
መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የተጀመረው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እነሆ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ሲከናውን ቆይቶ አሁን ፍሬ ሊያፈራ ከጫፍ ደርሷል። ፕሮጀክቱ ይጠናቀቃል ተብሎ ከተያዘለት ጊዜና ወጪ አንጻር ውስንነቶች ቢኖሩበትም በተለይ በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ፈጣን ማስተካከያዎችን በማድረግ ግንባታው እየተፋጠነ ይገኛል። በቀጣዩ ዓመት መጀመሪያም በሁለቱ ዩኒቶቹ አማካይነት ሃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ይጠበቃል።
ይህ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን መንግስትና መላው ህብረተሰብ ለዓመታት ጥረዋል። ዜጎች ከጉድለታቸውም ጭምር በመቆጠብ ለግድቡ ዕውን መሆን ከ15 ሺህ የሚበልጡ ዜጎች በስራው ላይ ተሳትፈዋል። በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች በገንዘባቸው፣ በንብረታቸውና በእውቀታቸው ተረባርበዋል። መንግስትም ግልፅነትን ለመፍጠር በአንድ በኩል ከተፋሰስ አገራት ጋር በየጊዜው ውይይቶችን ሲያካሄድ የቆየ ሲሆን በሌላ በኩል የግንባታው ሂደት እንዲፋጠን ሃላፊነቱን ሲወጣ ቆይቷል። ባለፈው ሳምንትም ከስምምነት ላይ ባይደረሰም ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የሶስትዮሽ ውይይት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። ውይይቱ ያልተሳካው ግን ግብጽ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ባላት የተዛባ ምልከታና እኔ ብቻ ልጠቀም የሚል አመለካከት እንደሆነ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የምትከተለው አቅጣጫ ግልፅ ነው። ይህንንም በተደጋጋሚ ለዓለም ማህበረሰብ ጭምር ይፋ አድርጋለች። በተለይ የግድቡ መገንባት ማንንም ለመጉዳት ሳይሆን ይልቁንም ሁሉንም የታችኛው የተፋሰሱ አገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ሱዳንም ይህንን የኢትዮጵያ አቋም በመገንዘብ እስካሁንም ድረስ ለፕሮጀክቱ ያላትን ድጋፍ እየገለጸች ትገኛለች።
ይሁን እንጂ በግብጽ በኩል ያለው አመለካከት በተደጋጋሚ ከዚህ የተለየ ሲሆን ይስተዋላል። “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” እንዳለችው እንስሳ አባይን ማንም አይንካ የሚለው የግብጽ ግትር አቋም የተሳሳተና የሁለቱን አገራት ግንኙነትም የሚያሻክር ነው። 80 ከመቶ የሚሆነውን የአባይን ውሃ የምታመነጨው ኢትዮጵያ ሆና እያለ የውሃው መዳረሻ የሆነችው ግብጽ የራሷን ጥቅም ብቻ በማየት መነሳቷ አዋጭና ዘላቂ መንገድ አይደለም።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን መሆን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው። በተለይ ለአካባቢ ጥበቃ ስራ ያለው አስተዋፅኦ የላቀ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በመላ ሃገሪቱ በተለይ በአባይ ወንዝ ተፋሰስ ዙሪያ እየተተከሉ የሚገኙ ሃገር በቀል ችግኞች ማሳያ ናቸው። እነዚህ ደኖች የተስተካከለ የአየር ንብረት እንዲኖር በማድረግ ለአካባቢ ጥበቃ ስራ አዎንታዊ ሚና ይኖራቸዋል። ይህ ደግሞ ለተፋሰሱ አገራት ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ጭምር ፋይዳ ያለው ነው።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ የካርቦን ልቀትን በመከላከል በየዓመቱ ከዕፅዋት፣ ከከሰልና ጋዝ የሚወጣውን 10 ነጥብ 6 ሚሊየን ቶን የካርበን ልቀት ብክለትን በመታደግ ከብክለት የፀዳች ዓለምን ለመፍጠር እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚያግዝና ከዚህ ጋር የሚስማማ በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው።
ከዚህም ባሻገር የፕሮጀክቱ ግንባታ እውን መሆን ለግብፅም ሆነ ለሱዳን ዓመቱን ሙሉ የተመጣጠነ ውሃ እንዲደርሳቸው እና በጎርፍ እንዳይጠቁ ከማድረጉም በተጨማሪ እነዚህ ሃገራት ከሚደርስባቸው አላስፈላጊ ደለልም እንዲጠበቁ የራሱን አስተዋፅኦ ያደርጋል። ነገር ግን ግብጽ በተደጋጋሚ ግድቡ ላይ የምታራምደው አቋም ከዚህ በተቃራኒ መሆኑ ለማንም አይጠቅምምና ዳግም ልታጤነው የሚገባው ጉዳይ ነው። እኔ ብቻ ልብላ ማለት በዚህ ዘመን የሚያዋጣ አመላከከትም አይደለም።
ይልቁንም ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ በመደገፍ ተያይዞ ለማደግ ጥረት ማድረግ ከእያንዳንዱ የአካባቢው አገራት የሚጠበቅ በመሆኑ ይህንን አቅጣጫ መያዝ ጠቃሚ ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያ የራሷን መንገድ በመከተል ወደ ልማት የጀመረችውን ጉዞ አጠናክራ ከመቀጠል የሚያደናቅፋት አንዳችም ሃይል እንደማይኖር ሊታወቅ ይገባል። ምክንያቱም የያዘችው መንገድ የጥፋት ሳይሆን የልማት፤ የመለያየት ሳይሆን ተያይዞና ተደጋፎ የማደግ ነውና። በመሆኑም ኢትዮጵያ ይህንን ቀና የብልፅግና መንገድ ዛሬም፣ ነገም ትቀጥልበታለች።
አዲስ ዘመን ጥር 3 ቀን 2012 ዓ.ም