«ጥያቄ አቅርቤያለሁ መልስ ብትሰጡኝ፣
ሀገሬ የማን ነች ሰዎች አስረዱኝ!?»
የግጥሙ ሦስት አራተኛ ሃሳብ የተኮረጀ ነው። የጽሑፌን መነሻ ለማሳመር በሁለቱ ስንኞች ውስጥ ያካተትኩት ሦስት ቃላትን ብቻ ነው። “ሀገሬ የማን ነች” የሚሉትን። በተረፈ ባለቤቱ አብዛኞቻችን የምናውቀው ቤተኛ ድምጻዊ ነው። ስለማንነቱ የምናውቀው ለማናውቀው ብናስረዳ ስለሚሻል በቀጥታ ወደ ጉዳዬ ልንደርደር።
ያልሰከኑና ያልጠለሉ ብዙ ሀገራዊ ጉዳዮች አሉብን። መቼ እንደሚጠሉና ገፈታቸው እንደሚገፈፍ ቀን ለመቁረጥም በእጅጉ የተቸገርን ይመስላል። በእንክርዳድ የተጠመቁ በርካታ የጉሽ ትርክቶችን ተግተን የተሳከርንባቸው ጉዳዮቻችንም እጅግ ብዙ ናቸው። ከሀገራዊ ስካራችን ማርከሻ አጥተንም እነሆ እንደ እውር ድመት የሚያድፈነፍኑንን ችግሮቻችንን ለመቋቋም አቅም ያጣን ይመስላል። እኮ ለምን?
ያሽመደመዱን ልምሻዎች እንደ ጥንታዊው የህዳር በሽታ መልካቸውና ባህሪያቸው ከቀን ወደ ቀን እየተለዋወጠ ለሐኪምም ሆነ ለመድኃኒት አሻፈረኝ እያሉ ነው። በስብሰባና በምክክር ዘመቻ ሆ! ብንልም አልሆነልንም። እንደየእምነታችን በጾም በጸሎት ብንቃትትም ለጊዜው ፈጣሪ ማርከሻውን ሊያመላክተን ወይንም በቃችሁ ብሎ አሳራችንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ የፈቀደ አይመስልም። መቼስ ሰው ከፈጣሪ ጋር አይላተምም፤ ምን ማድረግ ይቻላል።
ሽማግሌዎቻችንም ለማስታረቅ የቆሙበት ጉልበት ተብረክርኮ ተስፋ እየቆረጡ ኩርምት ብለው የተቀመጡ ይመስላል። የሰሜኑ ራስ ምታት ጋብ ሲል የደቡቡ ቁስል ያዣል፤ የምሥራቁ ህመም ፋታ ሲያገኝ የምዕራቡ ያገረሻል። የሀገሬን ወቅታዊ ሁኔታ ከዚህ በላይ ለጥጦ መግለጹ ትርፉ ድካም ነው።
ይህቺ ኢትዮጵያ የምትባለው የሠፈርንባት የሀበሻ ምድር የተፈጠረችው “ሠማይና ምድር በፈጣሪ ቃል በተፈጠሩበት ዕለት ነው።” ይህ እውነታ የጠፋቸው ካሉ ቅዱሳት መጻሕፍትን ይመርምሩ፤ እውነታው የማይጥማቸው የትናንት ትውልዶችም አሮጌውንና ቀን የመሸበትን የዲያሌክቲካል ማቴሪያልዝም መጽሐፍ እንደለመዱት አቧራውን አራግፈው ቢያመሳክሩ መብታቸው ነው።
ሀገሪቱስ በፈጣሪ ቃል አንዴ ተዘርግታለች፤ ለመሆኑ ነዋሪዎቿ ከየትና እንዴት ተሰባስበው ሰፈሩባት? ይህ ጥያቄ ቅን ዜጎች በየዋህነት የሚጠይቁት መሠረታዊ ጥያቄ ቢሆንም “ቁርጥ ያለው የአሰፋፈራችን መልስ ይሄ ነው” ብሎ በማስረጃ እያስደገፉ ለመግለጽ ከሆደ ባሻ ግራገቦች ጋር አላስፈላጊ አታካራ ውስጥ ስለሚያስገባ ታሪካዊ ትንታኔውን ለታሪክ ተንታኞቹ ትተን “ነበርን፣ አለን ወደፊትም እንዲሁ ተዋደንና ተጋምደን እንኖራን” በማለት በድርበቡ ማለፉ ይሻል ይመስለናል። ይህ ማለት ግን ታሪካዊ እውነታዎች ተድበስብሰው ይለፉ ማለት እንዳልሆነ “ለነገር ቆስቋሾች” አስረግጦ ማስገንዘቡ አግባብ ይሆናል። በዚህ ጉዳይ ላይ እስከ ዛሬ ስናመነዥክ የኖርንበት “ጉንጭ አልፋ” አታካራ አራራቀን እንጂ አላቀራረበንም። ዕድሜ ለጨለምተኛ ልብ አውልቆች።
እንዲያው ካነሳነው አይቀር ግን ሃይማኖትና ሳይንስ ሆድና ጀርባ የሆኑባት በፈረንጅኛው ሉሲ፣ በአማርኛ ድንቅነሽ፣ በአፋርኛ “የትውልድ ቋንቋዋ” ሄሎመሊ የምትባለው “የሰው ዘር መገኛዋ” እመ ፍጥረት መፈጠሪያዋ ይሄው የእኛው ቀዬ ነው ብለን ካመንን ኢትዮጵያ እንኳንስ ለእኛ ለልጆቿ ለዘረ አዳም ምንጭ ነች ብሎ መከራከሩስ ፋይዳ ይኖረው ይሆን። እንደ ሀገራዊ የቱሪስት መፈክራችን ይህቺ ሀገር ለብዙ ጉዳዮቻችን “ምድረ ቀደምት” መሆኗን አምነን ብንቀበል ችግሮቻችንን ሁሉ በመግባባት የማንጨርስበት ምክንያት አይኖርም።
ወደ ዝርዝሩ ጠለቅ ብለን ስንፈትሽ የሀገር ድርና ማግ የተሸመነው በቀደምት አባቶቻችን ደምና አጥንት፣ በዛሬዎቹ ትውልዶች የሥራ ውጤት መሆኑን ማስረዳቱ ለቀባሪ የማርዳት ያህል ሊቀል ይችላል። ኢትዮጵያ በትውልዶች ጅረት የለመለመች፣ በልጆቿ የሥራ ትጋት፣ የባህል፣ የቋንቋና የታሪክ ኅብር የተዋበች እመ ዜጎች ነች። የትናንቶቹ ትውልዶች የራሳቸውን ፀሐይ እየሞቁና በራሳቸው በረከት እየረኩ ወይንም በጥፋታቸው እየተቀጡ ኑሯቸውን ኖረው አልፈዋል።
“አመዱን እንጂ የእሳቱን ፍም ከታሪክ እንክርት ላይ መጫር” የተሳናቸው ፖለቲከኞቻችን ግን የዕለት እንጀራቸው እንዳይኮመጥጥባቸው ስለሚፈልጉ ጊዜ እየጠበቁ ያለፈን የታሪክ ስህተት በወቅታዊ እርሾ እያጎበጎቡ በመጋገር ለማሕበራዊ የግጭትና የብጥብጥ ቅርሻት ሲዳርጉን እያስተዋልን ነው። የከበረውን የሀገርና የሕዝቦች ትስስር ከማክበርና በጎነቱን ከማጉላት ይልቅም የተሸምንበትን ድርና ማግ ለማንተብ መሯሯጣቸው ውሎ አድሮ ለውርደት፤ ሲሰነበትም ለተጠያቂነት እንደሚዳርጋቸው የተረዱት አይመስልም። “ጉድፎችን” ብቻ እየነቀስን ያለፈ ታሪክን ዓይን ከመንጓጉጥ የመልካሞቹን ዱካ መከተሉ ይበልጥ ብልህነት ነው። የዚህች ሀገር አብሮነት በማህፀኗ ውስጥ አቅፋ ከያዘችው የተፈጥሮ ማዕድናት በተሻለና በበለጠ ሁኔታ እጅግ የገዘፈ መሆኑን ለማመን መፍትሔው ከራስ ህሊና ጋር ተሟግቶ መርታት ብቻ ነው።
ቀዳሚዎቹ አባቶቻችንና አያቶቻችን ሰሯቸው የምንላቸውና ወደ እኛ የተሸጋገሩ “ጥፋቶች” እየጎዱን ነው ብንል እንኳ እኛ በጨዋነትና በማስተዋል እያረምን ከችግሮቹ ነፃ መውጣት ይሻላል እንጂ እንደ ሙት መናፍስት ጠሪ አጽማቸውን ከመቃብር እየቀሰቀስን አደባባይ ላይ እንስቀላቸው ማለቱ ጅልነትም፤ እብደትም ነው። “አጥንቱን ልልቀመው መቃብር ቆፍሬ!” እያልን መካነ መቃብር መሃል ቆመን ካላቅራራን በስተቀር።
ይህቺን ክብርት ሀገር ዛሬ ዛሬ ከሕዝብና ከትውልዶች ባለቤትነት አፈናቅለው ለግላቸው የፖለቲካ መሸቀጫ ኪዮስክነት ለማዋል የሚሯሯጡ ቡድኖችም ሆኑ ግለሰቦች እየበረከቱ በመሄድ ላይ ናቸው። የሀገሪቱን ፖለቲካ እንዲያንቦጫርቁ ዕድሉን ያገኙ አንዳንድ “ምስለ የሕዝብ ተቆርቋሪዎች” እንኳንስ ሀገሪቱንና ሕዝቧን ለማወቅ ቀርቶ ራሳቸውንም ስለማወቃቸው ያጠራጥራል።
በፖለቲካ ጅምናስቲክ የተካኑ ውስን ዕድሜ ጠገቦችም ቢሆኑ የዕውቀትና የሕዝብ አክብሮት ድህነት ሲያጠቃቸው ደጋግመን አስተውለናቸዋል። ብዙ ተማሪዎቹ የሚያደንቁት ነፍሰ ኄር መምህር ደበበ ሰይፉ ደጋግሞ የሚያነሳው አንድ ዐረፍተ ነገር ከላይ የገለጽናቸውን ቡድኖችና ግለሰቦች ይበልጥ ይገልጻቸዋል። “እናንተ የአባቶቻችሁ ልጆች፤ የአያቶቻችሁ ቅድመ አያቶች።” በመወለድ ሁሉም ሰው የአባቱ ልጅ ነው። በአስተሳሰብ ጮርቃነት ግን ከአያቶቻችንም ዘመን ዘለን እንደ ቅድመ አያቶቻችን የሚያስቡ ሰዎች ብዙዎች ናቸው።
በፖለቲካው ምስባክ ፊት ለፊት የተገተሩት አብዛኞቹ ፖለቲከኞች ለዚህ ትውልድ በስጋም ሆነ በመንፈስ ወደ ቅድመ አያትነት የሚጠጉ ብቻ ሳይሆኑ የዛሬ አርባና ሃምሳ ዓመታት በተቸከሉበት ቦታ እንደቆሙ ያሉ ናቸው። እግሯን ተሰንክላ ለበርካታ ሰዓት የታሰረች በቅሎ ቢፈቷትም እስራቱ አብሯት ያለ እየመሰላት ከዚያ ቦታ አትንቀሳቀስም። እነርሱ ማለት እንደዚህ ናቸው። ሚናችሁ ምንድን ነው? ተብለው በትውልዱ አንደበት ሲሞገቱ “እንዲህ ነን” ብለው ለመመለስና የእርሱን ቋንቋ ለመናገር እንኳ አፍ የላቸውም። እነርሱን የሚቀናቸው ትውልዳቸው እርስ በእርሱ በተፋጀበት የቂም እርሾ የዛሬውን ፖለቲካ ካላቦካን እያሉ “እንዲያው ዘራፌዋን” ማንጎራጎር ነው።
ከፊሎቹ ደግሞ በገር ኮሲ ላይ እንደሚበቅል ተክል በአንድ ሌሊት ብቅ ብለው የበቀሉ አፈጮሌዎች ናቸው። ንግግር ይችላሉ። በማስመሰል ይበረታሉ። ሽንገላን ተክነውበታል። የሕዝቡን የልብ ትርታ ሳይሆን ለወቅታዊ ትንታው ይበልጥ ትኩረት በመስጠት የስልጣን ጥማታቸውን ለማርካት የሚተጉ ናቸው።
ሌሎችም አሉ። እንደ አብሮ አደግ ማኅበረተኞች ጽዋ የክብር ግምጃ ካልደረባችሁልን እያሉ በየአደባባዩ ሕዝቡ እንዲሳለማቸው የሚፈልጉ። እነዚህኞቹም ቢሆኑ ሃሳብና ርዕይ የሌላቸው የልሙጥ ስብእና መገለጫዎች ናቸው። የሕይወትና የፖለቲካ ፍልስፍናቸው “እሽ አትበሉን የሹም ዶሮ ነን” ይሉት ዓይነት ነው። ቦታቸውና ውሏቸው ሚዲያና ግብዣ ነው። አቀማመጣቸው ደግሞ ፊተኛው ወንበር ላይ። ይህንን ክብር ለማስጠበቅ የሚሞክሩት ልክ እንደ ሰብዓዊ መብት ነው።
ስለዚህም ነው በሰከነ መንፈስ ረጋ ብለን “ሀገር የማነው? የሕዝብ ወይንስ የፖለቲከኞች?” ብለን የምንጠይቀው። ከላይ የዘረዘርናቸው ልሂቃን ነን ባዮች ቢቻላቸው “ኢትዮጵያን አቡክተንና ጠፍጥፈን የሠራናት እኛ ነን” በማለት የሙሉ ባለቤትነት መብት ቢጠይቁ ይሉኝታ የሚሰማቸው ብጤ አይደሉም።
ቅዱስ መጽሐፍ የሰውን ዕድሜ በሰባና በሰማንያ ዓመት ገድቦ ከዚያ በላይ መንጠራራት ለድካም መጋለጥ እንደሆነ አጥብቆ ያስተምረናል። በጉብዝና ዕድሜ መሮጥ የተሻለ እንደሆነ ለማመልከት እንጂ ከዘጠናም ከፍ ብሎ በመቶ ላይ ምራቂ የጨመሩ የዕድሜ ቱጃሮችን ለመኮነን አይደለም። አንዳንድ የሀገራችን ፖለቲከኞች ግን እንደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከሰማንያ በላይ፣ እንደ ሙጋቤ በዘጠና የዕድሜ ጣሪያ ላይ ሆነውም ካልገዛን እያሉ እየፎከሩ በራሳቸው ድርጊት ጠብመንጃ የያዘ ወታደር ቤተመንግሥታቸውን ደፍሮ እንዲያዋርዳቸው ይመርጣሉ። የዕድሜም ሆነ የፖለቲካ ሥልጣን ናፋቂ አረጋዊያን በጊዜ ራሳቸውን ሰብስበው ከተመካሪነት ወደ መካሪነት ፈቅ ቢሉ ይበጃቸው ይመስለናል።
እንደ ዜጋ ደፈር ብለን ደጋግመን የምንጠይቀው ጥያቄ “ሕዝቡ!” እያሉ ጋሻ የሚያደርጉትና በስሙ አጀንዳ እየቀረጹ ተገን አድርገው እስከ መፎለል የደረሱት “ማን ወክሏቸው እንደሆነ ማብራሪያ ቢሰጡን አይከፋም”። በሕዝብ ስም እየማሉ ሲያስነጥሱ ታዘብናቸው እንጂ መቼ ይማራችሁ ብለን መረቅናቸው?
ከላይ ገበናቸውን የገለጥነውና ቁርሳቸውን፣ ምሳቸውንና እራታቸውን በፖለቲካ ጥገኝነት ስም እየተመገቡ ያሉት ግለሰቦች “ሆ!” በሉ እያሉ ሲያስጨፍሩን አለያም ደረት እያስመቱ ሲያስለቅሱንና ሲያፋጁን ስለምን የማገዶ እንጨት ለመሆን ፈቀድንላቸው? በሕዝቡ ስቃይ እነርሱ ከቆፈን እንዲላቀቁ እኮ ለምን መብት ሰጠናቸው? እንዲህ ብለን ብንጠይቃቸውስ። የስንት ሀገር ፓስፖርትና የስንት መንግሥታት ዜግነት አላችሁ? ልጆቻችሁ፣ ቤተሰባችሁና ዘር ማንዘራችሁ የት ነው የተጠለለው? ለጥፋት አጀንዳቸውስ ከኋላ ሆኖ የሚደግፋችሁ ጡንቸኛና ብርቱ ደጀናችሁ ማን ነው? የተመኟት የሥልጣን ሩር በለስ ቀንቷት ከግቧ ብታርፍና የሥልጣናቸው ወንበር ቢደላደል ቀድመው ጮማውን የሚያጎርሱትና መረቁን የሚያጠጡትስ ለማን ነው? በድፍረት፣ ሳንሸማቀቅ በአደባባይ ልንጠይቀቸውና ልንሞግታቸው ይገባል። ከመሞገትም አልፈን በሚቃዡለት የምርጫ ካርድ ልንቀጣቸው ይገባል። “እኔን ያየህ ተቀጣ!” እያሉ ለሌሎችም ትምህርት እንዲሆኑ ሊታረሙ ይገባል።
ሀገር ማንም በግድግዳው ላይ የሚለጠፋት ግዑዝ ካርታ ብቻ አይደለችም። ሕዝብም ቢሆን አስሬ ተነቅሎ አስሬ የሚተከል የሰነፍ ችግኝ አይደለም፡ ዲያቢሎስ ክርስቶስን እንደፈተነው “ሥልጣኔን አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤ በክብሬም አከብራችኋሁ። ስለዚህም በፊቴ ወድቃችሁ ብትሰግዱ ለእኔ የሆነው ሁሉ ለእናንተ ይሆናል።” ብለው ሲሸነግሉን ትምክህታቸውን በሃሳብ፣ እብሪታቸውን በጥበብ ልናርማቸውና ልንቀጣቸው ይገባል።
ሀገራችን ዛሬም ሆነ ነገ በእነዚህ እጅ ልትወድቅ አይገባም። ሀገር የሕዝብ ነች። እንዲመሯት የምንመኘውም ከሕዝብ የወጡ የሕዝብ ልጆችን ነው። ሕዝባቸውን በልባቸው ጽላት ላይ የጻፉ፣ ዕድገቱንም በርዕያቸው ውስጥ የጸነሱ አስተዋዮች ሲገኙ እነርሱ አሻፈረኝ ቢሉ እንኳ ሕዝቡ ካልመራችሁኝ ብሎ ጨርቃቸውን አንቆ መማጠኑ አይቀርም። እንጂማ ሀገርንና ሕዝብን የሕጻን ጥብቆ እያለበሱ በአሻንጉሊት የሚመስሉትን ማን ይፈልጋቸዋል! ማን ያስጠጋቸዋል! ማንስ ያደምጣቸዋል!? እኮ ማን ሊከተላቸው? ማንም። ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታህሳስ 29/2012
በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