የኅብረተሰባችን ግማሽ አካል፣ የቤተሰብ መሠረትና ምሰሶ፣ እናትና እህት ወዘተ የሆኑት ሴቶች በአገር ግንባታም ሆነ በቤተሰብ አኗኗር ውስጥ ያላቸውን ሚና በዚህች ትንሽ ጽሑፍ ለመዘርዘር መሞከር ዓባይን በጭልፋ ይሉትን ብሂል ያስታውሳል።
እናቶቻችን በከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ውስጥ ሆነውና ለመናገር የሚከብድ መስዋዕትን ከፍለው ልጆቻቸውን የተሻለ ደረጃ ለማድረስ ዕድሜ ዘመናቸውን ሁሉ ታትረዋል። ከአገር ግንባታ እስከ የአገር ሉዓላዊነትን ማስከበር የተጫወቱት ታላቅ ሚናም በታሪክ መዝገብ ውስጥ በወርቃማ ቀለም ተጽፎ ለዘላለም እንደደመቀና እንዳበራ የሚኖር ታላቅ የታሪክ ገድል ነው!
ግን ይህን መሰል መተኪያ የለሽ ሚና ያላቸው ሴቶች በታሪክ ሂደት እጅግ አስከፊ የጭቆና ቀንበርን ተሸክመው መኖራቸውን የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ፍንትው አድርገው ያሳዩናል። ቤተሰብን በመንከባከብ፣ የቤት ውስጥ አታካችና አድካሚ ሥራዎችን ያለምንም ረዳት በመሸከም፣ ልጆች በማሳደግ ወዘተ አገርና ቤተሰብን ተሸክመው እዚህ አድርሰውናል። ለዚህም ነው ሴትነት ጀግንነት ነው ተብሎ ሁሌም የሚወደሰው!
እንደተቀረው ዓለም ሁሉ በሀገራችንም ሴቶች ለአገር፣ ለቤተሰብና ለማኅበረሰቡ ተኪ የሌለው ሚና ቢጫወቱም ውለታቸው ተዘንግቶ እጅግ መራራ ሕይወት ሲገፉ መኖራቸው የአደባባይ ሀቅ ነው። ሀገራችን አሁን ላለችበት ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ መገኘትም ለሴቶች የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑ የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሴቶች በካቢኔና በትልልቅ መንግሥታዊ የሥራ ኃላፊነቶች ላይ መሾም፤ በመኖሪያ ቤቶች ክፍፍል ላይ ትኩረት ማግኘት እና የልማት ሥራዎችን በማቀላጠፍ የሴቶችን ጫና ለመቀነስ ወዘተ የተደረጉ ሙከራዎች ሊበረታቱ እና ተጠናክረው ሊቀጥሉ የሚገባቸው ጉዳዮች ናቸው።
ይሁንና ከችግሩ ክብደትና ለረጅም ዘመን ተንሰራፍቶ ከመቆየቱ ጋር በተያያዘ የተሰራው ሥራ ካልተሰራው ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ዛሬ ማንሳት የፈለግነው ለሴቶች ንጽህና መጠበቂያ የተሰጠው ትኩረት አናሳነትና ይህንንንም ተከትሎ ሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ማህበራዊ ጫና ነው።
ታኅሣሥ 30/2012 ዓ.ም በፕሬዚዳንቷ ጽ/ቤት በአንድ ትልቅ ጉዳይ ላይ የምክክር ስብሰባ ተደርጎ ነበር። በዚህ የምክክር ስብሰባ የተመከረበት ጉዳይ «የወር አበባና የሴቶች ንህጽና መጠበቂያ» የሚል ነበር። በመድረኩ ክብርት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ እንደተናገሩት «የወር አበባ የሴት ልጅ ወደ አንድ ትልቅ የዕድገት እርከን መሸጋገር ምልክትና የትውልድ መቀጠልም አንዱ ሂደት ነው።
ይሁንና ለዚህ ትልቅና በሴቶች ሕይወት ላይ ከፍተኛ ድርሻ ላለው ጉዳይ የተሰጠው ትኩረት በጣም አነስተኛ ነው። ይህን ሂደት እንደመርገም ከመቁጠር ጀምሮ፣ ከንጽህና መጠበቂያ እጥረት ጋር በተያያዘ በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለው የጤና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እጅጉን ከፍተኛ ነው። በመሆኑም ለዚህ ትልቅ ጉዳይ መንግሥት፣ ኅብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት ለየት የለ ትኩረት ለሲጡት» ይገባል።
በምክክር መድረኩ እንደተነሳው ከግንዛቤ ጉድለት የተነሳ በወር አበባ ወቅት በሴቶች ላይ የመገለል፣ በዚህ ጉዳይ ብቻ በወር ውስጥ እስከ አምስት ቀን ከትምህርት ማቋረጥ፣ የንጽህና መጠበቂያዎችን ለመጠቀም የሚያስችል አቅም በማጣት ለተለያዩ ኢንፌክሽኖች የመጋለጥ ጉዳቶች ይደርሱባቸዋል።
ከውሃ እጥረትና ከመገልገያዎች ምቹ አለመሆን ጋር ተያይዞ በገጠር በሚኖሩና አካል ጉዳተኛ ሴቶች ላይ የሚደርሰው ጉዳት ደግሞ ከዚህም እጅግ የላቀ ነው። ከዚህ በበለጠ አሳሳቢውና በመድረኩ ከአንድ ተሳታፊ የተነሳው አነጋጋሪ ጉዳይ ደግሞ በሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ላይ የተጣለው የግብር መጠን ከ67 እስከ 122 በመቶ የሚደርስ መሆኑ ነው። የኢኮኖሚ አቅም ደካማ በሆነበትና የቅንጦት ዕቃ ባልሆነው በሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ላይ ይህን ያህል የግብር መጠን መኖሩ እጅግ አሳሳቢ ነው።
ከላይ እንደጠቀስነው በወር አበባ ወቅት ከኢኮኖሚ አቅም አናሳ መሆን ጋር ተያይዞ ብዙ ሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ገዝተው መጠቀም አይችሉም። ይሄም ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የጤና ጉዳቶች እየዳረጓቸው ነው። የንጽህና መጠበቂያዎቹ ዋጋም ዕለት ዕለት እየናረ በመሄድ ላይ መሆኑም እየተነገረ ነው። ስለሆነም እንደ ሲኤን ኤን ጀግናዋ ፍሬወይኒ መብራህቱ እየታጠቡ ለረጅም ጊዜ የሚያገለግሉ የንጽህና መጠበቂያዎችን ከማምረቱ ጎን ለጎን የታክስ ሕጉንም ፈትሾ አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 4/2012