እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
የክርክሩ መነሻ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፕራይቬታይዜሽን ጉዳይ ሁነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል። መንግስት “በኢኮኖሚው ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ አመጣለሁ፤ ይህንንም ዕውን ለማድረግ የሚጠቅመኝ አንዱ መንገድ በእጄ ላይ የሚገኙትን ቁልፍ የምጣኔ ሐብት አውታሮችን ሳይቀር ለግሉ ዘርፍ አስተላልፋለሁ” ማለቱን ተከትሎ ነው ጉዳዩ የትኩረት ማዕከል የሆነው።
መንግስት “ልማታዊ ነው” በሚለው መስመር በነጻ ገበያ የኢኮኖሚ ማዕቀፉ ውስጥ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ቆይቷል። አየር መንገድን፣ ባቡርን፣ ቴሌኮምን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣ ስኳር ኮርፖሬሽንን፣ የንግድ መርከብና ሎጀስቲክስ አገልግሎትን እንዲሁም የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችን በእጁ በማድረግ በኢኮኖሚው ውስጥ ጉልህ ድርሻ ይዟል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታዲያ በተለይም “የምትታለብ ላም” የሚባለውን ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ የከፍታና የኩራት ልክ የሆነው አየር መንገድ ሳይቀር የተወሰነ ድርሻቸው ለግል እንደሚተላለፍ መንግስት መወሰኑን ተከትሎ ጉዳዩ በሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ መከራከሪያና መነጋገሪያ ሆኗል።
እኛም የዚሁ ክርክር አካል የሆነውንና መንግስት ፕራይቬታይዜሽኑን አስፈጽምበታለሁ በሚል ለፓርላማው ያቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ ይህንን ጽሁፍ አሰናድተናል።
የኢትዮጵያ የፕራይቬታይዜሽን ዳራ
“ፕራይቬታይዜሽን” የሚለው ቃል እንግሊዝኛ ሲሆን፤ ንብረትን ወይም የገበያ መዋቅርን ከመንግስት ወደ ግል የማዞር ሂደትን ይገልጻል። ፕራይቬታይዜሽን የነጻ ገበያ መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታ ነው። ይኸውም መንግስት በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ሚናና ተሳትፎ በመለወጥ የግሉ ዘርፍ የገበያው ሁነኛ አንቀሳቃሽ እንዲሆን ያግዛል።
በኢትዮጵያ በደርግ ውድቀት ማግስት ገበያ-መር የኢኮኖሚ መዋቅር መዘርጋቱን ተከትሎ ፕራይቬታይዜሽን የወቅቱ ዓይነተኛ መገለጫ ነበር። ከዛሬ ሃያ ዓመታት በፊት የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዛወር አዋጅ ቁጥር 146/1991 ወጥቷል። በዚሁ አዋጅ መሰረትም መጠነ ሰፊ ፕራይቬታይዜሽን ተከናውኗል።
እርግጥ ነው ሕጉ ከመውጣቱ በፊትም ቢሆን የፕራይቬታይዜሽን ፕሮግራሙ ፖሊሲ-መር በሆነ አቅጣጫ ሲተገበር
ቆይቷል። ይሁንና አዋጁ በተለይም የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል በማዛወር ረገድ መሠረት ለመጣሉ አሌ አይባልም።
አዋጁን መሰረት በማድረግም መንግስት ከጉሊትና ሱቅ በደረቴ እስከሚቀረው ድረስ ተቆጣጥሮት ከነበረው ገበያ በከፍተኛ ደረጃ እጁን አውጥቷል። ስትራቴጂክ እና በመንግስት እጅ ቢቆዩ ለሕዝብና ለኢኮኖሚው ጠቀሜታ አላቸው የተባሉትን ውስን የምጣኔ ሐብት አውታሮችን ብቻ ይዞ ሌሎቹን ወደ ግል አዛውሯል።
በዚሁም ምክንያት መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ሚናና ተሳትፎ ቀንሷል። በአንጻሩ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ድርሻውን በማስፋት በአገሪቱ ለታየው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የነጻ ገበያ የኢኮኖሚ ማዕቀፉ ወደ ሌላ ምዕራፍ የሚሸጋገርበትን አቅጣጫ መንግስት እየተከተለ ስለመሆኑ እያስተዋልን ነው። በተለይም መገበያውን ይበልጥ ክፍት ለማድረግና ለዓመታት በብቸኝነት ተቆጣጥሯቸው የነበረውን የኢኮኖሚ አውታሮች ሳይቀር በሙሉና በከፊል ወደ ግሉ ዘርፍ ለማስተላለፍ እየሰራ ነው።
ለዚህም መንግስት በወሳኝ የኢኮኖሚ አውታሮች በብቸኝነት በመሳተፍ ተቆጣጥሮ የቆየውን ሞኖፖሊ በማስቀረት የግሉ ዘርፍ በራሱም ሆነ ከመንግስት ጋር በቅንጅት ገበያውን እንዲያንቀሳቅስ የኢንቨስትመንት ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቷል።
በተለይም የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በግሉ ዘርፍ ሊሳተፉ የሚችሉባቸውን የኢንቨስትመንት ሥራዎች በመከለስ የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚ ዕድገትና ተወዳዳሪነት፣ በሥራ ፈጠራ እንዲሁም በቴክኖሎጂና ክህሎት ሽግግር ላይ ያለውን ሚና የማሳደግ ዓላማን ይዞ ነው አዲሱ የኢንቨስትመንት የህግ ማዕቀፍ እየተሰናዳ ያለው።
ይህንኑ እውን ለማድረግ ይመስላል ታዲያ ከ1991 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ የሚገኘውን የፕራይቬታይዜሽን አዋጅ ማሻሻል ያስፈለገው። የፕራይቬታይዜሽን ሂደቱን በውጤታማነትና በግልጽነት ለማከናወን ያግዛል በሚል የባለሙያዎች ቡድንም ተቋቁሟል።
አስፈጻሚው አካል ለፓርላማው ካቀረበው የረቂቅ ሕጉ ማብራሪያ ለመገንዘብ እንደሚቻለው በተለይም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ለፕራይቬታይዜሽን ካላቸው ዝግጁነት፣ በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ውስጥ ከሚኖራቸው ተወዳዳሪነት፣ የፕራይቬታይዜሽን አስፈጻሚ አካላት ከሚኖራቸው ኃላፊነትና ተጠያቂነት እንዲሁም የፕራይቬታይዜሽን ሂደቱን ግልጽና ታአማኒነት ያለው ከማድረግ አኳያ የህጉ መሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
በረቂቅ አዋጁ መግቢያ እንደተመለከተውም የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገትና ትራንስፎርማሽን ዘላቂነት እንዲኖረው ለማድረግና ለግል ኢንቨስትመንት አመቺ የፖሊሲ ከባቢዎችን ለመፍጠር ሲባል ነው ሕጉ የሚሻሻለው። የግል ዘርፉ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖረውን ሚናና ተሳትፎ ማስፋፋትና ማዳበርም አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
የትርጓሜና የዓላማ ለውጦች
የአሁኑ ረቂቅ ሕግ በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ውስጥ ለፕራይቬታይዜሽን ከተሰጠው ትርጉምና ዓላማ በተለየ መልኩ የአተረጓጎምና የዓላማ ይዘት በመያዝ ነው ብቅ ያለው።
በነባሩ አዋጅ ለፕራይቬታይዜሽን የተሰጠው ትርጓሜ የልማት ድርጅትን ወይም የተወሰነ ክፍል ወይም ንብረት ወይም አክሲዮኖች ከማስተላፍ በተጨማሪ የመንግሥት መዋጮ ማድረግን እንዲሁም የልማት ደርጅትን ማኔጅመንት ወደ ግል ማስተላለፍን ያካተተ ነው።
ረቂቅ አዋጁ ደግሞ ፕራይቬታይዜሽን የሚለውን “የልማት ድርጅትን ንብረት ወይም አክሲዮኖችን በሙሉ ወይም በከፊል ለግል ዘርፉ በሽያጭ የማስተላፍ ውጤት የሚያስከትል ግብይት ነው” በሚል ተርጉሞታል።
ይህም የልማት ድርጅት ወደ ግል የማስተላለፊያውን መንገድ ንብረትን ወይም አክሲዮኖችን በሙሉ ወይም በከፊል በመሸጥ እንዲወሰን መደረጉን ያሳያል።
ከዚህ ውጭ የልማት ድርጅትን ወይም የልማት ድርጅትን የተወሰነ ክፍል ማስተላፍ፣ የመንግሥት መዋጮ ማድረግ እንዲሁም የልማት ደርጅትን ማኔጅመንት ወደ ግል ማዛወር የሚለውን እንዳያካትት ተደርጓል።
የፕራይቬታይዜሽን ዓላማዎችን በተመለከተ ረቂቅ ሕጉ በሥራ ላይ ካለው ተመሳሳይ ዓላማዎችን ሰንቆ ነው የተቀረጸው። ይሁንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ውጤታማነት ማሻሻል፣ ተወዳዳሪነታቸውን ማጎልበት፣ የቴክኒክ ሙያንና ክህሎትን መጋበዝ እንዲሁም የካፒታል አቅርቦትን ማሻሻል ተቀዳሚ ዓላማው ማድረጉ በሥራ ላይ ካለው ሕግ የተለየ ያደርገዋል።
ቅድመ ፕራይቬታይዜሽን
በሥራ ላይ ባለው ሕግ መሰረት ወደ ግል የሚተላለፉ የልማት ድርጅቶች ዝርዝር የሚወሰነው በተቆጣጣሪው ባለሥልጣን (የመንግሥት የባለቤትነት መብቶችን ለመከታተል፣ ለመጠበቅ፣ ለመተግበር በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተሰየመ ባለሥልጣን) ነው።
ከዚህም ሌላ የደርጅቱ ማኔጅመንት ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ በሚሰጠው መመሪያ መሠረት ውሳኔ የተሰጠበትን የልማት ድርጅት ለፕራይቬታይዜሽን ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉ እርምጃዎችን ሁሉ የመውሰድ ግዴታ እንዳለበት ነው ነባሩ ሕግ በጥቅሉ የሚደነግግ ነው።
በሥራ ላይ ካለው ሕግ በተለየ ሁኔታ ደግሞ በረቂቅ አዋጁ ውስጥ ለቅድመ ፕራይቬታይዜሽን ሥራዎች የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ ወደ ግል የሚዛወረው የልማት ድርጅት የሥራ አመራር ቦርድ እያንዳንዳቸው የሚኖራቸው ኃላፊነቶች በዝርዝር ተመልክቷል።
በዚህም መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የገንዘብ ሚኒስቴርንና የተቆጣጣሪውን ባለሥልጣን የውሳኔ ሃሣብ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ወደ ግል መዞር ያለበትን የልማት ድርጅት ይወስናል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ደግሞ ማናቸውንም የቅድመ ፕራይቬታይዜሽን ሥራዎችን እንደሚያከናውን፣ ከሚመለከተው የመንግሥት የልማት ድርጅት ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር የቅድመ ፕራይቬታይዜሽን ሂደት መቼ መጀመር እንዳለበትና የትኞቹ ሥራዎችም መካተት እንዳለባቸው እንዲወስን ሥልጣን ተሰጥቶታል።
በተጨማሪም ከመንግሥት የልማት ድርጅቱ ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ጋር በመካከር የእያንዳንዱን ሽያጭ አመላካች የሽያጭ ዋጋ (ወይም መነሻና መድረሻ ዋጋ) እና ወደ ግል የሚዛወረውን የአክሲዮን መጠንን (የድርጅቱን መጠንን) ይወስናል።
ወደ ግል የሚዛወረው የልማት ድርጅት የሥራ አመራር ቦርድ በበኩሉ መረጃ የመስጠት፣ ለቅድመ ፕራይቬታይዜሽንና ለፕራይቬታይዜሽን ማዘጋጀት እንዲሁም የልማት ድርጅቱን የንብረት ዋጋ እያሽቀለቆለ አለመሄዱንና ለብክነት አለመዳረጉን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት።
በተጨማሪም በቅድመ ፕራይቬታይዜሽን ወቅትና በፕራይቬታይዜሽን ደረጃ ማናቸውንም አዲስ ኢንቨስትመንት ከማድረግ መቆጠብን እንዳለበት በአዲሱ ሕግ በግልጽ ተደንግገዋል።
ድርጅቶቹ ገበያ ወጥተው ገዢ እንዳያጡ
የአገራችን አርሶና አርብቶ አደር ከብቱን ለመሸጥ ባሰበ አንድ ወሳኝ ዝግጅት ያደርጋል። ከብቱን ወደ ገበያ ከማውጣቱ ቀደም ብሎ አስሮ ሲቀልበው፣ ጥሬ ሲያስቆረጥመውና ጨው ሲያስልሰው ይሰነባብታል። ይህን ጊዜ ከብቱ ወርቹ ይጠነክራል፣ ወገቡ ይሰፋል፣ ቆዳው ይለሰልሳል፣ ብቻ ባጠቃላይ ገበያ ሲቀርብ ጥሩ ዋጋ ያወጣለታል።
የአገራችን የልማት ድርጅቶች ከዓመታት በፊት ሲቋቋሙ በሰፊ መሰረት፣ በከፍተኛ ካፒታልና በጠንካራ አደረጃጀት እንደነበር አይዘነጋም። የኋላ ኋላ ግና አብዛኞቹ በበርካታ ችግሮች ተተብትበው እንደሰው “ከስተው” ነበር።
ፕራይቬታይዝ ሊደረጉ ወደ ገበያ የቀረቡትም ከነችግራቸው ነበር። በዚሁ መነሻ ወደ ግል የተዛወሩት የተሸጡበት ዋጋ የቱን ያልክ መናኛ መሆኑ የያኔው መነጋገሪያ ነበር። ገሚሶቹም ቢሆኑ ደህና ዋጋ የሚቆርጥላቸው ገዥ በመጥፋቱ “ሰነፍ ሙያተኛ እንደሰራችው ማሰሮ” ገበያ ወጥተው ጸሀይ መቷቸው ሲመላለሱ መክረማቸውን አንዘነጋውም።
