
በአገሪቱ የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ማዕከል ያደረጉ ግጭቶችን በማባባስ ያለማቋረጥ እየተሰሩ ያሉ አጥፊ ስራዎች የአገሪቱን መልካም ገፅታ ከማጠልሸት ባለፈ በለጋ እድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችን ህይወት እየነጠቀ ይገኛል፡፡
ብሄር ተኮር መልክ ያላቸው ግጭቶቹ በተለይ ደግሞ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ያነጣጠሩ ናቸው፡፡ በሁለቱ ክልሎች የሚገኙ እነዚህ ተቋማት ተከስቶ የነበረውን ግጭት እና ሁከት አስመልክቶ በርካት ሀሳቦች ቀርበው የተለያዩ የመፍትሄ እርምጃዎች ቢወሰዱም መሰረታዊ ለውጥ መምጣት ግን አልቻሉም፡፡ የፌዴራል ፖሊስ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ገብቶ ጉዳዩን እንዲያረጋጋ ቢደረግም የግጭቱን ዋና ችግር ለመፍታት ተስኖት ታይቷል፡፡
በሚፈጠሩ ግጭቶች ሳቢያ የሚጠፋውን የተማሪዎችን ህይወትና የሚወድሙ ንብረቶችን ማስቀረት እንዴት ይቻላል? በሚል ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች እና የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮች ሁኔታውን የገመገሙ ሲሆን የተለያዩ መፍትሄዎችንም አስቀምጠዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ግጭት እንዲከሰት የሚያደርጉ ገፊ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? የድርጊቱ ቁልፍ ተዋንያን እነማን ናቸው? በምን ያህል ደረጃ ነው ተሳትፏቸው የሚለውን ጉዳይ እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ ጥናት በማድረግ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን እንዲወስድ የጋራ አቋም ተይዞ ወደ ስራ ተገባ፡፡
በወንጀል ተግባር የሚሳተፉ አካላትን በወንጀል ህጉ የመጠየቅ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ዩኒቨርሲቲዎቹ በችግሩ ዋና ተዋናይ ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድ ጀምረዋል፡፡ ይህ ከቁልፍ መንስኤው የሚነሳ የመፍትሄ እርምጃ በሁሉም ተቋማት ሊተገበር የሚገባው ነው፡፡
በተለይ ባለፉት 15 ቀናት ውስጥ ብቻ በተወሰደው አስተዳደራዊ እርምጃ ከ170 በላይ ተማሪዎች ከአንድ ዓመት ጀምሮ ከትምህርት እስከ ማሰናበት የደረሰ እርምጃ ተወስዷል፡፡ 280 የሚደርሱ ተማሪዎች ደግሞ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ተደርጓል፡፡
ከዚህ አስተዳደራዊ ጥሰት ከመፈፀም ባለፈ ገንዘብ ተሰጥቷቸው ግጭት እና ብጥብጥ በመፍጠር ረገድ በወንጀል ጭምር የሚጠረጠሩ 50 ተማሪዎችን መያዙንም ፌዴራል ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ከእነዚህ 50 ተማሪዎች ውስጥ ተገቢው የወንጀል ምርመራ ሲደረግ በባንክ መዝገባቸው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የገባላቸው እንዳሉም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሌሎችም በርከት የሚሉ ተልዕኮዎች እየተሰጣቸው ወደ ተቋማት በመግባትና በመበጥበጥ አገርና ህዝብ ላይ ችግር እየፈጠሩ መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል፡፡ ይህንንም በተጨባጭ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
በችግሩ ተሳትፈዋል ተብለው ከተለዩ ተማሪዎች ባለፈ አጀብ ያሰኘው ጉዳይ ደግሞ የአስተዳደር አካላት እና መምህራን ሳይቀሩ ተቋማቱ የእንጀራ ገበታቸው መሆኑን በመዘንጋት ዩኒቨርሲቲዎቻቸው በግጭት እና ሁከት እንዲተራመሱ በማድረግ ‹የጭቃ ውስጥ እሾህ› ሆነው የዘለቁ ስለመኖራቸውም ፖሊስ ይናገራል፡፡
ይህንንም በተጨባጭ መለየት መቻሉን ተረጋግጧል፡፡ በዚህም ከ10 በላይ መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች የስራ ውሎቻቸው ተቋርጦ ከስራ ገበታቸው ተሰናብተዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በደመወዝ የተቀጡ እና በማስጠንቀቂያ ጭምር የታለፉ በመቶ የሚቆጠሩ አካላትም እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቹ ውስጥ ያሉ መምህራንና የጥበቃ ሰራተኞች ጭምር ሳይቀሩ ዋና ተዋንያን ሆነው የዘለቁበት ሁኔታ ችግሩን የከፋ አድርጎት ቆይቷል፡፡
እየተወሰደ ካለው አርምጃ ጋር ተያይዞ በአሁኑ ወቅት የተወሰኑ የትምህርት ተቋማት ሙሉ ለሙሉ ወደ መደበኛ ትምህርት የገቡ ሲሆኑ ቀሪውን የትምህርት ጊዜ በሰላማዊ መንገድ ለመመለስ ህዝቡ በተለይ ደግሞ ሰላማዊ ተግባር የሚፈፅሙ የዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ሰራተኞች እና መምህራን በአጋርነት ሊሰሩ ይገባል፡፡
በተለይ ቀጣዩ ስራ የትምህርት ጊዜውን በመከለስ ቀሪው የትምህርት ወቅት ወደ ሰላማዊው ሁኔታ ለመመለስ ሰፊ ስር ሊሰራ ይገባል፡፡ በዋናነት ግን ዩኒቨርሲቲዎችን የማረጋጋት ስራ በፍጥነት ሊሰራበት እና ሰላሙም አስተማማኝ ደረጃ ላይ መድረስ አለበት፡፡
እስከአሁን ከተወሰደ አርምጃ ጎን ለጎንም አሁንም በግጭቱ እጃቸው ያለበትን መምህራን፣ ተማሪዎች እና የአስተዳደር ሰራተኞችን በሚገባ የመለየቱ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው፡፡ በርጋታና በጥንቃቄ በማጣራት የሚወሰደው እርምጃም ሊቀጥል ይገባል፡፡ በዚህ ሂደት የፌዴራል ፖሊስም ሆነ የክልል ፖሊሶች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተጠናክረው እና ጥምረት ፈጥረው ሊሰሩ ይገባቸዋል፡፡
በአጠቃላይ በጥናት በሚለዩ ውጤቶች ላይ ተመስርቶ የሚወሰደው እርምጃ ጠንካራ እና አስተማሪ መሆን አለበት፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወላጆች እና የሚመለከታቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም ተማሪዎች በገንዘብ ተደልለው አገራቸውን ማውደም፤ በተለይ ደግሞ የራሳቸውን ሕይወት አደጋ ውስጥ ሊከቱ እንደማይገባ ሊመከሩና ሊገሰፁ ይገባል!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2012