ትምህርት ቤቶች የዕውቀት መፍለቂያ ቦታዎች ናቸው። ተማሪዎች በእውቀትና በስነምግባር ታንፀው የሚወጡባቸው ስፍራዎችም ናቸው። ለተማሪዎችም ከወላጆች ቀጥሎ ትልቁን ሀላፊነት የሚረከቡ እነዚሁ ትምህርት ቤቶች ናቸው። በመሆኑም የትምህርት ቤቶች ውጫዊና ውስጣዊ ከባቢዊ ሁኔታዎች ለተማሪዎች የተመቹ መሆን ይገባቸዋል። እውቀትን ለመገብየት፣ ለፈጠራና ምርምር ለማነሳሳት በትምህርት ቤት ቆይታቸው ወቅት ደስተኛ ሆነው ማሳለፍ አለባቸው።ለዚህም የትምህርት ቤት አካባቢዎች ፅዱ፣ ምቹና ማራኪ መሆን ይገባቸዋል።
በትምህርት ቤት ቆይታቸው እንዲሁም ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱና ሲመለሱ የሚመለከቱት ነገር አእምሮቸውን ለመጥፎ ነገር የሚገፋፋ ሳይሆን ለመልካም ነገር የሚያነሳሳ መሆን አለበት። ይሄ ሲሆን ተማሪዎች ከተለያዩ በሽታዎች የተጠበቁ፣ ከሱስ አምጪ ነገሮችም የራቁና ሙሉ ጊዜያቸውን ለትምህርትና ለጥናት የሚያውሉ ይሆናሉ። ሀገርም ከእነዚህ ወጣቶች የምትጠብቀው አለ።
ይሁን እንጂ አሁን በከተሞች አካባቢ ባሉ ትምህርት ቤቶችና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ የሚታየው ተማሪውን ለተሻለ ነገር የሚያነሳሳ ሳይሆን ለጉዳት የሚዳርግ ነው። በተለይም በትምህርት ተቋማት ዙሪያ በአይነትና በብዛት እየተስፋፋ የመጣው የጫት መሸጫና ማስቃሚያ፣ የሺሻ ቤት እና ማስጨሻ፣ የጭፈራ ቤት፣ የቁማር እና መሰል ቤቶች መበራከት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። እነዚህ ሱስ አምጪ ነገሮች ተማሪዎችን በማዘናጋት፣ ሱሰኛ በማድረግ እንዲሁም በትምህርታቸው ደካማ እና ለስርዓት አልበኝነት እያጋለጧቸው ይገኛል።
እነዚህ ንግዶች የሚካሄዱት ከፊሎቹ ከመንግስት ህጋዊ ንግድ ፈቃድ አውጥተው ነው። ይሁን እንጂ ስራውን የሚሰሩት ባወጡት ፈቃድ መሰረት ብቻ ሳይሆን በስተጀርባ ድብቅ ማስቃሚያ፣ ሺሻ ማስጨሻና ሌሎች ተግባራት የሚከናወኑባቸው ክፍሎችን በማዘጋጀት ጭምር ነው። የነገው ሀገር ተረካቢ ትውልድ በሱስ እየደነዘዘና ከመስመር እየወጣ መሆኑ በየአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች ቢያውቁም አይቶ እንዳለየ፣ ሰምቶ እንዳልሰማ እያዩ ማለፋቸው አሳዛኝ ነው። ዜጎችን የመቅረፅ ትልቅ ሀላፊነት የተጣለባቸው ትምህርት ቤቶች ግን ችግሩ እንዳሳሰባቸው በተደጋጋሚ ሲያሳስቡ ይደመጣል።
እነዚህ ቤቶች እንዲዘጉ ወይም ከትምህርት ቤቶች አካባቢ እንዲርቁ በተደጋጋሚ ጊዜ ከወላጆች፣ ከመምህራንና ከትምህርት ቤተሰብ ጥያቄ ሲቀርብ ተደምጧል። ጉዳዩ የሚመለከተው አካልም በተደጋጋሚ ጊዜም እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንና በቀጣይነትም የእርምጃው አካል እንደሚሆን አስታውቋል።ሆኖም ግን አሁንም ከመባባስ ይልቅ የተገኘ ለውጥ የለም።ከመስፋፋት ውጪ ሲቀንስ አልታየም። በትምህርት ቤቶች አካባቢ ያለው የተማሪዎች ማዘናጊያና የሱስ አጋላጭ ቦታዎች አድማሳቸውን እያሰፉ ናቸው። ነገ ሀገር ይረከባል ተብሎ ተስፋ የሚጣልበትን ወጣት ሀይል በሱስ በማደንዘዝ ላይ ናቸው።
አንዳንዶቹ ቤቶች በራቸው ላይ የጀበና ቡና ይባል እንጂ ውስጣቸው «ውስጡ ለቄስ» አይነት ነው። እንዲሁም በራቸውን ዘግተውና ጥበቃ አቁመው፣ የማሳጅ ቤት ብለው ውስጥ ለውስጥ ተመሳሳይ ስራ የሚሰሩ በርካቶች ናቸው ።
በኢፌዴሪ የፖሊሲ ጥናት እና ምርምር ማዕከል በትምህርት ተቋማት የስነዜጋና ስነምግባር ግንባታና ዴሞክራሲያዊነት፣ ተግዳሮቶችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች በሚል ግንቦት 2009 ዓ.ም በተካሄደው ጥናት ላይ የተመለከተውም የትምህርት ተቋማት ከፍተኛ የሆነ ኃላፊነት የተጣለባቸው ቢሆንም ይህንን ኃላፊነት በበቂ ሁኔታ እንዳይወጡ የሚያደርጉና ከትምህርት ተቋማቱ ዙሪያ የሚገኙ ውጫዊ ከባቢያዊ ሁኔታዎች መኖራቸውን ጠቅሷል። ከዚህም መካከል የጫት መቃሚያና መሸጫ፣ የአልኮል መጠጥ ቤቶችና ማከፋፈያዎች፣ የሀሺሽና ሺሻ ማጨሻ ቤቶች፣ ጭፈራ ቤቶች፣ ቁማር ቤቶች (የካርታ ጨዋታ፣ ፑልና ከረንቡላ) እና የቪዲዮ ወይም ፊልም ቤቶች ተማሪዎች ዓላማቸውን እንዲስቱና የትምህርት ተቋማትም የመማር ማስተማሩን ስራ በአግባቡ እንዳይወጡ ከሚያደርጉ መካከል በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።ጥናቱ የችግሩን ስፋትና አሳሳቢነት የሚያመለክት ነው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በየክፍለ ከተሞች የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተብለው ከተለዩት ጉዳዮች መካከል አንዱ ተማሪዎችን ለሱስ ተጋላጭ የሚያደርጉ ነገሮች በአይነትና በብዛት መስፋፋት ነው። ይሄ የትምህርት ቤት የፖሊስ ወይም ደግሞ የደንብ ማስከበር ጉዳይ ብቻ ተደርጎ መታየት የለበትም። የሚጠፋው ዜጋ ነው። የሚጠፋው ኢትዮጵያን ነገ ይረከባል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ወጣት ነው። በመሆኑም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
የትምህርት ቤቶችን አካባቢ ለመቆጣጠር የወጣ መመሪያ አለ፤ በዚህ መመሪያ መሰረት የንግድ ቤቶች ከትምህርት ተቋማት 500 ሜትር ርቀት ላይ መሆን አለባቸው። አሁን ባለው ሁኔታ ይሄንን የሚያሟላ አይደለም። ስለዚህ ይሄንን ማስከበር አንድም የህግ አካሉ ጉዳይ ቢሆንም ትምህርት ቤቶች ወላጆች እና ሌሎችም ይሄ ተግባራዊ እንዲሆን አጥብቀው ሊሰሩ ይገባል። በዚህም ተማሪዎችን ከሱሰኝነት እንታደግ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2011