በሸገር ከተማ የሰላም እና የጸጥታ ስጋት እንደሌለ ተገለጸ

ሸገር ከተማ፦ በሸገር ከተማ ምንም ዓይነት የሰላም እና የጸጥታ ስጋት እንደሌለ የከተማዋ የሰላምና ጸጥታ ጽ/ቤት አስታወቀ። በከተማዋ ሰላም እና ጸጥታን የማጽናት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን አመለከተ።

የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ስዩም በተለይ በስፍራው ለተገኘው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የጋዜጠኞች ቡድን እንደገለጹት፤ አሁን ላይ በሸገር ከተማ ምንም ዓይነት የሰላም እና የጸጥታ ስጋት የለም።

የከተማዋ ነዋሪ በቅኘት (ሮንድ) እና በልማት ቡድን ተደራጅቶ አካባቢውን የሚጠብቅበት ሁኔታ መፈጠሩን፤ ነዋሪው በከተማዋ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ተባብሮ አስፈላጊውን ጥበቃ በማድረግ፣ ፀጉረ ልውጥ የሆኑ ሰዎች እንኳን ሲታዩ በቶሎ ለጸጥታ መዋቅሩ መረጃን በማቀበል ከፍተኛ ተባባሪነት እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲገቡ፤ የተጀመሩ የልማት እና መልካም አስተዳደር ሥራዎች እንዲፋጠኑ ጽሕፈት ቤቱ ሰላምና ጸጥታን የማጥናት ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል።

እየተጠናቀቀ ባለው የበጀት ዓመት ሕዝቡ በሰላም እና ጸጥታ ዙሪያ ያለውን ተሳትፎ ለማጠናከር የሚያስችሉ ሰፋፊ መድረኮች መካሄዳቸውን ያመለከቱት አቶ ደሳለኝ፤ በመድረኮች በሰላም እና በጸጥታ ሥራዎች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል።

“ከእዚህ በፊት በከተማዋ የነበሩ የጥፋት አጀንዳዎች አሁን በእዛ ደረጃ የሉም” ያሉት የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ፤ በተለይ ከኢንቨስትመንት ጋር ከእዚህ ቀደም የነበሩ የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎች በጽሕፈት ቤቱና በኅብረተሰቡ ተሳትፎ እንደሌሉ አስታውቀዋል። አሁን ላይ ባለሀብቱ በከተማዋ ኢንስትመንት ላይ ለመሠማራት ትላልቅ ጥያቄዎችን እያቀረበ ነው ብለዋል።

በከተማዋ ሰላምና ጸጥታን አስተማማኝ ለማድረግ ሁኔታ የዳሰሳ ጥናቶችን በሰፊው በማካሄድ ስጋቶችን መለየት መቻሉን ያስታወቁት አቶ ደሳለኝ፤ በተለይ ጸረ ሰላም ኃይሎች የተለያዩ ተልእኮና አጀንዳ ይዘው በከተማዋ ችግር ሊፈጥሩ፣ ሁከት ሊያስነሱ፣ ሰላም የሌለ ለማስመሰል ሲሠሩ እንደነበር በጥናቱ መለየቱን ገልጸዋል። ድርጊቱን በሳይንሳዊ መንገድ በጥናት በማረጋገጥ፣ በመከታተል፣ በመረጃ በማስደገፍ፣ የመቆጣጠር እና ለሕግ የማቅረብ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።

“በከተማዋ ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ፤ ከተፈጸሙም በቶሎ ለመቆጣጠር ከሰው ኃይል ባለፈ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ መሆናቸውን አመልክተዋል። የሸገር ከተማ አስተዳደር ባሉት 12 ክፍለ ከተሞች የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ ለመከታተል የሲሲ ቲቪ ካሜራ ተክሎ እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የጋቸና ሲርና እና የሚኒሻ አባላት ሥልጠና እየወሰዱ በብዛት ወደ ሕዝቡ ገብተው በሰላምና ጸጥታ ዙሪያ እንዲያገለግሉ እየተደረገ መሆኑን ያነሱት ምክትል ኃላፊው፤ አባላቱ ሕዝባቸውን በቅንነት እያገለገሉ መሆኑን አስታውቀዋል። በሥራ ሂደት የሚፈጠሩ ጥቃቅን ስህተቶች በጸጥታ ኃይሉ የራሱ አደረጃጀት በመገምገም፣ የእርምት ርምጃዎች እንደሚወሰዱም ጠቁመዋል ።

በእዚህም የጸጥታ ኃይሉ፣ የኅብረተሰቡን ተሳትፎ እና የሚመለከታቸውን አካላት በጥምረት ሰላምና ጸጥታን ለማስፈን በሚያደርጉት ትብብርና ተሳትፎ ምክንያት በሸገር ከተማ እስካሁን ይህ ነው የሚባል የጸጥታ ችግር አለመከሰቱን አመልክተዋል።

“በአዲስ አበባ ከተማ እና በሸገር ከተማ ትልቁ አጀንዳ ቅሬታ ሲቀርብ የነበረው የጫኝ እና አውራጅ ችግር ነው” ያሉት አቶ ደሳለኝ፤ ጫኝና አውራጆች ማንኛውንም ሰው እቃ ለመጫን ወይም ለማውረድ የሚጠይቁት የገንዘብ መጠን በጣም ከፍተኛ እና ሕዝቡንም በጣም ያማረረ ነበር ብለዋል።

የሸገር ከተማ አስተዳደር የጸጥታው ምክር ቤት በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ላይ የቀረቡ ቅሬታዎች እንደ አንድ ትልቅ አጀንዳ በመያዝ አቅጣጫ አስቀምጧል። በአቅጣጫውም አሁን የሚደራጁት ወጣቶች የሚሰጡት አገልግሎት በባለ ንብረቱ ፈቃድ እና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሆን መደረጉን ገልጸዋል። የንብረቱ ባለቤት “አልፈልጋችሁም ራሴ አወርዳለሁ” ካለ መብቱን ጠብቀው የሚሠሩበት አሠራር መቀመጡን አስታውቀዋል።

እንደ ምክትል ኃላፊው ገለጻ፤ በተለይ በኮንዶሚኒየም አካባቢ ከጫኝ እና አውራጅ ጋር በተያያዘ ብዙ ውዝግቦች ይነሱ ነበር። ችግሩ በሸገር ከተማ ፉሪ አካባቢ፣ በኮዬ ፈጬ፣ በቱሉ ዲምቱ እና በሌሎች ክፍለ ከተሞች ላይም ተመሳሳይ ጥያቄ ይነሳ ነበር። አሁን ግን ለፖሊስ፣ ለሚሊሻ አባላት መመሪያ ተሰጥቷል። መሰል ውዝግብ የፈጠረ በጫኝ እና አውራጅ የተደራጀ አካል ካለ ተይዞ ለሕግ ይቀርባል።

“ድርጊቱን ለመቆጣጠር በቀጣይ የከተማዋን የሰላምና ጸጥታ ክትትልና ቁጥጥሩን በቴክኖሎጂ ለማገዝ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ” ያሉት አቶ ደሳለኝ ፤ በራዲዮ መገናኛ እና ካሜራዎች ዙሪያ ያለውን ውስንነት በመቅረፍ በስፋት የሚገኙበትን አማራጮች እየተተገበረ መሆኑን ተናግረዋል።

የከተማዋ ነዋሪ በቅኘት (ሮንድ) እና በልማት ቡድን ተደራጅቶ አካባቢውን የሚጠብቅበት ሁኔታ መፈጠሩን፤ ነዋሪው በከተማዋ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ተባብሮ አስፈላጊውን ጥበቃ በማድረግ፣ ጸጉረ ልውጥ የሆኑ ሰዎች እንኳን ሲታዩ በቶሎ ለጸጥታ መዋቅሩ መረጃን በማቀበል ከፍተኛ ተባባሪነት እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የሸገር ከተማ 12 ክፍለ ከተሞች እና በ36 ወረዳዎች የተዋቀረች ሲሆን፤ ከተመሠረተችም ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ሆኗታል።

በዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You