በቀጣይ ሳምንት መጀመሪያ የሚውለውን የጥምቀት በዓልን ለማክበር የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ሽርጉድ ላይ ናቸው። በእኔ አተያይ ጥምቀት በተለይ በጎንደር ልዩ ክብረበዓል ነው። በዓሉ በተለይ በዩኔስኮ ከተመዘገበ በኋላ የሚከበር የመጀመሪያው በዓል መሆኑ ለየት እንደሚያደርገው እየተገለጸ ነው። በበዓሉ ላይ ከውጭ አገር ይመጣሉ ተብለው ከሚጠበቁት እንግዶች መካከል ለኤርትራውያን ላቅ ያለ ግምት ተሰጥቷል። ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ ከዘለቀው ቁርሾ በኋላ የወረደው ሠላምና አዲስ ግንኙነት መሠረት ኤርትራውያን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ጎንደርን እንደሚያጨናንቋት ተገምቷል።
ስለጎንደር ተነሳ እንጂ የጥምቀት በዓል በመላ አገሪቱ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ በደማቅ ሁኔታ የሚከበር በዓል ነው። በዓሉ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ጥር 11 ቀን የሚከበረውን የጥምቀት በዓል በዓለም አቀፍ የማይዳሰስ ቅርስነት እንደመዘገበው ታህሳስ 1 ቀን 2012 ዓ.ም ገልጧል። ድርጅቱ ይህንን ውሳኔ ያደረገው በኮሎምቢያ፣ቦጎታ ባካሄደው ስብሰባው ነበር።
አንዳንድ ነጥቦች ስለጥምቀት
በሰው ልጅ ዘላለማዊ ድኅነት ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ሥርዓተ ጥምቀት ከሌሎቹ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን በቀዳሚነት የሚፈጸምና የማይደገም ሥርዓት ነው። “ጥምቀት” የሚለውን ቃል አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሲተረጉሙ “ጥምቀት” በቁሙ፡- “ማጥመቅ፣ መጠመቅ፣ አጠማመቅ፣ ጠመቃ፣ የማጥመቅና የመጠመቅ ሥራ፣ ኅፅበት፣ በጥሩ ውኃ የሚፈጸም” በማለት ተርጉመውታል። ምሥጢረ ጥምቀትን የመሠረተው ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ጌታችን ሥርዓተ ጥምቀትን የመሠረተው በሦስት ዓይነት መንገዶች እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል።
የበዓለ ጥምቀት አከባበር በኢትዮጵያ የተጀመረው የክርስትና እምነት እንደገባ መሆኑ ይታመናል። እስከ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ግን የጥምቀት በዓል አሁን በምናከብርበት ሁኔታ የሚታሰብ አልነበረም። በዓለ ጥምቀትን በሜዳና በውኃ አካላት ዳር ማክበር የተጀመረው በዓፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግስት (530 እስከ 544 ዓ.ም.) እንደሆነ ይነገራል። ይህም ከማኅሌታዊው ቅዱስ ያሬድ (505 እስከ 572 ዓ.ም.) ዜማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ታቦታቱ በየዓመቱ ጥር 11 ቀን ጠዋት ወደ ወንዝ ወርደው ማታ ወደ መንበረ ክብራቸው እንዲመለሱ ይደረግ ነበር።
ጻድቁና ጠቢቡ ንጉሥ ላሊበላ (1140 – 1180 ዓ.ም.) ሁሉም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ለየብቻቸው በሚቀርባቸው ቦታ በተናጠል ሲፈጽሙት የነበረውን ክብረ በዓል አስቀርቷል። በምትኩም በአንድ አካባቢ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በአንድነት ተሰባስበው በአንድ ጥምቀተ ባሕር እንዲያከብሩ ትእዛዝ አስተላልፏል። ይህም ተግባራዊ በመሆኑ የበዓሉ አከባበር ሥነ ሥርዓት ቅንጅትና ድምቀት እንዲኖረው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ሀ/ በዋዜማው ጥር 10 ቀን
በየሰበካው ቦታ ተለይቶና ተከልሎ ታቦታቱ በዳስ ወይም በድንኳን የሚያድሩበት፣ የተለያዩ የውኃ አካላት ተጠርገው የሚከተሩበት ወይም ሰው ሠራሽ የግድብ ውኃ የሚበጅበት ስፍራ “ባሕረ ጥምቀት”፣ “የታቦት ማደሪያ” እየተባል ይጠራል። ባሕር፡ የውኃ መሰብሰቢያ /ምእላደ ማይ/፣ የውኃ መከማቻ /ምቋመ ማይ/ ነው። በሌላ አነጋገር “የውኃ አገር” /መካነ ማይ፣ ዓለመ ማይ/ ነው። ጥምቀት፡ ከውኃ መንከር፣ መዝፈቅ፣ ከውኃ ማግባት፣በውኃ ማጠብ፣ ውኃን በራስ ገላ ላይ ማፍሰስ፣ መቸለስ፣ መርጨት፣ ማረብረብ ሲሆን፣ ምጥማቃት ሲል ደግሞ መጥመቂያ፣ ማጥመቂያ፣ መጠመቂያ ቦታ ማለት ነው /ኪ.ወ.ክ፡ 261 እና 502-503/። በመላው ኢትዮጵያ የታነጹት ከ20,000 በላይ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ጥር 10 ቀን በየአካባቢያቸው በተመደበላቸው አብሕርተ ምጥማቃት ይወርዳሉ። ካህናቱም ስብሐተ እግዚአብሔር ሲያደርሱ ያድራሉ። በመንፈቀ ሌሊትም ሥርዓተ ቅዳሴው ተጀምሮ ከሌሊቱ በ9 ሰዓት ሡርሆተ ሕዝብ ይሆናል።
በአክሱም የንግሥት ሳባ መዋኛን “ማይ ሹም”፣ በጎንደር የዐፄ ፋሲል መዋኛን፣ በላስታ የላሊበላ መዋኛን፣ በሸዋ የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ፍርድ መስጫ አደባባይን፣ አርባ አራት ታቦታት የሚያድሩበትን የሸንኮራ ሜዳን “ራቡቴ ወንዝ”፣ በአዲስ አበባ ደግሞ ጃንሆይ ሜዳን ጃንሜዳን ለአብሕርተ ምጥማቃት እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። እኒህ ቦታዎች ዛሬም ድረስ ተከብረው ይገኛሉ።
“የቃል ኪዳኑን ታቦት አክብሮ /ይዞ/ መጓዝና ወደ ወንዝ መውረድ የተጀመረው በአሮን ልጅ በአልአዛር ጊዜ ነው። ኢያሱ በሙሴ እግር ተተክቶ ሕዝበ እስራኤልን እየመራ ከዮርዳኖስ ወንዝ ሲደርስ ባሕሩ ከሁለት ይከፈልና ወራጁም ይቆም ነበር። እስራኤል ዘሥጋ ወደ ምድረ ርስት ለመግባት የዮርዳኖስን ወንዝ ሲሻገሩ፡ ድንኳን ጥለው የቃል ኪዳኑን ታቦት በድንኳን ውስጥ አድርገው ሌዋውያኑ በዙሪያው፣ ካህናቱ ደግሞ በውስጥ ሆነው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ አድረው ተሻግረዋል /መጽ ኢያሱ 3፡8-9/። የጥምቀት ዋዜማ “ከተራ” ተብሎ ይጠራል።
“ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት አክብረው /ይዘው/ የወንዙን ዳርቻ በረገጡበት ጊዜ እንደ ክረምት ማዕበል ይወርድ የነበረው ውኃ ግራና ቀኝ ተከፍሎ እንደግድግዳ ወደ ላይ ቆሟል። ሕዝቡ ተሻግሮ እስከሚያበቃም ታቦተ ጽዮንን ያከበሯት /የያዙት/ ካህናት ከወንዙ መሃል ቆመው ነበር። በዚህ መሠረት “ወተጠምቃ እገሪሆሙ ለካህናት” ተብሎ ተጽፏል። ይህም “የካህናት እግር የዮርዳኖስን ውኃ በመርገጡ እንደ ጥምቀት ሆናቸው” ማለት ነው። ቤተ ክርስቲያናችን የጥምቀትን ዋዜማ ከተራ ብላ የጠራችው ከዚህ በመነሳት ነው። ከተራ ማለት መዝጋት፣ ማቆም፣ ማገድ፣ ማጠር፣ ዙሪያውን መያዝ፣ መክበብ፣ መከለል ማለት ነው።
ታሪኩ ከጌታችን ጥምቀት ጋር በተያያዘ ምሳሌነት አለው። ጌታችን በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀበት ጊዜ የላይኛው ሸሽቶ ወደ ላይ ተመልሶ ሽቅብ ፈሷል። የታቹም ወደታች ሸሽቷል። የላይኛው ፈሳሽ ተቋርጦ እንደክምር ተቆልሎ መቅረቱ፣ ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ድረስ በዘር ይወርድ የነበረው ፍዳ መርገም በክርስቶስ ቤዛነት ተቋርጦ ለመቅረቱ፣ ከአበው ወደ ውሉድ ላለመተላለፉ፣ የታችም ፈጽሞ መድረቁ ኃጢአተ አዳም ከሥሩ እንደተነቀለ ወይራ ሆና ለመውደቋ ምሳሌ ነው። እስራኤል ፈለገ ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ኢያሪኮ አቅንተው መሄዳቸው ምእመናን በጥምቀት ከቁራኝነት ተላቀው እግራቸውን ወደ ልምላሜ ገነት፣ ወደ እረፍት መንግስተ ሰማያት አቅንተው ለመሄዳቸው ምሳሌ ነው።
በጠቅላላ ኢያሱ የጌታ፣ እስራኤል ዘሥጋ የምእመናን፣ ዮርዳኖስ የጥምቀት፣ ምድረ ርስት የገነት መንግስተ ሰማያት ምሳሌ ነው። ለአይሁድ በትእዛዝ ከታወጁት ስምንት በዓላት አንዱ የዳስ በዓል /በዓለ መጸለት/ ነው። ይህም የአዝመራ መክተቻ በዓል ነው። በሰባተኛው ወር በአሥራ አምስተኛው ቀን እህል ከተከማቸ በኋላ የእስራኤል ልጆች ለሰባት ቀናት ዳስ ጥለው ድንኳን ተክለው እየተቀመጡ አምላካቸውን ያመሰግኑ ነበር /ዘሌ 23፡39-42/። የበዓለ መጸለት ምሳሌነቱ ለሐዲስ ኪዳኑ በዓለ ጥምቀት ነው። ይህም ዛሬ እኛ በዚህ ወቅት ታቦት ይዘን፣ ከወንዝ ወርደን፣ ድንኳን ተክለን በማክበራችን ይፈጸማል።
ቀደም ባለው ጊዜ የአንድ አጥቢያ ታቦት በከተራ ዕለት የሚወርደው ከአንድ የተወሰነ ቦታ ብቻ ሳይሆን በየሰበካው አቅጣጫ ነበር። ታቦቱ የወረደበት ሰፈር ድግስ ይደገሳል። ይህም በየዓመቱ ስለሚለዋወጥ ሕዝቡ ደስ ብሎት ያደርገዋል። በገጠሩ ክፍል ውኃ በማይገኝበት አካባቢ ወንዶቹ ለባሕረ ጥምቀቱ ይሆን ዘንድ እየቆፈሩ ይከትራሉ። ሴቶች ደግሞ ከሩቅ ቦታ እየሄዱ ውኃ በእንስራ እየቀዱ እያመጡ የከተራው ግድብ በውኃ ተሞልቶ የዮርዳኖስን ባሕር እንዲመስል ያደርጉታል። ታቦተ ሕጉ ለአዳር ሲጓዝ እናቶች ለበዓሉ መስተንግዶ ምግቡንና መጠጡን አሰናድተው ካህናቱንና በባሕረ ጥምቀቱ የሚያድሩትን ይጋብዛሉ።
