ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የእግር ኳስ ቡድን ሆኖ የተመሰረተው ከ84 ዓመታት በፊት በታኅሣሥ ወር 1928 ዓ.ም ነበር። ቡድኑ የተመሰረተበትን ወር እንጂ ቀኑን የሚጠቅሱ ማስረጃዎች የሉም። ሳምንቱ የታኅሣሥ ወር መጠናቀቂያ መሆኑን ምክንያት በማድረግ ታሪኩን ዳሰነዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ የተመሰረተው በአዲስ አበባ ልዩ ስሙ ፒያሳ ቅድስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት በአብሮ አደግ ጓደኛሞቹ አየለ አትናሽና ጆርጅ ዱካስ ነበር። ሁለቱ ጓደኛሞች አንድ ዕለት ከአንድ የአራዳ ዘበኛ ለማምለጥ አይጋዝ የሚባል የጆርጅ አርመናዊ ጓደኛው ቤት በገቡበት ወቅት ስለ የአርመኑ አራራት የእግር ኳስ ቡድን ፎቶን ተመልክተው ሀሳብ ከተለዋወጡ በኋላ ኢትዮጵያዊ የእግር ኳስ ቡድን ስለማቋቋም አሰቡ።
ጆርጅ በሚማርበት የቅዱስ ጊዮርጊስ ትምህርት ቤት መምህር ለነበሩት ስንዱ ገብሩ ሀሳቡን ሲያማክራቸው ወቅቱ ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር ያሰፈሰፈበት ጊዜ በመሆኑ ከእግር ኳሱ በተጓዳኝ የአንድነትና ኢትዮጵያዊነት ስሜት በቡድናቸው ውስጥ እንዲያካትቱ ምክር ሰጧቸው። ቀጣዩ ሥራ ተጫዋቾች ማሰባሰብ በመሆኑ ሁለቱም ከሰፈራቸው አልፈው በሚማሩበት የተፈሪ መኮንንና የቅዱስ ጊዮርጊስ ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ ባልንጀሮቻቸው ሃሳባቸውን ሲገልፁላቸው ሃሳቡን የሰሙት አብዛኞቹ ሲያፌዙባቸው ፍቃደኛ የሆኑትን ብቻ መዝግበው ከብዙ ድካምና ጥረት በኋላ ውጥናቸው ዕውን ሆኖ በታኅሣሥ ወር 1928 ዓ.ም ለአንድ ቡድን የሚበቃ አስራ አንድ ልጆች ተሟልቶ የአራዳው ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድንን መሰረቱ።
በፈረሰኞቹ የመጀመሪያ ስብስብ ውስጥ ጆርጅ ዱካስ፣ አየለ አትናሽ፣ ታደሰ ጌጤ፣ መታሰቢያ ተሰማ፣ ተስፋዬ አበጋዝ፣ ካሳ ወልዴ፣ ከበደ ጌጤ፣ አፈወርቅ ገብረመስቀል፣ ተስፋዬ መምሬ፣ ታደሰ ተሰማ፣ በየነ ወልደማርያም እንዲሁም ከሁለት ወር በኋላ ደግሞ ይድነቃቸው ተሰማ ተቀላቀለ። በወቅቱ የነበሩ ልጆች ለትውልድ ሠፈራቸው መታሰቢያ እንዲሆን በማሰብ የአራዳው ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን ብለው ሰየሙት። ጆርጅ ዱካስ ወላጆቹን ለመሰብሰቢያ የምትሆን ቦታ እንዲያመቻቹለት በጠየቃቸው መሠረት ለስፖርት የነበራቸውን ስሜት እንዲሁም በመካከላችን ያለውን ጥልቅ ፍቅር በመረዳት ንብረታቸውን የሚያስቀምጡበት ከጨዋታ በኋላም ሆነ በፊት ጊዜያቸውን በመመካከር የሚያሳልፉበት አንድ ክፍል በግቢያቸው ውስጥ አዘጋጁላቸው።
በመጀመሪያዎቹ ዓመታት የቡድኑ ወጪዎች የሚሸፈኑት ተጨዋቾቹ ከግል ኪሳቸው በሚያዋጡት መዋጮ ነበር። ቡድኑ ታሪክ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ከአርመን አራራት ቡድ ጋር ነበር። ጨዋታውን ይድነቃቸው ራሱ ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለት ለዜሮ አሸንፏል።
ኢትዮጵያ ከ1929 እስከ 1934 ዓ.ም በጣልያን ቁጥጥር ስር በነበረችበት ጊዜ ይህ ክለብ የሃገራዊ አንድነትና የህዝቡ የነፃነት ምሳሌ ለመሆን ብዙም ጊዜ አልፈጀበትም። ይህ ግን ጣልያኖችን ያስከፋ ነገር ሆነ።
በቀጥታ ቡድኑን ለማፍረስ ብዙ ሙከራ ቢያደርጉም ያልተሳካላቸው ጣልያኖች ግን የራሳቸውን ‘6 ኪሎ (Cenco Maje)’ የተባለ ክለብ በመመስረት ቅዱስ ጊዮርጊስን ለማዳከም ትግል ገቡ። የጊዮርጊስ ተጫዋቾች ከጣልያኑ ክለብ ጋር የሚያደርጓቸውን ብዙዎቹን ጨዋታዎች ቢያሸንፉም በጨዋታዎቹ መጨረሻ ላይ ግን በአራዳ ፖሊስ (በዛን ጊዜ በጣልያን የሚመራ) የሚደርስባቸው ድብደባ ቀላል የሚባል አልነበረም። ይህ ግን ተጫዋቾቹን ተስፋ ከማስቆረጥ ይልቅ ተነሳሽነታቸውን ይበልጥ ጨመረው። በዚህ የትንቅንቅ ወቅትም ክለቡ ስሙን ወደ ሊቶሪዮ ውቤ ሰፈር እንዲቀይር ተገዶ ነበር። ፋሺስት ኢትዮጵያን ለቆ ከወጣ በኋላም ቢሆን በ 1938 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ሲጀመር ተሳትፎ ካደረጉት 5 ክለቦች ውስጥ ኢትዮጵያን በመወከል ብቸኛ ክለብ ነበር።
ለ11 ዓመታት በተጨዋቾቹ የግል ጥረት ከተጓዘ በኋላ በ1940 ዓ.ም ወደ ስፖርት ማህበርነት ተሸጋግሮ ህዝባዊ አደረጃጀት ያለው ቡድን ለመሆን በቃ። ይህም ቅዱስ ጊዮርጊስን በምስረታ ብቻ ሳይሆን ህዝባዊ አደረጃጀት በመያዝ በኢትዮጲያ የመጀመሪያው የእግር ኳስ ቡድን እንዲሆን አስችሎታል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ እስከ 1969 ዓ.ም ከተጓዘ በኋላ መንግስት ባወጣው አዲስ የስፖርት አደረጃጀት መሠረት ስፖርት ክለቡ በደረሰበት የመፍረስ አደጋ ከ1970 እስከ 1974 ዓ.ም ከውድድር ተገልሎ ቆይቷል። በ1975 ዓ.ም ወደ ውድድር ሲመለስም በአደረጃጀትና ስያሜ ግን እንደቀድሞ ሆኖ አልነበረም። ‹‹አዲስ አበባ ቢራ›› በሚል ስያሜ ወደውድድር ሲመለስ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ በባለቤትነት እያስተዳደረው ነበር። ቡድኑን መልሶ በማቋቋም ሂደት የቀድሞ የክለቡ ዝነኛ ተጨዋቾች ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።
ከተመሰረተ በኋላ በውድድር በቆየባቸው 50 ዓመታት አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ በተለያየ ጊዜያት በተለያዩ ምክንያቶች የስም ለውጥ ለማድረግ ተገዷል። ለመጀመሪያ ጊዜ ክለቡ የስም ለውጥ እንዲያደርግ የተገደደው በጣሊያን ወረራ ወቅት ሲሆን ‹‹ሊቶሪያ ውቤ ሠፈር አራዳ›› ተብሎ ነበረ። ከ1975 እስከ 1983 ዓ.ም አዲስ አበባ ቢራ፤ ከ1984 እስከ 1988 ዓ.ም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ተብሎም በተለያዩ ውድድሮች ላይ በቢራ ፋብሪካው ባለቤትነት እንዲሳተፍ ተደርጓል። ወደ ህዝባዊ ክለብነቱ የተመለሰው በ1988 ዓ.ም መጨረሻ 60ኛ ዓመት የልደት በዓሉን ሲያከብር ነበር።
የአራዳው ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመርያ መለያ ቡናማ እና ነጭ ቀለም ሲኖረው አሠራሩም በረድፍ ሆኖ እንደ መቀነት ነበር። ቀጥሎ ቡድኑ የለበስነው መለያ የሃገር ፍቅርን ስሜት የሚገልጽ ሲሆን መደቡ ነጭ ሆኖ ዙሪያውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ያለበት ነው። ትርጓሜው ነጩ የሰላም ምልክት ሲሆን ዙሪያውን ያለው ባንዲራ የአንድነት፣ የፍቅር እና ለሃገር የሚከፈል መስዋዕትነትን ያመላክታል። በዚህ ምክንያት መለያው በተጫዋቾቹም ሆነ በተመልካቹ በጣም ተወዳጅ ለመሆን ቻለ። ፋሽስት ጣሊያን ሚያዝያ ወር 1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ቡድኑ ይህን መለያ እንዳይለብስ አደረገ። በምትኩ በጣሊያን ሃገር ከሚገኙ ቡድኖች አንዱ የሆነው የኢንተር ሚላን ክለብ መለያ መደቡ ሰማያዊ ባለጥቁር ሪጋ መለያ እንዲለብስ ቡድኑን አስገደደው። በ1933 ዓ.ም ጣሊያን ከኢትዮያ ከተባረረ በኋላ ግማሽ ነጭና ግማሽ ጥቁር መለያን መልበስ ጀመረ። መለያው የተመረጠው የጣሊያን የዘረኝነት ጭቆናን ለመጋፈጥና ነጭና ጥቁር እኩል መሆናቸውን ለማመላከት በማሰብ ነበር። በመጨረሻ አሁን ድረስ ቡድኑ የሚታወቅበትን መደቡ ቡርትካናማ ሆኖ ደረቱ ላይ በቀይ ቀለም የ’ቪ’ ምልክት ያለበትን መለያ ከ1938 ዓ.ም ጀምሮ መልበስ ጀመረ። በመለያው ደረት ላይ ያለው የ’ቪ’ ምልክት የአሸናፊነት፣ የድል ምልክት ነው። መለያውን የቡድኑ ተጫዋች የነበሩት ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ሊል ከተባለ የፈረንሳይ የእግር ኳስ ቡድን ተመልክተው እንደመረጡት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ድረ ገጽ ላይ በሰፈረው የቡድኑን ታሪክ ተጠቅሷል።
በሀገር ውስጥ ውድድሮች ተሳትፎው ከ80 በላይ ዋንጫዎቹን ሰብስቧል ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጲያ የእግር ኳስ ስፖርት ውድድር በክለቦች መካከል መካሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተደረጉ ውድድሮች ሁሉ ተካፋይ ሆኗል። በተለያዩ ምክንያቶች ለጥቂት ዓመታት ሳይሳተፍ ከቀረባቸው ውድድሮች ውጪ ማለት ነው። በሀገር ውስጥና አህጉር አቀፍ ውድድር ተሳትፎም ቀዳሚ ነው። ክለቡ በተሳተፈባቸው ሦስት ሀገር አቀፍ ውድድሮችም አብላጫውን ዋንጫ በመውሰድም ግንባር ቀደሙ ነው። በኢትዮጵያ የክለቦች ውድድር የምንግዜም ውጤታማ ክለብ ለመሆን የቻለው ደግሞ በፕሪሚዬር ሊግ 29፤ በጥሎ ማለፍ 13 እንዲሁም በአሸናፊዎች አሸናፊ 10 ዋንጫዎችን በመሰብሰቡ ነው። ጊዮርጊስ ከእነዚህ ውድድሮች በተጨማሪ በተሳተፈባቸው የአዲስ አበባ ሻምፒዮናና ልዩ ልዩ የመታሰቢያ፤ ዕርዳታና የበዓላት ውድድሮች በርካታ ዋንጫዎችን አግኝቷል። በአጠቃላይ ቡድኑ በሀገር ውስጥ ውድድር ተሳትፎና ውጤት የሚስተካከለው የለም።
በኢንተርናሽናል ውድድሮች የኢትዮጵያ ውክልናው ግንባር ቀደም ነው።
ክለቡ በጥንካሬው እንዲዘልቅ ከፍተኛውን አስተዋፅኦ በማድረግ ክቡር ዶክተር ሼህ ሁሴን መሀመድ አሊ አል አሙዲን ይጠቅሳሉ። የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የክብር ፕሬዚዳንት (የበላይ ጠባቂ) ናቸው። ዛሬ ስፖርት ክለቡ የሚመራው በስራ አመራር ቦርድና በቋሚ ስራ አስኪያጅ ሲሆን ቦርዱ ክለቡን በባለቤትነት ከሚያስተዳድሩ ልዩ ልዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች የተውጣጣ 9 አባላት አሉበት። ሊቀመንበሩ አቶ አብነት ገብረ መስቀል ናቸው። የስፖርት ክለቡ ሁለንተናዊ የስራ እንቅስቃሴ የሚመራው ደግሞ በተቀጣሪ ዋና ስራ አስኪያጅ ነው።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጆርጅ ዱካስ ቤተሰቦች ከተሰጠች አነስተኛ ክፍል ጀምሮ ስድስት የአዲስ አበባ አካባቢዎች ጽህፈት ቤቶች ነበሩት። ዶሮ ማነቂያ አካባቢ፣ መርካቶ አዲስ ከተማ አካባቢ፤ በፒያሳና በራስ መኮንን ድልድይ መካከል እንዲሁም ከጽህፈት ቤት አገልግሎት በዘለለ የደጋፊዎቻችን መዝናኛ ማዕከል በመሆን ጭምር የተገለገለበት ከአዲስ አበባ ስታዲየም ፊት ለፊት የሚገኝ ቦታ የቀድሞዎቹ ጽህፈት ቤቶቹ ነበረ። ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የቅድስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ዋና ፅህፈት ቤት የሚገኘው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ በቅሎ ቤት አካባቢ ከሚገኘው ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ፊት ለፊት በሚገኘው የስፖርት ማህበሩ መዝናኛ ማዕከል ቅጥር ግቢ ውስጥ ነው።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2010 ዓም ክለቡ በቢሾፍቱ ከተማ መርቆ ያስከፈተውና በታላቅ ተጫዋቹ በአቶ ይድነቃቸው ተሰማ የሰየመው አካዳሚም በአሁን ሰዓት ለክለቡ ብሎም ለአገሪቱ እግር ኳስ የወደፊት ተስፋ የሚሆኑ ታዳጊ ተጫዋቾችን በማፍራት ላይ ይገኛል። ይህ አካዳሚ ከ60 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የፈሰሰበት ሲሆን በአንድ ጊዜ እስከ 100 የሚጠጉ ታዳጊዎችን ማስተናገድ ይችላል። በውስጡም ሁለት የእግር ኳስ ሜዳዎች፣ የመመገቢያና የመልበሻ ክፍሎች፣ ጂምናዚየም፣ ዘመናዊ የህክምና ማዕከልና የመኖሪያ ክፍሎች (ዶርሚተሪዎችን) አካቶ የያዘ ነው።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታህሳስ 29/2012
የትናየት ፈሩ