መሸ። የአውድ ዓመት ዋዜማ ነው። ሰዉ በየመሸታ ቤቱ ተጎዝጉዟል … እንደ ቄጤማ። መንገዱ በሰው ሰክሯል። ዝንቅ የአወድ አመት ማዕዛ ከዚህም ከዚያም ከች እያለ አፍንጫን ያጫውታል። አየሩ በአውድ አመት ሙዚቃ ደምቋል። በበዓል ዋዜማ ሁሉም ሙዚቃ ይጥሟል። የሚከፈተውም ሆነ የሚደመጠው በዓሉን በማስመልከት ስለሆነ ይሆን?
አንድ የሬዲዮ ጣቢያ የለቀቀው ዘፈን ጆሮዬ ገባ …
… እንደ ቄጤማ ልክ እንደ አሪቲ ጉዝጓዝ ሆነልሽ
ካንቺው መጣልሽ ያው ደረሰልሽ
ከቤትሽ ገብቶ ተነጠፈልሽ
እንደ ቄጤማ ልክ እንደ አሪቲ ጉዝጓዝ ሆነልሽ …
አዘጋጆቹ ይህን ሙዚቃ ያጫወቱት “ቄጤማ” የሚል ቃል ስለያዘ እንጂ የበዓል መንፈስ ስላለው እንዳልሆነ ግልጽ ነው። የቄጤማን ያህል ከአውድ ኣመት ጋር የተቆራኘ ምን ነገር አለ ? ልክ ናቸው። በዓል ያለ ቄጤማ አይደምቅም። የቄጤማና ዓውድ አመት ትስስር እኔንም አስሮኝ በየአንቀጹ ሀሳቤን በቄጤማ ሸብቤያለሁ፡፡
“ዓውድ አመት በለውጥ ማግስት” የሚያሰኘው አንዱ ምክንያት ለውጡን ተከትሎ በሁለቱ ታላላቅ ቤተ እምነቶች ውስጥ የነበሩ ቅራኔዎች ተፈተው መከፋፈሉ በእርቅ መደምደሙ ነው።ሌሎች ምክንያቶችም አሉ።ከለውጡ በፊት የሃይማኖት አባቶች በበዓላት የሚሰጧቸው ቡራኬዎች ከመንፈሳዊ ይልቅ ፖለቲካዊ ማዕዛቸው ያውድ ነበር።ከለውጡ በፊት የመንግስት ባለስልጣናት ድምጽ በግንቦት 20ና በብሔር ብሔረሰቦች ቀን ካልሆነ በቀር ጨርሶ አይሰማም ነበር።ታዲያ እጃቸውን አጣጥፈው አይቀመጡም። የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለሃይማኖት አባቶች አሸክመው ዘወር ይላሉ እንጂ።
ይህ ያልተጻፈ፣ ነገር ግን ከተጻፈው በላይ የሚተገበር ሕግ በመሆኑ የሃይማኖት አባቶች የቤተ እምነታቸውንና የመንግስትን መልዕክት በአንድነት ያስተላልፉ ነበር።ቆርጦ ቀጥሎቹ የሥርዓቱ ሚዲያዎችም “እንኳን አደረሳችሁ” ከሚለው አረፍተ ነገር ቀጥሎ የሃይማኖት አባቶቹ ስለ እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የተናገሩትን አምጥተው ይደነቅራሉ።ከዛ ምዕመኑ ከሰማያዊው ሕይወት ይልቅ ምድራዊው ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳ በመሆኑ ያጉረመርማል።
በዓሉን ለማድመቅ የተቆጠበ ገንዘብ ሁሉ ከየባንክ ቤቱ ታጭዷል … እንደ ቄጤማ! ውጭ አገር ዘመድ ያለው በተላከለት ዶላር እጁ ረጥቧል … እንደ ቄጤማ ! ዶሮ ፣ በግ፣ ቅርጫ፣ ልብስ፣ ጫማ፣ የቤት እቃና … ቄጤማ ተገዝቷል። የሌለው ሜዳ ላይ ቁጭ ብሎ ንፋስ እንደሚያወዛውዘው ሁሉ ጭንቅላቱን ወዲህ ወዲያ ያንቀሳቅሳል … እንደ ቄጤማ !
ለውጡን ተከትሎ መንግስት ራሱን ችሎ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ማስተላለፍ ጀምሯል።የበዓላቱን ሃይማኖታዊና ባህላዊ ገጽታዎች ከወቅታዊ ፖለቲካዊ ትኩሳቶች ጋር በማሰናሰን ማስተላለፍ የሚፈልገውን መልዕክት በራሱ አንደበት እያንቆረቆረ ነው።ዛሬ አውድ ዓመት በመጣ ቁጥር ከሚጠበቁ ነገሮች አንዱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ሆኗል።
የፌደራልና የመንግስት ባለስልጣናት ሃይማኖታዊና ባህላዊ ልብሶችን ለብሰው በዓላትን ለማድመቅ በሚሰናዱ የተለያዩ አዝናኝ ዝግጅቶች ላይ መታደም ጀምረዋል።ብዙ ህዝብ በሚሳተፍባቸው የአደባባይ በዓላት ላይ እንኳን መገኘት ከብዷቸው “ስራ ስለበዛባቸው አልተገኙም” እየተባለ መልዕክታቸውን በተወካይ የሚያስተላልፉ ባለስልጣናት ከተቋጠሩበት ተፈተው በአዝናኝ የበዓል ፕሮግራሞች ፈታ እያሉ በቴሌቪዥን መስኮት ህዝባቸው ቤት እየገቡ ነው። ባጭሩ መንግስት ከመንፈስነት ወደ ሰውነት ደረጃ ወርዷል።
ነጋ። አውድ ዓመት ነው።አረንጓዴ … እንደ ቄጤማ! ከለውጡ በኋላ መንግስት ለአውድ አመቶች ልዩ ትኩረት የሰጠ ይመስላል።ምን ? … “አሽቃባጭ” አልከኝ ? ይመስላል እኮ ነው ያልኩት።አልተዋጠልህም? እንግዲያውስ አስረጅ ልጥቀስ!
መላው ኢትዮጵያውያን የሚያከብሩት ዘመን መለወጫ መስከረም 1 ቀን 2012 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል።በብሄራዊ ቤተ መንግስት ጳጉሜን በመደመር የብሄራዊ የአንድነት ቀን የማጠቃለያና የአዲስ ዓመት የዋዜማ ስነ ስርዓት ተከናውኗል። ፕሬዚዳንቷን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤዋን ጨምሮ በርከት ያሉ ሰዎች በዚህ ዝግጅት ላይ ተገኝተዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያሰናዳው የዋዜማ ምሽት መርሃ ግብርም በአስተዳደሩ ቅጥር ግቢ ውስጥ ተከናውኗል። ለአዲሱ ዓመት አቀባበል ለማድረግ በከተማ አስተዳደሩ ቅጥር ግቢና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እያስገነባ ባለው ባለ 52 ፎቅ ህንጻ የመጨረሻ ወለል ላይ ደማቅ የርችት ተኩስ ስነ ስርዓት ተካሂዷል። ከወትሮ በተለየ መልኩ አዲስ አበባና ድሬዳዋን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች በሚገኙ ታላላቅ ሆቴሎች በዋዜማው በርከት ያሉ የሙዚቃ ድግሶች ተከናውነዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዛሬ አመት ገናን የዘውዲቱ መሸሻ የህጻናትና ቤተሰብ በጎ አድራጎትና ልማት ማህበርን ከባለቤታቸው ከቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው ጋር በመሆን በመጎብኘት አሳልፈዋል። ቀዳማዊት እመቤቷ የገናን በዓል በማስመልከት በማዕከሉ ላሉ ህጻናት የአልባሳትና የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ አበርክተው ነበር።
እኚሁ ጠቅላይ ሚኒስትር በረመዳን ጾም ፍቺ የኢድ ሶላት የሚሰገድበትን የአዲስ አበባ ስታዲየም ዙሪያ ከክርስትና እምነት ተከታዮች ጋር በመሆን በዋዜማው አጽድተዋል። በማግስቱ የኢድ አልፈጥር በዓልን ከጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማንና ከአዲስ አበባ ከተማ ምከትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ጋር በመሆን ከተስፋ አዲስ የወላጆችና የህጻናት ካንሰር ታካሚዎች ጋር በጋራ አክብረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን መንገድ ሌሎች ሚኒስትሮችና ባለስልጣናትም ተከትለዋል።የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የትንሳኤ በዓልን ከየወደቁትን አንሱ የነዳያን መርጃ ማኅበር ጋራ በጋራ አክብሯል። በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በትናንትናው ዕለት በድምቀት የተከበረው የገና በዓልም በመሰል ክስተት የታጀበ ነበር።የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “ገናን በጎ በማድረግ” በሚል መሪ መልዕክት 28 የህንጻ ተቋራጭ ባለሀብቶችን በማስተባበር ለዓመታት በመጠለያ ውስጥ ለቆዩ 120 ነዋሪዎች በ3 ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር 25 መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ አበርክቷል።
እንዲህ ያሉ በጎ ተግባሮች በመንግስት ባለስልጣናትና ተቋማት መፈጸም መጀመራቸው ለኢትዮጵያውያን መልካም ዜና ነው። ነገር ግን ድጋፎቹ በዓልን አስታከው ብቻ መደረግ የለባቸውም። በተደራጀ መልኩ ለዘለቄታው መቀጠል አለባቸው።ለዚህ ኢትዮ ቴሌኮም ጥሩ ምሳሌ ነው።
ኢትዮ ቴሌኮም ለዋና ስራ አስፈጻሚ ተጠሪ የሆነ ክፍል በማደራጀት ማህበረሰቡ ድጋፍ የሚሻባቸውን የትኩረት መስኮች ለይቶ ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ ነው።እያጠናቀቅን ባለነው ወር እንኳን በመላው አገሪቱ በሚገኙ 45 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ለሚማሩ አራት ሺ ተማሪዎች በየወሩ አራት መቶ ብር የኪስ ገንዘብ ለመስጠት 16 ሚሊየን ብር መድቦ ወደ ስራ ገብቷል።የልማት ድርጅቶችና ሌሎች የመንግስት ተቋማት እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠር ይጠበቅባቸዋል። ማህበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት ስራ በአደረጃጀት መመራቱ ማናቸውም አይነት ድጋፎች ዘለቄታ እንዲኖራቸውና ወንበሩ ላይ በተቀመጠው ሰው በጎ ፍቃድ ላይ እንዳይነጠለጠሉ ያደርጋል።
ዓውድ አመትን በመጠበቅ ድጋፍ ማድረጉ የሚቀጥል ከሆነ ግን ዓውድ አመቱ ሲያረጅ የተቸገሩ ሰዎች ገጽ መገርጣት ፤ መድረቅና መድቀቅ ይጀምራል … እንደ ቄጤማ ! እንደገና ለመውዛት ፣ መልሶ ለመፍካትና ዳግም ለመታወስ ሌላ ዓውድ አመት ይጠብቃል … እንደ ቄጤማ !
የአረጋኸኝ ዘፈን ጆሮዬ ላይ
እንደ ቄጤማ ልክ እንደ አሪቲ ጉዝጓዝ ሆነልሽ
ካንቺው መጣልሽ ያው ደረሰልሽ
ከቤትሽ ገብቶ ተነጠፈልሽ
እንደ ቄጤማ ልክ እንደ አሪቲ ጉዝጓዝ ሆነልሽ!
መልካም ገና!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታህሳስ 29/2012
የትናየት ፈሩ