የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመቆጣጠር የወጣ ረቂቅ አዋጅ እነሆ ፓርላማ ደርሷል። ረቡዕ ታህሳስ 22 ቀን 2012 ዓ.ም በፓርላማው በሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ የተዘጋጀው የሕዝብ አስተያየት መሰብሰቢያ መድረክም ተካሂዷል። አንዳንድ ወገኖችም አዋጁ ሕገመንግሥታዊ ድጋፍ ያለውን ሃሳብን በነጻ የመግለጽ ነጻነትን እንዳይጋፋ ያላቸውን ሥጋት በመድረኩ አንጸባርቀዋል። በግሌ ረቂቅ አዋጁን ሳጤን አንዳንድ ወሳኝ ጥያቄዎችን አጭሮብኛል። ከዚያ በፊት ግን ስለአዋጁ በሕግ አውጪው አካል የቀረበው ትንታኔ ላስቀድም።
አዋጁ ለምን አስፈለገ?
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት ዕውቅና ከተሰጣቸው መብቶች አንዱ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ነው። ይህ መብት በሕገ-መንግስቱ ብቻ ሣይሆን ሕገ-መንግስቱን ለመተርጐም እንደ አጋዥ ተደርገው በሚቆጠሩና የሃገራችን የሕግ ስርዓት አካል በሆኑት አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶችም የተካተተ ነው። ሕገ-መንግስቱንና እነዚህን አለም አቀፍ ስምምነቶች ስንመለከት፣ እንዲሁም ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን በማክበር ረገድ ጥሩ ሥም ያላቸውን ሃገራት ልምድም ስንመለከት ይህ መብት ፍፁም የሆነ መብት ሣይሆን፣ ገደብ ሊጣልበት የሚችል መብት መሆኑን እንረዳለን። በመብቱ ላይ የሚጣለውን ገደብ ዓላማ፣ የገደቡን አስፈላጊነትና ተመጣጣኝነትን በጥንቃቄ መርምሮና አመዛዝኖ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ላይ በሕግ ገደብ ማስቀመጥ በዲሞክራሲያዊ ሃገራት ተቀባይነት ያለውና የተለመደ አሰራር ነው። በሃገራችን ኢትዮጵያ ያለው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን የማጠናከር እንቅስቃሴም ከዚህ ልምድና አሰራር ውጪ ሊሆን አይችልም። በተለይም አሁን ካለው ፖለቲካዊ ነፃነት ጋር እየተበራከተ የመጣው የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ ንግግር ሥርጭት መፍትሔ ካልተበጀለት ለሃገራዊ ሠላምና ደህንነት እንዲሁም ለለውጥ እንቅስቃሴው ዘላቂነት ትልቅ አደጋ መሆኑ ግልፅ ነው።
የጥላቻ ንግግር ተስፋፍቶ በጠረገው መንገድ እ.ኤ.አ በ1994 በሩዋንዳ፣ እንዲሁም በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በጀርመንና በመላው አውሮፖ የደረሰው የከፋ እልቂት ተጠቃሽና ትምህርት ሊወሰድባቸው የሚገቡ ክስተቶች ናቸው። ይህን መሰል ጥፋት እንዳይደርስ የጥላቻ ንግግርን መከልከልና በወንጀልነት መደንገግ አስፈላጊ ነው። የአለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ወይም ICCPR አንቀጽ 19 (3) ሃሣብን በነፃነት የመግለፅ መብት ከኃላፊነት ጋር እንደሚመጣና አስፈላጊ የሆኑ ገደቦች፣ በተለይም የሌሎችን መብት፣ ብሔራዊ ደህንነትና ሠላምን ለመጠበቅ ሲባል በሕግ ሊደነገጉ እንደሚችሉ በግልፅ ያስቀምጣል። የዚሁ ስምምነት አንቀጽ 20 ከዚህም በማለፍ በሃገራት ላይ በብሄር፣ በዘር ወይም በሃይማኖት ላይ በመመስረት ጥላቻን፣ ጥቃትና መድልኦን የሚያራግቡ ንግግሮችን በሕግ እንዲከለከሉ ግዴታ ይጥላል። ከላይ ከተጠቀሱት እውነታዎች በመነሳት የጥላቻ ንግግርን በግልፅና በቀጥታ የሚከለክል ሕግ አስፈላጊነት ግልፅ ነው ማለት ይቻላል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጉዳይ ሆን ተብሎ የሚደረግ የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት ነው። በተለይም የማህበራዊ ሚዲያ መስፋፋትንና ከዚህ ጋር የተገናኙ የቴክኖሎጂ ትሩፋቶችን በመጠቀም ሃሰተኛ የሆኑና ሆን ተብሎ የተዛቡ መረጃዎችን ማሠራጨት በተለያዩ ሃገራት የፖለቲካ ቀውስ ከማስከተል አልፎ ለግጭትና ጉዳት መንስኤ ሆኗል። ይህ ችግር ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እድገት ጋር እየተስፋፋ የመጣና ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ጠንቅ መሆኑን በመገንዘብ የተለያዩ ሃገራት ችግሩን ለመቅረፍ ሕጐችን በማውጣት ላይ ይገኛሉ። ከነዚህ ሃገራት መካከል ፈረንሣይ፣ጀርመንና ኬንያ ተጠቃሽ ናቸው። በዓለማችን ትልቋ ዲሞክራሲ በሆነችው ህንድም የሃሰት መረጃ ስርጭት ያስከተለውን ጦስ ለመከላከል የሕግ ማሻሻያ ለማድረግ ሂደቱ የተጀመረ ሲሆን፣ የችግሩ አስከፊነት በተለያዩ ጊዜያት የኢንተርኔት አገልግሎት እስከመዝጋት ድረስ መንግስት እርምጃ እንዲወስድ አስገዳጅ ሆኗል። በሃገራችን ኢትዮጵያም በቅርቡ በሃሰተኛ መረጃ ስርጭት የተነሣ የተቀሰቀሱ ግጭቶችንና ጥቃቶች የሰው ህይወት እንዲጠፋና ሌላም ጉዳት እንዲደርስ መንስዔ መሆናቸው ይታወቃል። ሆኖም ይህንን ጉዳይ በቀጥታና በበቂ ሁኔታ ሊሸፍን የሚችል ሕግ አለመኖሩ የፈጠረው ክፍተት ችግሩ እንዲባባስና ከፍተኛ ሃገራዊ ጉዳት እንዲደርስ እድል ሊፈጥር ይችላል።
ስለዚህ ይህን ክፍተት የሚሞላና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ፈፅሞ አግባብነት በሌለውና ከመብቱ መነሻና ዓላማ በተቃረነ መንገድ በመጠቀም በሃገርና በሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት መከላከል ያስፈልጋል። ከዚህ አንፃር ልብ ሊባል የሚገባው የጥላቻ ንግግርንና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመግታት ሕግ የሚወጣው መሠረታዊ የሆኑ የዜጐችን መብቶች፣ የሃገርና የህዝብ ደህንነትን፣ ሠላምን ለመጠበቅ፣ዲሞክራሲንና ነፃነትን ከጥላቻና ከሃሰት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ነው። ስለዚህ በዚህ መነሻ ሃሣብን በነፃነት የመግለፅ መብት ላይ የሚጣል ገደብ፣ ተመጣጣኝና በጥንቃቄ ተግባራዊ የሚደረግ እስከሆነ ድረስ በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ተቀባይነት ያለው ነው።
የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ
አዋጁ የሚያተኩርባቸው “የጥላቻ ንግግር” እና “ሐሰተኛ መረጃ” የሚሉ ቃላትን ምንነት እንመልከት። “ንግግር” የሚለው ቃል እንዲሁ መታየት ይኖርበታል።
በረቂቅ አዋጁ ትንታኔ መሠረት “ንግግር” ማለት በቃል፣ በጽሑፍ፣ በምሥዕልና ሥዕል፣ በቅርጻ ቅርጽ እና በሌሎች ተመሳሳይ መንገዶች መልዕክትን የማሰራጨት ተግባር ነው። እንግዲህ ንግግር ውስጥ ጣት መቀሰር ጭምር በጥላቻ ንግግርነት ሊያስጠይቅ እንደሚችል ስናስብ የሕጉን ጥብቅነት እንረዳለን።
“የጥላቻ ንግግርን በተመለከተ ረቂቁ እንዲህ ይፈታዋል። የጥላቻ ንግግር ማለት የሌላን ሰው፤ የተወሰነ ማህበረሰብን ብሄርን፤ ሀይማኖትን፤ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ ጥላቻን፣ መድሎን ወይም ጥቃትን የሚያበረታታ ንግግር ነው።
“ሐሰተኛ መረጃ” ውሸት የሆነና የመረጃውን ውሸት መሆኑን በሚያውቅ ወይም የመረጃውን ውሸት መሆን ማወቅ በሚገባው ሰው የሚሰራጭ ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት፣ ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ እድሉ ከፍ ያለ ንግግር ነው።
ከአዋጁ ዓላማዎች መካከል ሰዎች ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን ተግባራዊ ሲያደርጉ ሰብዓዊ ክብርን፣ የሌሎችን ደህንነትና ሠላም አደጋ ላይ ከሚጥል ንግግር እንዲቆጠቡ ማስቻል የሚለው በእኔ ዕይታ ትክክለኛ ነው። ግን ችግሩ የሌሎችን መብት በማስከበር ስም ሐሳብን በነጻ የመግለጽ ነጻነት ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አፈና እንዳይኖር ማስቻል ላይ ነው።
በረቂቅ አዋጁ ሊታዩ የሚገባቸው
ከአዋጁ አንቀጾች መካከል እንደ ጉድለት ከሚነሱት አንዱ በተለይ ማህበራዊ ሚዲያው የሚመራበት ራሱን የቻለ ሕግ ሳይኖረው የቁጥጥር ሕጉ መቅደሙ ከፈረሱ ጋሪውን የማስቀደም ያህል ሆኖ ታይቶኛል። መጀመሪያ ማህበራዊ ሚዲያው የሚመራበት ሕግ መኖር ነበረበት። የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመቆጣጠር በተዘጋጀው በዚሁ ረቂቅ አዋጅ አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ 4 “ …በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1-3) የተደነገገውን ግዴታ አለመወጣት ሊያስከትል የሚችለው የፍትሃብሄር ተጠያቂነት እንደተጠበቀ ሆኖ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች በዚህ አንቀጽ የተቀመጠውን ግዴታቸውን ባግባቡ መወጣታቸውን እየተከታተለ ለህዝብ ይፋ የሚሆን ረፖርት ያዘጋጃል” በሚል ደንግጓል። ባለሥልጣኑ ለመቆጣጠር በሕግ ሥልጣን ያልተሰጠውን፣ ያልመዘገባቸውን ማህበራዊ ሚዲያዎች ሞኒተር አድርጎ ሪፖርት የማቅረቡ ፋይዳ ምን እንደሆነም ግልጽ አይደለም። በዚህ ላይ ከአምስት ሺ በላይ ተከታይ ያላቸው ግለሰቦችና የማህበራዊ ሚዲያው ቁጥር በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ከመሆኑ አንጻር ሲታይ ባለሥልጣኑ የቱን ሪፖርት እንደሚያደርግ በሚገባ የታሰበበት አይመስልም። ሪፖርት ከማድረግ ባለፈ የዚህ አዋጅ አስፈጻሚ አካል ማን ነው የሚለው በረቂቅ አዋጁ በግልጽ አለመመልከቱም በራሱ በአፈጻጻም ረገድ ክፍተቶችን ማምጣቱ አይቀሬ ነው። በዚህ ላይ በአሁኑ ሰዓት በሀገር ውስጥ ያሉትም ሕጉ ባለመኖሩ ምክንያት እየተመዘገቡ ያሉት ተያያዥነት ባላቸው እንደ ፕሬስ፣ የማስታወቂያ እና የፕሮሞሽን ፈቃዶችን በመያዝ ነው። እናም መንግሥት የማያውቃቸውን ወይንም ያልመዘገባቸውን የማህበራዊ ሚዲያዎች ለመቆጣጠር መነሳቱ አስገራሚ የሚያደርገው ለዚህ ነው።
የጥላቻ ንግግር ማለት የሌላን ሰው፤ የተወሰነ ማህበረሰብን ብሄርን፤ ሀይማኖትን፤ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ ጥላቻን፣ መድሎን ወይም ጥቃትን የሚያበረታታ ንግግር ስለመሆኑ በረቂቅ አዋጁ ተመልክቷል። ነገር ግን ብሄርን፣ ሃይማኖትን መሠረት አድርገው የሚሰጡ አስተያየቶች ወይንም ትችቶችን በጥላቻ ንግግር መመዘን እንችላለን ወይ የሚለው በአግባቡ መጤን የሚኖርበት ነው። በጥላቻ ንግግር፣ በትችት እንዲሁም በስም ማጥፋት መካከል ያለው ልዩነት እና አንድነት በረቂቅ አዋጁ ውስጥ በግሌ መመልከት አልቻልኩም። የዚህ ግልጽ አለመሆን በአፈጻጸም ወቅት ችግር ሊያስከትል እንደሚችል እገምታለሁ።
በተመሳሳይ መልኩ ሐሰተኛ መረጃን በተመለከተ ረቂቅ አዋጁ “ሐሰተኛ መረጃ” ውሸት የሆነና የመረጃውን ውሸት መሆኑን በሚያውቅ ወይም የመረጃውን ውሸት መሆን ማወቅ በሚገባው ሰው የሚሰራጭ ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት፣ ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ እድሉ ከፍ ያለ ንግግር ነው በሚል ፍቺ ተቀምጧል። ሐሰተኛ መረጃ ውሸት ነው ካልን መገናኛ ብዙሃን ጨምሮ ማህበራዊ ሚዲያው በቅንነት ስህተት ሊሰራ የሚችልበት ዕድል እንደሚኖር ዘንግቷል። ያጋጠመ ስህተት ደግሞ ለመደበኛው ሚዲያ አሁን በሥራ ላይ ባለው የመገናኛ ብዙሃን የመረጃ ነጻነት አዋጅ መሠረት በወጣበት ቦታ ማስተባበያ በማውጣት ማረም እንደሚገባ ይደነግጋል። አዲሱ ረቂቅ አዋጅ መንፈስ ግን ሙሉ በሙሉ ትክክለኝነትን የሚጠብቅ መስሏል። በቅንነት፣ በመረጃ እጦት፣ አንዳንዴም በቸልተኝነት ሐሰተኛ መረጃ ሊሰራጭ የሚችልበት ዕድል የተለመደ መሆኑን ከግንዛቤ አለማስገባቱ በግሌ ያሳስበኛል።
ሌላው በረቂቅ አዋጁ ትኩረት ከሚስቡ ጉዳዮች አንዱ ተከታዩ አንቀጽ ይመስለኛል። “…በዚህ አዋጅ…የተከለከለ ተግባር የፈጸመው ሰው ድርጊቱን የፈጸመው ከአምስት ሺ በላይ ተከታይ ባለው የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ከሆነ ወይም በብሮድካስት አገልግሎት ወይም በየጊዜው በሚወጣ የህትመት ውጤት ከሆነ ሶስት አመት በሚደርስ በቀላል እስራት ወይም ከብር 100 ሺ ባልበለጠ መቀጮ ይቀጣል።…”ይላል። ይህ አንቀጽ ከአምስት ሺ በላይ ተከታይ ያላቸው የማህበራዊ ድረገጾች ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ የሚል ግንዛቤን መነሻ ያደረገ ይመስለኛል። ግን የማህበራዊ ሚዲያ አሰራርን ጠንቅቆ ለሚያውቅ ሰው ይህ አረዳድ በጣም የተሳሳተ ነው። አንድ መቶም ይሁን አንድ ሺ ተከታይ ያለው የማህበራዊ ድረገጽ ተከታይ ሆን ብሎም ይሁን ባለማወቅ በብዙ ሚሊዮን ወገኖች ላይ ጉዳት የሚያደርስ መረጃ በሽርፍራፊ ደቂቃዎች ውስጥ ለመልቀቅ ምንም የሚከለክለው ነገር አይኖርም። ይህን አባባል ትንሽ እናፍታታው። አንድ ሰው አንድ መቶ የፌስቡክ ተከታይ አለው እንበል። አንድ መረጃ ወይንም የጥላቻ ንግግር ለፌስቡክ ኩባንያ በመክፈል (ቡስት በማድረግ) በአጭር ደቂቃዎች ጊዜ ውስጥ ለሚሊዮኖች እንዲዳረስ ማድረግ ይችላል። በረቂቅ አዋጁ መሰረት ግን ሰውየው ያሉት ተከታዮች ብዛት አንድ መቶ ብቻ በመሆኑ ወይንም በአዋጁ ከተቀመጠው አምስት ሺ ተከታይ በታች በመሆኑ አዋጁ አይመለከተውም ማለት ነው። በተለይ ዓለም አቀፍ የባንክ ሒሳብ (አካውንት) ያላቸው ይህ ዓይነቱ አሰራር በጣም የሚቀላቸው መሆኑም የሚታወቅ ነው። ለዚህም ነው፤ አዋጁ ከአምስት ሺ በላይ የማህበራዊ ድረገጽ ያላቸው ሰዎች ለየት ባለ መልኩ ከባድ ጉዳት እንደሚያደርሱ አስቦ መነሳቱ አለማወቅ የሚሆነው።
ሌላውና ትልቁ ነገር ይህን የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ የሚለቁ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወገኖች በብዕር ስም እና በውሸት ፎቶግራፍ የሚገኙ እንዲሁም ነዋሪነታቸውም በውጪ ሀገር የመሆናቸው ጉዳይ ነው። እነዚህ ወገኖች ለሚያሰራጩት የጥላቻና የሐሰተኛ መረጃ በምን መልኩ ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ የሚለው ረቂቅ አዋጁ አይመልሰውም። በሌላ አነጋገር እነዚህ ወገኖች የሚለቁት ሐሰተኛ መረጃን እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል በረቂቅ አዋጁ አልተመለከተም። ይህ ሲታሰብ ደግሞ በሀገር ውስጥ ያሉትን ወገኖች ጸጥ ለማሰኘት አቅም ያለው ሕግ ሆኖ እንዳይቀር ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል።
ዋናው ነገር እንደፌስቡክ ያሉ ማህበራዊ ድረገጾች የተመሠረቱበት ዋነኛ ዓላማ የሰዎችን የመረጃ ጥማት ለማርካት ነው። ማህበራዊ ግንኙነቶቻቸውን ለማሳለጥ ነው። በዚህም ምክንያት ኩባንያዎቹ ሀሳብን በነጻ ለመግለጽ ነጻነት ትልቅ ዋጋ የሚሰጡ ናቸው። እንዲህ ዓይነት ሕጎች በእነሱ ዘንድ እንደምን ይታያል የሚለውም ወሳኝ ጥያቄ ይሆናል። መንግሥት የጥላቻና የሐሰተኛ መረጃን ቁጥጥርን በተመለከተ ከእነዚህ ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች ጋር ተቀራርቦ ቢሰራ ይበልጥ አትራፊ ይሆናል የሚል ግምት አለኝ።
ሌላውና መዘንጋት የሌለበት ትልቁ ቁምነገር ቢኖር፤ የጥላቻ ንግግር በማሰራጨት ረገድ መንግሥት እና በመንግሥት ውስጥ የተሰገሰጉ አንዳንድ ባለሥልጣናት ያላቸውን ሚና አሳንሶ ማየት ተገቢ አለመሆኑን ነው። ባለፉት ዓመታት ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ “ጠላቴ” ያላቸውን ሁሉ በጅምላ ሲፈርጅ፣ ሲያጥላላ መክረሙ አይረሳም። በሕግ የፖለቲካ ድርጅት መስርተው፣ ሕግና ሥርዐት አክብረው የሚቃወሙትን ወገኖች ሳይቀር በጅምላ “ነፍጠኛ፣ አክራሪ፣ ግንቦት ሰባት፣ የሻዕቢያ ተላላኪ፣ ኦነግ…” እያለ ሲያጥላላና ሲያሸማቅቅ መኖሩ ስናስታውስ የጥላቻ ንግግር መሠረቱ የት እንደነበር ቁልጭ ብሎ ይታየናል። ዛሬም ይህ ክፉ ደዌ ያለቀቃቸው ሹማምንት ወይንም አመራሮች በገዥው ፓርቲ ውስጥ ፈልጎ ማግኘት ያን ያህል አስቸጋሪ አይደለም። እናም መንግሥት ሕጉን ለማስከበር ከመንቀሳቀሱ በፊት ሕግና ሥርዓትን ማክበሩን ወይንም የሚያከብሩ ሹማምንት በየደረጃው መያዙን እርግጠኛ ሊሆንም ይገባል። (ማጣቀሻዎች፡- የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመቆጣጠር የወጣ ረቂቅ አዋጅ፣ ድሬቲዩብ ኦንላይን ሚዲያ…)
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታህሳስ 29/2012
ፍሬው አበበ