የሰላም አያያዙን እንወቅበት

እስቲ ለመሆኑ ሰላምን የማንፈልግ አለን? ቅሉ ምርጫችን ሳይሆን ግዴታችን ነው። ምክንያቱም ከመኖር በፊት ለመወለድም ሰላም ይሻል። ተወልዶ ለመኖር ብቻ ሳይሆን ሞቶ ለመቀበርም ሰላም ያስፈልጋል። ‘አሟሟቴን አሳምርልኝ’ ከማለታችን በፊት ጸሎታችን ለሰላም መሆን አለበት።

“የዕለት እንጀራችንን ስጠን” ብለን እንጀራው ካለ ሰላም አይመጣም። ቢመጣና መሶባችንን ቢሞላ እንኳን ለመብላቱም የሰላም ወሳኝነት አለው። ገና ወጥተን ገብተን፣ ሠርተን ለምናመጣው ይቅርና ዙሪያችን ያለውን አየር መማግ፣ መተንፈሱም በሰላም እጅ ነው።

ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊ… ዓለማዊና መንፈሳዊ፣ ቁሳዊና ንፋሳዊ ሕይወትና ኑሯችን በአንድም ሆነ በሌላ ከሰላም ጋር የተቆራኘ ነው። ታዲያ ይህንን ሰላማችንን ነው ካስማው ፖለቲካ አድርገን ያረፍነው። የእኛ ሰላም ሕልውናው ፖለቲካ እንዲሆን ከፈቀድን ሁሌም ማዕበል ላይ እንደምትናጥ መርከብ ነን።

አሁን ላይ በጥቂቱ ለማኮብኮብ እያለ ያለ አንጻራዊ የሰላም ሁኔታ እየተመለከትንም ነው። ለአብዛኛዎቻችን ይህ ሁኔታ በግልጽ ባይታየንም፤ በጦርነት ላይ የነበሩ አካባቢዎች ስሜቱንና ልዩነቱን በሚገባ ያጤኑታል። አንዳንድ ጊዜ ከርቀት ሆነን በመሰለኝ የምናደርጋቸው ነገሮች የሚጎዱት በእኚሁ አካባቢዎች የሚኖሩትን ማኅበረሰብ ነው። በጊዜው የምናደርገው ለእዚያው ማኅበረሰብ ሰላምና ፍትሕ ብለን ይሆናል፤ ግን ሁሉም ነገር ጊዜና ሁኔታ፣ ብልሃት ያስፈልገዋል።

ፖለቲካው አካባቢ ያሉ አንዳንድ ለሕዝብ ጥብቅና ቆምን የሚሉ ግለሰቦችና አካላት ከፖለቲካዊ መንፈስ ወጥተው ለሁኔታው አግባብ የሆነውን ነገር ለማድረግ ሲሳናቸው እናስተውላለን። ፖለቲካችን የሰላማችን ዘብ ሊሆን እንጂ፤ ሰላማችን በፖለቲካችን የሚዘወር ተነጂ ሊሆን አይገባውም። ሰላማችን እንደ ዊንድቬን የፖለቲካችንን የነፋስ አቅጣጫ ጠቋሚ ከሆነ አደጋው የከፋ ነው።

ወርደው የአካባቢውንና የማኅበረሰቡን የልብ ትርታ ለመስማት ከማይችሉበት ባሕር ማዶ ቁጭ ብለው ‘እኔ አውቅላችኋለሁ’ በማለት ብዙ ነገሮች ይበላሻሉ። ጥቂት መተንፈስ የጀመረው ማኅበረሰብ ትንፋሽ እናሳጣዋለን። ነገሩ አይመለከተንም፣ ምንም አናድርግ አይደለም፤ ግን በአሳቢነት የምናደርጋቸው መልካምነቶች ውጤታቸው ሁሌም ጥሩ አይሆንም።

“ዓሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል” የሚለውን ዓይነት ነገር እናስከትላለን። ስለ ሰላም ስንንቀሳቀስ ትክክለኛው “ዓሳን መብላት በብልሃት” የሚለው ነው። የሚታየው ጥሩ ነገር እንዳልሆነ እያወቅንም፣ የባሱ መጥፎ ሁኔታዎች እንዳይከሰቱና ሕዝቡ የያዘውንም እንዳያጣ ፖለቲካችንም የብልሃት መሆን አለበት። እዚህ ጋር አንዳንዴ የአንጻራዊ (ሪላቲቭዝም) ሕግን መጠቀም ያስፈልገናል።

በፖለቲካ ባህላችን ውስጥ ልማድ ያደረግናት “ሳይደፈርስ አይጠራም” አካሄዳችን ዋጋ እያስከፈለን ነው። የሕዝባችንን ሰላም ያመጣል ያልነው ምንጭ ላይ ቆመን ይጠራል እያልን አደፈረስን…አደፈረስን…ሁሌም አደፈረስን፤ ታዲያ እንዴት ይጥራ? እስከ መቼስ ውሃ ስንወቅጥ እንኑር? እየተገበርን ያለነው ፖለቲካዊ ኬምስትሪያችን የተሳሳተ በመሆኑ ውጤቱ አልመጣ ብሎናል።

በአሲድና በቤንዚል መካከል ለመፍጠር የምናደርገውን የፖለቲካ ‘ሪያክሽን’ ጠንቅቀን ካላወቅነው አደገኛ አደጋ ነው የምንከስተው። በቅድሚያ ስለ እያንዳንዱ ኬሚካል ምንነት ማወቅ ይኖርብናል። ቀጥሎ የትኛው ከየትኛው ጋር፣ በምን ያህል መጠን ቢቀየጥ ነው ትክክል የሚለውን መቀመር ያስፈልጋል። ራሳቸውን ችለው ጉዳት የማያደርሱ የነበሩ ሁለት ኬሚካሎች ተቀላቅለው ለአደጋ የሚያጋልጡ እንዳሉም ማወቅ ግድ ይላል።

ሰላማችን አንጻራዊም ሆነ ዘላቂነት ያለው እንዳይሆን እንቅፋት ከሚያበዙ ነገሮች አንዱ አጀንዳዎችን መደራረብ ነው። አንዱን ሳንጨብጥ ደግሞ ለሌላ እንዘረጋለን። ኮረብታ ላይ ሆነን ከድንጋይ ወደ ድንጋይ ስንዘል የምናደክመው ራሳችንን ብቻ ሳይሆን ሌላውንም እረፍት እንነሳለን። እርቦንና ጠምቶን፣ ምግብና ውሃ ለማግኘት የምንሄድበት መንገድ የምንተነፍሰውን አየር የሚያሳጣን መሆን የለበትም። አለበለዚያ ምግብና ውሃ ማግኘታችን ምንም ትርጉም አይኖረውም።

ሰላም ልክ በትንፋሻችን እንደሚመላለሰው አየር ነው። አንድ ማኅበረሰብም ሆነ ግለሰብ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ሊያጣው የማይገባ የመጀመሪያው ነገር ሰላም ነው። አጀንዳዎቻችን የሰላማችንን ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ ከሆኑ ‘ቅድሚያ ለሰላም’ ማለት ይኖርብናል። ሌላውን ለማግኘት ስንል ሰላማችንን መስዋዕት ማድረግ በቀላሉ የማይፈታ ትልቁ ስህተታችን ይሆናል። “ለሁሉም ጊዜ አለው” እንዲል ጠቢቡ፣ ሁሉን ለትክክለኛው ጊዜ ሰጥተን፣ ሰላም ግን በሁሉም ጊዜ ወሳኙ ነገር እንደሆነ መገንዘብ ጥበብ ነው። ሁልጊዜ ፖለቲከኞች ብቻ ሳንሆን ጥበበኞችም ጭምር እንሁን።

የምንኖረው በዘመነ ዲጂታላይዜሽን ዝማኔ ውስጥ ነውና ሰላማችንም በእሱ ሕልውና ስር መውደቁ አልቀረም። ብዙ ጥሩ ነገሮችን አምጥቶ ሰላም ጋር ሲደርስ ግን ከፋ። በተለይ ልቅነት የበዛባቸው የማህበራዊ ሚዲያዎች ከጊዜ ጊዜ አሳሳቢነታቸው የሚጨምር እንጂ ሰላማዊ እረፍት የሚሰጥ አልሆንም። በሀገራችን ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም አጠቃቀሙን በመሳት ከግለሰቦች እስከ ማኅበረሰብ አደጋ ላይ ይወድቃሉ።

በግዴለሽነትና በክፋት የሌላውን ሰላም ከመንሳት አልፎ ራሳቸውን ለሞት የዳረጋቸው በየሳምንቱ ሳይሆን በየዕለቱ ሞልተዋል። ሥነልቦናዊ ቀውሱ ከግለሰቦች አልፎ ወደ ማኅበረሰብ ተዛምቷል። የዲጂታሉ ዓለም አደገኛ ወረርሽኝ እንበለው። ‘የጸረ ሰላም ኃይሎች’ ብለን ከጠራንም እዚህ ውስጥ ተወሽቀው ሴራ የሚጎነጉኑ መርዛማ ፓራሳይቶችን ነው። ፖለቲካዊ ንቃተ ሕሊናችን ገና በሆነና በማህበራዊ ኑሯችን ተጠጋግተንና ተቀራርበን ለምንኖር በተለይ ለእኛ ተያይዘን የምናልቅበት ወረርሽኝ ነው።

መጥፎዎች ብቻ ሳይሆኑ ስለ ማኅበረሰባቸው ግድ የሚላቸው ጥሩዎችም ተደባልቀው የሚኖሩበት እንደመሆኑ ምርቱን ከግርዱ ለመለየት ከሕዝቡ ይልቅ ምናልባት ኢንሳ ይቀርባል። ይህ ማለት ግን “ከስንዴ የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ” ዓይነት ሊሆን በፍጹም አይገባም። መብት ያለው ሁሉ ግዴታም አለበትና የመናገርና ሌሎች መብቶችንም ከሕግና ከማኅበረሰብ ሰላም አንጻር መታረቅ ይኖርባቸዋል።

ሀገራችን ውስጥ በምንመለከተው ሁኔታ የልማት እና የሰላም ጋዜጠኝነት ፖለቲካዊ ዳራ እንዲኖራቸው አድርገን ስለምንጠቀምባቸው በሁለት አመለካከቶች መካከል ከአንዱም ሳይሆኑ መሐል ሰፋሪ ሆነው ይታያሉ። በማኅበረሰቡ፣ በመንግሥት እና በሚዲያው ዘንድ ያሉ እሳቤዎች ሙሉ ለሙሉ መቀየር ያለባቸው ናቸው።

እንደ ኢትዮጵያ ባለች በልዩነቶች የታጨቀች ሀገር ውስጥ የሰላም ጋዜጠኝነት ጠቀሜታው እንዲሁ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም። ባደጉ ሀገራት ውስጥ ራሱን ችሎ በራሱ ባለሙያ የሚመራም ጭምር ነው። አሁን በምናቦጫርቀው መልኩ ሳይሆን፤ መፍትሔ ሊሆን በሚችልበት መልኩ ቀርጸን ለውጦችን በመፍጠሩ የግልም ሆኑ የሕዝብ ሚዲያዎቻችን ሊጨነቁበት ይገባቸዋል።

ሰላማችንን ሰላማዊ ለማድረግ ጣት ከመቀሳሰር ወጥተን እያንዳንዳችን በግል ኃላፊነት መውሰድን እንለማመድ። የሌሎችን ጉድፍ ከመንቀሳችን በፊት ራሳችንን በመስታወት ፊት አቁመን፣ ሌላውን የሚመለከቱ ዓይኖቻችንን እናስተውላቸው። ከፊት ገጽታችን ላይ በመልካችን ውስጥ የሚነበበው ምን እንደሆነ ማወቅ አለብን።

ቆም እያለ ራሱን ውስጡን የሚፈትሽ መንግሥት የሕዝብን የልብ ትርታ ለማድመጥና ቀጣይ ርምጃውን ለማወቅ አይከብደውም። በፓርቲም ሆነ በግል የራሱን ፖለቲካዊ አቋም የያዘም በእውነትና በሕዝብ ውስጥ የእኔ ትክክለኛው ቦታ የቱ ጋር ነው፣ እንዴት መሄድ፣ ምንስ ማድረግ አለብኝ ብሎ ከራሱ ጋር ለማውጋት ይችላል።

ሁሉም ግን ‘የእኔ ፖለቲካ ተጠሪነቱ ለሕዝብ ወይንስ ለፓርቲ… ለግላዊ አቋምና ጥቅም?’ ብሎ ራሱን ይጠይቅ። ዝንጀሮ እንኳን “ቅድሚያ የመቀመጫዬን” ነበር ያለችው። ማኅበረሰባችንስ ምን ይላል? ‘ቅድሚያ ለሰላሜ’ በማለት ከአውሎ ንፋሱ ገለል ብሎ የሚያስተውል ብልህ መሆን ይጠበቅበታል። ሁላችንም ሰላምን መፈለጉን ብቻ ሳይሆን በአንጻርም በዘለቄታም አያያዟንም እንወቅ።

ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

በሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You