂምና በቀል በጥልቀት ሥር ሰዶ የሀገሪቱን አንድነትና ሰላም አናግቶ ሊታረም የማይችል ጥፋት ከማድረሱ አስቀድሞ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በመላ ሀገሪቱ የምህረትና የይቅርታ አዋጅ ቢታወጅ።” የሚል ይዘት ነበረው።
ጉባዔው የወከላቸው ጥቂት ሰዎች ለሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ተቋማት የሰላም ጥሪያቸውን ለማድረስ በተንቀሳቀሱባቸው ቢሮዎች ሁሉ ተመካክሮ የተደረገ በሚመስል ሁኔታ የተሰጣቸው መልስ እጅግ የሚያሳፍር ብቻ ሳይሆን ሥርዓቱ እንደምን ልቡ ደንድኖ እንደገማ የሚያሳይ ጥሩ ማረጋገጫ ነበር። ሁሉም ኃላፊዎች ለመልዕክተኞቹ የሰጡት መልስ “ኢህአዴግ ከማንም ጋር ስላልተጣላ፤ ችግር ያለበት ግለሰብና ቡድን ይቅርታ መጠያየቅ ይችላል። ለጊዜው ኢህአዴግ ከማንም ጋር አልተጣላም፤ ከማንም ጋርም አይታረቅም” የሚል ነበር። እንዲያውም ከዋናዎቹ መሪዎች መካከል በአንቱታ የከበሩት አንድ መሪ “እኛ ኢህአዴጎች ቂምም ጥልም አናውቅም። እናንተ የስልሳ ስድስት ትውልዶች ችግር ካለባችሁ ሄዳችሁ እርስ በእርስ ታረቁ” የሚለውን እንደ ዕንቆቆ የመረረ መልስ ጸሐፊው በዘመኑ የሚረሳው አይደለም።
ልቡ እንደ ፈርዖን የደነደነው ኢህአዴጋዊው ሥርዓት የማታ ማታ ተንኮታኩቶ ወደ ግባ መሬቱ የገባው ሕዝቡ የንስሐ ዕድል ሰጥቶት ራሱን ማለዘብ ባለመቻሉ ነበር። ያን መሰል መራራ መልስ የሰጡ ሹማምንት ዛሬ የዴሞክራሲ ጠበቃና የሕፃኑ የብልፅግና ፓርቲ ሞግዚቶች ነን ብለው አደባባዩን ሲያደምቁ ማስተዋል እነርሱን ሳይሆን የሚያሳፍረው እኛን ነው። እነርሱማ ከኅሊናቸው ጋር ቁርባናቸውን ካረከሱ ሰንብተዋል።
እኮ ምን ይደረግ?
ዛሬም ሰሚ ከተገኘ መሪዎቻችን ማስቀደም ያለባቸው አንድ መሠራዊ አጀንዳ ነው። ስያሜው ምንም ሊባል ይችላል። ቢያሻ “ብሔራዊ ዕርቅ”፣ ካስፈለገም “ብሔራዊ መግባባት” በሚሉ መሪ ሃሳቦች ሁሉን አቀፍ የሆነ ጉባዔ ተዘጋጅቶ ራስን በንስሐ ማፅዳቱ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም። እንደ አምና ካቻማና መሪዎች የአመራሩን ኮምፓስ የጨበጡ መሪዎቻችን ዛሬም የትናንቱን የማንአለብኝ ዜማ እያንጎራጎሩ “ዕርቅ የሚያስፈልገው ማን ከማን ስለተጣላ ነው?” ብለው እውነታውን የሚያጣጥሉ ከሆነ ጊዜያችን በከንቱ ባክኖ ይከንፍ ካልሆነ በስተቀር እንደ መጥምቁ ዮሐንስ በምድረ በዳ የምንጮኸው ጩኸት ቀን ቆጥሮ “መሲሁን” ማዋለዱ አይቀርም።
በሉ ደፍረን እንነጋገር! ሕዝብና ሀገር ተኮራርፈዋል። በሚገባ። እኮ እንደምን ኩርፊያው ሳይበርድ ለሀገራዊ ምርጫ ቀጠሮ ይያዛል? መጠየቅ መብታችን ስለሆነ እንጠይቃለን። ቤተ እምነቶቻችን በጤና ውለው እያደሩ ነው? ኩርፊያና ቂም የለም? ብሔር ብሔረሰቦቻችን በፍቅር እጅ ለእጅ እንደተጨባበጡ ነው? ይህንንም እንጠይቃለን። የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን የሰላም እንቅልፍ ተኝተው ያድራሉ? ጌቶቻችን ቢቆጡም ይቆጡ እንጂ አምርረን እንጠይቃለን። የፖለቲካ ህመምተኞች ሕክምናቸውን ጨርሰው አደብ ገዝተዋል። አክቲቪስቶችስ ከግፋ በለው ቀረርቷቸው ፋታ አግኝተው ሰክነዋል? በሀገራችን ወርድና ስፋቷ ልክ እንደልብ ተዘዋውረን መኖርና መሥራት እንችላለን? አስሬ የተጠየቀውን ጥያቄ አስሬ መልሰን እንጠይቃለን። “እኮ ያ ቀን ዛሬ ካልሆነ መቼ ሊሆን ይችላል” ብሎ ለምርጫ መንደርደር ለከፋ እርግጫ እንዳይዳርግ እንደ ዜጋ እንጨነቃለን።
ስለዚህ፤ ከፖለቲካው ሥልጣን መጨበጫ ምርጫ በፊት ሀገር አቀፍ የብሔራዊ እርቅ ያስፈልገናል። የሕዝብ ቆጠራውን ከመጀመራችን አስቀድሞ ሀገራዊ መግባባትን ልናስቀድም ይገባል። እንዴትና መቼ? ለሚሉ ጥያቄዎች ጸሐፊው ዝግጁ የሆነ መልስ የለውም። የእርሱ ጩኸት በየጥጋጥጉ የገነባናቸውን “የኢያሪኮ ግንቦች” በይቅርታ ጩኸት እናፍርስ የሚል ምክረ ሃሳብ መሰንዘር ብቻ ነው። ልብ ያለው ልብ ያድርግ። የዘንድሮ ቆሌ ከትናንቱ አዋይ ጋር ተስማምቶ የደም ግብር ሳያስከፍለን በፊት እንንቃ። ቀድመን ከራሳችን ጋር ታርቀን ወደ ሌላው ወገን እንዘርጋ። ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን ጥር 6/2012