በአማራ ክልል ከመኸር ወቅት እርሻ 187 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል

አዲስ አበባ፡- በአማራ ክልል ከመኸር ወቅት እርሻ አምስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ 187 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። እስካሁን ከ75 ሺ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች መሠራጨቱን አመለከተ።

በቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ/ር) ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ በክልሉ አምስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ 187 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል። እስካሁንም አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት ታርሷል።

ከታረሰው መሬት 817 ሺህ ሔክታሩ በዘር መሸፈኑን ያመለከቱት ዳይሬክተሩ፤ ከተዘሩ ሰብሎች መሃል በቆሎ፣ ማሽላ፣ የምግብ ገብስ፣ ቦሎቄና ለውዝ እንደሚገኙበት አስታውቀዋል።

እንደ ዶክተር ማንደፍሮ ገለጻ፤ በክልሉ ለመኸር ወቅት ሁለት መቶ ሺ ኩንታል ምርጥ ዘር ለማሰራጨት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል። ይህም በባለፈው ዓመት ከተሰራጨው ጋር ሲነጻጸር የ30 ሺህ ኩንታል ጭማሪ አለው።

“እስካሁን ከ75 ሺ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለክልሉ አርሶ አደሮች ተሰራጭቷል። እስከ ሐምሌ መጨረሻ የሚዘሩ ሰብሎች በመኖራቸው ወቅቱ ሳያልፍ ምርጥ ዘር የማሰራጨት ሥራ በትኩረት ይከናወናል” ብለዋል።

በክልሉ አሁን ላይ ስንዴ መዝራት እንዳልተጀመረ፤ ስንዴ ከሰኔ መጨረሻ ጀምሮ ሐምሌን ሙሉ የሚዘራ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ጤፍም በተመሳሳይ የማሳ ዝግጅት ቢጀመርም መዝሪያው ወቅት እንዳልደረሰ አመልክተዋል።

የስንዴ፣ የጤፍም ሆነ የሌሎች ሰብሎችን ምርጥ ዘር ወቅቱ ሳያልፍ በማሰራጨት ገበሬው ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በክልሉ ስምንት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለማሰራጨት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ማንደፍሮ፤ ስርጭቱ ባለፈው ዓመት በመኸር ወቅት ከተሰራጨው ሰባት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት ከአራት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ደርሷል። ወደ ክልሉ ከደረሰው ማዳበሪያ ሦስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታሉ ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቷል። የተቀረውም በፌዴራል ግዢው ተፈጽሞ በጉዞ ሂደት ላይ ይገኛል።

ለመኸር ወቅት የሚያስፈልገው ምርጥ ዘርም ሆነ ማዳበሪያ በወቅቱ ወደ ክልሉ እንደሚደርስ አመልክተው፤ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ከመጠቀም በተጨማሪ ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎችን ጥቅም ላይ በማዋል ግብርናውን የማዘመን ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከእዚሁ ጋር በተያያዘም ዘንድሮ ለማረስ ከታቀደው አምስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት 982 ሺህ ሄክታሩን በትራክተር ለማረስ በእቅድ መያዙን ገልጸው፤ እስካሁንም 729 ትራክተሮችን በመጠቀም 304 ሺህ ሄክታር መሬት ታርሶ በዘር መሸፈኑን አመልክቷል።

በክልሉ በትራክተር ለማረስ ከታቀደው የታረሰው 30 በመቶ አካባቢ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ማደፍሮ፤ በትራክተር የታረሰው መሬት የማነሱ ምክንያት በክልሉ በትራክተር በማረስ የሚታወቁትና መልክዓ ምድራቸው ለእዛ የተመቸው አካባቢዎች የዘር መዝሪያ ወቅት ገና በመሆኑ እንደሆነ ጠቁመዋል። እነዚህ አካባቢዎች ሲታረሱ አፈጻጸሙ ከፍ እንደሚል አስታውቀዋል።

በቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You