
የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎችን ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ እያስተናገደች የምትገኘው ጅማ ከውድድሩ ጎን ለጎን 3ኛውን የስፖርት መሠረተ ልማት(ፋሲሊቲ) ፎረም አስተናግዳለች። በጅማ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደውን ፎረም በይፋ ያስጀመሩት የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሀመድ፤ መንግሥት በዘርፉ በዋናነት ከሚሠራቸው ሥራዎች ውስጥ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን መገንባት፣ ማስተዳደር እና መምራት እንደሆነ ተናግረዋል።
“በሀገራችን በስፖርት ፋሲሊቲ ግንባታ ሰፊ ሥራዎች ሠተርተዋል። ከእዚህ ረገድ አዲስ አበባ ከተማ የተገነቡ የስፖርት መሠረተ ልማቶች በቅድሚያ የሚነሱ ናቸው” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚሠሩ መሠረተ ልማቶችም አበረታች እንደሆኑ ገልጸዋል። ነገር ግን እንደ ሀገር ያሉንን መሠረተ ልማቶች በትክክል አለማወቅ፣ አለመጠቀም እንዲሁም ለሌሎች ያለማሳወቅ ችግር መኖሩን ጠቁመዋል።
እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እንዲሁም ያሉትን የስፖርት መሠረተ ልማቶችን ቁጥር በትክክል ለማወቅና ቅንጅታዊ አሠራር ለመዘርጋት አሠራሮችን ዲጂታላይዝ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል። በመሆኑም ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ከINSA ጋር በመሆን በሚቀጥለው በጀት ዓመት በእዚህ ዙሪያ እንደሚሠራ ተነስቷል።
በፎረሙ የኦሮሚያ ክልልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተሞክሮዎች፤ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፋሲሊቲ ተሞክሮ፤ በስፖርት ኢንቨስትመንት ላይ የግሉ ሴክተር ተሳትፎ በተጨማሪም የስፖርት ፋሲሊቲ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። የስፖርት ዘርፍ ከአደረጃጀት ፣ ከመመሪያ እንዲሁም ከሕግና ደንብ አንጻር የዓለም ተሞክሮ ከሀገር አቀፍ ሁኔታ ያነጻጸረ እንዲሁም ሀገራዊ መፍትሔዎችን ያካተተ ተሞክሮ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተዘጋጀው ሰነድ ቀርቧል። የስፖርት ዘርፍ በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ ፣ በኢኮኖሚና በዲፕሎማሲ ዘርፍ ያለውን ሚና አልቆ የሚያሳይ ተሞክሮ በዶ/ር ዋቅጅራ ሲና ለፎረሙ ቀርቧል።
በኦሮሚያ ክልል የተጀመረው “አንድ የስፖርት ማዘውተሪያ ለአንድ ቀበሌ” ኢንሼቲቭ ወደ ሌሎች ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች መስፋፋት እንዳለበትም ተመላክቷል። የስፖርት ምክር ቤት ገቢን በማሳደግ፣ የሕግና ደንብ ማሻሻያ በማድረግ የኅብረተሰቡን የስፖርት ተሳትፎ ማሳደግ እንደቻለ በተሞክሮ ኦሮሚያ ክልል በፎረሙ አሳይቷል። የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ማልጠኛ ጣቢያዎችን በማስፋፋትና ጥራት በመጠበቅ ተተኪዎችን እያፈራ እንዳለ በተሞክሮ ያሳየው ክልሉ ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ የባለሙያዎችን ክህሎት የማሳደጊያ ስልጠና እንደሰጠ በተሞክሮ አቅርቧል።
የስፖርት ፋሲሊቲ እና መሠረተ ልማት በሚፈለገው መንገድ ስታንዳርዳሩን ጠብቆ ተደራሽ እንዲሆን መንግሥት፣ሕዝብ እና የግል ባለሀብቱ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙ በፎረሙ ተነስቷል።
በየስፖርት ዓይነቱ 2581 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዳሉ በተሞክሮ ያቀረበው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከስታንዳርድ አንጻር የተሠሩ ሥራዎችም ቀርበዋል። በመንግሥት፣ በኅብረተሰብ ተሳትፎ፣ በባለሀብት ተሳትፎ እና በጤና ቡድን ተሳትፎ የተገነቡ የስፖርት ፋሲሊቲና መሠረተ ልማቶች እንደተለዩ የተሞክሮው ሰነድ ያስረዳል።
ከተማ አስተዳደሩ በኮሊዶር ልማት የተገነቡ የስፖርት ፋሲሊቲና መሠረተ ልማቶች ለሌሎች በተሞክሮ እንዲወሰዱም አቅርቧል። የስፖርት መሠረተ ልማቶች በአግባቡ እንዲጠናከሩ የባለቤት ሕጋዊነትን በማረጋገጥ በቀዳሚነት እንደሠራ ያሳየው ከተማ አስተዳደሩ፤ አገልግሎት የሚሰጡና ጥገና የሚያስፈልጋቸውን በመለየት ለፎረሙ አሳይቷል።
ዶ/ር ሳምሶን ወንድራድ ከማስተማር ጎን ለጎን በጅማ ዩኒቨርሲቲ ያሉ አባጅፋር ሜዳ፣ ጅማ ስታድየም፣ ስፖርት አካዳሚ ጅምናዚየም፣ሀጫሉ ሁንዴሳ ጅምናዚየም የሚሰጡትን አገልግሎቶች በተሞክሮ አቅርበዋል።
በፎረሙ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የክልልና ከተማ አስተዳደር ስፖርት አመራሮች ተሳታፊ ናቸው። በፎረሙ የቀረቡ ተሞክሮዎች የስፖርት ፋሲሊቲን ለማጠናከር የሚያስችሉ መሆናቸውንም የፎረሙ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።
መንግሥት የግል ባለሀብትን አቅም መጠቀም እንደሚገባ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል ለፎረሙ የቀረበው የስፖርት ኢንቨስትመንት ሰነድ ነው። የግል ባለሀብቱ በስፖርት ዘርፍ የሀገርን ስፖርት ለማሳደግ ከዓለም አቀፍ አንጻር በማነጻጸር የሚያስቃኝ ተሞክሮ የቀረበ ሲሆን፤ ከፋይናንስ ተቋማት ፣ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር እንደሚያስፈልግ ሰነዱ ያስረዳል።
ሀገር አቀፍ የስፖርት ፋሲሊቲ መረጃዎችን አያያዝ ለማዘመን እየተሠራ እንዳለ የማጠቃለያ ሃሳብ የሰጡት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ስፖርታዊ ጨዋነት ላይ በቀዳሚነት መሥራት ይጠይቃል ብለዋል።
ለስፖርት መሠረተ ልማት የሚውለው የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ለታለመለት ዓላማ ባለመዋሉ የዘርፉን እድገት ገትቶታል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በቀጣይ ይህን ለማስተካከል ከክልል፣ ከተማ አስተዳደርና ከባለድርሻ አካላት ጋር አመለካከትን ከመቀየር ጀምሮ ጠንካራ ሥራ እንደሚሠራ አስገንዝበዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም