
ሕዝባችን ላለፉት ሰባት አስርት ዓመታት በሀገራችን መሠረታዊ የሆነ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን ለማምጣት ሰፊ ጥረቶች አድርጓል። የ1966 ዓ/ም አብዮትን ጨምሮ በየወቅቱ የተለያዩ የለውጥ ንቅናቄዎች ተካሂደዋል። በተለይም በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብን በማስፋት ለአስተሳሰቡ የተገዛ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር በየዘመኑ የነበረው ትውልድ ብዙ መስዋዕትነት ከፍሏል።
የ1966 ዓ.ም ትውልድ ስለዴሞክራሲ ድምጹን ከፍ አድርጎ መጮህ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የዴሞክራሲ ጉዳይ የየትውልዶች መሠረታዊ ጥያቄ በመሆን እስከዛሬ ዘልቋል። አሁን ላይ ያለው ትውልድም ቢሆን ከስድስት አስርት ዓመታት በኋላ ጥያቄውን በአደባባይ ይዞ ወጥቶ ብዙ ዋጋ የከፈለበት እውነታ ስለመኖሩም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
ብዙዎች እንደሚስማሙበት በቀደሙት ዘመናት ስለዴሞክራሲ የተደረጉ ሀገራዊ መነቃቃቶች በአንድም ይሁን በሌላ የታለመላቸውን ግብ ሳይመቱ በቡድናዊ ፍላጎቶች ከሽፈዋል። ትውልዶች በብዙ መነቃቃት እና የሕይወት መስዋዕትነት ያደረጓቸው ትግሎች ከፕሮፓጋንዳ ግብአትነት ባለፈ በተጨባጭ ሕዝባችን የሚፈልገውን የዴሞክራሲ ሥርዓት መገንባት አላስቻሉም።
ገና ከጅምሩ በብዙ የአስተሳሰብ መዛነፎች ላይ መሠረቱን ያደረገው የሀገራችን የዴሞክራሲ ጥያቄ እና የሥርዓት ግንባታ፣ በየወቅቱ ሀገራችንን እና ሕዝባችንን ላልተገባ ችግር እና መከራ ዳርጓል። ለዴሞክራሲ ሁሌም ባይተዋር እንዲሆን ከማድረግ ባለፈም፤ ተስፈኛ እንዲሆን አስገድዶታል። ይህም አጠቃላይ የሆነውን የሕዝባችን እጣ ፈንታ አደብዝዞት ቆይቷል።
ለእዚህም በሀገሪቱ የነበሩ እና ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ልሂቃን በዋነኛነት ተጠያቂዎች እንደሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ። የሕዝባችንን የዴሞክራሲ መሻት እውን ማድረግ የሚያስችል ሁለንተናዊ ዝግጁነት አለመፍጠራቸው፣ ስክነት እና ብስለት ማጣታቸው፣ ከሁሉም በላይ ዴሞክራሲን የትግል ስትራቴጂ ከማድረግ ባለፈ ተጨባጭ የትግል ግብ አድርገው አለመንቀሳቀሳቸው ለችግሩ በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው።
ዜጎችን ጠብመንጃ አሸክመው ለዓመታት ስለ ዴሞክራሲ እየማሉ እና እየተገዘቱ የትግላቸው ዜማ ያደረጉት ሳይቀሩ በብዙ የሕዝቦች መስዋእትነት ወደ ሥልጣን በመጡ ማግስት ጀምሮ ብዙ ሲደሰኩሩለት ለነበረው ዴሞክራሲ ራሳቸው ባይተዋር ሆነው የታዩበት እውነታ የሩቅ ዘመን ትውስታ አይደለም። ስለዴሞክራሲ ጥያቄ ይዞ በተነሳ ትውልድ ላይ የጠብመንጃ ቃታ መሳብ ቀልሏቸውም ታይቷል።
በእርግጥ ዲሞክራሲ የአስተሳሰብ መታደስን የሚጠይቅ በተጨባጭ ተሞክሮ የሚያድግ እና የሚጎለብት ነው። ለእዚህም ከንድፈ ሃሳብ ባለፈ በተጨባጭ የዴሞክራሲ ሥርዓት ገንብተው፤ የሥርዓቱ ሁለንተናዊ ተጠቃሚ የሆኑ ሀገራት እና ሕዝቦች ተሞክሮ በተግባር የሚናገረው እውነት ነው። እኛም ቢሆን ከትናንት ክሽፈታችን በብዙ ስለ ዴሞክራሲ መማል እና መገዘት በራሱ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተማመኛ እንደማይሆን ምስክሮች ነን።
የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትርክቶች እንደሚያመለክቱት፤ ሀገራዊ የዴሞክራሲ ሥርዓት በጠብመንጃ አፈሙዝ ሳይሆን በሃሳብ ልእልና ላይ መሠረቱን አድርጎ የሚወለድ፣ የሚያድግ እና የሚሰፋ ነው። ለእዚህም ነው ላለፉት ስድስት አስር ዓመታት በጠብመንጃ ትግል የቱንም ያህል ዋጋ ብንከፍል፤ ወንድም ወንድሙን ገድሎ ከመፎከር ባለፈ የዴሞክራሲ ሥርዓት ገንብተን ተጠቃሚ የሆንበት እውነታ አልተፈጠረም።
ዛሬም ዴሞክራሲን እውን ለማድረግ እንደ ሕዝብ ከፍ ባለ መነሳሳት ላይ ብንሆንም፤ አንዳንድ ፖለቲከኞቻችን ከትናንት ክሽፈታችን መማር ባለመቻላቸው፣ በሚጠበቀው መጠን ለሥርዓቱ ግንባታ የሚሆን ሕዝባዊ ታማኝነት መፍጠር ባለመቻላቸው፣ ከተለመደው የሴራ እና የኃይል መንገድ ለመውጣት ባለመፍቀዳቸው ሕዝባችንን ላልተፈለገ መስዋእትነት እየዳረጉት ነው።
ዛሬ ላይ የሀገሪቱን ፖለቲካ መድረክ ለማዘመን፣ ዘመኑን እንዲዋጅ ለማድረግ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የተፈጠሩ ተስፋ ሰጪ ዕድሎች ቢኖሩም፤ ጽንፈኝነት፣ ጠብመንጃ አምላኪነት፣ ጠቅላይነት፣ ዳተኝነት፣ አድር ባይነት እና ባንዳነት ትልቅ ፈተና ሆነውበታል። የራስን እና የቡድንን ፍላጎት የማስቀደም የትናንት ልክፍት ፣ የክሽፈቶቻችን ምንጭ፣ ለጀመርነው አዲስ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ተግዳሮት ሆኖብናል።
ለሕዝቦች ፍላጎት እና ለሃሳብ የበላይነት የማይገዛ የፖለቲካ አስተሳሰብ፣ እዚያም እዚህም የሚረግጥ መርህ አልባ የትግል ስትራቴጂ፣ በሕዝብ ፍላጎት እና በብሔራዊ ጥቅሞች ላይ የሚደራደር ስንኩል የፖለቲካ አካሄድ፣ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገን ጭምር የሚያጠፋ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” በሚል ሰውኛ ባልሆነ ያልተገባ እሳቤ፣ የትውልዱን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሻት እና ከእዚህ የሚመነጨውን ትግል በብርቱ እየፈተነ ነው።
እንደ ሕዝብ እና ሀገር ብሩህ ትናንቶቻችንን ካሳጣን፣ የብዙ ትውልዶችን ተስፋ ከተናጠቀ፣ ዛሬም የትውልዱን ሆኖ የመገኘት መሻት እየተፈታተነ ካለው ስንኩል የፖለቲካ አስተሳሰብ ተሻግሮ ለማለፍ ከሁሉም በፊት ፖለቲከኞቻችን ከእዚህ የአስተሳሰብ መርገምት ራሳቸውን ነጻ ማድረግ እና ለእዚህ የሚሆን ዝግጁነት መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም