እንደመንደርደሪያ
ሉባር ኢንደስትሪ በ45 ሺ ዮሮ ሳፌት ኤስ ፒ ኤ (SAFET S.P.A) ከተባለ የጣሊያን ኩባንያ የማምረቻ እቃዎችና ጥሬ እቃ ግዢ ይፈጽማል። ግን ከ16 ዓመታት በፊት ይህንን ያህል የውጭ ምንዛሬ ወጥቶበት ትልቅ ራዕይና ተስፋን ሰንቆ የተፈጸመው ግዢ የተጠበቀውን ያህል ውጤት አላስገኘም። ግዢውን የፈጸመውን ድርጅትም ለከፍተኛ ኪሳራ ይዳርጋል።
ያመርታሉ የተባሉት የማምረቻ ማሽንና ጥሬ እቃዎቹ አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ የማይሰሩ ሆነው ተገኝተዋል። ሆን ተብሎ በተፈጸመ ወንጀል ኩባንያው የማይሰሩ የማምረቻና ጥሬ እቃዎች በመላኩ፣ ሃሰተኛ ሰነድ ለባንክ አቅርቦ ገንዘብ በመውሰዱና የጉምሩክ ዲክላራሲዮን ተሞልቶ እቃው አገር ውስጥ በመግባቱ ምክንያት ኩባንያውና ስራ አስኪያጁ ላይ ክስ ይመሰረታል።
ጣልያናዊው ወንጀለኛ ተይዞም በምርመራ ላይ እያለ የጣልያን ኤምባሲ ለኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ‹‹በኤምባሲው ዋስትና እንዲፈታና ሲፈለግ እንደሚያቀርበው›› የተጻፈን ደብዳቤ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን መሰረት አድርጎ ለፖሊስ በጻፈው መሰረትም ወንጀለኛው ተፈትቶ ከአገር እንዲሸሽ ተደርጓል። ይህ በመሆኑም አቤቱታ አቅራቢው መብታቸውን መጠየቅ እንዳልቻሉ፣ ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጋቸውንና የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን እርምጃ እንዳልወሰዱም ይመለክታሉ። ዝግጅት ክፍላችን አቤቱታውን ተቀብሎ የሚመለከታቸውን አካላት አናግሮ የዛሬው የፍረዱኝ አምድ ጉዳይ አድርጎታል።
ወንጀለኛው በሌለበት ክሱ ቀጥሎ በኩባንያው ላይ የገንዘብ ቅጣት በስራ አስኪያጁ ላይ ደግሞ 15 ዓመታት ጽኑ እስራት ይጣላል። የተሸጡት እቃዎችም መንግስት እንዲወርሳቸው ይፈረዳል። ጉዳዩ ከተፈጸመ ዓመታት ቢቆጠሩም፤ አመልካቹ በተደጋጋሚ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመልክተው መስመር ሲይዝ በሃላፊዎች ቸልተኝነት ወደ ኋላ እንዲመለስ መደረጉን ያስታውሳሉ። በ2008 ዓ.ም በወቅቱ ለነበሩት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመልክተው ስለዋስትናው ህጋዊነት በኢትዮጵያ የጣልያን አምባሳደር ተጠርተው እንዲጠየቁ፣ ለጣልያን የውጭ ጉዳይ ደብዳቤ እንዲጻፍ፣ ቀጥሎም ለጣልያን መንግስት ደብዳቤ እንዲጻፍና በሁለቱ መንግስታት በኩል ተገቢው ሁሉ እንዲደረግ ከሚኒስትሩ ለአውሮፖ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ትእዛዝ መሰጠቱን ያስታውሳሉ። ግን በወቅቱ የነበሩት ዳይሬክተሩ ምንም ሳይፈጽሙ እንዳስቀሩትም ያመለክታሉ።
በወንጀለኛው ላይ የተላለፈው ፍርድ አለመፈጸሙንና በደል አድራሾቹ በአገር ውስጥ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር እና የባለስልጣኖችን ቸልተኛነት ጠንቅቀው ያውቃሉ ሲሉ አቶ ሰለሞን ይጠቁማሉ። በደሉን ፈጽመው ፍርድ ቤት ጥፋተኝነታቸውን አረጋግጦባቸውም ችግሩን በሰላም ለመፍታት እንኳን ፍላጎት አለማሳየታቸውን ይናገራሉ። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ባለስልጣናት ለዜጎች መብት መከበር ማድረግ ያለባቸውን ባለማከናወናቸውም ከፍተኛ ኪሳራና ጉዳት እያስተናገዱ እንደሚገኙም ነው የሚገልጹት።
አቤቱታ አቅራቢው ወንጀለኛውን ኤምባሲው በገባው ዋስትና መሰረት አቅርቦ እስራቱ እንዲፈጸምበት ማድረግ እንደሚገባ ያመለክታሉ። ይህ ሲሆንም ድርጅታቸው ግለሰቡን ከስሰው መብታቸውን ለማስከበር እንደሚንቀሳቀሱም ይጠቁማሉ። ተቋሙ ይህንን ማድረግ ካልፈለገና የሁለቱን አገራት መልካም ግንኙነት መጠበቅ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘውና ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይሻላል ከተባለም ባንክን በማጭበርበር የተወሰደባቸው ገንዘብ ከነወለዱና ለ17 ዓመታት የደረሰው ጉዳትና ኪሳራ ታስቦ እንዲከፈል አስፈላጊው እንዲደረግላቸው ይጠይቃሉ።
በተያያዘም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በእዚሁ ጉዳይ ሁለት ቋሚ ኮሚቴዎች የጠየቁትን እንዳስፈጸሙላቸው ይጠቁማሉ። የንግድና ኢንደስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ኩባንያው ያደረሰባቸውን በደል በ2010 ዓ.ም በደብዳቤ በዝርዝር ጠቅሶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ቢያሳውቅም ቋሚ ኮሚቴው ደብዳቤውን ተመልክቶ ያደረገው ምንም ምላሽ እንዳልሰጠ ይናገራሉ። ምላሽ አለማግኘታቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና የተቆጣጣሪው ቸልተኝነትን የሚያሳይ ነው ባይ ናቸው አቤቱ አቅራቢው።
የሉባር ኢንዱስትሪ ስራ አስኪያጅ የአቶ ሰለሞን አበበ አቤቱታ
የኢንቨስትመንት ፍቃድ በማውጣት በተፈቀደላቸው የውጭ ምንዛሬ ከጣሊያን አገር የማምረቻ ማሽኖችና ጥሬ ዕቃ ግዢ ስምምነት ፈጽመው እንደነበር ያስታውሳሉ። በስምምነቱ መሰረትም የትራንስፖርት፣ የኢንሹራንስና የቀረጥ ክፍያን ሳይጨምር በባንክ በኩል 45 ሺ ዮሮ ክፍያ በመፈጸም የማምረቻ ማሽኖችና ጥሬ ዕቃ ማስገባታቸውን ነው የሚገልጹት።
ይሁን እንጂ ይላሉ ቅሬታ አቅራቢው የተላከላቸው ዕቃ ምንም የማያገለግል፣ ለታቀደለት አላማም ሊውል የማይችል ሆኖ ተገኝቷል። ኩባንያውና ስራ አስኪያጁ በባንክና በጉሙሩክ ሕግ ላይ ወንጀል መፈጸማቸውን የተገነዘቡት አቶ ሰለሞን ጉዳዮን ለፖሊስ ያሳውቃሉ። ፖሊስም ከቅሬታ አቅራቢው ጋር በመሆን ክትትል ማድረጉን ይቀጥላል።
የኩባንያው ስራ አስኪያጅ ሚስተር ሰርጂዬ ዴሚ አዲስ አበባ ከተማ ሲገባ ይያዛል። ተይዞ ምርመራ ላይ ሳለም አዲስ አበባ የሚገኘው የጣልያን ኤምባሲ የአዲስ አበባ ፖሊስን ተጠርጣሪው ዋስ በመሆን እንዲፈቱለት ይጠይቃል። ፖሊስ ፍቃደኛ አለመሆኑንና እንዲህ አይነት ጥያቄ ህጋዊ መስመሩን ጠብቆ መፈጸም እንደሚገባው በማስረዳት ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይልኳቸዋል።
በእዚሁ መሰረትም መጋቢት 27 ቀን 2004 ዓ.ም (4 April 2012) የጣልያን ኤምባሲ ለኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግለሰቡ የማያገለግል ማሽን ሸጠዋል በሚል ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ መታሰራቸውን ገልጾ ይጽፋል። በጻፈው ደብዳቤም ግለሰቡ ያለባቸው የጤና ችግር ከግምት በማስገባት በኤምባሲው ዋስትና ሆቴላቸው ሆነው መከታተል እንዲችሉ ድጋፍ እንዲደረግለት ይጠይቃል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም የኤምባሲውን ጥያቄ መሰረት አድርጎ መጋቢት 27 ቀን 2004 ዓ.ም ጣልያናዊ ዜግነት ያለው ሚስተር ሰርጂዩ ዴሚን አስመልክቶ በተጠየቀው መሰረት ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ደብዳቤ ጽፏል። በደብዳቤው መሰረትም ተጠርጣሪው ከእስር እንዲለቀቅ ተደርጓል። ግለሰቡ በተፈታ እለትም ከአገር ለቅቆ በመውጣት ለማምለጥ ችሏል። ጥፋተኛው ሊያመልጥ የቻለው በተቀነባበረ መንገድ መሆኑን የሚናገሩት አቤቱታ አቅራቢው ቁጭት እና እልህ እየተናነቃቸው ወንጀለኛው ቢያመልጥም የወንጀሉ ክስ መቀጠሉን ይናገራሉ።
ሚስተር ሰርጂዮ ዴሚ እና (SAFET S.P.A) ሳፊት ኤስፒኤ ኩባንያ የተመሰረተባቸው ክስ በአጭሩ
ያለንግድ ፍቃድ በመነገድ ወንጀል የኩባንያውን ስራ አስኪያጅ ሚስተር ሰርጅዎ ዴሜንና ድርጅቱን ሳፌት ኤስ ፒ ኤን፣ ለንግድ ሚኒስቴር ሃሰተኛ ሰነድ በማቅረብ የንግድ እንደራሴ ፍቃድ ማውጣትና ማሳደስ እንዲሁም ለባንክ ሃሰተኛ ሰነድ አቅርቦ በውጭ ምንዛሬ ገንዘብ መውሰድ ናቸው።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዐቃቤ ህግን ማስረጃ ሰምቶ ጉዳዮን ካጣራ በኋላ ሚስተር ሰርጂዮ ዴሚን እና የሸጠውን ኩባንያ (SAFET S.P.A) ሳፊት ኤስፒኤ ወንጀለኛ ሆነው አግኝቷቸዋል። ጥፋተኛ የተባለው ኩባንያ በአንድ ክስ በአንድ አንቀጽ ሥር በመሆኑና የተፈጥሮ ሰው ያለመሆኑን ግምት ውስጥ ያስገባው ፍርድ ቤት የገንዘብ ቅጣት ሲወስን፤ ጣልያናዊውን ወንጀለኛ ሚስተር ሰርጄዮ ዴሚን ደግሞ በሶስት አንቀጾች ስር ጥፋተኛ ሆኖ መገኘቱን በማገናዘብ በ15 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ሲል ወስኗል።
ሚስተር ሰርጄዮ ዴሚ ቅጣቱ የተላለፈበት በሌለበት በመሆኑ ፖሊስ ፈልጎ ለማረሚያ ቤት እንዲያስረክብ ያዘዘው ፍርድ ቤት የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ደግሞ በኩባንያው ላይ የተጣለውን የገንዘብ ቅጣት እንዲያስፈጽም ትዕዛዝ አስተላልፏል። እንዲሁም የወንጀል ፍሬ ተብሎ በሁለተኛ ክስ የተጠቀሰው የጣልያን ስሪት የሆነ ማምረቻና ጥሬ እቃ በሻጩ ኩባንያ ወንጀል የተፈጸመበት በመሆኑ ለመንግስት ገቢ እንዲሆንና በመንግስት እንዲወረስ አዝዟል።
የዋስትና መብት የሚገደብባቸው የሕግና የሁኔታ ምክንያቶች
አዲስ ዘመን ጋዜጣ በታህሳስ 08 ቀን 2012 ዓ.ም የ‹‹ዘመን ችሎት›› አምዱ የዋስትና መብት ስለሚገደብባቸው የሕግና የሁኔታ ምክንያቶች ጉዳይ አንስቶ ዘርዝሮ አስነብቧል። የተያዙ እና የተከሰሱ ሰዎች በዋስትና የመፈታት ህገ መንግስታዊ መብት እንዳላቸው በመጥቀስ፤ ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች የቀረበባቸው ክስና ምክንያቶቹ በዝርዝር ወዲያውኑ በሚገባቸው ቋንቋ ሊነገራቸው እንደሚገባና በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ ያለባቸው መሆኑን ጠቁሟል።
በአምዱ እንደተጠቀሰው፤ የተያዙና የተከሰሱ ሰዎች ፍርድ ቤት ከመቅረባቸው አስቀድሞም ሆነ ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ በዋስትና የመፈታት መብት አላቸው። የዋስትና መብት በመርህ ደረጃ ዕውቅና የተሰጠውና ጥበቃም የተደረገለት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ፍፁማዊ መብት ባለመሆኑ በሕግ በሚቀመጡ ልዩ ሁኔታዎች መገደቡ አይቀርም። በመሆኑም የዋስትና መብት እንዲሁ ገደብ የሚጣልበት ወይም ሊከለከል የሚችልም መብት ነው። እነዚህም በሕጉ የተቀመጡ ዋስትናን የሚያስከለክሉ የመርህና የሁኔታ ምክንያቶች ናቸው።
አሁን ‹‹በፍረዱኝ አምድ›› በተነሳው ጉዳይ በህግ ሁኔታዎች ምክንያት ግለሰቡን የዋስትና መብትን አያስከለክልም። ግን የሁኔታ ምክንያቶች ሆነው በተዘረዘሩት ውስጥ ጉዳዩን ማየት የሚገባ ይሆናል።
የታሠሩና የተያዙ ሰዎች በዋስ የመፈታት መብት ቢኖራቸውም በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች ፍርድ ቤት ዋስትናን ሊከለክላቸው ይችላል። በሕግ የተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች የሚባሉት ሕጉ ራሱ በመርህ ደረጃ የዋስትና መብት የሚነፍግባቸው ብሎ የዘረዘራቸው ምክንያቶች ናቸው። በተጨማሪም ወንጀሉ በመርህ ደረጃ ዋስትና ባያስከለክልም ሕጉ እነዚህ፤ እነዚህ ሁኔታዎች ከተሟሉ ዋስትናን ለመከልከል ምክንያት ይሆናል በሚል የሚያስቀምጣቸው የሁኔታ ምክንያቶች አሉ።
የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ዋስትናን ለመንፈግ ሦስት የሁኔታ ምክንያቶችን ያስቀምጣል። የመጀመሪያው ተጠርጣሪው በዋስትና ከተፈታ በኋላ በቀጣይ ቀጠሮዎች ላይ የዋስትና ግዴታውን አክብሮ በችሎት በመቅረብ ጉዳዩን የማይከታተል ከሆነ ነው። ሁለተኛው ምክንያት ተጠርጣሪው ቢለቀቅ ሌላ ወንጀል ይፈፅም ይሆናል ተብሎ ሲገመት ሲሆን፤ በዋስትና ከተፈታ በኋላ ማስረጃዎችን ያጠፋል በተለይም ምስክሮችን በማባበል፣ በመግዛት፣ በማስፈራራት ወይም በሌላ ምክንያት ያሸሻል ተብሎ ሲገመትም ዋስትና የሚከለከልበት ሦስተኛው የሁኔታ ምክንያት ሆኖ ተቀምጧል።
ፖሊስ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኩል ተጠርጣሪው እንዲቀርብ በደብዳቤ የጠየቀበት
ደብዳቤው የጣልያን ዜጋ የሆኑት ሚስተር ሰርጂዮ ዴሚ ያለፈቃድ በመነገድ እና ሀሰተኛ ሰነዶችን ለባንክ አቅርበው ገንዘብ እንዲከፈላቸው አድርገዋል በሚል ለመምሪያው ክስ ቀርቦ እንደነበር ያስታውሳል። ግለሰቡን በቁጥጥር ስር በማዋል በምርመራ ላይ እንደነበሩም ይጠቅሳል። በኢትዮጵያ የሚገኘው የጣሊያን ኤምባሲ ግለሰቡ በኤምባሲው ዋስትና እንዲለቀቁልን በማለት እ.ኤ.አ 04/2012 ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጻፈውን ደብዳቤ በማስታወስ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኤምባሲውን ጥያቄ መነሻ በማድረግ መጋቢት 27 ቀን 2004 ዓ.ም ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ደብዳቤ በመጻፍ ተጠርጣሪው እንዲለቀቁ ተደርጓል በማለት ያስታውሳል።
በአሁኑ ሰዓት (ደብዳቤው የተጻፈበት ዕለት የካቲት 03 ቀን 2006 ዓ.ም) ደግሞ በግለሰቡ ላይ ክስ እንዲቀርብባቸው የተወሰነ በመሆኑ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል እንዲቀርብ ይጠየቅልን ሲል የጨርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ በደብዳቤ መጠየቁን ይጠቅሳል። ስለዚህም ከላይ በስም የተጠቀሱትን ግለሰብ ኤምባሲው ተጠይቆ ጨርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ እንዲቀርቡ እንዲደረግ የዘወትር የስራ ትብብራችሁን እንጠይቃለን ይላል።
ቅሬታ አቅራቢው
የጣልያን ኤምባሲውን መጠየቅ የሚችለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ብቻ መሆኑን የሚያመለክቱት አቶ ሰለሞን፤ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን በፖሊስ ብናስጠይቀውም ተገቢውን ምላሽ ሊሰጠን አልቻለም ይላሉ።
በአካል ጭምር ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመቅረብ የሚመለከታቸውን
ሃላፊዎች፣ የካቢኔ ሹምና የኢኮኖሚና ዳያስፖራ ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታን በተደጋጋሚ
ቢጠይቁም ያደረጉላቸው ነገር አለመኖሩን ይገልጻሉ። ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ አቤቱታ አቅራቢው ጉዳዩን በአካል ቀርበው አስረድተው እንደነበር ያስታውሱና፤ ጉዳዩንም ለአለም አቀፍ ህግ ዳይሬክቶሬት መርተውት አስተያየት እንዲሰጥበት ተደርጎ እንደነበርም ይጠቁማሉ።
የተሰጠውን አስተያየት እና ትእዛዝን አስመልክተው ሲናገሩም ‹‹ጉዳዩ ህጋዊ ዋስትና ስለነበረ ሁለቱን አገሮች በዋስትናው ሊያይዝ የሚችል ስለሆነ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የጣሊያንን አምባሳደር አስቀርቦ ስለጉዳዮ በመነጋገር ሰውየውን እንዲያስመጣ፣ ግን የጣሊያን አምባሳደር በተጠየቀው መሰረት ሰውየውን የማያስመጣ ከሆነ ለጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደብዳቤ እንዲጻፍ ቀጥሎም ለጣሊያን መንግስት ደብዳቤ እንዲጻፍ በማድረግ ጉዳዩ ደረጃ በደረጃ የፖለቲካ እና የመንግስት ጉዳይ እንዲሆን ማድረግ›› የሚል ነበር። የተባለውንም የአውሮፖ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት እንዲያስፈጽም በወቅቱ ተመርቶ እንደነበር ይገልጻሉ። ግን በወቅቱ ሊፈጸምላቸው እንዳልቻለም ይጠቁማሉ።
በመሆኑም ቀጥለው ለጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አመልክተዋል። ዐቃቤ ህግም የተሰጠውን ፍርድ በጣልያንኛ በማስተርጎም እንዲፈጸም በጣልያን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል እንዲደርስ ደብዳቤ እና ፍርዱን የላከ መሆኑን ያመለክታሉ። ሆኖም ይህም ሊፈጸም ያልቻለው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቸልተኝነት ነው ሲሉ አቤቱታ አቅራቢው ይወቅሳሉ። ‹‹ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለዜጎቹ ስለማይከራከር የደረሰብን በደል ነው›› ባይ ናቸው። ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለእኛ ከመከራከር ይልቅ ለእነርሱ ተባባሪ ነው ይላሉ። ለእዚህ መገለጫ ብለው የሚያቀርቡትም መጋቢት 27 ቀን 2004 ዓ.ም ከጣሊያን ኤምባሲ ደብዳቤ ተጽፎለት በእዛው ቀን በሰዓታት ልዩነት ለአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን ደብዳቤ ጽፎ ወንጀለኛው እንዲለቀቅ ማድረጉን ያነሳሉ።
ተበዳዮቹ ግን ለዓመታት ቅሬታቸውን እያቀረቡ ደብዳቤ በመጻፍ ምላሽ የሰጣቸው አንድም አካል አለመኖሩን ነው የሚናገሩት። ሆኖም በግልባጩ የጣሊያን ዜጎች ተበድለው ቢሆን፣ እኛ ጥፋተኞች ብንሆን እና የእኛን ያክል ማስረጃ ቢይዙ ኖሮ የጣልያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣናት ለማንኛውም ጥቅማ ጥቅም ሳይንበረከኩ ለዜጎቻቸው ጥቅም እና ለአገራቸው ክብር ይከራከሩ ነበር ሲሉም ይጠቁማሉ። በስምምነቱ መሰረትም ሆነ ኤምባሲው በሰጠው ዋስትና መሰረት ወይም በሌላ በማናቸውም መንገድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር አቅርበውት ለጉዳዩ እልባት ይሰጡት ነበር ሲሉ በቁጭት ይናገራሉ።
የኢፌዲሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሌላው ቀርቶ እስካሁን ለጣልያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንኳን ደብዳቤ እንዳልጻፈ፣ የጣሊያን አምባሳደርን በአካል ጠርቶ ባግባቡ እንዳላናገረ ነው የሚያብራሩት። ይህ ሁሉ በደል ሊደርስባቸው የቻለው በኢትዮጵያ የጣሊያን ኤምባሲ በአገር ውስጥ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግርና የኤምባሲውን ቸልተኝነት፣ ባለስልጣናቱ ለዜጎቻቸው እንደማይከራከሩ ስለሚያውቁ ነው ይህንን ሁሉ የሚያደርጉት ባይ ናቸው አቶ ሰለሞን።
ተከራካሪ በማጣታችን ወይም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቸልተኝነት የተዘረፍነውን ገንዘብ ማስመለስ አልቻልንም ይላሉ። ወንጀለኛው ሚስተር ሰርጂዮ ዴሚ ገንዘባችንን ዘርፎ እየነገደበት ሲሆን በአንጻሩ ደግሞ እኛ በተቃራኒው ወንጀለኛው የላከልንን ዕቃ ታቅፈን ብናከራየው ከፍተኛ ገንዘብ ሊያወጣለን በሚችል መጋዘን ውስጥ አስቀምጠን ለጠባቂ እየከፈልን ላላስፈላጊ ወጪ ተዳርገው እስካሁን እየጠበቁ እንደሚገኙ በምሬት ይናገራሉ።
የጣሊያን ኤምባሲን ከሰን ጉዳያችንን እንዳንጠይቅ በአለም አቀፍ ህግ መሰረት ኤምባሲን መክሰስ አይቻልም የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ በመሆኑም ከፍተኛ ጉዳት ላይ መውደቃቸውን እና ችግር እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ነው የሚያመለክቱት።
መብታቸውን ለማስከበር በምክር ቤት የተደረጉ ጥረቶችና የአቤቱታ አቅራቢው ቅሬታ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ለሚከታተለው እና ለሚቆጣጠረው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የደረሰባቸውን በደል ዘርዝረው በ2010 ዓ.ም ደብዳቤ ጽፈው ቢያቀርቡም ምንም እንዳልሰራላቸው ይናገራሉ። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና ተቆጣጣሪው መስሪያ ቤት ቸልተኞች እንደሆኑ የሚያረጋግጥ ነው ባይ ናቸው።
ይህንን ለማለት ያነሳሳቸውን ምክንያት ሲናገሩም ከእዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር ጋር በነበራቸው ችግር ጥፋተኛው አገር ውስጥ እንዳይሰራ እርምጃ እንዲወሰድ ላቀረቡት ጥያቄ ምላሽ ማግኘታቸውን ያስታውሳሉ። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም በተመሳሳይ መልኩ በኢትዮጵያ ውስጥ አለም አቀፍ ጨረታ ሲጫረት እገዳ እንዲጣልበት አመልክተው እንደነበረ ያስታውሱና፤ እርምጃ ባለመውሰዱ ለሚከታተላቸውና ለሚቆጣጠራቸው አካል ማለትም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለንግድና ኢንደስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክን ለሚቆጣጠረው ለገቢ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በ2011 ዓ.ም ክስ አቅርበው ሁለቱም ቋሚ ኮሚቴዎች በጉዳዩ ላይ ክትትል አድርገው በድርጅቱ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረጋቸውን ይናገራሉ።
በምክር ቤቱ ድጋፍና ክትትል የተገኘ ውጤት
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወሰደው እርምጃ
የገቢ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሐምሌ 10 ቀን 2011 ዓ.ም ለሁሉም ባንኮች በጻፈው ደብዳቤ እንዳሳወቀው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 163862 ሳፌት ኤስ.ፒ.ኤ በአገር ውስጥ የሚሰራ አስመጪና ላኪ ሳይሆን ከሀገር ውጭ የሚገኝ ድርጅት እንደሆነ ጠቅሷል። ባንኮችንም በማጭበርበር ሃገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ተገቢ ባልሆነ መንገድ እንድታጣ ማድረጉ ተረጋግጦ የቅጣት ውሳኔ እንደተላለፈበት ተብራርቷል።
በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ሳፌት ኤስ.ፒ.ኤ ወንጀለኛነቱን አረጋግጦ የቅጣት ውሳኔ ያስተላለፈበት በመሆኑ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ከብክነት ለመከላከል ሲባል ከዚህ የውጭ ድርጅት ጋር ማንኛውም ባንክ ከገቢና ወጪ ንግድ ወይም ሌሎች ተዛማች ክፍያዎች ጋር በተያያዘ የሚኖር የስራ ግንኙነት እንዲቆምና ወደፊትም ቢሆን ድርጅቱን በጥቁር መዝገብ ውስጥ በመመዝገብ አገልግሎት እንዳትሰጡ እናሳስባለን የሚል መመሪያ አስተላልፏል።
የንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር የወሰደው እርምጃ
ሳፌት ኤ ስ ፒ.ኤ ኩባንያ በህገ ወጥ የንግድ ስራ ላይ ተሰማርቶ የተገኘና በህግ የተፈረደበት ኩባንያ መሆኑ፤ አሁንም ከላይ ቀድሞ በተመዘገበበት የንግድ አድራሻ በህገ ወጥ መንገድ የንግድ ስራ እንቅስቃሴ እያካሄደ ያለ መሆኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለንግድና ኢንደስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረባችሁት ቅሬታ መሰረት፤ ኩባንያው በንግድ እንቅስቃሴ ላይ ስለመሆኑ በተጠቀሰው የንግድ አድራሻ እና ከንግድ አገልግሎት ፋይል ለማረጋገጥ መቻሉን ይጠቅሳል።
በአድራሻው የውል ስምምነት በመያዝ ትሰራ የነበረችው ወይዘሮ አስመረት ተፈራ በቀረበው ጥቆማ መሰረት የንግድ ፈቃድዋ ታግዶ የውል ስምምነቱ ተሰርዟል። ግለሰቧ ከሌላ የቱኒዚያ ድርጅት ጋር ውል መፈጸሟንም አረጋግጧል። አቤቱታ የቀረበበት ኩባንያም በተጠቀሰው የንግድ አድራሻ ላይ ከንግድ ውል የተሰረዘ መሆኑን በተጠሪ መስሪያ ቤት በኩል የተረጋገጠ መሆኑን በመጥቀስ ለቅሬታ አቅራቢው ለሉባር ኢንደስትሪ ምላሽ ሰጥቷል።
ይህም የሚመለከታቸው አንዳንድ ቋሚ ኮሚቴዎች የህዝብን ጥያቄ መሰረት አድርገው ምላሽ እንዲሰጥ ማድረጋቸውን የሚያሳይ መሆኑን የሚጠቁሙት ቅሬታ አቅራቢው ሆኖም ግን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ጉዳያችንን ሊከታተልልን አልቻለም ሲሉ ይወቅሳሉ። የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ለጥያቄያችን ምላሽ ሳይሰጥ ለአመታት አቆይቶናል ይላሉ። በርግጥ ቋሚ ኮሚቴው መጋቢት 03 ቀን 2010 ዓ.ም ለውጭ ጉዳይ ደብዳቤ ጽፎ እንደነበረ ያስታውሳሉ።
ጉዳያችንን በአካል ቀርበን እንዳናስረዳም ወደ ምክር ቤቱ ቅጥር ጊቢው መግባት እንደማይቻልም ይጠቁማሉ። ለቅሬታ ማቅረቢያ ያቀረቡት ስልክ ቁጥርም ለይምሰል የቀረበ እንጂ ሲደወል የማይሰራ፣ በሰራ ወቅትም ምላሽ እንዳልተሰጠም ነው የሚጠቁሙት።
ተስፋችን ተሟጥጧል፣ ምንም ተስፋ የለንም የሚሉት አቤቱታ አቅራቢው አሁን መናገር የፈለግነው ህዝብ እንዲያውቀውና እንዲፈርድ ነው እንጂ በአሁን ሰዓት በውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ላይ በተሰባሰቡ አባላት ጉዳያችን ይፈታል የሚል እምነት እንደሌላቸውም ይናገራሉ። ሁለቱ ቋሚ ኮሚቴ ፈጥነው ምላሽ ሲሰጡ ይህ ቋሚ ኮሚቴ ግን እስካሁን ምላሽ ሊሰጧቸው አለመቻሉ እንዳሳዘናቸውም ይመሰክራሉ።
ተበዳዩ የሚጠይቁት ፍትህ
በኢትዮጵያ የጣሊያን ኤምባሲ በተለያየ ጊዜ ችግሩን እንዲፈታ ጥያቄ ቀርቦለት እንደነበረ አቶ ሰለሞን ያስታውሳሉ። የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት አባል መሆናቸውን በአንጻሩ ደግሞ ጥፋተኛው ሚስተር ሰርጂዮ ዴሚም የጣሊያን ቶሪኖ የንግድ ምክር ቤት አባል መሆኑን ይጠቁማሉ። በሁለቱ አገራት ንግድ ምክር ቤት አባላቶች ላይ ችግር ቢፈጠር ለመፍታት ስምምነት ማድረጋቸውንና ችግር ቢፈጠር ምክር ቤቶቹ ጉዳዩን እልባት እንዲሰጡም ስምምነት መደረጉን ይጠቅሳሉ። በርካታ ጊዜያት በኢትዮጵያ ለጣልያን ኤምባሲና ለቶሪኖ ንግድ ምክር ቤት ጉዳዩ በሰላማዊ ሁኔታ እንዲፈታ ደብዳቤ መጻፉን ያስታውሳሉ። ግን ኤምባሲው ይህንን ማድረግ አልፈለገም ባይ ናቸው።
ፖሊስ ጉዳዩን እንዲከታተል ታዝዟል ሲሉ አቤቱታ አቅራቢው ያስታውሳሉ፤ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ለኢንተርፖል አለም አቀፍ ፖሊስ ትብብር ዳይሬክተር በ191 አገራት ደብዳቤ ተበትኖ ጥፋተኛው ተይዞ እንዲመጣ እየታደነ መሆኑንም ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢኮኖሚና ዳያስፖራ ዘርፍ በኢትዮጵያ የጣልያን ኤምባሲን አስገድዶ በተገባው ዋስትና መሰረት ሰውየው ተይዞ እንዲቀርብ እና እስራቱ እንዲፈጸምበት ማድረግ እንደሚገባ ያሳስባሉ። ሰውየው ሲቀርብ እኛ ክስ በማቅረብ ከባንክ የተወሰደብንን ብር፣ እስካሁን የደረሰብንን ኪሳራ፣ የምንጠብቀውን ነገር ሁሉ በፍርድ ቤት መብታችንን እንድናስከብር መደረግ አለበት። ይህ አይሆንም ሂደቱ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ያሻክራል ከተባለ ደግሞ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታልን ማድረግ አለባቸው ሲሉ ያመለክታሉ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
ሰብሳቢው አቶ ተስፋዬ ዳባ፤ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ምክር ቤት ሪፖርት ሲያቀርቡ በጥያቄ መልክ አንስተው ማብራሪያ እንደሰጡበት ያስታውሳሉ። በወቅቱ የአቶ ሰለሞን መብት መከበር እንዳለበት፣በተለያዩ አካላትም አስፈላጊው ትብብር እና ድጋፍ እንዲደረግላቸው ሀሳብ ማቅረባቸውን ይገልጹና፤ ሁለቱን አካላት በማነጋገር ኪሳራው እንዲከፈል ተሞክሮ የከሸፈው በሂሳብ ግምት አለመግባባት ምክንያት መሆኑን ነው የሚናገሩት።