የዚህ ዋነኛ ምክንያቱ መንግስት በአብዛኛው ፕራይቬታይዝ ለማድረግ ብቻ ማሰቡን በሚያሳብቅ መልኩ ከነችግራቸው ለገቢያ ስለሚያወጣቸው ነበር። ይህ የሆነበት መነሻ ደግሞ በሥራ ላይ ባለው ሕግ ከፕራይቬታይዜሽን በፊት የመንግሥት የልማት ድርጅትን እንደገና ማዋቀርን በተመለከተ የተዘረጋ የህግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ ነበር።
አዲሱ አዋጅ ታዲያ ይህንን ችግር ለመፍታት ያለመ ይመስላል። ሕጉ አንድ የልማት ድርጅት ወደ ግል ከመዛወሩ በፊት እንደገና ሊዋቀር የሚችልበትን የሕግ ማዕቀፍ አስቀምጧል።
አዲሱ ሕግ ይህን ማድረጉ በፕራይቬታይዜሽን ሂደቱ ውስጥ ውጤታማነትንና ግልጽነትን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ይታመናል። በተለይም ይህ እንደገና የማዋቀር ሥራ አንድ የልማት ድርጅት ተፈላጊነቱ እንዲጨምርና ዋጋው እንዲያድግ ያግዛል።
በዚሁ መነሻ በአዲሱ ሕግ መሰረት የልማት ድርጅቱ ወደ ግል ከመዛወሩ በፊት ተገቢው የካፒታል አደረጃጀቶች፣ የንግድ ስትራተጂ፣ የኮርፖሬት አስተዳዳር መዋቅሮች፤ የሪፖርት አቀራረብና የመረጃ አገላለጽ ልምዶች ያለው መሆኑ በመንግስት ይገመገማል። ጉድለት ከተገኘበትም አስፈላጊው የማስተካከያ እርምጃ ይወሰድለታል።
የአንድ ባለአክሲዮን ባለቤትነት
ሥለ አክሲዮን ማህበራት ምስረታ የሚደነግገው የንግድ ሕጉ ቁጥር 307 የአክሲዮን ኩባንያ ለመመስረት በትንሹ አምስት አባላት ሊኖሩ እንደሚገባ ያስቀምጣል።
ከዚህ በተለየ ግን በሥራ ላይ ያለውም ሆነ የአሁኑ ረቂቅ የፕራይቬታይዜሽን ሕግ አንድን የመንግሥት የልማት ድርጅት ለፕራይቬታይዘሽን ዝግጁ ለማድረግ በአንድ ባለአክሲዮን ባለቤትነት ወደሚያዝ የአክሲዮን ማኅበርነት ሊለወጥ እንደሚችል ይደነግጋሉ።
በዚሁ መሰረት የልማት ድርጅቱ ወደ አክሲዮን ማኀበርነት በሚለወጥበት ወቅት አክሲዮኖቹ ወደ ግል ባለቤትነት እስከሚዛወሩ ድረስ የድርጅቱ ካፒታል በአክሲዮኖች ተከፋፍሎ አክሲዮኖቹ በሙሉ በመንግሥት ይያዛሉ ማለት ነው።
እንዲህ ያለው የኩባንያ ዓይነት በአንድ ባለአክሲዮን ባለቤትነት የተያዘ የንግድ ድርጅት (Single Member Company) ይባላል። በአገራችን የንግድ ሕግ ማዕቀፍ ውስጥ እንግዳ ሥርዓት ቢሆንም በተለይም ሥልጡን በሚባሉት በሌሎች አገራት ኩባንያዎች የሚመሰረቱበት ዓይነተኛው መንገድ ነው።
በአንድ ባለአክሲዮን ኩባንያ መመስረት በንግድ ሕጉ ያልተፈቀደ ቢሆንም መንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ከማዛወሩ በፊት በኩባንያ ቅርጽ በድጋሜ በማደራጀት ብቸኛ ባለአክሲዮን ሆኖ እንዲይዛቸው የማድረጉ ጅምር በበጎ ጎኑ የሚታይ ነው።
“ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” እንደሚባለው እንዳይሆንበት ደግሞ እየተሻሻለ በሚገኘው የንግድ ሕጉም ውስጥ የትኛውም ባለሀብት ካፒታል እስካለው ድረስ ብቻውን የአክሲዮን ኩባንያ እንዲመሰርት የሚፈቅድ የንግድ ሕግ ማዕቀፍ በዝርዝር እንዲያካትት ይመከራል።
ከዚህም ሌላ የልማት ድርጅቱ ወደ አክሲዮን ማኀበርነት በሚለወጥበት ወቅት አክሲዮኖቹ ወደ ግል ባለቤትነት እስከሚዛወሩ ድረስ የድርጅቱ ካፒታል በአክሲዮኖች ተከፋፍሎ አክሲዮኖቹ በሙሉ በመንግሥት ከተያዙ በኋላ አክሲዮኖቹ የሚተላለፉት በንግድ ሕጉ በተመለከተው አግባብ ቢያንስ ለአምስት ባለሀብቶች ስለመሆኑ በሕጉ ውስጥ በግልጽ ሊቀመጥ ይገባል።
የተጣራ የመዝገብ ዋጋቸው ሊፈተሽ ይገባዋል
መንግሥት የልማት ድርጅትን ወደ አክሲዮን ማኅበርነት እንዲለውጥ ከሚፈቅደው ሕግ ጋር በተያያዘ በአግባቡ ሊፈተሽ የሚገባ ሌላም ጉዳይ አለ። ይኸውም ድርጅቶቹ ወደ አክሲዮን ኩባንያነት በሚለወጡበት ጊዜ ለአክሲዮን ማኅበሩ የሚተላለፉትን የመንግሥት የልማት ድርጅቱን ሀብትና ዕዳዎች እንዲሁም ንብረቶቹ እንደገና የሚገመቱበትን ሥርዓት ይመለከታል።
ጥቂት የማይባሉት የልማት ድርጅቶች በማቋቋሚያ ደንቦቻቸው ላይ የተመሰረቱበት የተፈቀደ የካፒታል መጠንና በትክክል በእጃቸው ላይ ያለው የተከፈለ ጥሬ ገንዘብና የዓይነት ካፒታል የተጣጣመ ባለመሆኑ ለካፒታል እጥረት ሲጋለጡ ተስተውሏል።
የችግሩ ዓይነተኛ መነሾ ድርጅቶቹ በሚቋቋሙበት ወቅት የካፒታል ስሌት በተለይም በዓይነት የነበራቸው የሀብት ምዝገባ መሰረታዊ ችግሮች የነበሩበት መሆኑ ነው። ድርጅቶቹ በምስረታ ወቅት የነበሯቸው ቋሚ ንብረቶች እንደ ካፒታል ይቆጠሩላቸዋል።
ነገር ግን በወቅቱ ያላቸው ሀብት በተገቢው ሁኔታ ሳይቆጠር የተቋቋሙ ድርጅቶች አሉ። ለአንዳንዶቹ ድርጅቶች ቋሚ ንብረት ተብለው የተመዘገቡት አንዳንድ ንብረቶች ያረጁና አገልግሎት የማይሰጡ፤ የተበላሹና የአሁን የገበያ ዋጋቸው በጣም የወረደ ንብረቶች ናቸው።
ቡክ ኦፍ አካውንታቸው ውስጥ በሀብትነት የተመዘገቡ ነገር ግን የራሳቸው ሀብት ያልሆኑ ንብረቶች እንደድርጅቶቹ ሀብቶች ተቆጥረው በካፒታልነት እንዲመዘገቡ የተደረጉባቸው የልማት ድርጅቶችም አሉ።
እንዳንዶቹም በሚያስገርም ሁኔታ በደርግ ዘመነ መንግስት ኤርትራ ውስጥ የነበሩ ንብረቶች ሳይቀሩ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉ ተቆጥረው በስህተት የቋሚ ሀብት ካፒታላቸው ውስጥ የተመዘገቡባቸውም አሉ። ኢትዮጵያም ውስጥ ቢሆን በሌሎች የመንግስት ተቋማት እጅ ያሉ ንብረቶችን በሀብት መዝገባቸው ውስጥ ያሰፈሩ ኩባንያዎችም እንዲሁ።
ሥለዚህ እነዚህ ከሀብት ምዝገባ እና ከካፒታል ስሌት ጋር የተያያዙትን ነባር ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችል ግልጽ የሕግ ማዕቀፍ በረቂቅ አዋጁ ውስጥ ሊካተት ይገባል። ይህም የልማት ድርጅቶቹን ወደ ግል ከመዛወራቸው በፊት የተጣራ የመዝገብ ዋጋ እንዲኖራቸው ያደርጋል።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታህሳስ 29/2012
በገብረክርስቶስ