ፎቶግራፍ- የፋሽን የጀርባ አጥንት

የፋሽን ሳምንቶች ለሕዝብ ክፍት በሆኑ ቦታዎች ላይ የተለያዩ አልባሳትና ጌጣጌጦችን በማሳየት የሚደረጉ ዝግጅቶች ናቸው። ይህ አይነት ፅንሰ ሃሳብ በይፋ መተዋወቅ የጀመረው በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ ነው።

በዋናነት አዳዲስ አልባሳትና የመዋቢያ ጌጣጌጦች ለገበያተኛው ማቅረብ በሚያስፈልግበት ወቅት ዲዛይነሮችና የፈጠራው ባለቤቶች በፓሪስ ጎዳናዎች ላይ ቆነጃጅቶች ሥራዎቻቸውን እንዲ ያሳዩላቸው መመልመል ጀመሩ። በዚህ አጋጣሚ በአደባባዮችና ለእይታ ምቹ በሆኑ ስፍራዎች ላይ በዲዛይነሮች የተሠሩ የመዘነጫ ቁሳቁሶች በይፋ አስተዋወቁ። ይሄ እንቅስቃሴ ቀስ በቀስ የፋሽን አብዮት በመሆን እነዚህን ተወዳጅ ሳምንታት መፍጠር ቻለ። በፈረንጆቹ የዘመን አቆጣጠር ከ1900 እና ከዚያ በፊት የፋሽን ሳምንታት ቀስ በቀስ እያደጉ የመጡበት ጊዜያት እንደሆነ ይነገራል።

ፋሽን ሞዴሊንግን፣ ዲዛይንና ሌሎች ጥበባዊ ውጤቶችን አካትቶ የሚይዝ ተወዳጅ ዘርፍ ነው። በዚህ ሙያ ውስጥ የሚገኙ የፈጠራ ባለሙያዎች ሥራዎቻቸውን ለዓለም እንዲያስተዋውቁ ደግሞ ፎቶግራፍና ባለሙያዎቹ እጅግ ቁልፍ ሚናን ይጫወታሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን የፋሽን አልባሳትና ሌሎች የፈጠራ ውጤቶች በፎቶግራፍ አማካኝነት ለተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ሲደርሱ ደግሞ ሥራዎቻቸው ላይ ያሉትን መልካም ጎንና መሰል አስተያየቶችን በቀላሉ ለማግኘት ያስችላቸዋል።

የማኅበራዊ ድረ ገፆችና መገናኛ ዘዴዎች ልክ እንደ አሁኑ ባልተስፋፋባቸው ጊዜያት የፋሽን ወዳጆች በቀላሉ ዲዛይነሮችና የፈጠራ ባለሙያዎች ይፋ የሚያደርጓቸው አልባሳት፣ የመዋቢያ ቁሶችና ጌጣጌጦችን ለመመልከት አጋጣሚው አልነበ ራቸውም። ይህ ደግሞ የፋሽን ውጤት ተከታይና አድናቂዎች በቀጥታ ተሳትፎ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ አይፈጥርላቸውም ነበር።

አሁን ላይ ከሕፃን እስከ አዋቂ ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ የፌስቡክና መሰል ማኅበራዊ ገፅ አካውንቶች አሉት። ይሄ ደግሞ ለፋሽን ውጤት አድናቂዎችና ዲዛይነሮች ልዩ አጋጣሚ ፈጥሯል። ዲዛይነሮች በቀላሉ በፎቶግራፍ አማካኝነት ሥራዎቻቸውን በማኅበራዊ ገጾች ሲያጋሩ አድናቂና ተከታዮቻቸው ደግሞ የሚወዱትን ሥራዎች ብዙ ሳይለፉ የመመልከት እድሉን ማግኘት ችለዋል። ከዚህ ባለፈ ጥሩም ይሁን መልካም አስተያየቶችን ለመለዋወጥ ይውላል። በዚህ ምክንያት ነው ፎቶግራፍና የፎቶ ባለሙያዎች በፋሽን ኢንዱስትሪው ላይ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳላቸው እንዲታመን ያደረገው። ዲዛይነሮችም ይህን መተኪያ የሌለው ዕድል በማግኘታቸው ሥራዎቻቸውን ሳይለፉ ለማስተዋወቅ የቻሉት።

በዓለማችን ላይ እጅግ ብዙ የፋሽን ሳምንቶች ይዘጋጃሉ። በርካታ ሺህ የፈጠራ ባለሙያዎች፣ ሞዴሎችና የጥበቡ ዓለም ባለሙያዎችም ሥራዎ ቻቸውን ያቀርባሉ። በሚሊዮኖች የሚገመቱ የፋ ሽኑ ዓለም አድናቂዎችም በቀጥታ በነዚህ ተወዳጅ ዝግጅቶች ላይ ይካፈላሉ። ታዲያ ከእነዚህ ቁጥ ራቸው ከበዛው አድናቂዎች በተለየ መንገድ በርካታ ሚሊዮን ሰዎችም በተለያዩ አማራጮች የሚወዱት ትዕይንትን ይታደማሉ። ይህን ዕድል ከሚፈጥሩት የሙያ ዘርፎች ውስጥ አንዱ ደግሞ የፎቶግራፍ ሙያ ነው። በተለያዩ ተወዳጅ የፋሽን ሳምንቶች ቁጥራቸውን መገመት የሚከብዱ ብቃታቸው ጫፍ የደረሰ ፎቶግራፈሮች ይገኛሉ። በካሜራዎቻቸው የሚያነሷቸውን አስደናቂ ምስ ሎችን በድረ-ገፆቻቸውና በማኅበራዊ ገፆች ያሰራጯቸዋል።

ዝግጅቶቹ ተጠናቀው ሳያበቁ ድባቡ ሳይፋዘዝ ፎቶግራፎቹ እያንዳንዱ ፈላጊያቸው ደጃፍ ይደርሳሉ። ይሄ መልካም አጋጣሚ ሚሊዮኖች በእያንዳንዱ ሀገርና የፋሽን ሳምንታት የመሳተፉ አጋጣሚን ባያገኙ እንኳን እቦታው ድረስ እንደ መሆን ልዩ ስሜት የሚፈጥሩትን የፎቶግራፍ ውጤቶች የመመልከት አጋጣሚውን ያገኛሉ።

ያን ጊዜ ነው ፋሽንና ፎቶግራፍ ቁርኝታቸው ጎልቶ የሚወጣው። አሁን አሁን እነዚህን ሁለት ሙያዎች ነጥሎ መመልከት እስኪከብድ ድረስ ትስስራቸው ጥልቅ ሆኖ ይስተዋላል። የጥሩ ዲዛይነር አልባሳት ውጤቶች ድንቅ ችሎታ ያለው የፎቶ ባለሙያ ሲነሳ የፋሽኑ ዓለም ተከታይና ደንበኞች አይናቸው በቶሎ የሚወዱት አልባሳትና መዋቢያ ጌጦች ላይ በቀላሉ ማረፍ ይችላል። ምን ይሄ ብቻ የዲዛይነሮችን ሥራ በእይታ ውስጥ እንዲገባ ለማስቻል ሞዴሊንግ ትልቁን ኃላፊነት ይወስዳል። በአልባሳቱ ሆነ በጌጣጌጦቹ ተውበው የሚታዩት ሞዴሎች ደግሞ በፎቶግራፍ ባለሙያዎች ቅንጡ የፎቶ አነሳስ ዘዴ ደምቀው እንዲታዩ ይሆናል። ያን ጊዜ ነው አዳዲስ የፋሽን ውጤቶች በዓለማችን ውብ ከተማዎችና ወጣት ዘመናዊነት ተከታዮች ዘንድ የሚደርሱት።

ባህላዊ ሀብቶቻችንን ለቀሪው ዓለም ከምናስተዋውቅበት መንገድ አንዱ የፋሽን ኢንዱስትሪው ነው። ዘርፉ እንዲመነደግ ደግሞ በዛሬው ርዕሳችን ላይ እንዳነሳነው ፋሽንና ፎቶግ ራፍ ጥብቅ ቁርኝት መፍጠር ይኖርባቸዋል። ይህ ዘርፍ በብዙ አይነት መንገዶች እድገት አሳይቶ ስኬት ላይ የሚደርስ ከሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ባህላዊ እሴቶቻችንን ሳንበርዝ ለቀሪው ዓለም ማስተዋወቅ ያስችለናል። ከዚህ ባለፈም ሀገራችን ኢትዮጵያ የፋሽን ቱሪዝም ተደራሽ ሆና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲኖራት ያስችላል። አሁን አሁን ፋሽንና ፎቶግራፍ በሀገራችን ኢንዱስትሪ ውስጥ መልካም ውጤት ላይ እየደረሰ ለመሆኑ ማሳያ የሚሆኑ የማኅበራዊ ድረ ገጽ እንቅስቃሴዎችን ማስተዋል ይቻላል።

በኢንስታግራም ላይ ዲዛይነሮች ሥራዎቻቸውን በጥሩ የፎቶግራፍ ባለሙያ እያስነሱ ማቅረብና ማስተዋወቅ እየቻሉ ነው። በዚህ የመገናኛ ዘዴ ብቻ ሳይሆን በሌሎች መሰል አማራጮችም ዲዛይነሮችና የፈጠራ ባለሙያዎች አዕምሯዊ ውጤቶቻቸውን ይፋ እያደረጉ ከአድናቂዎቻቸው መልካም ምላሽና ተሳትፎ እያገኙ ነው። ይህ ግን ጅምር እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። የፋሽኑ ዓለም የደረሰበት የዘመናዊነት ጫፍ ለመድረስ ግን ገና ብዙ ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግ ይታመናል።

ከላይ ያነሳነውን ጥረት ለስኬት እንዲበቃ ዓለም አቀፍ የፋሽን ሳምንቶች በሀገራችንም በስፋት ሊለመዱ ይገባል። ያን ጊዜ የተፈለገው ግብ ላይ ለመድረስ ሰፊ መንገድ ማበጀት ይቻለል። የዛሬው ርእሰ ጉዳይ የሆነው የፋሽንና ፎቶግራፊ ዝምድናንም እድገቱ በሚያመጣው አጋጣሚ በቀላሉ እንመለከተዋለን።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You