ለቋሚ ኮሚቴው ቅሬታ የሚቀርብበት ምክንያት የለም የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ እንደ ህግ አውጭ ክትትልና ቁጥጥር ተግባር ተከታትለን አስፈጻሚው አካል ጉዳያቸውን እስከመጨረሻው ተከታትሎ እንዲያስፈጽም ማድረጉንም ይጠቅሳሉ።
አሁንም ቢሆን ምንም ችግር የለም። ያልተፈጸመላቸው ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው ለቋሚ ኮሚቴው ማመልከቻቸውን ማስገባት ይችላሉ። ቅሬታው ያልተፈታ መሆኑን ጠቅሰን ጉዳዩ እንዲፈጸም ማድረግ እንችላለን ብለዋል አቶ ተስፋዬ። ጉዳዩን ችላ አላልነውም ጥያቄውን አቅርበን ምላሽም ተሰጥቶበታል ችግሩ ካልተፈታም ግለሰቡ ማሳወቅ አለበት ይላሉ ሰብሳቢው። በተመሳሳይ የዴሞክራቲክ ኮንጎ ኤምባሲ ሰራተኞች ተመሳሳይ ቅሬታ ቀርቦ እንደነበር ያስታውሱና፤ ለሚኒስቴሩ ደብዳቤ መጻፉን ነው የሚናገሩት። በተመሳሳይ መንገድም ጉዳዩ አለማለቁን ማሳወቅ ይገባው ነበር ይላሉ።
አቤቱታ አቅራቢው
ታህሳስ 03 ቀን 2012 ዓ.ም አቶ ሰለሞን አበበ እንደገና ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመልክተው እንደነበር ነግረውናል። የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ጉዳዩን አስመልክተን ታህሳስ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ለኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስልክ ደውሎ ነበር። ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በእለቱ ቅሬታ አቅራቢውን አስጠርቶ ሚኒስቴሩ ከሚመለከታቸው ዳይሬክቶሬት ጋር ሆነው እንዳነጋገሯቸው መረጃ አግኝተናል። ይህንንም ቅሬታ አቅራቢውም አረጋግጠውልናል። ስልክ ተደውሎ ቀርበው እንዲያስረዱ መደረጉን፣ ባግባቡ ማስረዳታቸውን ገልጸውልናል።
‹‹ኤምባሲን መክሰስ ስለማይቻል ነው እናንተ ጋር ለመምጣት የቻልኩት እንጂ መብቴን በህግ አስከብር ነበር። የማንኛውም አገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የዜጎቹን መብት እንደሚያስከብር ሁሉ እናንተም ማስከበር አለባችሁ፣ ልታስከብሩም ይገባል። ብዙ ጊዜ ተመላለስኩ ምንም ልታደርጉልኝ አልቻላችሁም›› ብዬ ነግሬያቸዋለሁ ጉዳዩን በደንብ መረዳታቸውንም ነግረውናል። ከሚኒስትሩ ለሚመለከተው ዳይሬክቶሬት አስቸኳይ ትዕዛዝ መተላለፉንም ገልጸውልናል። ለአመታት የተንገላቱበት ጉዳይ እልባት ያገኛል የሚል ተስፋ መሰነቃቸውንም ነግረውናል።
የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
የሚኒስትሩ ቃል ዐቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው፤ ቅሬታ አቅራቢው (አቶ ሰለሞን) አቤቱታቸውን እንደገና ለሚኒስቴሩ ከፍተኛ ባለስልጣን (አቶ ገዱ አንዳርጋቸው) አቅርበዋል። ጉዳዩን በዝርዝርና በልዩ ሁኔታ እንዲመለከቱትና በአጭር ጊዜ ምላሽ እንዲያቀርቡም ጉዳዩ ለሚመለከተው ዳይሬክቶሬት መመሪያ ተላልፏል ብለዋል።
በአቤቱታ ደረጃ ዜጎች በተለይ ከዲፕሎማትና ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ጋር በተያያዙ ቅሬታዎች እንደሚቀርቡ ያነሳሉ። የዲፕሎማቲክ ከለላና መብት ያላቸው አካላት ሲከሰሱ ቀጥታ ፍርድ ቤት ስለማይወሰዱ እነሱን የሚመለከት የማስማሚያ ክፍል አለ። አሁን የቀረበው ቅሬታ የንግድ ጉዳይ ሆኖ ኤምባሲው ጣልቃ በመግባቱ ወደ ተቋማቸው ሊቀርብ መቻሉን ይጠቁማሉ። እንጂ ዜጎች የሚያደርጉት የንግድ ውዝግቦች ወደ ተቋሙ አይመጣም። ከአለም አቀፍ ጉዳይ ጋር የተያያዘ ቢሆንም በማህበራቸውም አማካኝነት መብታቸውን ያስከብራሉ። ይህ ያልተቋጨ ጉዳይ ነው።
‹‹አሁን አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷል። ከእዚህ በኋላ የሚደረገው ሂደት ይዞ የሚመጣውን ውጤት እናሳውቃለን ›› ብለዋል አቶ ነቢያት።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታህሳስ 29/2012
ዘላለም ግዛው