ጥር 10 ቀን /ከተራ/ ቅዳሜና እሁድ ገጥሞ በዓለ ሰንበት ካላገደ በቀር በዚህ ቀን ገበሬው ሞፈር ቀንበሩን አቀናብሮ በቅርብ ማሳ ላይ በሮዎቹን ጠምዶ መሬቱን ተልሞ አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት ፈር ከዚያም በላይ ቢሆን ማረስ የተለመደ የሃገር ባህልና ልማድ ነው። በዚህ ቀን መሬቱ ሲተለም ረድኤት፣ በረከት እንደሚገኝ ያምንበታል /ዶር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ፡ የቤተ ክርስቲያን የአማርኛ መዝገበ ቃላት፡ቅጽ 12፡ ገጽ 196/
ጥር 10 ቀን ከቀኑ በአራት ሰዓት በመላው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ዋዜማ ይቆማል። ከሰዓት በኋላ ታቦታቱ በተለያየ ሕብር በተሸለሙ የክህነት አልባሳት በደመቁ ካህናትና የመጾር መስቀል በያዙ ዲያቆናት ከብረው፣ ከቤተ መቃድስ ወደ ቤተ አብሕርተ ምጥማቃት ለመሄድ ሲነሡ መላው አብያተ ክርስቲያናት የደወል ድምጽ ያሰማሉ። ምእመናን ከልጅ እስከ አዋቂ በነቂስ ወጥተው በአጸደ ቤተ ክርስቲያንና ታቦታቱ በሚያልፉባቸው መንገዶች ይሰበሰባሉ። ካህናቱ “ወረደ ወልድ ውስተ ምጥማቃት በፍስሐ ወበሰላም፣ ቅድመ ዓለም የነበረ እግዚአብሔር ወልድ በሰላምና በደስታ በእደ ዮሐንስ ለመጠመቅ ከሰማያት ወረደ፤ ከዊኖ ሰብአ በዮርዳኖስ ተጠምቀ፣ ሰው ሆኖ በዮርዳኖስ ተጠመቀ” እያሉ ይዘምራሉ። እልልታ፣ ሆታ፣ሃሌታ፣ ግርግርታ ይሰማል። የሰንበት ት/ቤት መዘምራን በዝማሬና በሽብሸባ፣ ጎበዙ በሆታ፣ ሴቶች በእልልታ… ሁሉም በሚረዱት መንገድ እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ። ታቦታቱን አጅበው ወደ ባሕረ ጥምቀቱ በኅብረት ያመራሉ።
በአጠቃላይ በበዓለ ጥምቀት ዋዜማ የታቦታቱ ወደ ወንዝ መውረድና የባሕረ ጥምቀቱ መዘጋጀት የሚከተለው ሃይማኖታዊ ታሪክና ምሳሌ አለው። ታቦቱ የጌታችን፣ ታቦቱን አክብሮ /ይዞ/ የሚሄደው ካህን የቅዱስ ዮሐንስ፣ ባሕረ ጥምቀቱ የዮርዳኖስ ወንዝ፣ ታቦታቱን አጀበው የሚሄዱትና በዓሉን የሚያከብሩት ምእመናን ወደ ዮሐንስ እየመጡ የንስሐ ጥምቀት ሲጠመቁ የነበሩት ሰዎች ምሳሌዎች ናቸው። ታቦታቱ በጥምቀት ዋዜማ ከመንበራቸው ወደ ጥምቀተ ባሕር መውረዳቸውና በዚያ ማደራቸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ከማታው ጀምሮ መውረዱንና ተሰልፎ ተራውን ሲጠብቅ ማደሩን ያጠይቃል። “ጥምቀት የሞቱ አርአያ፣ የመቃብሩ አምሳል ነው።
ከኃጥአን ጋር ተቆጥሮ እንዲጠመቅና እንዲሰቀል የተጻፈውን ቃል ንስሐና ጥምቀት የሚሻ ፍጹም ኃጥእ መስሎ በዮሐንስ እጅ ለመፈጸም በዮርዳኖስ እግር ተጠመቀ።” /ኪ.ወ.ክ. 517/። ጌታችን የተጠመቀበት ወርኀ ጥር በእስራኤላውያን ዘንድ የዝናም፣ የበረዶ ወራት ነው። እንኳንስ ከወንዝ ዳር ከማናቸውም ቦታ ቢሆን ያለ መጠለያ መዋልና ማደር አይቻልም። በመሆኑም ከዮሐንስ ለመጠመቅ የሚሄዱ ሰዎች ሁሉ በዮርዳኖስ ዙሪያ ድንኳናቸውን ተክለው ያርፉ ነበር። በዚህ አንጻር ዛሬም በባሕረ ጥምቀት ዙሪያ በድንኳኖች የተከለሉ ዳሶች ይጣላሉ።
ለ/ በዕለቱ ጥር 11 ቀን የበዓለ ጥምቀቱ አከባበር
ጥር 11 ቀን ንጋት፡ ካህናቱ ባሕረ ጥምቀቱን ከበው መጽሐፈ ጥምቀት ይነበባል። ተስማሚው ቃል እግዚአብሔር ደርሶ ሲያበቃ ጥምቀቱ የሚገኝበት ቦታ መንበረ ፓትርያርክ ያለበት ከሆነ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ የመንበረ ጵጵስና ቦታ ከሆነ ሊቀ ጳጳሱ፣ ጳጳሱ ወይም ኤጲስ ቆጶሱ፣ ይህም ካልሆነ ቆሞስ አልያም በቦታው በክብርና በሥልጣን የሚበልጠው ካህን ወይም ገባሬ ሠናይ ቄስ ባሕረ ጥምቀቱን ይባርካል። አራት የሚበሩ ጧፎች የታሰሩበት መስቀለኛ እንጨት ወደ ባሕሩ ይለቀቃል። ይህም ጌታችን ሲጠመቅ ብርሃን የመውረዱ ምሳሌ ነው። ጸሎተ አኮቴት ደርሶ ሥርዓተ ቡራኬው ከተፈጸመ በኋላ ሕዝቡ በረከት ለመቀበል እየተጋፋ ጠበሉን እየተሻማ ይረጫል። …
ምእመናኑ በመረጨትም ይሁን በዋና ቡራኬ ካገኙ በኋላ ታቦታቱ ካደሩበት ወጥተው በተዘጋጀላቸው ቦታ ይቆማሉ። መዘምራንም ከታቦታቱ ፊት “ኀዲጎ ተስዐ ወተስዐተ ነገደ ቆመ ማዕከለ ባሕር ገብአ ወወፅአ በሰላም፤ ዘጠና ዘጠኙን የመላእክት ነገድ ትቶ በባሕር መሀል ቆመ” የሚለው ግስ በባለተራው /የምራት ባለተረኛ/ ደብር መሪነት ተቃኝቶ ይሸበሸባል። የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችም በዓሉን የተመለከተ መንፈሳዊ መዝሙር ይዘምራሉ።
የበዓሉን መንፈሳዊ ታሪክ የተመለከተ ትምህርት ይሰጣል። በተገኙት አባት ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ ተሰጥቶ ካህናቱ “ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ” የሚለውን ግስ እየዘመሩ ታቦታቱን ከድንኳን አንስተው መንቀሳቀስ ሲጀምሩ እልልታው ይደምቃል። መንገዶች በሕዝባዊ ማዕበል ይጥለቀለቃሉ። ሕዝቡ ግን ግፊያውን አይሰቀቀውም። ይልቁንም ለእግዚአብሔርና ለቅዱሳኑ ካለው ፍቅር የተነሣ ላቡን እያፈሰሰ፣ ፍጹም ኃይል በተሞላበት ደስታ እያመሰገነ ታቦታቱን አጅቦ ጉዞውን ይቀጥላል። …
ሁሉም በየወገኑ እንዲህ ባለው ሁኔታ በክብር አጅቦ ያወጣውን ታቦት በክብር አጅቦ ወደ ቤተ መቅደሱ ይመልሳል። ታቦታቱ ከጥምቀተ ባሕር ተነስተው ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄዳቸው፣ ጌታችን ከተጠመቀ በኋላ ሳይውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ መሄዱን ያጠይቃል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በገዳመ ቆሮንቶስ ትመሰላለች።
የበዓለ ጥምቀት ትውፊታዊ አከባበር በስብከት ከሚገለጠው ይልቅ የተጨበጠ ክርስቲያናዊ ማስረጃ ሆኖ ክርስትናን ጠብቆ ኖሯል። ብዙዎች ጥንታዊውን ክርስቲያናዊ ትውፊት በተመለከቱ ጊዜ እናት ቤተ ክርስቲያናቸውን እያስታወሱ የሚመለሱበት ታላቅ ምክንያት ሆኗል። በማኅበራዊ ኑሮና በባህል በኩል ደግሞ ሕዝብ ከሕዝብ የሚገናኝበት፣ የግል ስሜቱን የሚገልጥበት፣ ባህላዊ ጨዋታን የሚያሳይበት ዕለትና በዓል ስለሆነ ሕዝቡ በናፍቆት ይጠብቀዋል። (ማጣቀሻዎች፡-የአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት፣ ማኅበረ ቅዱሳን፣ ሐመር )
አዲስ ዘመን ጥር 6/2012
ፍሬው አበበ