
ዜና ሀተታ
ሀብቶም ፅጋቡ ፀጋዬ ይባላል። ከትናንት በስቲያ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ለ11ኛ ጊዜ በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብር ካስመረቃቸው 1ሺ203 ተማሪዎች መካከል ተመሳሳይ ነጥብ በማምጣት የወርቅ ተሸላሚ ከሆኑ ሁለት ተማሪዎች አንዱ ነው።
የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ወስዶ የተሻለ ውጤት በማምጣት አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መመደቡን ይናገራል፤ በጊዜው ዩኒቨርሲቲውን የሚመለከቱ አሉታዊ ሃሳቦች ከተለያዩ አካላት ቢነገሩትም፤ እሱ ግን የይቻላል መንፈስን በልቡ ሰንቆ፤ በቅድመ ምረቃ መርሃ ግብር ከኤሌክትሮ መካኒካል ምህንድስና ትምህርት ከፍል 3 ነጥብ 96 ውጤት በማምጣት የወርቅ የሚዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።
ወደ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በሚገባበት ወቅት ያጋጠመውን ነገር ሲያስታውስ እንዲህ ይላል፤ “ገና ግቢ ስንገባ ዩኒቨርሲቲውን የሚመለከቱ አሉታዊ ሃሳቦች ይሰሙ ነበር፤ ትምህርቱም ያን ያህል ነው የሚሉ አንዳንድ አሉባልታዎች ነበሩ”
በትምህርት ወቅት ያጋጠመን ግን ከእዚህ በተቃራኒው ነው። የትምህርት አሰጣጡ ጥሩ ነበር፤ ጠንክሮ ማጥናት ከተቻለ የተሻለ እውቀት እና ውጤት ማግኘት እንደሚቻልም በተግባር ማየት አስችሎታል።
በዩኒቨርሲቲ ቆይታው በክፍል የተማራቸውን ትምህርቶች በየቀኑ የመከለስ፣ መምህራን ከሚያስተምሩት ሞጁል በተጨማሪ የተለያዩ መጻሕፍትን የማንበብ ልምድ እንዳለው፤ ይህንንም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቆይታው ያካበተው የጥናት ልምድ እንደሆነ ለውጤታማነቱም በከፍተኛ ሁኔታ እንደረዳው ይናገራል።
ተማሪዎች ወደ ትምህርት በሚገቡበት ወቅት ሥራ መቀጠርን ብቻ ትኩረት አድርገው መግባት እንደሌለባቸው፣ ሥራን ብቻ ታሳቢ አድርገው ከገቡ የተለያዩ ተግዳሮቶች ሲያጋጥሟቸው ተስፋ ለመቁረጥ ቅርብ እንደሚሆኑ፤ ዋና ትኩረታቸው ሊሆን የሚገባው በሚያገኙት እውቀት እና ክህሎት ላይ ሊሆን እንደሚገባ ይመክራል።
በቀጣይ በተማረው የትምህርት ዘርፍ የማስተርስ ዲግሪውን መሥራት እና በሮቦቲክ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ ተሠማርቶ ለሀገሩ የተሻለ ነገር የማበርከት ሃሳብ አለው።
በኬሚካል ምህንድስና 3 ነጥብ 96 በማምጣት የዋንጫ እና የወርቅ ሜዳሊያ በመሸለም ተመርቋል። በእጅግ ከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀችው ሌላኛዋ ተመራቂ ሰሃረን ኑረዲን ናት።
ሰሃረን በበኩሏ፤ ወደ ዩኒቨርሲቲው ስትመደብ እንደ ሀብቶም ተመሳሳይ አሉታዊ ሃሳቦች ቢገጥሟትም፤ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ተቋቁማ ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት እንዳደረገች ተናግራለች።
ዘመኑ ተሻሽሎ አሁን ላይ በየትኛውም የትምህርት መስክ የሴቶች ተሳትፎ እየጎለበተ መሆኑን በማንሳት፤ ጠንክሮ መሥራት ከተቻለ ውጤት ለማምጣት ሴትነት ፈተና እንደማይሆን፤ ሴቶች ተስፋ ባለመቁረጥ ዓላማቸውን ለማሳከት ጠንክረው ሊሠሩ ይገባልም ትላለች።
በቀጣይም በተማረችበት የትምህርት መስክ በተለይም በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ ያላትን ሙያዊ እውቀት በማበርከት የድርሻዋን በመወጣት ለሀገር እድገት እንደምትጥር አመልክታለች።
ዩኒቨርሲቲው በእለቱ በመደበኛና ተከታታይ የትምህርት መርሃ ግብር በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሁለተኛ ዲግሪና እና በሦስተኛ ዲግሪ ሴት 362 ወንድ 841 በአጠቃለይ 1ሺህ 203 ተማሪዎች አስመርቋል፤ ከተመራቂዎቹም 30 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።
ዩኒቨርሲቲው ከተመሠረተ 14 ዓመት ሲሆነው፤ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ከ14 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል።
በዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም