
አሜሪካ በኢራን ሦስት የኒውክሌር ተቋማትን በቦምብ መደብደቧን ተከትሎ ቴህራን አሜሪካ ቀዩን መስመር ማለፏን ገለጸች። ጥቃቱን ሪፐብሊካኖች ሲያወድሱት ዲሞክራቶች ግን አሜሪካ ወደ ሌላ “ማብቂያ ወደሌለው” ጦርነት እየገባች ነው ሲሉ ነቅፈውታል።
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰይድ አባስ አራግቺ ጥቃቱን ተከትሎ፤ ጥቃቱን አስከፊ ነው ሲሉ አውግዘው፤ ኢራን ሉዓላዊነቷን ለመጠበቅ ሁሉንም አማራጮች እንደምትመለከትም አመልክተዋል።
ሚኒስትሩ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባጋሩት ጽሑፍ “ትናንት ማለዳ የተከሰተው ጥቃት እጅግ አስፈሪ እና ማቆሚያ የሌለው መዘዝ የሚያስከትል ነው፤ ሁሉም የተባበሩት መንግሥታት አባል ሀገራት በእዚህ እጅግ አደገኛ፣ የወንጀል ባህሪ ሊደናገጡ ይገባል”ብለዋል።
አሜሪካ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አባል ሆና በድርጅቱ ቻርተር ላይ “ከባድ ጥሰት ፈጽማለች” ሲሉም ኮንነዋል። በጥቃቱ ቀይ መስመሩን አልፋለች። ለእዚህ ድርጊቷ ሀገራቸው ሁሉንም አማራጭ እንደምትጠቀም አስታውቀዋል።
ቀደም ሲል የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በእስራኤል እና በኢራን ግጭት ውስጥ የአሜሪካ ተሳትፎ “በጣም አደገኛ ነው” ማለታቸው፤ጣልቃ ብትገባ በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ የአሜሪካን ጦር ሠፈሮች ላይ ጥቃት እንደምታደርስ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
የኢራን መገናኛ ብዙኃን በበኩላቸው ፎርዶ የኒውክሌር ተቋም “በጠላት ጥቃት ደርሶበታል” ሲል የጉዳቱን መጠን አሳንሰው ዘግበዋል።
አሜሪካ ኢራን ውስጥ በሚገኙ ሦስት የኒውክሌር ተቋማት፤ ናታንዝ፣ ኢስፋሃን እና ፎርዶ ላይ ማስታወቋ ይታወሳል። ፎርዶ በተራራዎች ውስጥ የሚገኝ እጅግ በጣም ለመድረስ አስቸጋሪ እንደነበር ሲነገርለት ነበር።
ጥቃቱን ተከትሎ ትራምፕ በቴሌቪዥን ባደረጉት ንግግር ዘመቻውን “አስደናቂ ወታደራዊ ስኬት” ሲሉ አሞካሽተው፤ ቴህራን በፍጥነት ሰላም እንድትፈጥር ወይም “ከእዚህ የባሰ” ጥቃት እንደሚደርስባትም አስጠንቅቀዋል።
እስራኤል በበኩሏ፤ በአሜሪካን ጥቃት መደሰቷን የገለጸች ሲሆን፤ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ “ድፍረት የተሞላበት ውሳኔ” እና “የታሪክን ሂደት የሚለውጥ” ሲሉ ጥቃቱን አንቆለጳጵሰውታል።
የአሜሪካንን ጥቃት ተከትሎ ኢራን በእስራኤል የተለያዩ ከተሞች ላይ ጥቃት ፈጽማለች። የእስራኤል የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ኢራን በፈጸመችው ጥቃት 11 ሰዎች ተጎድተው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ገልጿል።
ጉዳቱ ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል አንድ የ30 ዓመት ሰው በፍንጥርጣሪዎች በላይኛው የሰውነት ክፍሉ ላይ ተመትቶ መካከለኛ ጉዳት እንደደረሰበት ገልጿል።የተቀሩት 10 ሰዎች ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸውም አመልክቷል።
የእስራኤል የአየር ኃይል በበኩሉ፤ በምዕራብ ኢራን በሚገኙ “ወታደራዊ ዒላማዎች” ላይ አዲስ የጥቃት ዘመቻ መጀመሩን ተናግሯል። በኢራን ግዛት በሚገኙ የሚሳኤል ማስወንጨፊያዎች ላይ ጥቃት ማድረሱንም አስታውቋል።
ጥቃቱን ተከትሎ ሪፐብሊካኖች የትራምፕን ርምጃ ሲያወድሱ፤ ዲሞክራቶች ደግሞ አሜሪካ ወደ ሌላ “ማብቂያ ወደሌለው” ጦርነት እየገባች ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የኢራን የኒውክሌር ኃላፊ መሀመድ ኤስላም ቴህራን በአሜሪካ ጥቃት ላይ ምርመራ እንዲደረግ እንደምትፈልግ እና ተቆጣጣሪው አካል የአሜሪካንን ርምጃ እንዲያወግዝ ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም