
ስለትምህርት ሲነሳ ቀድሞ የሚታወሰን የትምህርት ጥራት ጉዳይ ነው። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን የትምህርት ጥራት ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ መንግስት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ዘርፉን ለመለወጥ እየሰራ ይገኛል፡፡ ዘንድሮ ተግባራዊ የተደረገው የትምህርት ፍኖተ ካርታም የዚሁ አካል ነው፡፡
በሌላ በኩል የስነምግባር ጉዳይም በዘርፉ ከሚነሱ መሰረታዊ ግድፈቶች አንዱ ጥያቄ ነው፡፡ በተለይ ከተማሪዎች ስነምግባር ጋር ተያይዞ የሚነሱት ጥያቄዎች በኅብረተሰቡ ዘንድ መነጋገሪያ ናቸው፡፡
ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጀምሮ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃና አልፎ አልፎም የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች አለባበስ፣ የጸጉር አቆራረጥ፣ ሱሰኝነት፣ ፆታዊ ግንኙነቶችና መሰል የስነምግባር ግድፈቶች በአደባባይ ሲጣሱ ማየት አዲስ አይደለም። አልፎ አልፎም የአንዳንድ መምህራን የስነምግባር ችግር ከተማሪዎቹ ባልተናነሰ መልኩ የሚነሳበት አጋጣሚም አለ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማም ችግሩ ከሚታይባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው። በከተማዋ በትምህርት መውጫና መግቢያ ሰዓቶች በትምህርት ቤቶች አካባቢ የተገኘ ማንኛውም ዜጋ ይህንን የተማሪዎች ስነምግባር ጉድለት በቀላሉ ሊገነዘብ ይችላል፡፡ በርካታ ተማሪዎች በተለይ በሁለተኛ ደረጃ የሚማሩ ወጣት ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ እስከሚገቡ ድረስ የትምህርት ቤት ዩኒፎርሞቻቸውን ልጃገረዶቹ በቦርሳቸው፣ ወንዶቹ ደግሞ ከትከሻቸው ላይ ጣል በማድረግና አንዳንዴም ለሴት ጓደኞቻቸው በመስጠት ተማሪ ላለመምሰል የሚደረጉ ጥረቶች በገሃድ የሚታዩ ናቸው፡፡
ይህ ብቻም አይደለም፤ አንዳንድ ተማሪዎች የተሰጣቸውን ዩኒፎርም በአግባቡ በተሰፋበት አግባብ ከመልበስ ይልቅ በአዲስ መልኩ አሰፍተው ወይም ከፊሉን ቀድደው የመልበስ፣ የተሟላ ዩኒፎርም ከመልበስ ይልቅ ግማሹን ብቻ የመጠቀም፣ በዩኒፎርሙ ላይ ሌላ የመደረብ፣ ወዘተ ህገወጥ አለባበስ ሲከተሉ ይስተዋላል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዘንድሮው በጀት ዓመት ከስድስት መቶ ሺህ ለሚበልጡ ተማሪዎች ከ300 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ዩኒፎርሞችን ማሰፋቱና መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ይህ ዩኒፎርም ደግሞ በአንድ በኩል ቀደም ሲል የነበረውን የተዘበራረቀ የዩኒፎርም አለባበስ በማስቀረትና ተማሪዎች በነፃነት የመበላለጥ ስሜት ሳያድርባቸው እንዲማሩና ትኩረታቸውን ትምህርት ላይ እንዲያደርጉ ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡
ይህንን ስራ ሲያከናውን በአንድ በኩል የወላጆችና የመላውን የከተማዋን ነዋሪዎች ችግር ለመጋራት አስቦ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ መልካም ስነምግባርን የተላበሰ ተማሪን ለመፍጠርና የትምህርት ስርዓቱንም የተሻለ ለማድረግ ታስቦ ነው፡፡ አስተዳደሩ ይህንን መልካም ተግባር ካከናወነም ገና ከስድስት ወር ያልበለጠ ጊዜ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጂ ገና በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ እነዚህ ዩኒፎርሞች አላግባብ ስራ ላይ ሲውሉና አንዳንዶቹም መጀመሪያ የነበራቸውን ውበት አጥተው ባልተገባ መልኩ ተሰፍተው ከዩኒፎርም ይልቅ የፋሽን መገለጫ ሲመስሉ ይስተዋላል፡፡ እንዲህ አይነት በዩኒፎርም ላይ የሚደረጉ የተበላሹ የአለባበስ ስርዓቶች ደግሞ በአንድ በኩል ተማሪዎች ለስነምግባር አለመገዛታቸውን የሚያመላክት ነው፡፡
አንድ ተማሪ የተሟላ ስብዕና ይዞ የሚወጣው በሚያገኘው የቀለም ትምህርት ብቻ አይደለም፤ በሚማረው ስነምግባር ጭምር እንጂ፡፡ ለትምህርት ቤቱ ስነምግባር ያልተገዛ ተማሪ ደግሞ በትምህርቱም ስኬታማ ይሆናል ማለት አይቻልም፡፡ በመሆኑም እንዲህ አይነት የስነምግባር ጉድለቶች ላይ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ከትምህርት ባለድርሻ አካላት ይጠበቃል፡፡
በተለይ ወላጆች፣ መምህራንና የትምህርት ቤት የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም መላው ህብረተሰብ እንዲህ አይነት በአደባባይ የሚጣሱ የስነምግባር ጥሰቶችን በዝምታ ማለፍ አይጠበቅባቸውም፡፡ በአጠቃላይ ገና በተማሪነት ህይወት በዩኒፎርም ላይ ደባ የሚፈጽሙ ተማሪዎች ለትምህርታቸው የሚኖራቸው ታማኝነትም አጠራጣሪ በመሆኑ ከወዲሁ ሊታሰበብት ይገባል፡፡ “በእንቁላሉ ያልተቀጣ ህፃን ሲጎረምስ በሬ ቢሰርቅ አይገርምምና”።
አዲስዘመን ጥር 1/2012