
የሰኔ ወር ከኢትዮጵያ ግብርና በተለይ ከሰብል ልማት ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላት። ይህንን መነሻ በማድረግ፤ ‹‹በሰኔ ካልዘሩ፤ በጥቅምት ካልለቀሙ፤ እህል የት ይገኛል በድንበር ቢቆሙ›› ይባላል። በዚህ ወቅት በግብርና ለተሰማራ ሰውም ሆነ ባለሙያ ሥራ የሚበዛበት ወቅት ነው። በዚህ ምክንያት ሌላ ጊዜ የገጠሩ አካባቢ የሚታወቅበት ማኅበራዊ ሕይወት ቀንሶ የነገሮቹን ትኩረት በሙሉ ሥራና ሥራ ላይ ብቻ ይሆናል።
በዚህ ወቅት መሬት ተደጋግሞ ይታረሳል፤ ይዘራል፤ ለግብርናው አስፈላጊው ግብዓት የመሰብሰብ ሥራ ይከናወናል። በሰኔ የተዘናጋ ሰው መመለሻ እንደሌለው ሲገለጽም፤ የገጠሩ ሰው “አንድ ሰኔ የነቀለውን ሰባት ሰኔ አይመልሰውም” ብሏል። እንዲሁም “ሰነፍ ገበሬ በሰኔ ይሞታል!” የተባለላትን ሰኔ ማጋመሱን ተከትሎ በአማራ ክልል ለክረምቱ ምን ዓይነት ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ መቃኘትን ምርጫችን አድርገናል፡፡
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ/ር) በአማራ ክልል በመኸር፣ በበልግ እንዲሁም በመስኖ የግብርና ምርቶች የሚመረቱ ቢሆንም፤ ለክልሉ መኸር ዋና የሰብል ማምረቻ ጊዜ መሆኑን ጠቅሰዋል። ለዚህም ክልሉ የመኸር ወቅት ከመግባቱ አስቀድሞ አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የተለያዩ ተግባራት አከናውኗል።
ለሰብል ልማቱ የሚያግዙ አዲስ የተሻሻሉ ዝርያዎች፣ ማዳበሪያና መሰል የግብርና ግብዓቶች አንጻር የተሻለ ምክረ ሀሳቦችን በመለየት የፓኬጅ ክለሳ ተደርጓል። ለተከለሰው ፓኬጅ ማንዋል የተዘጋጀ ሲሆን፤ በአዲሱ ፓኬጅ ላይ በመመሥረት ከዞን እስከ ቀበሌ ያሉ ፈጻሚ ባለሙያዎች ሠልጥነዋል። በክልሉ የተሻለ ሥራ ለመሥራት የሚያስችል አስቻይ መደላድል መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ አምስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማረስ መታቀዱን የሚናገሩት ማንደፍሮ (ዶ/ር)፤ 187 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን አስረድተዋል። በክልሉ ወቅቱ ማሳ የሚታረስበትና የሚዘራበት ወቅት ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት ታርሷል። ከታረሰው መሬት 817 ሺ ሔክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል። ከተዘሩ ሰብሎች መሐል በቆሎ፣ ማሽላ፣ የምግብ ገብስ፣ ቦሎቄና ለውዝ ይገኙበታል ብለዋል፡፡
የትኛውም የእርሻ ተግባር ወቅትን መሠረት ያደረገ ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ሌሎች ዘርፎች ላይ ግብዓት ሲሟላ ሥራዎች ሊሠራ የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ተናግረዋል። እርሻ ግን ሁሉ ነገር ራሱን የቻለ ወቅት ያለው በመሆኑ በወቅቱ ሁሉም ግብዓት ሊሟላ ይገባል። ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት እስካሁን ከ75 ሺ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለክልሉ አርሶ አደሮች ተሰራጭቷል። ስርጭቱ የተከናወነው ቅድሚያ የሚዘሩ የሰብል ዓይነቶችና ቅድሚያ የሚዘሩ አካባቢዎችን ትኩረት በመስጠት ነው። እስከ ሐምሌ መጨረሻ የሚዘሩ ሰብሎች በመኖራቸው ወቅቱ ሳያልፍ ምርጥ ዘር የማሰራጨት ሥራ በትኩረት የሚከናወን መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደማንደፍሮ (ዶ/ር) ማብራሪያ፤ በክልሉ ስን ዴ መዝራት አልተጀመረም። ስንዴ ከሰኔ መጨረሻ ጀምሮ ሐምሌን ሙሉ የሚዘራበት ሁኔታ አለ። ጤፍም በተመሳሳይ የማሳ ዝግጅት ቢጀመርም መዝሪያው ወቅት አልደረሰም። የስንዴ፣ ጤፍም ሆነ ሌሎች ሰብሎች ወቅቱ ሳያልፍ በማሰራጨት ገበሬው ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ለመፍጠር ታስቧል። አምና 170 ሺህ ኩንታል የተሻለ ዘር ለክልሉ አርሶአደሮች ተሰራጭቶ ነበር። ዘንድሮ 30ሺህ ኩንታል በመጨመር ሁለት መቶ ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለማሰራጨት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።
ባለፈው ዓመት በነበረው የመኸር ወቅት ሰባት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ መሰራጨቱን የሚያስታውሱት ዳይሬክተሩ፤ በዘንድሮ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል በመጨመር ስምንት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለማሰራጨት ታቅዶ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ይናገራሉ። ከዚህ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ከአራት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ደርሷል። ወደ ክልሉ ከደረሰው ማዳበሪያ ሦስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች መሰራጨቱን ጠቅሰዋል።
መጀመሪያ አካባቢ የዝናብ መዘግየትና መቆራረጥ ነበር የሚሉት ማንደፍሮ (ዶ/ር)፤ በአሁኑ ወቅት ስርጭቱ ጥሩና ለእርሻ ሥራ ምቹ ዝናብ መኖሩን ጠቁመዋል። ከዘር አሸፋፈንም ሆነ ከእርሻ አንጻር በክልሉ የተያዘውን እቅድ ማሳካት የሚያስችል ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል።
በክልሉ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር አስቻይ ሁኔታዎች አሉ የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ማዳበሪያና ምርጥ ዘርን ከመጠቀም ባሻገር ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎችን በመጠቀም ከተለመደው በሬ፣ ሞፈርና የሰው ጉልበትን ተጠቅሞ ከሚከናወን ግብርና መዘመን የሚያስችል አሠራር መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል። ለእዚህም በክልሉ ከተለዩ አማራጮች አንዱ መልክዓ ምድራቸው የሚስማማ አካባቢዎችን በኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴ ማረስ ነው ይላሉ።
እንደማንደፍሮ (ዶ/ር) ገለፃ፤ በክልሉ ሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር የእርሻ መሬት በኩታ ገጠም ለማረስ በእቅድ ተይዟል። በዚህም ለማግኘት ከታቀደው 187 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ወደ 116 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት በኩታገጠም ለማግኘት ታቅዷል። ይሄም የአስተራረስ ዘዴው ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር አስቻይ መሆኑን የሚያሳይ ነው።
ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለኩታ ገጠም እርሻ ተስማሚ በመሆኑ በኩታ ገጠም ለማረስ የተለየ መሆኑን የሚናገሩት ማንደፍሮ (ዶ/ር)፤ ከዚህ ውስጥ ከአምስት መቶ 21 ሺ ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ በመጠቀም በዘር ተሸፍኗል ብለዋል።
በዋናነት በቆሎ፣ ስንዴ፣ ማሽላ፣ የቢራ ገብስ፣ ቦሎቄና ሩዝ በኩታ ገጠም የተዘሩ ሰብሎች ናቸው። ዋናው የእርሻና የዘር ጊዜ ገና በመሆኑና የታቀደውን እቅድ ለማሳካት በክልሉ ምቹ ሁኔታ በመኖሩ በመደበኛው እርሻም ሆነ በኩታ ገጠም በመጠቀም የታቀደውን እቅድ ማሳካት እንደሚቻል አመላክተዋል፡፡
በክልሉ አብዛኛው አርሶ አደር መሬት አነስተኛና በተበጣጠሰ ሁኔታ የሚገኝ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በዚህ የተነሳ ለመካናይዜሽን (በትራክተር ለማረስ) እርሻ የተመቸ አለመሆኑን አመላክተዋል። ይሁንና የኩታ ገጠም እርሻ በትራክተር ማረስን በክልሉ አስቻይ አድርጓል። በተለይ በክልሉ በሩዝ ልማት በሚታወቁ አካባቢዎች በኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴ እንዲጠቀሙ በማድረግ ሩዝን በስፋት እንዲያለሙ ማድረግ ተችሏል። በተመሳሳይ በጤፍና በበቆሎም ሙሉ ሳይንሳዊ አስተራረስን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ መኖሩን በማንሳት የኩታ ገጠም አስተራረስ በክልሉ በየጊዜው ጭማሪ ማሳየቱን ጠቅሰዋል።
እንደማንደፍሮ (ዶ/ር) ገለጻ፤ በክልሉ የኩታገጠም እርሻ ከዓመት ዓመት መሻሻል እያሳየ ነው። በክልሉ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ በኩታ ገጠም የታረሱና የተዘሩ ማራኪ ሰፋፊ ማሳዎች መታየት ጀምረዋል። ዘንድሮም ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ ይሆናል። የኩታ ገጠም እርሻ በጥሩ ሁኔታ ላይ ከመገኘቱም ባሻገር የክልሉ አርሶ አደር ለዘመናት ሲተገብረው ከቆየው ማሳን በበሬ ከማረስ ሥራ ወደ ትራክተር እርሻ መዘዋወር የግድ ነው። በዚህ የተነሳ ዘንድሮ ለማረስ ከታቀደው አምስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር 982 ሺ ሄክታሩን ወይም አንድ አምስተኛውን በትራክተር ለማረስ በእቅድ ተይዟል። እስካሁን 304 ሺ ሄክታር መሬት 729 ትራክተሮችን በመጠቀም ታርሶ ዘር ተዘርቶበታል።
በክልሉ በትራክተር ለማረስ ከታቀደው መሬት የታረሰው 30 በመቶ አካባቢ መሆኑን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በትራክተር የታረሰው መሬት የማነሱ ምክንያት በክልሉ ትራክተርን በመጠቀም በማረስ የሚታወቁት አካባቢዎች የዘር መዝሪያ ወቅት ገና በመሆኑ እንደሆነ አስረድተዋል።
ቆላማ አካባቢ የሆኑት ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ሁመራ፣ መተማ፣ ጃዊና መሰል ሰሊጥና አኩሪ አተር በማልማት የሚታወቁ አካባቢዎች ዘር መዝራት ስላልጀመሩ ትራክተርን በመጠቀም የሚለማው ሰብል አፈጻጸም ዝቅ ብሏል። እነዚህ አካባቢዎች ትራክተርን በመጠቀም በማረስ የሚታወቁ መሆናቸውንና አካባቢውም ለትራ ክተር እርሻ የተስማማ መሆኑን በማንሳት አካባቢዎች ሲታረሱ አፈጻጸሙ ከፍ ይላል ብለዋል፡፡
በክልሉ ምርት ሲመረት በሦስት ዋና ዋና ዓላማዎች ላይ በመመሥረት ነው የሚሉት ማንደፍሮ (ዶ/ር)፤ የምግብ ሰብል የምግብ ፍጆታን ለማሟላት በማሰብ፤ የኢንዱስትሪ ፍላጎትን ማሟላት የሚያስችሉ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችና ወደ ውጭ የሚላኩ ሰብሎች እንደሚመረቱ ጠቁመዋል። በክልሉ እነዚህን ከግምት ውስጥ አስገብቶ ምርት እየተመረተ ሲሆን፤ ይህንን ለማገዝ ከዚህ ቀደም አንድ ቀበሌ ላይ አንድ የግብርና ባለሙያ ብቻ እንደነበር ያስታውሳሉ።
አሁን ግን በየሙያው በርካታ ባለሙያዎች እንዳሉና ከዞን እስከ ቀበሌ ተመሳሳይ አደረጃጀት ተፈጥሮ አርሶ አደሮች የተሻሻሉ አሠራሮችን እንዲተገብሩ እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል። ገበያ ተኮር ምርቶች እንዲያመርቱ፣ ማሳውን በየእለቱ እንዲፈትሹ፣ ፈጥነው እንዲያርሙ፣ ማሳቸው በተባይ እንዳይጠቁ ተባይ በተከሰተ ጊዜ ፈጥነው መከላከል እንዲችሉ ምክር መስጠት የሚችሉ በቂ ባለሙያዎች በክልሉ መኖራቸውን ጠቅሰዋል። ለዚህም በክልሉ ከበፊቱ በተሻለ አደረጃጀትና ባለሙያ ተፈጥሮ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ይላሉ።
የክልሉ አመራሮችና የዘርፍ የፌደራል መሥሪያ ቤቶች ለክልሉ የግብርና ዘርፍ በቂ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ለአብነት የአፈር ማዳበሪያ በፌደራል ደረጃ ግዢው ተፈጽሞ ክልሉ ከሚያስፈልገው ከ50 በመቶ በላይ ማዳበሪያ ደርሶ ተሰራጭቷል ይላሉ። የተቀረውም ግዢው ተፈጽሞ በጉዞ ሂደት ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል። በክልሉ የሚመለከታቸው ሴክተሮች ተቀ ናጅተው እቅዱን ከማሳካት አንጻር ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል። በክልሉ የታቀደውን ለማሳካት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ ሕዝብ ሕይወት 86 በመቶ ግብርና ላይ የተመሠረተ ነው ያሉት ማንደፍሮ (ዶ/ር)፤ አብዛኛው የክልሉ ሰው መተዳደሪያ የሆነው ግብርና ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል። ክልሉ ላይ የሚመረት ምርትና የሚመጣ ለውጥ በፌደራልም አበርክቶው ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰው፤ በክልሉ የሚመረት ምርት 36 በመቶ ለሀገራዊ ምርት ሽፋን እንዳለው በማንሳት፤ ከክልል ባለፈ ሀገርን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
በቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም